የኛ ነገር ክፍል ፪

የኛ ነገር  ክፍል ፪

አንዱ ዓለም ተፈራ፤  ሰኞ፣ ጥቅምት ፲ ፭ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፬ ዓ. ም.

ሥልጠናው ይሄ ነው የሚባል ባይሆንም፤ ለትሕነግ ያለው ጥላቻ፤ የተሠጠውን ሥልጠና በደንብ እንዲከታተል ረድቶት፤ ልቡ ሞላ። ከሠልጣኞቹ ሁሉ የተሻለ ሆኖ ተገኘና፤ ጉብዝናው ታውቆለት፤ ለበለጠ ሥልጠና፤ የመደበኛ ወታደሮች ወዳሉበት ተላከ። የተዋጊ ዕጥረት ስለነበር፤ ሥልጠናውን በደንብ ሳይጨርስ፤ እሱ ያለበት ቡድን ወደ ግንባር ተጠራ። ምን ያደርጋል፡ በጣም ጓጉቶ የተቀላቀለው ክፍል፤ እሱን ወደ መሐል እንዲገባ አልፈቀደለትም። ምክንያት ተብሎ የተነገረው፤ “ይሄን መሪ ሆኖ የሚታገለው መከላከያ ነው!” የሚል ነው። እሱ በዚህ ደስተኛ አልነበረም።

“እኔ ነኝ ባለቤቴን የተነጠቅሁ! የኔ ርስት ነው የተወሰደው! የኔ ከብቶች ናቸው የታረዱት! ጎጆዬን፣ ንብረቴን፣ ሚስቴን፣  ቀንና ሌሊቴን የተነጠቅሁት እኔ እያለሁ፤ ምን ባይ ነው መሪ የሚጣልብኝ!” ብሎ አኮረፈ። ቋዝሞ ከተቀመጠበት አሻግሮ ሲመለከት፤ እንደሱው ቆዝመው የተቀመጡ ሌሎች መኖራቸውን ዓዬ። ዙሪያውን ዓይኖቹን ለቆ ሲያማትር፤ ስብስብ ብለው ከተቀመጡ ሶስት ወጣቶች ጋር ዓይኖቻቸው ተገጣጠሙ። የተሰባሰበው ፊቱና የተጨመቁት ዓይኖቹ ፈታ አሉ። የተሰቀዘው ልቡ ተስፋ አገባ። እነሱም የፈገግታ ፊት አሳዩት። ዓይኖቹን መለሰና፤ ወደ መሬት እያየ የተሠጠውን አሮጌ የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ጠበቅ አደረገ። አዛዣቸው የተነሱ ጥሪ አስተላለፈና፤ ሁሉም ወደየምድቡ አመራ። የመከላከያ ወታደሮች ፈጠን ብለው ሲራመዱ፣ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ፈጠን ብለው ሲራመዱ፣ ፈተናና ሶስቱ ወጣቶች ረጋ ብለው ነበር ወደ ተጠሩበት የሚሄዱት።

ፈተና ወደ ወጣቶቹ ሲጠጋ፤ “ከየት ነው የመጣችሁ!” አላቸው። ከመካከላቸው ተለቅ ያለው፤ “እኛ ከአዘዞ ነው አሁን የመጣነው። ከዚያ በፊት ግን፤ ባድሜ ነበርን።” አለው። “ባድሜ ምን ጣላችሁ? ወታደሮች አትመስሉም!” አለ። “አይ! ቀደም ሲል አባታችንና እናታችን እዚያ ይኖሩ ነበር።” ብሎ ዝም አለ። በሆዱ ምን ሊያደርጉ ባድሜ ወላጆቻቸው እንደሄዱ ሲያብላላ፤ “ወላጆቻችን እዚያ ይኖሩ ነበር። ነጋዴዎች ነበሩ። እኒህ ምናምንቴዎች ጦርነት ሲከፍቱ፤ እዚያ የነበረውን አማራ ሁሉ መፍጀት ጀመሩ። ከኛ ቤት መጥተው፤ እናታችን አረዷት። አባታችን ከራሱ ሱቅ አውጥተው ረሸኑት። እኔ ለሱቃችን ሽቀጥ ላመጣ ገበያ ወርጄ ነበር። እኒህ ሁለቱ መንታ ወንድሞቼ ደሞ፤ ትምህርት ቤት ቀርተው፣ እናቴ ለታመመች ጎረቤታችን ምሳ አዘጋጅታ ስጧት! ብላ ልካቸው ነበር። ከሩቅ በቤታችንና በሱቃችን የሆነውን ዓይተው ሮጠው ወደኔ መጡ።

ሲነግሩኝ አላመንኩም ነበር። አድብተን ወደቤታችን ስንጠጋ፤ በማምለጥ ላይ ያሉ አንድ አማራ ሽማግሌ፤ ‘እናንተ ሞኞች፤ ጥፉ ከዚህ! ወላጆቻችሁን ገድለዋቸውል! እናንተንም አይምሯችሁም! ነፍሳችሁን አውጡ!’ አሉን። ከዚያ ከሳቸውና ከሌሎች እያመለጡ ያሉ አማራዎች ጋር ተደብቀን ወደ መከላከያ ተጠጋን። መከላከያ ወደ አዘዞ ሸኘን።” አለና ዘርዝሮ አስረዳው። “እንደኔው የተበደሉ ናቸው!” አለና በጣም ለነሱ አዘነ።

ሁሉም የያዟቸው አሮጌ የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች ናቸው። ከመከላከያውና ከአማራው ኃይል ጋር አይነጻጸሩም። የጉዳዩ ባለቤቶች ግን እነሱ ናቸው። መከላከያዎች የነሱ ዕቃ ተሸካሚዎችና ቁስለኛ አሸሺዎች እንዲሆኑ ነው የሚፈልጓቸው። ይሄ ደሞ ለነፈተና አጉል ነው። በዚህ መሐል ሶስቱ ወንድማማቾች ይንሾካሾካሉ። የሚናገሩቱን በውል ባይሰማም፤ እንደሱው እንዳኮረፉ ገብቶታል። እነሱን፤ “ምን እያላችሁ ነው?” ብሎ ደፍሮ መጠየቁንም አልወደደም። በፈገግታ ብቻ ጉዳዩን ለማወቅ መፈለጉን የሚያሳይ ዕይታ ሠጣቸው። እነሱም የበለጠ ተቀራርበው መንሾካሾካቸውን ቀጠሉ። አሁንም ፈገግ እያለ ተመለከታቸው።

በመሐል ቤት፤ ትልቅየው ወደሱ ተጠጋና፤ “እኒህ ሰዎችኮ እኛን የትግሉ ባለቤት ቀርቶ፤ የሚያገባን አላደረጉንም። የተጎዳነው እኛ! ታዲያ በኛ ትግል እነሱ ባለቤቶች የሚሆኑበት ምን ዕጣ ነው!” አለው። ይቺ የስለላ መንገድ መክፈቻ ሃሳብ መሆኗ ገብቶታል። “እሱማ በኔም ልብ ያለ ነው!” አለና አቆመ።

“ታዲያ እስከመቼ እዚህ ስናረጠርጥ እንቆያለን!” ሲል መለሰለት። “እና ምን ይሻላል ትላላችሁ! አንተስ ማን ትባላለህ?” ብሎ ጠየቀው። “ኧ! እሱንማ አብረን እንምከር! ስሜ ያየሽ ነው።” ሲለው ደስ አለው። ያየሽና መንታ ወንድሞቹ ቆርጠው መነሳታቸውንና ለብቻቸው ሄደው፣ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አባላትን መግደል እንደፈለጉ ተረዳ። “ይህን ቅራቅንቦ ነፍጥ ብለንስ፤ ምናምንቴዎችን በዚህ ልንዋጋ አንሰለፍም! ተሹለኩከን ሄደን ከነሱ ታጣቂ ዘመናዊ መሳሪያ ነጥቀን እንታጠቃለን!” ብለው መዶለታቸውን አወቀ። እነሱም ደጋግመው፤ “ሠራዊቱ እናቱን አላጣም! ሠራዊቱ አባቱን አላጣም! ሠራዊቱ ርስቱን አላጣም! ከቤት ንብረቱ አልተባረረም! እንዳንተም ቤቱ አልተቃጠለበትም! መንደሩ አልፈረሰበትም!” አሉት።

“የለም በደንብ እናስብበት! ደሞ ረጋ ብለን፣ እንደኛው የተበደሉትን ይዘን፣ ጉልበት ከገነባን፤ የሚጠቅም ውጤን ማግኘት እንችላለን!” አላቸው።

“አይ ያንተ ነገር! እኛ፤ አንተ አገሩን ታውቃለህ! ከኛ ደሞ ትልቅ ስለሆንክ ትረዳናለህ! ብለን ነው እንጂ፤ የቁጥር መብዛት ፈልገን አይደለም። በል ተወው! ይሄን ሚስጢር ለማንም ብትናገር፤ አንተኑ እዚህ ደፍተንህ ነው የምንሄድ!” አሉት።

“አይ እናንት ምኞች! እኔ ሚስቴን የተነጠቅሁት! ቤት ንብረቴን ያጣሁት! ልጄን የበተነኩት! ካሁን ወዲያ ለምኑ እኖራለሁ ብላችሁ ነው! እንዲያው ደም መመለሱ ብቻ ሳይሆን፤ ወደ መጨረሻ መቃብራቸው ተያይዘው ሁሉም እንዲገቡና እንዲያልቁ ፈልጌ ነው እንጂ! ደሞ የናንተን ማስፈራራት፤ ከጉዳይ አላስገባውም። እውነትም ከቆረጣችሁ ግን፤ አብሬያችሁ ነኝ! የኔዋ ነፍስ እኒህን ምናምንቴዎች ለማጥፋት ተሰልፋለች! ከኔ ደግሞ እናንተ ሶስት ስለሆናችሁ፤ ባሰባችሁት እስማማለሁ!” አላቸው። አሁን ተግባቡ። ሁሉም ደስ አላቸው። እናም አብረው ለመጥፋት ይስማማሉ።

መሽቶ ሁሉም ወደ አዳሩ ሲያመራ፤ ሶስቱ ወንድማማቾችና ፈተና፤ ጨለማውን ተገን አድርገው፤ በመጣበት በኩል ወደ ቆላ ወገራ አቀኑ። ጨረቃዋ ወለል ብላ ወጥታለች። ተያይዘው የሚጸዳዱ መስለው ወደ ቁጥቋጦዎቹ አመሩ። በዚያ በኩል ወደ ገደሉ የሚወስደውን ታከው፤ ስልም አሉ። እኒህን ታጣቂዎች፤ ፈተናና ሶስቱ ወንድማማቾች ብቻ ሳይሆኑ፤ ያካባቢው ሰው በሙሉ ምናምንቴዎች! ነው ብሎ የሚጠራቸው። የሰው ዘር የሚያደርገውን አይደለም የሚያደርጉት! እንደ አውሬ እንኳ የራሳቸውን ሰው አያዝኑለትም። እምነትም ሆነ ውል የላቸውም። ዛሬ ለባላገሩ እንድ ነገር ተናግረው፤ ነገ ያፈርሱታል! እናማ እኒህ ምናምንቴዎች ናቸው! ብሎ ነው ሰው የተረዳቸውና የሚጠራቸው።

ከላይ ከደባርቅ ሆኖ መከላከያ ያወርድባቸዋል። ለካስ እሱ የሄደባትን መንገድ ተከትለው፤ ምናምንቴዎቹ ገስግሰዋል። አሁን እሱና ወጣቶቹ ወጥመድ ውስጥ ገብተዋል። ቁጥር ስፍሩ የማይታወቅ የምናምንቴዎች ታጣቂዎች እንደጎርፍ ይተማሉ። እነሱን አልፈው በዳባትና በደባርቅ መካከል ገብተዋል። በበለሳ በኩል ደሞ እየገፉ ናቸው። ወንድማማቾቹን ሰበሰበና፤ “ስሙ! እንግዲህ ወደ ኋላ መመለስ የሚባል ነገር አብቅቶለታል። አሁን ተማምለን አብረን መሞት ነው! የደባርቁ መከላከያ ይትረፍ አይትረፍ አናውቅም። የምታዩት የምናምንቴ ታጣቂ ምንትዬለሌ ነው! እንደ ደረሰ ጤፍ ታጭዶ ታጭዶ ካልተመተረ ማለቂያ የለውም። አስቤ የነበረው፤ ላሄንና ሻግኔ ገብተን፣ እስካዳርቃይ ባለው ጎራ እየተሹሎከለክን አንዳንዱን እያልን እንድናረግፍ ነበር። አሁን ግን ያን አይሠራም። በዚህ ዋልድባ መቃብር በኩል መሽገን፤ እኛው በመረጥነው ቦታና ጊዜ፤ ራቅ እያልን እያደባን ለይተን ማጥቃት ነው። ባንድ በኩል ደግሞ፤ እንደኛው ካሉት ጋር ግንኙነት አበጅተን መጎልበት አለብን። መላላኪያ መንገድ ማብጀት አለብን። ለትጥቁና ቀለቡ ምናምንቴዎች አሉልን!” ይላቸዋል።

ያየሽና ወንድሞቹ ተስማሙ። መመሸጊያ ቦታቸውን በመፈላለግ እያሉ፤ እንድ አንከስ እያለ የሚሄድ ከብት ጠባቂ ያገኛሉ። ከብቶቹ የሚታለቡ ላሞች ብቻ ናቸው። እሱም በድንጋጤ ሲርበተበት፤ “አይዞህ! እኛ ያገርህ ሰዎች ነን! እኔ ፈተና አቸናፊ ነኝ! አዳርቃይ እኖር ነበር። በላሄንና ሻግኔ ብዙ ዘመዶች አሉኝ!” በማለት እራሱን አስተዋወቀ። በጨዋታቸው መሐል ይህ እረኛ አብረውት የነበሩት ሽማግሌ የልጅ ልጅ እንደሆነ ተረዳ። ሽማግሌውም በሕይወት እንዳሉና፤ ምናምንቴዎቹ ምግብ አዘጋጆች አድርገው እሳቸውን እና ሶስት አሮጊት ሴቶችን እንደተው፤ እሱንም ከብት አጋጅ አድርገው እንዳተረፉት ነገራቸው። ፈተና በጣም ደስ አለው። መሽቶ ሽማግሌውን እስኪያገኛቸው ቸኮለ። ሲደጋግዝ እረኛውን በሩቅ እየተከተለ፤ ፈተና ብቻውን ወደ ሽማግሌው መኖሪያ ሄደ። አገኛቸውና፤ ከድንጋጤና ከደስታ ጋር መንሾካሾክ ያዙ። ምግብና የሚጠጣ ተሸክሞ ወደነያየሽ ገሰገሰ። በልተውና ጠጥተው ከጨረሱ በኋላ፤ ከሽማግሌው ጋር ስለነበረው ውይይት ነገራቸው። በሳቸው በኩል ወደ ደባርቅ የግንኙነት መስመር እንደሚዘረጋ፣ ካጠገባቸው ካለው ወንዝ ባለው ትልቅ የግራር ዛፍ ሥር ምግብ እንደሚያኖሩላቸውና፣ የጠላትን እንቅስቃሴ መረጃ እንደሚያቀብሏቸው መስማማታቸውን ነገራቸው። ሁሉም ደስ አላቸው።

አሁን ተኩሱ ተጋግሏል። ከሽማግሌው ቤት በስተቀር፤ አንድ የሚታይ ሌላ ቤት ባካባቢው የለም። ከብቱ ሁሉ ወደ ትግራይ ተነድቷል። እህሉም ማጭድ ይዘው ከትግራይ በመጡ ገበሬዎች ታጭዶ ተወስዷል። ሽማግሌውና አሮጊቶቹ በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ጥድፊያ ምግብ አዘጋጅ ሆነዋል። በበነጋታው፤ ሶስት የምናምንቴዎቹ ታጣቂዎች ወተትና ምግብ ሊወስዱ ሲመጡ ዓዩ። ፈተና እነ ያየሽን፤ “ስሙ! እነዚህን መግደል ቀላል ነው። አመቺም ነው። ነገር ግን እዚህ እነሱን ብንገድል፤ መጋለጣችን ነው። እኒህን ሽማግሌና ሴትችንም እናስፈጃለን። ሽቅብ ወደ ላይ ሲመለሱና ወደ ደባርቅ ሲዘልቁ ይሻላል!” ይላቸዋል።

“አንተ ምን ዓይነቱ ነህ! እንደ ስከረ አሳ ከፊታችን ቀርቦልን፤ ኋላ ትላለህ! አንተስ የምትገርም ነህ!” አለ የያየሽ መንታ ወንድም ትንሹ።”              

(ሶስተኛው ክፍል ይቀጥላል)