የኛ ነገር ክፍል ፬

አንዱ ዓለም ተፈራ፤  ሰኞ፣ ጥቅምት ፳ ፱ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፬ ዓ. ም.

የልብ ወርቅ መልዕክቱ ሲደርሳት፤ “አሃ! ቀርቧል። ፈተና ወደኔ እየመጣ ነው!

ውጪና ፈልጊኝ ቀርቤያለሁ እኔ፤

በሩን ክፈቺልኝ አስገቢኝ ወገኔ!

ብሎ ነው የላከብኝ!” ብላ፤ ሁለት ልጆቿን አስከትላ፣ እሷ ነጠላዋን ተከናንባ፤ መልዕክቱን ካመጣችው ሴት ጋር አብረው ሄዱ። ከነፈተና እንደደረሱ፤ እሷና ፈተና ተያይዘው ለብቻቸው ራቅ ብለው ተነጋገሩ። ፈተና ብቻውን ተመለሰ። የልብ ወርቅ አብራው አልመጣችም። ሁለቱ ልጆቿ እነፈተናን ተቀላቀሉ። ፈተና ሁሉን ባንድ ላይ ሰበሰበና፤ “ሁኔታው ለኛ እያማረ ነው! የልብ ወርቅ ጥሩ ዜና ነግራኛለች። ሁለቱ ልጆቿ፤ አንድ ሴትና አንድ ወንድ ልጅግሮች ከኛ ገር ተቀላቅለዋል። የምናምንቴዎች ታጣቂዎች ቁጥራቸው አነስተኛ ነው። በወልቃይት ያለው ሙከራቸው ዋጋ ሲያጣና የወገራው ሙከራቸው ሲከሽፍ፤ ዋናውን ኃይላቸውን ከስሜን ወደ ወሎ ስበው፤ በዚያ ወደ ኦነግ ሸኔ ቡችሎቻቸው እያቀኑ ነው። ወልቃይቴዎች ደግሞ፤ የኛን እንቅስቃሴ ሰምተው፤ አንድ ቡድን ወደኛ ልከዋል። የልብ ወርቅ በዚህ ሳምንት ውስጥ ይገባሉና አንድ ቦታ እንድንደርስ ጠቁማናለች። በየዳ የሚንቀሳቀሱትንም ልካባቸዋለች። ከሁሉ በላይ ግን፤ አሁን ካለንበት ትንሽ ራቅ ብሎ፤ ምናምንቴዎች በሚቆጣጠሩት ቦታ የሚገኝ አንድ የኛ ሰው በድብቅ እናገኛለን። አሁን አንድ ሽማግሌ ምግባችን ያመጡልናል። አንደተረከብናቸው፤ ጉዟችንን ወደ ሽማግሌው እናደርጋለን።” ብሎ ሲጨርስ፤ ሽማግሌው ምግቡን ይዘው ደረሱ። ሽማግሌውን ተሰናብተው ጉዟቸውን ጀመሩ።

ዋናው ዓላማቸው፤ የነሱን ጥረት ከሌሎች መሰሎቻቸው ጋር ለማጣመርና፤ በኒህ ምናምንቴዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ነው። ይህ የነሱ ዋና ተልዕኮ ነው። በመከላከያው ላይ ዕምነታቸው ጎድሏል። ከላይ መጣ በሚሉት ትዕዛዝ፤ እንዴ ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ባላችሁበት ቁሙ እንጂ ወደፊት አትሂዱ! የሚለው፤ ጠቅላላ ውጊያውንና የየዕለት እንቅስቃሴውን አደጋ ላይ ጥሎታል። የአማራው ኃይልም፤ በማይገባው መንገድ በመከላከያው እየታዘዘ፤ የኒህን ምናምንቴዎች ወረራ አጓጉል ነው የያዘው። ቆራጥነት የጎደለው ወይንም ለመዋጋት የማይፈልግ መስሎ ነው የታያቸው። መንገዳቸውን ወደ ማይፀብሪ አቅጣጫ አደረጉ። ትንሽ እንደተጓዙ፤ የተኩስ እሩምታ ሰሙ። ተኩሱ አላባራም። የጉዞ መስመራቸውን ቀይረው፤ ወደ ፀሐይ መግቢያ አቀኑ። የተኩሱ ድምፅ እየራቀ ሄደ። ከነሱ ጉዞ ጋር አለመያያዙን አረጋገጡ። ተመልሰው ወደ ማይፀብሪ ዞሩ።

በምሽት ወደ አንድ መንደር ተጠጉ። እዚህ መንደር ሁለት ትልልቅ ሰዎች አሉ። አንደኛው በምናምንቴዎች የተሾሙ አገልጋያቸው ናቸው። ለምናምንቴዎቹ የማያደርጉት ነገር የለም። ካዘዟቸው የበለጠ በሙሉ ልባቸው ስለሚፈጥሙላቸው፤ የመንደሩ ሰው፤ “ውሻው!” ብሎ ነው ከጀርባቸው የሚጠራቸው። ሌላው ሽማግሌ አሁን የሚያገኟቸው ናቸው። አንገታቸውን ደፍተው፣ ለመኖር ሲሉ የሚታዘዙትን ብቻ የሚፈጽሙና፤ አንጀታቸው ያረረ የወገን ተቆርቋሪ ናቸው። እሳቸው ናቸው ለየልብ ወርቅ መልዕክት ሰደው ግንኙነቱ የተፈጠረው። አድፍጠው ከተቀመጡበት፤ ሽማግሌው መጡ። ስማቸውን አያውቁም። ተጠጉና “ፈተና አጋጠመኝ!” አሉ። ፈተና ተነሳና አንገቱን በመድፋት እጅ ነሳቸው። ተያይዘው ወደ አንድ ቁጥቋጦ ተጠጉ። ቆይተውም ሽማግሌው ሄዱ። ፈተና ተመለሰና፤ “ተነሱ!” የሚል ትዕዛዝ ሠጥቶ፤ መንገዳቸውን ወደ መጡበት ተያያዙ።

ራቅ ካሉ በኋላ፤ ሰበሰባቸውና፤ “ያያችኋቸው ሽማግሌ፤ ነገ ወደ ማይፀብሪ ይሄዳሉ። የምንፈልገው ነገር እንዳለ ጠይቀውኝ፤ ምንም ነገር አንፈልግም ብያቸዋለሁ። ነገር ግን፤ ሄደው በከተማው ያለውን የምናምንቴዎች እንቅስቃሴ እንዲያጠኑ፣ ከቻሉ የምናምንቴዎች ታጣቂዎችን ብዛት፣ የመሳሪያቸውን ዓይነት እንዲያጠኑና የምንተማመንባቸው ሰዎችን እንዲፈልጉ ጠይቄያቸዋለሁ። ከነገ ወዲያ እዚሁ ልንገናኝ ተቀጣጥረናል። አሁን ራቅ ማለት አለብን!” አላቸውና መንገዳቸውን ተያያዙ።

በወገራ ወልቃይትና በስሜን ድብባሕር መካከል ጫካ አለ። ይህ ጫካ አብዛኛው በዋልድባ ሥር ነው። ገዳማት አሉበት። ዋልድባ መቀበር የሚፈልግም እዚህ ካለው አንዱ ገዳም ውስጥ ነው የሚቀበረው። አብዛኛው ዱር ብዙ ዘመን ባገቡ ዛፎች ነው የተሞላው። ብዙ የዱር አውሬዎች አሉበት። እነ ፈታና በዚህ ዱር ገብተው ቆዩ። ከሽማግሌው በተቀጣጠሩበት ቀንና ሰዓት፤ ፈተና ቀድሞ ደረሰና ዙሪያውን ፈተሸ። ካንድ ዛፍ ሥር ተጠግቶ ቆያቸው። እሳቸውም በሰዓቱ መጡ። የከተማውን ሁኔታ ካስረዱት በኋላ፤ አንድ መነኩሴ ከዋልድባ እንደሚያገኙት ነግረውት ወደ ቦታቸው ተመለሱ። ፈተና ወደ ጓዶቹ ሄደ።

ሁኔታውን ነግሮ ሰውዬውን ወደሚያገኙበት ቦታ ሄዱ። ከዋልድባ የመጡት መናኝ ቄስ ነበሩና፤ ሁሉም መስቀላቸውን ሳሙ። አረፍ ካሉ በኋላ፤ መናኙ፤ “እኔ ካብረንታንተ ወጥቼ፣ በበረሃው የዱርፍሬ እየለቀምኩ በጾምና ጸሎት እኖር ነበር። ስለ ምድሩ ዓለም ትቼ፣ ዓለም በቃኝ ብዬ፣ ነፍሴን በገነት እንዲያኖርልኝ፣ አምላኬን እለምን ነበር። አንድ ቀን፤ ከተጠጋሁበት ዛፍ ሥር ሆኜ የብዙ ሰው የጉዞ ድምድምታ ሰማሁ። ባጠገቤ ሲያልፉ፤ የመናኝ ልብሴንና ቆቤን ከቅጠሉ አመሳስዬ ተሰወርኳቸው። ለነፍሴ ያደርኩ ነኝ ብዬ፤ ሁሉንም እንዳላየሁ አሳልፌ፤ ወደ ሱባዔዬ ተመለስኩ። በበነጋታው አብረንታንተ ሳለሁ የማውቃቸውን መነኩሴዎች ስብስበው ሲነዷቸው ዓየሁ። ሁሉም አማራዎች ናቸው። ዝንታለም የኛ ወገን መሪ ይሁን የለም የኛ ወገን ይሁን ጭቅጭቅ፤ በትግሬ፣ በጠለምት፣ በበለሳና በወልቃይት መናኞች መካከል ነበር። በቅርቡ ግን ከትግራይ የመጡት አምርረው ገዳሙን ሊያፈርሱት ሲሉ፤ አማሮቹ፤ “ይቅርብን! ይሁን ግዴለም! እኛ የመጣነው ለነፍሳችን ነው!” በማለት አመራሩን ተውላቸው። ከትግራይ የመጡት ግን መሪነቱንም ቂምም ይዘው ቆዩ። ሰው ለነፍሴ አደርኩ ብሎ! ቂም መያዝና ለሥጋ ቦታ ጭቅጭቁ የሚገርም ነው። መሪም ሆነው እኒህ ከትግራይ የመጡቱ፤ አማሮችን ጠመዷቸው። ያ ፍሬ እንደሠጣቸው ገባኝ። በጣም ቆረቆረኝ! እናም አድብቼ ተከተልኳቸው።

“‘አንተ አማራ! አድጊ!’ እያሉ እያመናጨቁና እያዋከቡ ሲነዷቸው ተመለከትኩ! ከመናኝነት ወጥቼ ሰው ሆንኩ! ሰውነቴ ሥጋዬን ተላበሰ! የሚያዩትን ማመን ያቃታቸው ዓይኖቼ፤ የበለጠ ማፍጠጥ ያዙ። ከሰውም ሰው አማራ ሆንኩ! አማራነት ወንጀል መሆኑ ከነከነኝ! ይሄን እያሰብኩ በስውር ስከተላቸው፤ አንዱ አዛውንት መነኩሴ እንቅፋት መቷቸው ወደቁ። ‘ተነስ! አንተ አድጊ!’ አለና በያዘው ጠመንጃ ሰደፍ፤ ጀርባቸውን ነረታቸው። እንደ እንቧይ ተንከባለሉ። መትቶ ደግሞ፤ ይነሳሉ ብሎ ካጠገባቸው ቆመ። የደከመው ሰውነታቸው እምቢ አለ። የስድብ ውርጅብኝ ካወረደባቸው በኋላ፤ ጭንቅላታቸውን በጥይት ሲበታትነው በዓይኖቼ ተመለከትኩ። ያኔ ሰው ሆኜ መፈጠሬን ጠላሁት። ባለሁበት ደረቅሁ! ጥሏቸው ሄደ። መንቀሳቀስ አልቻልኩም። ሰውነቴ ደነዘዘ! ተንቀጠቀጥኩ! ዓይኖቼ ተገጠሙ! እንደገና ሁሉን ልመለከት ብፈልግም፤ ዓይኖቼ አልከፈት አሉ። ባለሁበት እንደደረቅሁ ብዙ ቆየሁ። ራቅ ብሎ የጥይት እሩምታ ሰማሁ! ተደጋገመ። እንደጨረሷቸው አወቅሁ!” ብለው ዓይኖቻቸውን ገጥመው ዝም አሉ።

አሁን ወደ አሉበት ሲመለሱ፤ “ዓያችሁ! የሰው ልጅ ከአውሬ ብሶ ሲገኝ!!! እንሰሳት እንኳን፤ አጥቂ ሲመጣባቸው፤ ከበው ይተባበሩና የሚችሉትን በማትረፍ፤ ለወደፊት ትውልዳቸው ቀጣይ ያበጃሉ! ተተኪ ያኖራሉ! የሰው ልጅ ግን፤ ለመጨራረስ ጦር ይስላል! ታዲያ፤ ለኛ ሲዖል ቢዘጋጅ ምን ያንሰናል!” አሉ። ቆየት ብሎ የሰው ድምጽ ሰሙ። “አይዟችሁ! እኔ የላኩባቸው ሰዎች ናቸው። እዚህ እንዲመጡ ነግሬያቸው ነው” ብለው አረጓጓቸው። ሰዎቹ ቀረቡ። ፀጉሮቻቸው የተንጨባረሩ፣ ልብሶቻቸው የተቀዳደዱና ሰውነታቸው በራብ የተጎዱ ናቸው። እነ ፈተናን ሲያዩ ፊታቸው በተስፋ ፈካ። መሪያቸው ወደ መናኙ ቀርቦ ተሳለመና፤ ሌሎችን አቀረበ። ትውውቁ ቀጠለ።

መሪያቸው አንተሁነኝ ክንዴ ነው። አንተሁነኝ ጎንደር አስተማሪ ነበር። የምናምንቴዎቹ ዛሬማ መግባት ከንክኖት፤ “ከዘመዶቼ ጋር ሆኜ የቻልኩትን አደርጋለሁ እንጂ፤ እዚህ ለሆዴ ማደር አይሆንልኝም!” ብሎ ዛሬማ ከዘመዶቹ ጋር ተሰለፈ። ርስታቸው ሲወረርና ከብቶቻቸው ሲነዱ፣ ቤታቸው ሲፈርስና እርሻቸው ሲበላሽ፣ እህላቸው ሲቀማና መኖራቸው ከጥያቄ ውስጥ ሲገባ፣ ያለቁት አልቀው፤ የሚችለውን ያህል ያተረፋቸውን ዘመዶቹን ወደ ቆላ ወገራ ሽኝቶ፤ ከተወሰኑ የቅርብ ወጣት ዘመዶቹ ጋር ወደ ዋልድባ ተጠጋ። ከመናኙ ጋር ግንኙነት ፈጠረ። እናም ከሌሎች ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩለት ጠየቃቸው። መናኙም ከማይፀብሪው ሽማግሌ ጋር ግንኙነት ፈጠሩ። አንተሁንና ወጣቶቹ እንዲት ሴትና ስምንት ወንዶች ናቸው። ከነፈተና ጋር ለመቀላቀል እንደሚፈልጉ ተናገሩ። በዚህ ስምምነት መሠረት ቁጥራቸውን አሳድገው፤ የወደፊት ዕቅዳቸውን ነደፉ።

ፈተና የቡድናቸው መሪ ሆኖ ተመረጠ። ያየሽ፣ በለጠች፣ አረጋና አንተሁነኝ ምክትል ሆነው ተመደቡ። አረጋ ከጃኖራ ከተቀላቀሉት መካከል አንዱ ነው። ቁጥራቸው ወደ ሃያ አንድ አድጓል። በለጠች አምስት ራሷን ሆና፤ ከዛሪማ ወደ አዳርቃይ የሚወስደውን መንገድ እንድትከታተል ኃላፊነቱ ተሠጣት። አንተሁነኝ አምስት ራሱን ሆኖ፤ ከአዳርቃይ ወደ ማይፀብሪ የሚወስደውን መንገድ እንዲቆጣጠር ኃላፊነቱ ተሠጠው። አረጋ አምስት ራሱን ሆኖ፤ ከማይፀብሪ ወደ ወልቃይት የሚያገናኘውን መስመር እንዲቆጣጠር ኃላፊነቱ ተሠጠው። ያየሽ ደግሞ፤ ፈተና አብሮት ሆኖ፤ አጠቃላይ የቡድናቸውን እንቅስቃሴ እንዲያቀናጅ ኃላፊነቱ ተሠጠው። ፈተና፤ የአራቱን ምክትሎቹን እንቅስቃሴና የደጋፊዎቻቸውን ግንኙነት እንዲከታተል ተወሰነ። መናኞቹን፤ ሽማግሌዎቹን እና እነ የልብወርቅን፤ ፈተና ብቻ እንዲያገኛቸው ተስማሙ።

ፈተና ምክትሎቹን ይዞ መነጋገር ጀመረ። “ምናምንቴዎች ጉዳያቸው ምንድን ነው? አምባገነንነት ወይንስ ሕዝባዊነት! የጥቂቶች ጥቅም ወይንስ የብዙኀን ፍላጎት! መከላከያ ይሄንን ወረራ ለምንድን ነው የአማራ መወረር አድርጎ የሚመለከተው? ይሄንንስ ካደረገ፤ ለምንድን ነው የውጊያውን መሪነት ለአማራው ያልተወው? መንግሥት ለምንድን ነው ሁሉን ነገር እኔ ብቻ ልምራው የሚል ግትርነት የያዘው? እኛስ ምን ብንከተል ነው ስኬታማ የምንሆነው?” በሚሉት ላይ መነጋገር ያዙ። ውይይቱ ቀላል አይደለም። ብዙም መረጃ ስለሌላቸው፤ በጥልቀት ጉዳዩን እስከፍጻሜው ድረስ ሊነጋገሩበት አልቻሉም። ለነዚህ በቂ መልስ ማግኘት፤ ለሚያቅዱትና ላጠቃላዩም የምናምንቴዎችን ወረራ መከላከልና መልሶ ማጥቃት ወሳኝ ነው።

(አምስተኛው ክፍል ይቀጥላል)