አፍሪካና የወደፊቷ! በስታንፈርድ ዩኒቨርሲቲ የሁቨር ኢንስቲቱት መድረክ

አፍሪካና የወደፊቷ! በስታንፈርድ ዩኒቨርሲቲ የሁቨር ኢንስቲቱት መድረክ
ማክሰኞ፣ ጥር ፯ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፩ ዓመተ ምህረት፤ (1/15/2018)

“የወደፊቱ ክፍት ነው። ገና ምንነቱ አልተረጋገጠም።”
ተናጋሪውን ገና ያላወቅሁት

በዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ፤ የአስተዳደር መመሪያዎች የሚመነጩት፤ አብዛኛው ሕዝብ ይወደዋልና ይደግፈዋል ከሚል ግንዛቤ ተነስተው ነው። ለዚህ እንዲረዳ፤ የጉዳዩ አቀንቃኞች፤ ሕዝቡን ለማግባባት፤ በየቦታውና በየጊዜው መድረኮችን ፈጥረው ምሁራንን በመጋበዝ፤ በርዕሱ ዙሪያ፤ የሚፈልጉትን በማስቀደም፤ ለታዳሚዎቹ ተደጋጋሚ ገለጣዎች ያደርጋሉ። ከነዚህ መድረክ አዘጋጆች አንዱ ካሊፎርኒያ በሚገኘው ስታንፈርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለው የሁቨር ኢንስቲቱት ነው። በዚህ ኢንስቲቱት ውስጥ፤ ከፍተኛ የቀድሞና የወደፊት የፌዴራሉ መንግሥት ኃላፊዎች ተሰግስገው ይገኙበታል። ባሁኑ ሰዓት፤ ቀድም ሲል በነበሩት የሬፓብሊክ ፓርቲ ፕሬዘዳንቶች ወቅት የስቴት ዲፓርትመንት ጸሐፊ የነበሩት ጆርጅ ሹልትዝ እና ኮንዶሊዛ ራይስ ከሌሎች ዕውቅ ምሁራንና አኳያዎቻቸው ጋር ይገኛሉ።

ጆርጅ ሹልትዝ “በታዳጊው ዓለም ክፍል፤ የአስተዳደር ጉዳይ” የሚል ተከታታይ መድረኮችን የሚያቀርብ ዝግጅት አላቸው። ትናንት ሰኞ፣ ጥር ፮ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፩ ዓመተ ምህረት፤ (1/14/2018) በዚሁ በስታንፈርድ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ፤ “አፍሪካ፤ በታዳጊው ዓለም ክፍል፤ የአስተዳደር ጉዳይ” በሚል ርዕስ፤ ራሳቸው ጆርጅ ሹልትዝ በተገኙበት፤ ከሰዓት በኋላ፤ ከምሽቱ ፲ ሰዓት እስከ ፲ ፩ ከሩብ ድረስ፤ መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። ማስታወሻና ግንዛቤዬ እነሆ!
stanford hoover discussionፎቶግራፉን የወሰድኩት ከዝግጅቱ ድረገጽ ላይ ነው።

በመድረኩ ላይ እነማን ተገኙ?

ለሕዝብ ክፍት ሆኖ በጆርጅ ሹልትዝ በተከፈተው ውይይት፤ በአስተዳደር፣ በቴክኖሎጅ፣ በንግድ፣ በአየር ጠባይ የለውጥ ሂደት፣ በእርሻ፣ በተቋማት ምንነትና ጥቅም፣ በአፍሪካ ፖለቲካና ዕድገት፣ በተለያዩ ወገኖች መካከልና በርስ በርስ ባሉ ግጭቶች ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው የዩኒቨርሲቲ ልሂቃንና የቀድሞ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ነበሩ።

በዕለቱ የተሳተፉት፤ አንቶኒ ኬሮል ከማንቸስተር ንግድ ድርጅት፣ አምባሳደር ቸስተር ክሮከር ከጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲና በአሜርካ መንግሥት የቀድሞ የአፍሪካ ጉድዮች ረዳት የስቴት ጸሐፊ፣ ማርክ ጅዎርዲኖ ከጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲ፣ ጃክ ጎልድስቶን ከጆርጅሜሰን ዩኒቨርሲቲና አንድሬ ፒየናር ከ ሲፋይፍ ካፒታል ነበሩ። መድረኩን የመሩት ብቸኛው ጥቁሩ የጆርጅታውን መምህርና በአሜርካ መንግሥት የቀድሞ የአፍሪካ ጉድዮች ረዳት የስቴት ጸሐፊ፣ አምባሳደር ጆርጅ ሙስ ነበሩ።

የመድረኩ ዋና መወያያ ነጥብ ምን ነበር?

በኒህ ልሂቃን ግንዛቤ፤ በአፍሪካ ውስጥ የቴክኖሎጂ ግስጋሴ፣ የሕዝብ ቁጥር ዕድገትና፣ የአየር ጠባይ መለዋወጥ ወደፊት ተደማምረው የሚያመጡትን የለውጥ ሂደት መመልከት አስፈላጊ ነው። በዚህ ላይ፤ እኒህ ጉዳዮችና የለውጥ ግስጋሴያቸው፤ በአፍሪካ ውስጥ በሚገኙት ሃምሳ አራት ሀገራት የሚያስከትሉትን መመርመር አስፈላጊ ነው። በኒህ ጉዳዮች ላይ እየተከተለ ያለው ለውጥ፤ በመንግሥታቶቹና በመዋቅሮቻቸው፣ በብቃታቸውና በአስተዳደር ዝግጅታቸው፣ በተጨማሪ ደግሞ በኅብረተሰቡ ውስጥ ባሉ ሕዝባዊ ተቋማት ላይ የሚያመጣው ጫናና እኒህ ክፍሎች ግንዛቤያቸውና ሊያደርጉ የሚችሉት ምንድን ነው? የሚለውን መመለከት ነበር ጉዳዩ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች፤ አዳማጩ እንዲገነዘብ የፈለጉት፤ በዓለም ዙሪያ ቀልጣፋ ለውጦች እየተንጎደጎዱ መሆናቸውን፤ የሕዝብ ቁጥርና የሕዝብ ብዛት መኖሪያ ቦታዎች እየተቀያየረ መሆኑን፤ የቴክኖሎጂ ዕድገት ከመቼውም በላይ እየናረ መምጣቱን ነው። እኒህ ቅይይሮች ደግሞ በሁሉም ቦታ እየተደመጡ እንደሆኑ ነው። እና እንዴት አድርገን ነው ይሄን አፍጥጦ ከፊታችን የተጋረጠ አዲስ ዓለም እንድንጋፈጠው የሚረዳን ዘዴ የምንቀምረው? የሚል ጥያቄ ለራሳቸው ደግነው፤ መልሱን ሁኔታውን በመረዳት መጀመር እንችላለን! በሚል ምሁራኑ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

ሁቨር ኢንስቲቱቱ ግራ ቀኙን ሲቃኘው፤ የዓለም ሕዝብ ሰፈራ ሁኔታ እየተቀያየረ ነው። ይህ ደግሞ በሁሉም ኅብረተሰቦች ዘንድ ከፈተኛ ጫናን ይፈጥራል። በሥልጣኔ ቀድመው የሄዱ ሀገራት፤ የተኪ ትውልድ ቁጥር መቀነስ ችግር እያጠቃቸው፤ የሕዝቦቻቸው የመኖር ዕድሜ ደግሞ ከፍ እያለ ነው። ለሥራ የሚሰማራው ወገን ቁጥሩ ሲመነምንና የአዛውንቱ የጡሮታና እንክብካቤ ዋጋ ሲንር፤ መንግሥታቱ ሌሎች አፍሪ መዋዕለ ንዋዮችን ማድረግ እጁ ያጥራቸዋል።

በዕለቱ የተደረገው ውይይት መድረኩ ይህ ነበር።

ያሳሰባቸው ምንድን ነው?

እንግዲህ ከላይ እንደሰፈርው፤ ምሁራኑን ያሳሰባቸው፤ በአፍሪካ የወጣቱ ቁጥር እየበረከተ፤ በቴክኖሎጅ ዕድገትና በሀብት ክምችት ግን ያን ያህል ያልዳለበ፤ መንግሥታቱ ደግሞ በቂ ዝግጅት ያላደረጉና አስፈላጊ ተቋማት በቦታው የሌሉበት መሆኑ ነው። ከነሱ ጥቅም አኳያ፤ የአፍሪካ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄድ፤ በዚህ ቁጥር ደግሞ አብዛኛውን ቦታ የሚይዘው ወጣቱ መሆኑን፤ እንደ ዕድልም እንደ ዕርግማንም ያዩታል። ዕድል ብለው ያሉት፤ ወጣቱ መብዛቱ፣ ሠራተኛ መብዛቱ ነው። አፍሪካ በሥልጣኔ ወደፊት ስትሄድ፤ ከተማዎቹ እያደጉ፤ የገጠር ሰፈራው እየመነመነ ይሄዳል። በየከተማው የሚኖረው የወጣት ስብስብ፤ ትልቅ ጉልበት ይሆናል ማለት ነው። ይህ ወጣት የቴክኖሎጂ ከመቅጽበት ዕድገትን በቀላሉ እየተቀበለ፤ ትምህርትና ገንዘብ ካገኘ፤ በያለበት አምራች ሆኖ፤ ከአፍሪካ አልፎ ለነሱም እንደሚረዳ ያምናሉ።

በተቃራኒው ዕርግማን የሚሆነው ደግሞ፤ አይቀሬው የከተማዎች መድለብና የገጠር ነዋሪዎች እያነሱ መሄድ፤ ወጣቱን ከተማ ውስጥ እንዲከማች መሆኑ ዕውቁ ነገር ነው። ይሄን በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ነገር ግን፤ አሁን ያሉት የአፍሪካ መሪዎች ትክክለኛ አስተዳደር ይዘዋል ወይ? የሚለው አስግቷቸዋል። መጪዎቹንም ይጠይቃሉ። አስተዳደር ማለት፤ መምርያ አውጪ ሰዎች፣ ውሳኔ መሥጠትና አሠጣጡ፣ የውሳኔዎቹ ጥራትና ሂደቱ፣ ሕጎች፣ ደንቦች፣ ተቋማትና ባህላዊ አሠራሮች ባንድ ላይ ተደምረው ነው። እኒህ ደግሞ በሥልጣን ላይ የተቀመጠውን ክፍል ወሳኝ ያደርጋሉ።

እዚህ ላይ በሰዎች መካከል የሚደረገውን የግንኙነት መሰመር፣ የአየር ጠባዩ መለዋወጥ፣ የመዋዕለ ንዋይ ስምሪትና የቴክኖሎጅው ዕድገት ተጽዕኖ ያደርግበታል። እንዲያውም አልፎ ተርፎ ይወስነዋል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ በሀገራችን፣ በዘላኖች መካከል የወንዝ መድረቅ ግጭት ያስከትላል። በዘላኖች መካከል ብቻ ሳይሆን፣ ባካባቢው ነዋሪ ሕዝብና በመንግሥት አካላትም ውስጥ ችግር ይፈጥራል። በአፍሪካ ባጠቃላይ፤ የቅኝ ግዛት ርዝራዥ የሆነው አሠራሩ፣ ሀብት ክምችቱ፣ የፖለቲካ ሥልጣት አወራረሱ፣ ለወደፊቱ ለሞከተለው እውነታ ተፅዕኖ አላቸው።

የትምህርት ጉዳይን አንስተው አቅርበዋል። በቅርብ ጊዜ ብዙ ከፍተኛ ተቋማት መቋቋማቸውን በማሞገስ አንስተዋል። ወደ ኢትዮጵያ ተመልክተው፤ ተቋማቱ ቢበዙም፤ የትምህርቱ ደረጃ የዘቀጠ ነው ሲሉ የነበረውን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት አንኳሰዋል። ድሮም ሀገር ለመጥቀም ሳይሆን፣ ይህ ለወግ የተደረገ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀድሞ ያውቀዋል። አንደኛው ተናጋሪ፤ ይህ የቴክኖሎጅ ዕድገት፣ የአየር ጠባይ መለዋወጥና የሕዝብ ቁጥር መጨመር ሂደት፤ በቅጡ ካልተያዘ፤ ግጭቶች እንደሚበዙ አትተዋል። ግጭቶች ደግሞ በሀገራት መካከልና በሠራዊት መካከል ብቻ ሳይሆን፣ የታጠቁ ኃይላት በያሉበት የሚያደርጉት እንደሆነ አስምረውበታል። በዚህ መልክ በተደረገ ግጭት የሚመጡ መሪዎች፤ ቅንነትና ሀገር አቀፍ አመለካከት ሳይሆን የሚኖራቸው፤ የግሌ የራሴ የሚልና ለተለየ የራሳቸው ወገን የሚሠራ መመሪያና ተግባር ነው የሚከተሉት አሉ። በእኛ ሀገር ባለፈው መንግሥት ሂደት የተከሰተውን ምሳሌ ማድረግ ይችሉ ነበር።

የዓለም አቀፍ ዕርዳታ፣ የዚህ ዕርዳታ አሠጣጥ እና ተቀባዮቹን በሚመለከት፤ ሰፋ ያለ ማብራሪያ አቅርበዋል። በመነሻ፤ አንድ የዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ የሚባል ነገር የለም አሉ። ይልቁንም የውድድር ጥድፊያ፣ የተለያየ የጥቅም መስመር ይዞ ሩጫ፣ የተለያዩ ግፊቶች የሚደረግበት ነው፤ ሲሉ የዕርዳታውን ሂደት ገለጡት። አፍሪካን በሚመለከት፤ አንድ የዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ የለም። የተለያዩ የውጪ ኃይላት ነው ያሉት። እኒህ ኃይላት ደግሞ፤ የየራሳቸው የሆነ የተለያየ ዕይታዎች ነው ያሏቸው። ከነዚህ ውስጥ ቅኖች ሆነው፤ አህጉሩን ለመርዳት ያሰቡ ይገኙባቸዋል። በአንጻሩ ደግሞ በተቃራኒው የቆሙ አሉ። ሁሉንም ወደዚህ የሳባቸው፤ የየራሳቸው የሆነው ፍላጎትና ይህ ፍላጎታቸው የፈጠረው ግፊት ነው።

ለኒህ ምሁራን ጥያቄዎቻቸው፤ ለመጪው አይቀሬ ለውጥ፤ የአፍሪካ መንግሥታት ምንድን ነው ዝግጅታቸውና ምንድን ነው እያደረጉ ያሉት? ከመንግሥታቱ ውጪ ያሉ የተደራጁ ክፍሎችስ በመንግሥታቱ ላይ ምን ያህል ጫና ማድረግ ይችላሉ? እያደርጉስ ናቸው ወይ? የሚሉት ናቸው።

መቼም ሳይነኩት የማያልፉት ነውና፤ የቻይናን ጉዳይ አነሱ። ባሁኑ ጊዜ ቻይና በአፍሪካ የምታደርገውን እንቅስቃሴ አትኩረው ተመለከቱ። ለኛ ደግሞ፤ ከኢትዮያ አንጻር ይህ ምንድን ማለት ነው? ብለን እንየው።ቻይና በሀገሯ ማምረት የምትችለውን የጨርቃ ጨርቅና አላቂና ተለዋዋጭ ዕቃዎች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ እያመረተች፤ ወደ አውሮፓ ማጋዝ ይዛለች፤ በሰፊውም አቅዳለች። ይህ እንግዲህ ከሁለት አንጻር ይወሰዳል። እኒህ ውጤቶች በኛ ሀገር ሲመረቱ፤ በርካሽ የጉልበት ዋጋ ነው። አስከትሎ ደግሞ፤ በአጭር ጊዜ ወደ አውሮፓ ስለሚቀርቡ፤ ጊዜ እንዳያልፍባቸው ይሆናል። ላጭር ጊዜም ቢሆን እኛ እንጠቀማለን። የጥቅሙን ያንበሳውን ድርሻ ወሳጇ ቻይና ናት።

ባጠቃላይ ቻይና በአፍሪካ ውስጥ ስለሚካሄደው የሰብዓዊ መብቶች ረገጣና የሙስና ተግባር፤ አንዲት ቅንጣት ደንታ የላትም። ይልቁንም መሪዎቹ ለሚመዘብሩት የሀገር ሀብት ማግበስበስ ዐይኗን ትጨፍናለች። ይህ ደግሞ ወጣቱን እንዲያማር ያደርገዋል። ሀብቱ ሲመዘበርና ሀገሪቱ በትክክል ሳትመራ ስትቀር፤ ሕዝቡ ይነሳል። ይህ እኒህን ምሁራን አሳስቧቸዋል። በሂደቱ የአፍሪካ መሪዎች ሁለት ናሙናዎች አሏቸው፤ ይላሉ። አንደኛው የምዕራባዊን ተምሳሌ ይሆናል። ሌላው የቻይና ተምሳሌ ነው። እናም ከሁለቱ መምረጥ አለባቸው፤ ሲሉ አቅርበዋል። እኛ ቅኖች ነን የሚል መልዕክት አውለብልበዋል።

በጥያቄና መልሱ ወቅት፤ አንዲት ታዳሚ፤ አፍሪካ ብዙ ማዕደናት እንዳሏትና፤ ሁሉም የውጪ መንግሥታት ያን ለመመዝበር ወደኋላ እንዳላሉ በማስመር፤ የቻይናም ሆነ የምዕራባዊያን ጥቅም ፍለጋ እንዴት እንደሚካተት ጠየቀች። ይሄን ከንግድ ጉዳይ ጋር አስማምተው፤ አህጉሩ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት እንዳለውና ይሄን በትክክል መጠቀም እንዳለበት ብቻ ጠቅሰው አለፉ። ቀደም ሲል መፍትሔውን በሚመለከት፤ በየሀገሩ በቦታው የተቀመጡ መንግሥታት ጥራት ወሳኝ ነው። ከመንግሥት አጓዳኝም ያሉ ተቋማት፤ ኃላፊነት አለባቸው። እኒህ የሚሠጧቸው ውሳኔዎች ሁሉን ነገር ይነካካሉ። የመጀመሪያ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃና ሶስተኛ ደረጃ ትምህርትና ተማሪዎች ጥራታቸው የተጠበቀ ሆኖ መገኘቱ አስፈላጊ ነው። የሀገር ውስጥና የውጪ መዋዕለ ንዋይ ባግባቡ እንዲመጣጠን መንግሥት መወሰን አለበት። በውጪ ዕርዳት ላይ ያተኮሩ መንግሥታት፤ ለራሳቸው ሕዝብ ደንታ አይኖራቸውም፤ ሲሉ ገልጠዋል።

ኢትዮጵያን በሚመለከት፤ አሁን በሥልጣን ላይ ባሉት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ላይ ከፍተኛ ተስፋ አላቸው። የአስተዳደራቸውን ሂደት በጣም አድንቀዋል። እንዲህ ያሉ መሪዎች ሀገራቸውን ይጠቅማሉ በማለት ዘክረዋቸዋል። አፍሪካ የሃምሳ አራት ሀገራት ስብስብ መሆኗን ደጋግመው አንስተዋል። እናም ሌላው ችግር፤ የተለያዩ ሀገራት የየራሳቸው የጉዳይ ቅደም ተከተል ስለሚኖራቸው፤ ይሄ ከፍተኛ አደጋ አለው፤ ሲሉ ተችተዋል። የአፍሪካ ችግር የኛ እንዳይሆን የሚለው ስጋታቸው፤ ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ድረስ በግልጥ ይታይ ነበር። የሚገርመው፤ ከአፍሪካ ምጡቅ ተማሪዎችን አምጥተን እዚህ እኛ ማስተማር አለብን። ለዚህም የአፍሪካ ሰዎች ወደ ሀገራችን እንዲገቡ የምናደርገውን አቀባበል ማስተካከል አለብን፤ በማለት አቅርበዋል። እዚህ ተምሮ፣ እዚ ቆይቶ፤ ወደ አፍሪካ የሚመለሰውን፤ ታሪክ ይታዘበው።

እዚህ ላይ መገለጥ ያለበት ጉዳይ አለ። ይህ ውይይት፤ ለሕዝብ ነፃ የሆነው የአንድ ሰዓት ከሩብ መድረኩ ነበር። ምሁራኑና ባላሥልጣናቱ፤ ሙሉውን ቀን፤ የዝግ ስብሰባ ሲያደርጉ ከዋሉ በኋላ ነው ይሄን ለሕዝብ ነፃ የሆነ መድረክ ያዘጋጁት። በዝግ ስብሰባቸው ላይ ምን እንደተነጋገሩ ማወቅ አይቻልም። በዚያ ላይ ዝርዝር ከመነጋገር ሌላ፤ ለነፃው መድረክ፤ ማን ምን ማቅረብ እንዳለበት ተዘጋጅተዋል የሚል ዕምነት አለኝ። በተጨማሪም ለመንግሥታቸውና ለተቋሞቻቸው የሚሆን የአቋም መግለጫ እንደሚያዘጋጁም እምነት አለኝ። ሆኖም ጨረፍታውን ማግኘቱ ቀላል አይደለም።

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in እስከመቼ - ESKEMECHE. Bookmark the permalink.

አስተያየት ያስቀምጡ