የሽግግር መንግሥት ማቋቋሙ፤ ግዴታ ነው።

የሽግግር መንግሥት ማቋቋሙ፤ ግዴታ ነው።
አንዱዓለም ተፈራ
ሐሙስ፣ ሐምሌ ፲ ፪ ቀን ፳ ፻ ፲ ዓመተ ምህረት

የተራበች እናት ምግብ ማግኘቷ፤ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው።
ምርጫ የሚሆነው ሰጪና ነሺ ካለ፤ ለዚሁ አካል ብቻ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መሐመድ የኦሕዴድ መሪ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መሐመድ የኢሕአዴግ ወኪል ናቸው። አሁን ኢትዮጵያን እያስተዳደሩ ያሉት፤ በኢሕአዴግ መዋቅርና ሰዎች ነው። በርግጥ የያዙት መንገድ፤ እስከዛሬ በትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ገዥዎቻችን ሲመራ የነበረው ኢሕአዴግ ሲከተለው ከነበረው ለየት ያለ ነው። አሁንም መሠረቱ ግን ኢሕአዴግና ኢሕአዴግ ሲመራበት የነበረው የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ ነው። እናም አንድን ወገን ብቻ ወክለው፣ ነገር ግን በጣም ጥሩ ነገር ለብዙኀን በማድረግ ላይ ያሉ ናቸው። ይህ በጎ ተግባራቸው፤ ከመጡበት አኳያ ስናየው ውስንነት አለበት። በአንድ ሰው ቅንነት ሀገር አትመራም። የሚቀጥለው ምንድን ነው? ብለን ከመጠበቅ በላይ፤ ምን መሆን አለበት የሚለውን ሁላችን በያለንበት መነጋገር አለብን። የሀገራችን ችግር ምስቅልቅል ነው። ይህች ሀገር የሁላችን ናት። ለውጡን ተባብረን ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ፤ ሁላችን መታቀፍ አለብን።

የሀገራችን ችግር ምስቅልቅል ነው። በቀጥታ አንድና አንድን እንደመደመር ሊወሰድ የሚችል አይደለም። ይሄ ምስቅልቅል ችግር፤ መሠረታዊ የሆነ ከሥሩ መንግሎ የሚጥል መፍትሔ ካልተገኘለት፤ እምቧለሌ ዙሪያ የሚሽከረከርና የማይለቅ ይሆናል። የክልል ጉዳይ አንድ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ፤ አከላለሉ፣ አስተዳደሩ፣ “እኛ” እና “ሌሎች” የሚለው ግንዛቤ፣ ርስ በርስ ሕዝቡ እንዲጋደል የተደረገው ሂደት፣ የመፈናቀልና በግፍ የመገደል ጉዳይ ሌላው ነው። አድልዖ፣ ሙስና፣ የመንግሥት ሥልጣንና የተዋረዱ ሂደት ሌላው ጉዳይ ነው። የመንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ የመግባት ሁኔታ፤ ሌላው ጉዳይ ነው። በገፍ ከሀገራቸው የተሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ሌላው ነው። አንዱን አካባቢ ከሌላው አስበልጦ የማሳደግና ዕድሉን ሁሉ በዚያ መንዳት ሌላው ጉዳይ ነው። ብዙ ከዚህ የከፉ ሌሎች ሊዘረዘሩ የሚችሉ እንዳሉ ሁላችን እናውቃለን። የሚከተለው ምንድን ይሆን? ብለን ከመጠበቅ በላይ፤ ምን መከተል አለበት የሚለውን መነጋገር አለብን።

ይህች ሀገር የሁላችን ናት። እናም ሁላችን የኔ ብለን መፍትሔ ማምጣቱ ላይ መረባረብ አለብን። ግዴታውን ለአንድ ግለሰብ ወይንም ክፍል ሠጥተን፤ ሌሎቻችን እጆቻችንን አጣጥፈን መቀመጥ የለብንም። ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የደረሰው ጥፋት፤ በኢትዮጵያዊያን የተፈጸመ በመሆኑ፤ የኛው ታሪክ ነው። እናም አብሮን ለምጥ ሆኖ ለዘለዓለሙ ይኖራል። አሁን እንዲቀጥል የምንፈቅድበት ወይንም በትብብር እንዲቆም የምናደርግበት ዕድል ገጥሞናል። ኋላ ዞረን ያኔ እንዲህ ቢደረግ ኖሮ! ወይንም እኔ እንዲያ ባደርግ ኖሮ! ብለን የመቆጫው ጊዜ፤ ሊመጣ አይገባውም። አሁን ማድረግ ያለብንን፤ አሁን ማድረግ አለብን። እናም ትክክለኛው ጥያቄ፤ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ነው።

የሽግግር መንግሥትን መቋቋም የማይፈልጉ አሉ። እኒህ በሁለት ይከፈላሉ። የመጀመሪያዎቹ፤ አሁን ያለውን የለውጥ ሂደት ስለሚጠሉት፤ እንዲከሽፍና የነበሩበት መንበር እንዲመለስላቸው የሚደክሙት ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ፤ የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል ስለሚፈልጉና ለውጡ ይነጋነጋል ብለው ስለሚፈሩ፤ ሁሉን ነገር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንተውላቸው ባዮች ናቸው። የመጀመሪያዎቹን መነጋገር ያለብን አይመስለኝም። እናም አልፈዋለሁ። ሁለተኛዎቹን በሚመለከት፤ ያንድ ሰው ድካም ይበቃል ወይንስ ሁላችን የምንረባረብበት? በሚል እመልሰዋለሁ።

አንድ ብቻቸውን የሚደክሙት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ባሁኑ ጊዜ፤ ዙሪያቸውን ከከበቡት መካከል ነባር የሕዝቡ ጠላቶች አሉ። በግለሰብ ደረጃ እሳቸውን፤ ያን ካልቻሉ ደግሞ ሥራቸውን ለማደናቀፍ ወደኋላ የማይል ኃይል አለ ማለት ነው። መርሳት የሌለብን፤ ሕይወታቸውን ለማጥፋት ሞክረዋል። እሳቸውን ማጣት ከባድ ውድቀት ነው። ነገር ግን፤ በሳቸው ተማምኖ መጋለብ ኃላፊነት የጎደለው ሂደት ነው። እሳቸውን መንገር ያለብን፤ አሁን ሀገራችን የምትፈልገው፤ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞ፤ ውስብስቡን የሀገራችን ችግር፤ ባገር አቀፍ ጥሪ መፍታት ነው። እንዴት ሊቋቋም ይችላል? እንዲህ አይሆንም ወይ? ያ ችግር አያስኬድም? የመሳሰሉ ምክያቶችን መደርደር ይቻላል። ነገር ግን ከዚህ የቀለለ ሌላ መንገድ የለም። ስለ ሽግግር መንግሥት አቋቋም፤ በሚቀጥለው ጽሑፌ በሠፊው እሄድበታለሁ። ወይንም ሌሎች ሊያቀርቡ ይችላሉ። ዋናው ግን፤ ካለንበት አዘቅት መውጣት የምንችለው፤ ካሁኑ ቦታችን ወደምንፈልገው ቦታ ለመድረስ፤ የሽግግር መንግሥት ግዴታ ነው። ምን ትላላችሁ?

ከታላቅ አክብሮት ጋር
አንዱዓለም ተፈራ

Advertisements
Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ

የለውጡ የወደፊት ሂደት

የለውጡ የወደፊት ሂደት

አንዱዓለም ተፈራ

ማክሰኞ፣ መስከረም ፰ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፩ ዓ. ም. ( 9/18/2018 )

ከመነሻው፤ ለውጡን የምንፈልግ በብዛት እንደምንገኝ ሁሉ፤ ለውጡን የማይፈልጉ ብቻ ሳይሆን፤ ለውጡን የሚቃወሙ እንዳሉ ማመን አለብን። ባሁኑ ሰዓት ለውጡ እንቅፋቶች ገጥመውታል። እኒህ እንቅፋቶች፤ መሠረታዊ ችግሮች ናቸው? ወይንስ በሂደት የመጡና ሊወገዱ የሚችሉ? ለውጡ የጎደለው እንዳለ ጠቋሚዎች ናቸው? ወይንስ የለውጡ ምንነት ችግር? የለውጡ ሂደት የፈጠራቸው ናቸው? ወይንስ ከለውጡ ምንነት ጋር የተያያዙ? ከምን የመጡ ናቸው? ይሄንን ሳይመለከቱ፤ በደፈናው እንዲህ ሆነ እንዲያ እናድርግ በሚል መጓዙ፤ የእምቧለሌ ሽክርክር ይሆናል።

መጀመሪያ ማድረግ ያለብን፤ ለውጡ ለምን መጣ? በማን ላይ መጣ? ማን አመጣው? እንዴት መጣ? የሚለውን መመለስ ነው። አዎ! ችግር አለ። ይሄን መካድ አይቻልም። አዲስ አበባ ውስጥ ሆነ አርባ ምንጭ፣ ኢትዮጵያ ሶማሊም ሆነ ቤንሻንጉል፤ በየቦታው የተፈናቀሉትም ሆነ፤ ሆን ተብሎ የሚዘመትባቸው ሰዎች፤ መሠረታዊ በሆነ ችግር ምክንያት እንጂ፤ ሰዎቹ ስለተጠሉ ወይንም ወንጀል ስለሠሩ አይደለም።

በአንድ ሀገር የሚከሰተው ለውጥ፤ እንዲህ መሆን አለበት! ወይንም እንዲያ መሆን አለበት! ተብሎ በተቀመጠ ቅምር እንደ ተዘጋጄ እጄ ጠባብ፤ የሚጠለቅ አይደለም። ተጨባጩ የሀገሪቱ ሁኔታ፣ የወቅቱ የፖለቲካ ሀቅና፣ በሂደቱ ያሉት ተሳታፊዎች አሰላለፍ፤ ይወስነዋል። ያም እንኳን ሆኖ፤ ለውጡን በትክክል መተንበይ አይቻልም። የኛን እውነታ ስንመለከት፤ ለውጡ ኢሕአዴግ በፈጠረው በደልና ጥፋት የተነሳ የመጣ ነው። ለውጡ ኢሕአዴግን ለማፍረስና፤ ያራመዳቸውን የፖለቲካ ቀውሶች ለማስተካከል ነው። ለውጡን ኢሕአዴግ ሊመራው አይችልም። የመጀመሪያው ችግር፤ ለውጡ የመጣበት ኢሕአዴግ፤ ለውጡን እየመራ መገኘቱ ነው። ይህ ማለት፤ በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ለውጥ ፈላጊዎች ተሳታፊ አይሆኑም ማለት አይደለም። ነገር ግን፤ እነሱ የለውጡ አካል ይሆናሉ እንጂ፤ የለውጡ ባለቤትና ግለኛ መሪዎች መሆን አይችሉም። ይህ፤ በመፈንቅለ መንግሥት ከሚደረግ የለውጥ ሂደት ጋር ይመሳሰላል። አብዛኛውን ጊዜ፤ የሥርዓቱ ምሰሶ የሆነው ወታደራዊ ክፍል፤ መፈንቅለ መንግሥት ያደርግና፤ “እኔ ባለቤት ነኝ፤ ሌሎቻችሁ አርፋችሁ ተቀመጡ!” ይላል። ይህ ያንን ያስታውሰኛል። ከራሳችን ታሪክ መማር ይገባናል።

ቀጥሎ ደግሞ፤ የለውጡን መሠረታዊ መነሻዎች ወደ ጎን ትቶ፤ ሌሎችን ማስተካከሉ ላይ ነው። ለውጥ ሲደረግ፤ መነሳት ያለባቸው ሰዎች፤ አሁንም አድራጊ ፈጣሪ ሆነው መገኘታቸው ነው። በዐማራው ክልል ሆነ በደቡብ ክልል፣ አሁንም የኢሕአዴግ መሪ የነበሩ ናቸው በማስተዳደርና፤ የለውጡ መሪዎች ነን ብለው ተሰልፈው የሚገኙ። ማገናዘብ ያለብን፤ እኒህ ሰዎች ባሉበት ቦታ ከፍተኛ በደል በሕዝቡ ላይ በደል ፈጻሚ ነበሩ። የተበደሉትና ከፍተኛውን መስዋዕትነት የከፈሉት ናቸው፤ የለውጡ ባለቤቶች። በምንም መለኪያ ቢሆን፤ ለውጡ የመጣባቸው ለውጡን ሊመሩ አይችሉም። አሁን እየታዬ ላለው ሁኔታ፤ ይህ ሀቅ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው።

ከላይ የተቀመጠው አሁን ያለውን መንግሥት አስመልክቶ ነው። ነገር ግን ያ ብቻ አይደለም ችግሩ። ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት የሚንቀሳቀሰው፤ በኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት ነው። ያ ብቻም አይደለም። ባሁኑ ሰዓት፤ በወታደራዊ ክፍሉ፣ በደህንነት መሥሪያ ቤቱና በመንግሥቱ አጠቃላይ መካከለኛ አመራር ላይ ተሰግስገው የሚገኙት የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ሰዎች ወይንም እነሱ በገንዘብ የገዟቸው ሰዎች ናቸው። እኒህ ሰዎች ሕልውናቸውን የተከሉት፤ ለትግሬዎቹ ገዥ ቡድን ጥቅም ነው። ዐማራ ሆኑ ሶማሊ፤ ኦሮሞ ሆኑ የደቡብ ክልል ስዎች፤ የሚወክሉት ሕዝብ ኖሯቸው ሳይሆን፤ ለሆዳቸው ለትግሬዎቹ ገዥዎች ተገዝተው የቆሙ ናቸው። እናም አሁን በትክክል የሚወክሉት ሕዝብ የላቸውም። ስለዚህ፤ የሚያገለግሉት ያንኑ አሳዳሪያቸውን ነው። በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየወሰዱ ያሉትን ትክክለኛ እርምጃዎች፤ ማድነቅ አለብን። ያ ግን መሠረታዊ አይደለም። የግለሰቦች መልካም ፈቃድ፤ የሀገርን ሂደት ወሳኝ መሆን የለበትም። አሰራሩ ነው ወሳኙ። ለውጡን ያመጣውን ክፍል አግልሎ፤ ወደፊት መሄድ አይቻልም። አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወክሉት ኢሕአዴግን እና ኦሕዴድን እንጂ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ አይደለም። ውክልና የሠጣቸው ኢሕአዴግ ነው። አሁንም የኢሕአዴግን መዋቅር ነው እየመሩ ያሉት። ይሄ ሁሉ በገዥው ክፍል ላይ ቢነሳም፤ በአንጻሩ ደግሞ አማራጩ ጨለማ ነው።

በተቃዋሚ በኩል እስከዛሬ የነበረውና አሁን በተፎካካሪነት አለን የሚለው ክፍል፤ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ፤ አንድነት የሌለው፣ ግልጥ ራዕይ ያላስቀመጠ፣ አማራጭ ሆኖ ያልተገኘ ነው። ቁጥሩ መብዛቱ ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ ድርጅት ራሱን ወደላይ ክቦ፤ ከማንም ጋር ላለመሥራት ችግሮችን ደርድሮ፤ “እኔ ነኝ!” እያለ ሲደነፋ ይገኛል። “ሌሎቹ አይረቡም!” የሚል ጉራም አለበት። ይሄ በሆነበት እውነታ፤ ይህ ክፍል፤ በሥልጣን ላይ ያለውን ክፍል፤ በምንም መንገድ ሊወቅስ አይገባውም። ራሱን አያውቅምና! ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ባንድ በኩል፤ ሀገር አቀፍ ነን የሚሉ በሌላ በኩል ተኮልኩለዋል። በጣም አጽናፋዊ አቋም ያላቸው፤ ኢትዮጵያዊነትን እርግፍ አድርገው ጥለዋል። በሀገር አቀፍ ዓላማ የተደራጁትም በመካከላቸው የርዕዩተ ዓላማ ልዩነት ሳይሆን የመሪዎች ልዩነት አንቋቸው፤ መቀራረብ አላሳዩም። መሰባሰብ ይጠቅማቸው ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ፤ ከገዥው ክፍል የሚለዩበትን የርዕዩተ ዓለም ጉዳይ፤ በግልጥ ለሕዝብ አላቀረቡም። የምርጫ ቀን መሆን የለበትም። ከዚያ በፊት፤ ለምን እንደተቋቋሙ መናገር አለባቸው። አማራጭነታቸው የምርጫው ወቅት አይደለም የሚሰመረው። ከዚያ በፊት ከሕዝብ ጋር ሲተዋወቁ፤ ማንነታቸውን መግለጥ አለባቸው። አዎ! የሀገራችን የፖለቲካ ሂደት በየቀኑ እየተለዋወጠ ነው።

ሀገራችን አሁን ካለችበት ወጥታ ወደፊት ለመሄድ፤ ሀገራዊ የሆነ ራዕይ፣ መስማሚያ ጉዳይ፣ አሰባሳቢ መድረክ ያስፈልገናል። ሕዝቡ የኔ የሚለው መንግሥት በቦታው መቀመጥ አለበት። ድክመቱ ያለው በሁሉም ወገን ነው።

አሁን ወዳለንበት ሀቅ ስንመለስ፤ የለውጡ ሂደት እየተካሄደ ያለው፤ የኢሕአዴግ አባል ሆነው፤ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉ ጥቂት ግለሰቦች፤ የሚችሉትን በማድረግ ነው። እንግዲህ የለውጡ ግስጋሴና ጥልቀት፣ የለውጡ ፍጥነቱና ይዘቱ፤ በኒሁ ግለሰቦች ፍላጎት ይመራል ማለት ነው። ይህ በጣም ሊያሳስበን ይገባል። ይሄንን ሊያደርጉ የምችሉት ደግሞ፤ የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት በፈቀደላቸው መሠረት መሆኑን ከላይ አስፍሬያለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታጋዩን ክፍል ልብ ሰልለው፤ “ለውጡ እኔ ነኝ። የማሸጋግርህ እኔ ነኝ። የሽግግር መንግሥቱ እኔ ነኝ! ከፈልግህ ተደራጅና፤ እኔ አስመራጭ፣ ምርጫ አዘጋጅ፣ የምርጫ ሂደቱን ተከታታይ በሆንኩበት ምርጫ፤ የሽግግሩን ዘመን ከጨረስኩ በኋላ ተሳተፍ!” ብለው ቁጭ አሉ።

ወደፊት እንሂድ። አሁን ለውጡን የሚመሩት፤ መጀመሪያ ሕጋዊነት ያግኙ። የኢሕአዴግ ሕጋዊነት በለውጡ እውነትነት ፈርሷል። የሕዝቡን ውክልናን ለማግኘት፤ የፖለቲካ መሠረታቸውን ማስፋት አለባቸው። ይህ ማለት፤ የሕዝቡን ታጋዮች ያካተተ መንግሥት ማለት ነው። ይህ ሰቅዞ ከያዛቸው የኢሕአዴግ ሰንሰለት ነፃ ያወጣቸዋል። ቆራጥ እርምጃ እንዲወስዱ ይፈቅድላቸዋል። ሕዝቡ የኔ ብሎ እንዲከተላቸው በር ይከፍትላቸዋል።

በተፎካካሪው ክፍል ያሉት ደግሞ፤ ትክክለኛ አማራጭ ሆነው መቅረብ አለባቸው። ዓርማ መለጠፍ፣ መርኀ-ግብር ማውለብለብ፣ መሪዎችን ባደባባይ ማዞር ብቁ ድርጅት መኖሩን አያሳይም። መጥቆ የወጣ ራዕይ፣ የተጠናከረ ድርጅትና በዛ ያሉ አባላት፣ የሚመዘን ተልዕኮና በግለሰቦች ፍላጎት ሳይሆን በድርጅታዊ አሰራር የሚመራ የፖለቲካ ድርጅት ሆነው መገኘት አለባቸው። ያ አለ ወይ?

Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ

በረራ፤ የ፲፭ኛው ከፍለ ዘመንና የ፲፮ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነገሥታት ከተማ

Berara - በረራየጽሑፉ ጭምቅ ይዘት፤

በረራ፤ የ፲ ፭ኛው ከፍለ ዘመንና የ፲ ፮ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነገሥታት ከተማ (ኢትዮጵያ)፤ በየረር ተራራና ወጨጫ ሸንተረሮች፤ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን እና ከዚያ ቀደም የነበረ ሕዝብ ሰፈራ፤ የቅርብ ጊዜ የምርምር ጥናቶች ውጤት፤

ይህ ጽሑፍ፤ የበረራን እና በ፲ ፭ኛው ከፍለ ዘመን እና በ፲ ፮ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበሩ የሰፈራ ቦታዎችን ታሪክኅ ዞሮ ይመረምርና፤ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የሆነችውን በረራን፤ ቦታዋን ለይቶ፤ በደቡብ ሸዋ፤ በአሁኗ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፤ አዲስ አበባ ከተማ አቅራቢያ፤ መሆኗን ለማመላከት የታሰበውን የመስክ ጥናት ውጤቶችን ይገልጣል። ታሪካዊ ምንጮች እና የሳተላይት የጥልቀት ዕይታዎች፣ የመልክዐ ምድር አቀማመጥ ሁኔታዎች እና ተጨባጭ የአካባቢ መሬት ጥናቶች ላይ በመንተራስ፤ ደራሲዎቹ ወደኋላ ወደ ቅድመ መካከለኛው ክፍለ ዘመን የሚደርሱ የሚመስሉ አዳዲስ ቦታዎችን በማሳወቅ፤ ረጅሙን እና የኢትዮጵያ የዚህ አካባቢ አስካሁን ያልታወቀ ታሪክ አሳይተውናል። ሆኖም ግን፤ በረራን በትክክል ቦታው ላይ ማስቀመጡ አዳጋች ሆኗል። እናም የመካከለኛው ዘመን በኢትዮጵያ የክርስቲያን “ከተሞች” ዕውቀታችን እንዲዳብርና እስካሁን በትክክል ያልተጠናውን ለሕዝቡና ለባህሉ እንቅስቃሴው ማዕከላዊ የሆነውን የዚህ አካባቢ የቅድመ መካከለኛው ዘመን ታሪክ እንዲገልጥልን፥ ተጨማሪ ጥናቶች ያስፈልጋሉ።

( ሙሉውን በፒዲኤፍ ለማንበብ ይሄን ይጫኑ –>  የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጥራዝ ፪ ሺህ ፩ – ፪ ቅጽ ፳፬, ገጽ ፪፻፱ እስከ ፪፻፵፱

Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ

ወደ ፊት ለመሄድ

አሁን ካለንበት ተነስተን ወደፊት ለመሄድ፤ የግድ የነበርንበትን ማወቅ አለብን። የነበርንበትን ማወቅ የምንችለው፤ ታሪካችንን ስናጠና ነው። ታሪካችንን የምናጠናው፤ ከዚያ በጎው ከሆነውም ሆነ በጎ ካልሆነው ትምህርት ለመውሰድ ነው። ታሪካችንን ካላጠናን፤ ከዚያ የነበረውን ስህተት አንማርበትምና ልንደግመው እንችላለን።

Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ

ዐማራው ያለበት ሁኔታና የወደፊት ጉዞው አቅጣጫ ( ክፍል ፩ )

ዐማራው ያለበት ሁኔታና የወደፊት ጉዞው አቅጣጫ ( ክፍል ፩ )
አንዱዓለም ተፈራ
ነሐሴ ፰ ቀን ፳ ፻ ፲ ዓ. ም.

ከምን ተነሳን? ( የመጀመሪያው ጉዳይ )

ዐማራው አሁን ያለበት ሁኔታ፤ እስከዛሬ ከደረሰበት በደል የተነሳ የወደቀበት አዘቅት ነው። ይሄን ረግጦ በመነሳት፤ ወደፊት ጥሶ መሄድ ያስፈልጋል። ስለፈለጉ ብቻ ግን፤ ወዳሰቡት ቦታ መሄድ አይቻልም። መመርመር አለ። ማቀድ አለ። ማመቻቸት አለ። መተግበር አለ። ይህን ሂደት፤ መመርመሩን እና ማቀዱን፣ ማመቻቸቱን እና መተግበሩን፤ ከኛ ውጪ ላሉ፤ ለሌሎች መሥጠት አንችልም። እኛው ራሳችን፤ የኛ የራሳችን ጉዳይ ነው ብለን፤ ባለቤትነቱን ወስደን፤ ተግባር ላይማዋል አለብን። በኔ በኩል፤ ከዚህ በማከታተል፤ የነበረውን ተመልክቼ፣ አሁን ያለንበትን አካትቼ፣ ወደፊት ልንጓዝ ወደ ምንፈልገው ግባችን የሚወስደንን መንገድ ተልሜ፤ አሁን ማድረግ ያለብንን እጠቁማለሁ።

የዐማራው የሕልውና ጉዳይ መልክ ያበጀው፤ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ገና ሲመሠረት፤ “በዐማራው መቃብር ላይ፤ የትግራይን ሩፑብሊክ እመሠርታለሁ!” ብሎ በወረቀቱ ላይ ያሰፈረ ጊዜ ነው። ከዚያ ቀጥሎም በ፲ ፱ ፻ ፸ ፪ ዓ. ም. ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይት ሲገባ፤ ሕዝቡን ስብስቦ፤ “ከዛሬ ጀምሮ እናንተ ትግሬዎች ናችሁ! የምትናገሩት በትግርኛ ብቻ ነው! የምታለቅሱት በትግርኛ ብቻ ነው! የምትዘፍኑት በትግርኛ ብቻ ነው! አቤቱታችሁን የምትጽፉት በትግርኛ ብቻ ነው። የምትጽፉትም ለኛ ብቻ ነው!” የሚል አወጀ። ወልቃይትን ከ፲ ፱ ፻ ፸ ፪ ዓ. ም. ጀምሮ፤ በአዋጅ ትግራይ አደረጋት። አውራ ላይ ከኢሕአፓና ከሕዝቡ ትልቅ ጦርነት ገጠመው። ወጣት የትግራይ ልጆችን ማገደ። ነገር ግን፤ ኃላፊነቱ ለወጣቱ ነፍስ ሳይሆን፤ ለዓላማቸው ነበርና፤ የማገደውን ማግዶ ወልቃይትን ተቆጣጠረ። ወደ ጠለምት አመራ።

በዚህ ጊዜ፤ የጠለምት፣ የብራ ዋስያ፣ የወልቃይትና የጠገዴ አርበኞች፤ “እኛ አርሶ አደሮች ነን። መንግሥት ከሆናችሁ፤ ዋና ከተማውን ያዙና፣ ከዚያ ሆናችሁ ስትጠይቁን፣ ግብራችን እንልካለን። በዚህ በቦታችን ግን ተውን! እኛ ማንነታችንን ራሳችን እናውቃለን! ሌላ ሰው ማንነታችን አይነግረንም! እኛ ትግሬዎች አይደለንም! እኛ ዐማራዎች ነን!” በማለት፤ “ከፋኝ!” ን አቋቁመው፤ ትግላቸውን ጀመሩ። በቀጥታ ማጥፋት ስላልቻለ፤ በካህናት ልመናና ሽምግልና በማባበል፤ የመጀመሪያውን መሪ፤ ገብረመድሕንን በዕርቅ አባብሎ አስገብቶ ገደል። በመቀጠል፤ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ መንግሥት የሚያደርገውን ግፍና በደል በመቃወም፤ ሕዝቡን መቀሰቀስ ሲይዙ፤ ኢትዮጵያ የብሔርና ብሔረሰቦች ስብስብ እንጂ፤ ኢትዮጵያዊ የሚባል ሕዝብ የለም ስለተባሉ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያሰቡትን ተገደው፤ የመላ ዐማራ ሕዝብ ድርጅትን በማቋቋም፤ ትግላቸውን ገፉ። ነገር ግን፤ ከሁሉም በላይ ዐማራውን ይፈራ የነበረው የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ የዐማራውን ትግል ለማጥፋት እሳቸውን መግደል አስፈላጊ ነው ብሎ በማመን፤ እሳቸውን ለሞት ዳረጋቸው።

የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር፤ በመርኀ-ግብሩ እንዳሰፈረው፤ ዐማራውን ማጥፋት ዋና ጉዳዩ ነበርና፤ ባቋቋማቸው ተቀጥላ የብሔር ድርጅቶቹ አማካኝነት፤ የራሱን መንግሥት ሲያቋቁም፤ ዐማራው ያላተሳተፈበት ሕገ-መንግሥት አረቀቀ። በሕገ-መንግሥቱም ዐማራው ስፍራ እንዳይኖረው ተደረገ። ዐማራው በዐማራነቱ የሕዝብ ጠላት ተደረገ። ከየመሥሪያ ቤቱ ተባረረ። የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር በአጠራቸው ክልሎች ውስጥ፤ ዐማራው እንዲጨረስ፤ በአሽከሮቹ በነ ታምራት ላይኔ አማካኝነት፣ ተገደለ፣ ተፈናቀለ፣ ተሰደደ፣ ተዘረፈ፣ ታሰረ፣ የሁለተኛና የሶስተኛ ደረጃ ዜግነት እንኳን ተነፈገው። ከ “ደቡብ ኢትዮጵያ” ከ “ኦሮሚያ” ከ “ኢትዮጵያ ሶማሊያ” ከ “ትግራይ” የዐማራ ሰው እንዳይገኝ ተገፋ። ይብስ ብሎ፤ በራሱ በ “ዐማራ” ክልልም የትግሬዎቹ የበላይነት ነገሠበት። ዐማራው ቤት የሌለው ሆነ። በደል ምን ጊዜም በደሉን የሚቃወም ያፈራልና፤ ዐማራው በእምቢተኝነት ትግሉን ሳያባራ ቀጠለ።

በከፋኝ የጀመርነው ሰዎች፤ በራሳችን ድክመትና በሁኔታው አለመመቸት፤ ስንከፋፈልና ስንነቃቀፍ፤ መሸናሸንና መበታተን ተከተለን። ፕሮፌሰር አስራትም ከዕረፍታቸው በኋላ፤ ትክክለኛ መሪና ትክክለኛ መርኅ ባለመኖሩ፤ መዐሕድ ተዳከመ። ይሄም ሆኖ፤ ባንድ መልኩም ሆነ በሌላ፤ የዐማራው ትግል አልቆመም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ ክስተት ተፈጠረ። በወያኔ አገዛዝ ውስጥ ያደጉ ትንታግ የዐማራ ወጣቶች፤ የዐማራ ብሔርተኝነትን በማንገት፤ ቤተ ዐማራ ብለው ብቅ አሉ። እኒህ ወጣቶች፤ አዲስ ፈር ቀደው፣ ወጣቱን በራሱ እንዲተማመን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። የኛው አባዜ አልለቃቸው ብሎ፤ ባንድነት እንደጀመሩት መቀጠል አቅቷቸው፤ እነሱም በመከፋፈል ተዳከሙ። የጀመሩት የዐማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ግን አልበረደም።

እንግዲህ በዚህ ሁሉ አልፈን ነው እዚህ የደረስነው።
እዚህ አሁን ያለንበትን ሁኔታ በሚቀጥለው በክፍል ፪ አቀርባለሁ።

Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ

እና ዐማራ!

እና ዐማራ!
አንዱዓለም ተፈራ
አርብ፣ ነሐሴ ፬ ቀን፣ ፳፻፲ ዓመተ ምህረት

ለውጡ እስካሁን በጀመረው መንገድ ይሄዳል የሚል ተስፋ ሁላችን ሰንቀናል። ባሁኑ ጊዜ፤ መሠረታዊ የሆኑት የኢሕአዴግ የአስተዳደር መተክሎቹ እንዳሉ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ፤ የዘር ፖለቲካው ባጭር ጊዜ ውስጥ እንደማይለውጥ አስምረውበታል። ከውጪና ከውስጥ የዘር ፖለቲከኞች የሰላ የመቀራመቻ ስንጢያቸውን አሰልስለው “የኔ!” “የኔ!” ታቸውን ተያይዘውታል። በዚህ ሂደት አንድነት የሌለው የዐማራው የድርጅቶች ጋጋታ፤ ቁጥሩ የሚጨምርበት እንጂ፤ ወደ አንድ የሚሰባሰብበት ሁኔታ አይታይም። እና ዐማራ!

የሾህ አጥር በመካከላችን ማበጀቱን ትተን፤ ይሄን ጉዳይ የሁላችን አድርገን መነጋገር እንችላለን። የዐማራው ጉዳይ የእከሌ ወይንም የእከሊት አይደለም። የሁላችንም ነው። የአንድ ድርጅት ወይንም የሌላም አይደለም። የዐማራዎች በሙሉ ነው። ይሄን ጉዳይ ደግሞ ካልተነጋገርንበት፤ ሌላ ከዚህ የከበደ ምን አለ? ሀቁን መመልከትና እውነቱን መነጋገር አለብን። በዐማራው ላይ የተደረገው ጭፍጨፋ፤ በዐማራነት እንጂ፤ ግለሰቦች በሠሩት ተግባር የተመሠረተ አይደለም። ይህ ሆን ተብሎ ታምኖበትና በመምሪያ በተግባር የዋለ በመንግሥት ደረጃ የተከናወነ ጥፋት ነው። እናም ዐማራ የሆን ሁላችን፤ ልንቆረቆርበት ይገባናል። ባሁኑ ሰዓት የዐማራውን የፖለቲካ ምህዳር አጣበው የያዙት፤ የብሔረ ዐማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብዐዴን) እና የዐማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዐብን) ናቸው። የዐማራ ጉዳይ ደግሞ፤ የብዐዴን ወይንም የዐብን ብቻ፤ የግል ጉዳይ አይደለም። የብዐዴን አመራር፤ ከመካከለኛው መንግሥት ጋር ሆኖ፤ ሀገር የመምራትና ሀገር አቀፍ ፓርቲ የመመሥረት ዓላማ ያለው ይመስላል። ዐብን ደግሞ፤ እኔ ነኝ የዐማራ ብሔርተኝነት ማዕከል ብሎ፤ በብቸኝነት ቢሮዎቹን በየቦታው በመክፈት ላይ ነው። የነኝህ የየራሳቸው ሩጫ፤ ዐማራውን ይጎዳዋል። እኒህ ሁለቱ፤ አንዳቸው አንዱን አጽናፍ፤ ሌላቸው ሌላኛውን አጽናፍ ይዘው የሚጓተቱበት መሆን የለበትም። ሁለቱም በየበኩላቸው የየራሳቸው ጥናካሬና ድክመት አላቸው። በኔ በኩል፤ እኒህ ሁለቱ ቢጣመሩ ጥንካሬያቸው አይሎ፤ ሁሉን ዐማራ ሊወክሉ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል እምነት አለኝ።

የዐማራ ሕዝብ አንድ ነው። ለዐማራው የሚቆም ደግሞ ባንድ መሰለፍ አለበት። ይህ ለዐማራው መቆም፣ የርዕዩተ ዓለም ባለቤትነትን አይጠይቅም፣ አያካትትም፣ አያስፈልገውም። ይህ ለአንድ ወገን የመቆርቆር ጉዳይ ነው። ተቆርቋሪዎች ደግሞ፤ በሙሉ በአንድነት ተሰባስበው መመካከር አለባቸው እንጂ፤ ወዲያና ወዲህ ሆነው መጓተት የለባቸውም። ከዚህ በመነሳት፤ ለዐማራው እንቆማለን ያሉት በሙሉ፤ የየድርጅታቸውን ጥንካሬም ይሁን ድክመት ሳይመዝኑ፤ ለዐማራው መቆም አለባቸው። እናም አንድ የዐማራ ጠንካራ ድርጅት ነው የሚያስፈልገው። ብዐዴንና ዐብን ወደ አንድ መምጣት አለባቸው ስል፤ ከዚህ እምነት በመነሳት ነው። ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮነንና ለዐማራው ፕሬዘዳንት ገዱ አንዳርጋቸው፤ ከኦሕዴድ በፊት፤ አብን ይቀርባቸዋል። ከኦሕዴድ ጋር ከመደራደራቸው በፊት፤ በዐማራው በኩል ያለውን በአንድነት ቢመሩት፤ ለራሳቸውም ጥንካሬ፤ ለዐማራውም ትክክለኛ ውክልና ይኖራል።

የሁለቱን ድርጅቶች ድክመት እዚህ ላይ ማተቱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያይል አልሄድበትም። ጥንካሬያችውን ስንመለከት ደግሞ፤ በብዐዴን በኩል፤ መንግሥታዊ መዋቅር፣ ንብረትና ግዝፈት አለው። በዐብን በኩል ደግሞ ወጣቱ፣ የጠነከረ የዐማራነት ብሔርተኝነትና ትኩስነት አላቸው። እኒህ የሁለቱ ወገኖች ጥንካሬዎች ባንድ ላይ ሲጣመሩ፤ ከፍተኛ የሆነ የደቦ ጉልበት ይፈጥራሉ። በሕዝቡ ዘንድ ደግሞ ቀስቃሽ ስሜትን ፈጥሮ፤ ብዙዎችን ያነሳሳል። እስኪ በያላችሁበት ይሄን ምከሩበት።

Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ

ድልድይ የሌለው ተቆርቋሪነት

ድልድይ የሌለው ተቆርቋሪነት
አንዱዓለም ተፈራ
ማክሰኞ፤ ነሐሴ ፩ ቀን ፳ ፲ ዓመተ ምህረት

ድልድይ ሁለት ጎን ለጎን የሆኑ ቦታዎችን ያገናኛል። ድልድይ በሌላቸው ቦታዎች የሚገኙ ሰዎች፤ መገናኘት ያስቸግራቸዋል። ባንጻሩም፤ ከትናንት ወደ ዛሬ የሚያሸጋግር ድልድይ ከሌለ፤ ዛሬ ትናንት የተሠራውን እንደገና እንዳዲስ በመሥራት ይጠመድና፤ ዛሬ ሁልጊዜም ትናንትን እንደሆነ ይቀጥላል። ይህ ነው በኢትዮጵያ፤ ለሕዝብ ተቆርቋሪዎች የእንቅስቃሴ ሂደት፤ በተደጋጋሚ እያየን ያለነው። ከትናንት መማር እያቃተን፤ ዛሬም የትናንቱን መልሰን ስንዳክርበት እንገኛለን። ለምን? መማር ስለማንችል አይደለም። የትናንቱ ስላልተመዘገበም አይደለም። የማስተላለፉ ሥርዓት በትክክል ስላልተከናወነ ነው። የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ይህ ነው።

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፤ “በአቸነፈ እና በአሸነፈ የተላለቃችሁ!” ብለው ያስቀመጡትና አዳራሹን የሞላው ያጨበጨበበት፤ ብዙ ሕይወት ያለፈበትን የሁለት የተለያዩ የፖለቲካ አሰላለፎችን ትግል አቅልለው በማስቀመጣቸው ቢሆንም፤ ይህ የግል ስህተታቸው ሳይሆን፤ በብዙኀኑ ተቀባይነት ያለው መሆኑ ነው። አጨብጫቢዎቹ ስለ ነበረው ትግል ያላቸው ዕውቀት አነስተኛ ነው። በስድሳዎቹ የነበርነው ተማሪዎች፤ ስለ ሀገራችን ታሪክ፣ ስለ አርበኞቻችን ተጋድሎ፣ ስለ መንግሥት ሂደት፣ ስለ ታሪክና ማንነት የነበረንን ዕውቀት በግሌ ስመለከተው፤ ጎደሎ ነበር። እንዲሆን የምንፈልገውን፤ ከሀገራችን ታሪክና ተጨባጭ እውነታ ጋር አላጋባነውም ነበር። እዚህ ላይ፤ እኔ ሁሉን ወክዬ ሳይሆን፤ በግሌ ሁን የማምንበትን ነው የማስቀምጠው። እናም በተማርነው መሠረት፤ ለሁሉም ነገር ፊታችንን ያዞርነው ወደ ውጪ ነበር። ከትናንታችን የወረስነው አጥተን ሳይሆን፤ በቀጣይነት ያስረከበን ድልድይ አልነበረውም። ይህ ትልቅ ስህተት መሆኑን አምናለሁ።

ደርግ፤ ከትናንት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቆርቋሪዎች ለዛሬዎቹ ምንም ዓይነት መወራረስ እንዳይኖር፤ ትውልዱን ጨረሰው። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አነጋገር፤ በዚያ ወቅት ደርግ ባደረገው የትውልድ መጨረስ፤ በተተካ የፈጠራ ትረካ ውጤት ነው። መተላለቁ፤ በአንድ ቃል ሁለት አጠራር ላይ የተመሠረተ አልነበረም። መግለጫውን እንደ ዋናው ቁም ነገር መውሰድ፤ ስህተት ነው። ከዚያ በኋላ የተከተለው የፖለቲካ ታጋይም ሆነ የተማሪ ተንቀሳቃሽ፤ ሀ ብሎ እንደገና መፍጠር ነበረበት። ልምዱም ሆነ ግኘቶቹ ለቀጣዩ ትውልድ አልተላለፉለትም። ጉድለቶቹም ሆነ ጥንካሬዎቹ በትክክል አልተነገሩትም። በዚያው በደርግ ጊዜ የተደረጉት ግድያዎችና የቀይ ሽብር ዕልቂቶች በትክክል ተመዝግበው አልተላለፉም። የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ዙፋኑን ዘርፎ፤ ራሱ ያደረጋቸው ጭፍጨፋዎችና ግድያዎች፤ አሁንም ሳንማርባቸው ተድበስብሰው ወደፊት መቀጠሉ፤ እየተንደረደርንበት ስለሆነ፤ ትምህርት ሳናገኝ፤ ነገ እንዳይደገም ሰግቻለሁ።

አዲሱ ወጣት፤ አዲስ ትግል ብሎ፤ እንደገና ከ ሀ እየጀመረ መቀጠሉ፤ ወደፊት የሚባል ሳይሆን፤ ባለህበት እርገጥ የሚል ጉዞ ላይ ያስቀምጠናል። ከትናንቶቹ በጎ የሆኑና ግድለቶች አሉ። ያን መርምረን፤ ከዚያ መማር ካልቻልን፤ የዚያ ጊዜ ድከመቶችን ተሸክሞ መጓዝና መድገሙ አይቀሬ ነው። ለምን? የስድሳዎቹ ተማሪዎች እንቅስቃሴ መሪዎች ምን ጥሩ ነገር ሠሩ? ምንስ ድክመት ነበራቸው? ከነሱ በፊት የነበሩት ምሁራንስ? ደርግስ? የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባርስ? ነገ የሚከተለውስ? ያን ማሰብና መመርመር ካልቻልን፤ በድክመቶቻቸው ተዘፍቀን፤ ያንኑ እያሸተትን፣ ከዚያው የማንወጣ እንሆናለን።

Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ

የለውጡን መሠረታዊ ምክንያትና ዓላማ መሳት የለብንም።

የለውጡን መሠረታዊ ምክንያትና ዓላማ መሳት የለብንም።

አንዱዓለም ተፈራ
አርብ፣ ሐምሌ ፳ ፯ ቀን ፳ ፻ ፲ ዓመተ ምህረት ( 8/3/2018 )

አለባብሰው ቢያርሱ፤ ባረም ይመለሱ!

አሁን በሀገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ለውጥ፤ በተለይ በዐማራ፣ በኦሮሞ፣ በኢትዮጵያዊ ሶማሊ ወጣቶች፤ ባጠቃላይም በኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘ ነው። ይህ ለውጥ፤ ኢሕአዴግ መራሽ አይደለም። ይልቁንም ለውጡ በኢሕአዴግ ላይ የተነሳ ነው። የለውጡ ዒላማ፤ ኢሕአዴግና የኢሕአዴግ የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ ናቸው። ኢሕአዴግ፤ የመለስ ዜናዊ፣ የበረከት ስምዖን፣ የሺፈራው ሽጉጤ፣ የአብዲ ኤሊና አሁንም በየቦታው ተሿሹመውና በወታደሩም ውስጥ በጄኔራልነታቸው ብዙውን የሀገራችንን ሀብት እየተቆጣጠሩ ያሉት፤ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎች ድርጅት ነው። ወጣ ካለም ለነሱ ሲያገለግሉ የነበሩ አድር ባዮች የተሸከሙት ድርጅት ነው። ይህ ነው ሕዝብን ያፋጀ፤ በሙስናና በአድልዖ የተሞላ፣ የአንድ ወገኑ የኢሕአዴግ ሥርዓት። ይህን ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቃኝ ያለው። የለውጡ መሠረታዊ ምክንያትና ዓላማ ይህ ነው።

አሁን ፈጠው ያሉት ጥያቄዎች ግልጥ ናቸው። አንደኛ ለውጡን ያልፈለገው አምባገነኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ መቀሌ መሽጎ፤ አሁንም ዘረኛና ለትግራይ ሕዝብ አደገኛ የሆነ ዝግጅት ይዟል። በሌላ በኩል፤ አዲስ አበባ ኢሕአዴግ ለውጥ እያካሄደ ነው። ማለትም ኢሕአዴግ በኢሕአዴግ ላይ ለውጥ እያካሄደ ነው። ዋናው ጠላት መቀሌ ላይ መሽጎ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚችለውን ያህል ሁሉ እየሸረበ ያለው የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ነው። በዚህ ላይ ምንም ዓይነት ብዥታ ሊኖር አይገባም። ይሄን ክፍል ጠላቴ ብሎ የፈረጀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። እናም ለውጡን መምራትም መግፋትም የሚችለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ለውጡን ያመጡትና ከፍተኛውን መስዋዕትነት የከፈሉት ተመካች እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። ማን ባመጣው ለውጥ ነው፤ ማን ተመልካች የሚሆነው? ማን እንዲወገድ ነበር፤ ብዙዎቹ ሕይወታቸውን የገበሩት? ይህ ማለት፤ በትግሉ የተሳተፉትና ግንባር ቀደም ሆነው የተደራጁ ወገኖች፤ ለውጡን ከሚፈልገው የኢሕአዴግ ክፍል ጋር በመሆን፤ ትክክለኛ ለውጥ እንዲመጣ፤ አብረው የሽግግር ወቅቱን መምራት አለባቸው።

መመንጠር ያለበት፤ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው የሕዝብ ጠላት ነው። ይህ ደግሞ በትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፤ በሌሎቹን ይህ ቡድን በመሠረታቸው የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥም ነው። አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ እንዳይሆን! ለኔ እስካሁን ጥሩ ተሠርቷል። በዚህ ግን ብዙ መሄድ አይቻልም። ለውጥ አምጪው ክፍል የተሳተፈበት ብቻ ነው፤ ትክክለኛና ዘለቄታነት ያለው ለውጥ የሚያመጣው። ሀገራችን ደግሞ፤ ላለፉት አርባ አምስት ዓመታት ብዙ ደምታለች። ደሙ ያብቃ። የተወሰኑ ሰዎች ሀገር ቤት ለመግባት በመጓጓት የሀገራችንን የፖለቲካ ማህደር ቢኳኩሉት፤ መልኩ እንጂ ውስጣዊ ይዘቱ አይቀየርም። አሁን መሠረታዊ ለውጥ ሥር እንዲሰድ አመቺ ሁኔታዎች አሉ። ለዚህ የለማ ቡድን ምስጋና ይገባዋል። ነገር ግን የለማ ቡድን እየመራው የሚካሄድ ከሆነ፤ ዘለቄታ የለውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመራውና የሚሳተፍበት መሆን አለበት። ይህ ለውጥ ከዚህ ቡድንና ከኢሕአዴግ በላይ ነው። እናም የሽግግር መንግሥት መቋቋሙ የግድ አስፈላጊ ነው።

Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ