ደርሶ መልስ

ደርሶ መልስ 

( ክፍል ፩ )

አንዱዓለም ተፈራ
የካቲት ፱ ቀን ፳ ፻ ፲ ፪ ዓመተ ምህረት  ( 2/17/2020 )

ኢትዮጵያ ሀገሬ ደርሼ ከመጣሁ ሶስት ቀን ሆነኝ። ልቤ ውስጥ ተሰንቅሮ የተቀመጠ ጉዳይ አላስተኛኝ ስላለ፤ ይሄን መጻፍ ጀመርኩ። የምጽፈው ለማንም ሳይሆን ለራሴ ነው። መጻፉን የወደድኩት፤ ከጭንቅላቴ ወጥቶ በፊቴ ላይ ሳየው ቀለል ይለኛል በማለት ነው። በርግጥ ከራሴ አልፎ በድረገጽ ላይ ስላሳረፍኩት፤ የግሌ ብዬ ማለቱ ችግር ነው። ለገር ግን በድረገጽ ላይ የሰፈረው በኔው መናዘዣ የእስከመቼ መድረኬ ላይ ስለሆነ፤ አሁንም የራሴ ከመሆን አያልፍም። ይሄን የእስከመቼ የድረገጽ መድረኬን ከጫርኩበት ብዙ ጊዜ ሆኖኛል። እናም እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑ ጎብኝዎቼ፤ ለረጅም ጊዜ እንዳልዳሰስኩት ሲገነዘቡ፤ መጥተው ማየታቸውን ትተውታል! ብዬ ወስጃለሁ። አሁን ወደ ጽሑፌ ልመለስ።

በስደት ላይ ከመሆኔ በፊትም ሆነ በኋላ፤ ለስደት ያበቃኝን ምክንያት ትቼው አርፌ አልተቀመጥኩም። ዛሬ ከረጅም ጊዜ በኋላ ደርሼ ስመለስ፤ ጥልቅ ግንዛቤ አደረግሁ። በርግጥ ምን ጊዜም ቢሆን ኢትዮጵያዊነቴ ከኔ ሊወጣ አይችልም። ይህ ምን ጊዜም አብሮኝ የሚኖር ሀቅ ነው። ደርሶ መልሴ፤ ምንነቴን፣ የሕይወቴን ጉዞ፣ የቤተሰቤን ኃላፊነት፣ የኔን የፖለቲካ ተሳትፎና ውጤት፣ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ያለኝን ግንኙነት፣ የወደፊቴን እንድመረምረው አደረገኝ። ለዚህ ሁሉ መሠረቱ በሀገራችን ውስጥ ያለው ሀቅ ነው። እንዴት ተረዳሁት? ምን ሁኔታ አለ? ወደየት እየተሄደ ነው? ምን ሊከተል ይችላል? ይህ እንዲሆን ነበር ወይ ያለፉትን የሕይወቴ ሃምሳ ዓመታት በትግል ስንገላታ ያሳለፍኩት? ሕይወታቸውን በሂደቱ ያጡ ጓደኞቼስ ትርክት ምን ሊሆን ነው? ይህ ነው የዚህ ጽሑፌ ትኩረት። በዚህ በመጀመሪያው ክፍል፤ ላይ ላዩን የተመለከትኩትን እዘክራለሁ። በተከታታዮቹ ደግሞ፤ ጥልቁንና ወደፊት የሚለውን አሰፍራለሁ።

አብዛኛውን ጊዜዬን ያሳለፍኩት ጎንደርና አዘዞ ነው። አዲስ አበባ ቆይቻለሁ። ባሕርዳርን ጎብኝቻለሁ። መራይን ውየባታለሁ። አዲስ አበባ ሉሲን እንደ የውጪ ሀገር ጎብኚ ሆኜ ዓይቻታለሁ። የቀይ ሽብር ሰለባዎች መታሰቢያውን ጎብኝቻለሁ። ጎንደር አስደናቂውን የሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓመተ ምህረት የጥምቀት በዓል ታድሜበታለሁ። ሰዎች መደርደሪያው ተንዶ ጉዳት ሲደርስባቸው እዚያ ነበርኩ። አዘዞም የሎዛ ማርያም አስተሮዬን በዓል አክብሬያለሁ። አስቤ የነበረውን የሀገሬን ታሪካዊ ቦታዎች መጎብኘት ሳላሳካው ተመልሻለሁ። ከዚያ በተረፈ ግን፤ በጣም ጥቂት የሆኑ በሕይወት ያሉ የሚያውቁኝና የማውቃቸውን አዲስ አበባና ጎንደር አግኝቼ፤ አብሬያቸው የድሮውን ስዘከር፣ ስበላና ስጠጣ፣ ከሕዝቡ ጋር በየመንገዱና በየታክሲው ስተራመስ ከርሜያለሁ። ይሄው ከሕዝቡ ጋር ስተራመስ የሰነበትኩበት የላይ ላይ ዕይታ እነሆ!

ዕድሉን አግኝቼ ሀገሬ ገብቼ፤ በቀብር ስነሥርዓቷ ላይ ልገኝ ያልቻልኩትን እናቴን፤ ከብዙ ጊዜ በኋላ የመቃብር ቤቷ ሄጄ፤ በተደጋጋሚ አነጋገርኩና ተሰናበትኳት። ይሄን በመታደሌ ደስታ ተሰምቶኛል። አጠቃላይ ደርሶ መልሴ የተደባለቀ ስሜት አሳድሮብኛል። ሀገርን ተገዶ አርባ ዓመት የሚጠጋ እንዳይመልስ የተደረገ ሰው፤ በሚመለስበት ወቅት የሚጠብቀውን አያውቀውም። እኔም ስመለስ ምን ሊሰማኝ እንደሚችል ቀርቶ፤ ምን እንዲሚገጥመኝ በትክክል አላውቀውም ነበር። እናም ይቅር አዲስ አበባና ጎንደር፣ ተወልጄ ላደግሁባት አዘዞ እንኳ፤ እኔ ለሷ፣ እሷ ለኔ አዲስ ነበርን። በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ነበሩ ያወቁኝና ያወቅኋቸው። እንግዲህ በዚህ ተጀምሮ የት ሊደረስ እንደሆነ መገመቱ አይቸግርም!

አንዳንድ የታዘብኳቸው ነገሮች አሉ። የማውቀውን የአዲስ አበባ ፒያሳ፣ ከማዘጋጃ ቤቱ ተነስቼ በሲኒማ ኢትዮጵያ አልፌ፣ በግሬ እስከ አራት ኪሎ ድረስ፤ ገና ደርግ ደርግ ነኝ ብሎ ሳይወጣ እንደተውኩት አገኘሁት። በተመሳሳይ መልኩ የጎንደር ፒያሳም እንዲያ ነበር። በሌላ በኩል የየከተማዎች ነዋሪ ሰው ቁጥር ከመጣን በላይ አድጓል። ቁጥሩን የሚያውቅ ሰው አለ ብዬ አልገምትም። አዲስ አበባም! ጎንደርም! አዘዞም! ከተማዎቹ ተለጥጠው፣ ተለጥጠው፣ ተለጥጠው፤ ካንዱ ጫፍ ወደሌላው ጫፍ ለመድረስ፤ ሌላ ሀገር የመሄድ ያህል ሆኗል። የመኪናው ቁጥር እጅግ በዝቷል። መንገዶቹ ጠበዋል፣ በዝተዋል፣ አስፋልትና የኮብል ንጣፍ በየቦታው ተደቅድቋል። ይሄ ሁሉ ሆኖ፤ የመኪናዎቹ ቁጥር፤ የሕዝቡን የመጓጓዝ ፍላጎት ያሟሉ አልመሰለኝም። ይሄን ልል የቻልኩት፤ በየታክሲዎች ማቆሚያ ላይ ያየሁት እጅግ ቁጥሩ የበዛ የሕዝብ ሰልፍ ነው። ባጃጅ እንዳፈር መሬቷን ሞልቷታል። ከተማዎችም ሆኑ የገጠር አካባቢዎች፤ ባጃጅ ያልገባባቸው አላየሁም። በዚህ ሁሉ ልክ፤ በየከተማዎቹ የመጸዳጃ ቦታዎች በየቦታው አለመኖራቸው፤ እንደልብ መንቀሳቀስ ለአፍንጫ አስቸጋሪ ነበር። አንዳንድ ቦታማ መረገጫ ቦታ እንኳን አሳጥተውኛል። ሰዎችን ያለቦታው ሲከፍሉ ማየት፤ “ድሮኮ ነውር ነበር!” አስብሎኛል። በየከተማው ያየሁት የሆቴሎች፣ የምግብ ቤቶች፣ የቡና መጠጫ ስፍራዎች ብዛት፤ ዓይኖቼን አፍጥጬ መዝጋት እስኪሳነኝ አስገርሞኛል። “እውነት እኒህ ሱቆች በሙሉ ለባለቤቶች በልቶ ማደሪያ ትርፍ ያስገኛሉ?” ይሄን ደጋግሜ ለራሴ ጠይቄያለሁ! መልስ እንዳላገኝ፤ የጠየቅሁት አዋቂ አልነበረም። በየቦታው ያየኋቸው የፎቆች ጋጋታ፤ ከግራሞት በላይ ነበሩ። ግዝፈታቸው! መለያየታቸውና ቁንጅናቸው! አፍ ያስከፍታል። አዲስ አበባ መገናኛ፤ አንድ የገበያ አዳራሽ ገባሁና፤ የፎቅ መውጫ ተንቀሳቃሽ ደረጃውን፣ በየሱቆቹ ያሉትን ልብሶችና የቤት ዕቃዎች ተመልክቼ፤ እውነት አዲስ አበባ ነው ያለሁት! በማለት ዙሪያዬን አገላብጬ አትኩሬ ፈትሻለሁ።

ከቻይና የምዕራባዊያን ዕቃዎች በቅጅ ተገልብጠው፤ የበለጠ አምረው ጥራታቸው ግን ወደታች ወርዶ በየቦታው ዓይቻለሁ። ገዥና ዋጋ ይፈራረሙበት! ብያለሁ። ለነገሩ ምን የምዕራባዊያን ዕቃዎች ብቻ! የኛው የጅ ሥራም አልቀረለት! የሴቶች የፈትል ቀሚስ በቻይናዎቹ ቀጂዎች ከነጥለቱ ተኮርጆ፤ በየሱቁ ተደርድሮ ሳየው፤ “ወየሁ ጉድ! ፈታይ፣ ሸማኔና ጠላፊ ሥራ ፈት ሊሆንና፤ ብር ወደ ቻይና! ረሃብ ወዳገሬ!” አሰኝቶኛል። ለሺያጭ የተደረደሩትን ዕቃዎች በሙሉ ስመለከት፤ የት ነው ያለሁት? ብዬ እንድጠይቅ ደጋግሞ ነካክቶኛል። ቀድሞ የነበርኩበትና የአሁኑ አለመዛመዳቸው ብቻ ሳይሆን፤ ፍጹም የማይገናኙ መሆናቸው፤ አእምሮዬን በጥርጣሬ ስለሞላው፤ የትኛው ነው እውነት? ብዬ እንድጠይቅ ተገድጃለሁ! መቼም በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያና በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ መካከል ያለውን የመቶ ዓመታት ክፍተት፤ ባንድ እመርታ ዘሎ መግጠም አይቻልም!

ከከተማዎች ሲወጡ፤ ከሞላ ጎደል የገጠሩ ሰው አለባበስ ተለውጧል። የማውቀው የአርሶ አደር ልብስ እየጠፋ ሄዷል። ይሄ ለበጎ ነው፤ ለሥራ የሚያመችና የጸዳ ልብስ ማየት ደስ ያሰኛል። በተለይ ደግሞ፤ በአርሶ አደሩ ዘንድ ገንዘብ እንዲያ ደርቶ ሲንሸራሸር ማየቴ አዲስ ሆኖብኛል። የማልክደው ደግሞ፤ በልመና የተሰማራው ሰው ቁጥር እጅግ በዝቶ አግኝቸዋለሁ። ምንም እንኳን በትክክል ወይንም ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ በልመና የተሰማሩ አሉ! የሚለውን በግንዝቤዬ ውስጥ ባስቀምጥም፤ በውል ቁጥሩ ራሱ አስደንግጦኛል። በተለይም ሕጻናትን የያዙ፣ አካላቸው በአውነት የጎደለና አዛውንቶችን ሳይ በጣም ተሳቅቄያለሁ። እንግዲህ ይሄ ሁሉ የሚታየው እውነታ ነው። ከሚታየው ጀርባ ያለው፤ ይሄን ሁሉ አንቀሳቃሹ የፖለቲካው፣ የኢኮኖሚውና የባሕሉ ሀቅ፤ ጭንቅላት ያሳክካል። ያን በሚቀጥሉት ተከታታይ ክፍሎች አቀርባለሁ።

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in እስከመቼ - ESKEMECHE. Bookmark the permalink.

2 Responses to ደርሶ መልስ

  1. አሴር ዳንኤል ይላሉ:

    እንዴት እስከ ዛሬ ሳላይ መቅረቴ ይቆጨኛል ።ጎብዝ ፅሁፎቹ ወዝ ያላቸዉ ናቸዉ ።

    Like

  2. አመሰግናለሁ አሴር ዳንዔል

    Like

አስተያየት ያስቀምጡ