ራስ ዳሸን ምን ማለት ነው?

ጥር ፪ ቀን ፳፻፭ ዓመተ ምህረት

በተደጋጋሚ ሲባል ሰምቻለሁ። እንዲያው ሲገርመኝ ብቻዬን አሟገታለሁ። አሁን ግን መድፈር ብሎኛል። ራስ ዳሸን ምን ማለት ነው? እባካችሁ ንገሩኝ?

ነገርን ነገር ያመጣዋልና ጨዋታዬን በራሴ ገጠመኝ ልጀምር። ሱዳን ተሰድጄ ነበር። ካርቱምና ኦምዱርማንን ለይቶ በሚያልፈው የአባይ ወንዝ ላይ በተሠራው ድልድይ ላይ ቆሜ፤ ሁለቱ አባዮች የሚጋጠሙበትን ትኩር ብዬ ተመለከትኩት። የኛው አባይ፤ ከስድስቱ አምስት እጁን ውሃ ይዞ፤ ጭቃ መስሎ ጭቃ ተሸክሞ ይተመለመላል። በዚያኛው የሌሎቹ አባይ ደግሞ፤ ኩልል ያለ ባዶ ውሃ አቅፎ፤ ከስድስቱ አንዱን እጅ ይዞ ይኮላል። አንዱን ነጭ አብሮኝ የሚሠራ ሙግት ገጠምኩት። እሱ፤ “አየኸው ናይል ያገርክን ውሃ ይዞ ሲዶል አለኝ።” እኔ ቀጠል አልኩና እሱ በሄደበት መንገድ መሄድ ጠላቼ፤ “ስማ እንጂ፤ እኛኮ አባይ ነው የምንለው። እንድምታዬው ውሃው የአባይ ስለሆነ፤ ለምን አባይ ብለህ አትጠራውም?” ስል ወጠርኩት። እሱ ከኔ የባሰ ነገረኛ ነበርና፤ “አንተ ሁሉን ነገር ኢትዮጵያዊ ካላደረግክ አያጠግብህም።” አለኝ። መልሼ፤ “ይኼኮ የኔ የግል ጉዳዬ ሳይሆን፤ የመታዬውን ነው የምነግርህ። ውሃው የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ነው። ወንዙ የኛ ስለሆነ፤ ስሙን የምናወጣው ደግሞ እኛ ነን።” አልኩት። ምሽግ አድርጎ ያቀረበልኝ መከላከያው፤ “ስማ፤ በመጽሐፎች ሁሉ የተከተበው፤ ናይል ነው። ማንኛውም ዓለም በሚያውቀው ቋንቋ የተቀመጠው ናይል ተብሎ ነው። አሁን ላንተ ሲባል፤ አባይ ተብሎ፤ የተጻፉት መጽሐፎች ሁሉ ሊቀየሩልህ ነው?” አለና በንቀት አፈጠጠብኝ።

የስደቱ አንጄቴን ማማስል አንሶት በማንነቴ ስለመጣብኝ፤ ለዚህስ መንገድ አልሠጥም አልኩና፤ ክርክር ያዝኩ። ሁለታችንም አጥባቂዎች ሆን። አብረን የምንሠራ ስለሆነ ማለሳለስ ፈልጌ ነበር። ነገር ግን፤ ለዚህ መንገድ መሥጠት አልፈለግሁም። ጥቃት መስሎ ታዬኝ። ቢሆንስ እሱ ምን ቸገረው፤ ባለቤቱና የተጎዳሁ እኔ በማለት ላሳልፈው አልፈለግሁም። ማታ ተኝቼ፤ አዲስ አበባን ሲጽፉ አባባ ብለን እንድናነብ ማድረጋቸው ድሮ የሚቆረቁረኝ ነገር ነበር። አሁን ደግሞ፤ በተለይም በዓይኔ የወሃውን ሚዛን ካየሁ በኋላ፤ ናይል ብዬ ላልጠራና ሲጠሩትም ላልቀበል ልቤን አደነደንኩ። የወሃው እኮ ባለቤት እኛ ነን።

አሜሪካ ከመጣሁ በኋላ ይኼው ጉዳይ አልለቀቀኝም። በፈረንጆቹ አቆጣጠር በአሥራ ዘጠኝ መቶ ስማንያዎቹ መጨረሻ ላይ ሎስ ኤንጄለስ የኮሚኒቲ ኮሌጅ ተማሪ ሆኜ፤ ሚስተር ግሬኔል የሚባል የፊዚክስ መምህር ነበረኝ። ታዲያ ለውጭ ሀገር ተወላጆች ንቀቱ የትዬለሌ ነበር። ስማችንን መጥራት ስለሚፀየፍ በአባቶቻችን ስም የመጀመሪያ ቃል ብቻ ነበር የሚጠራን። ታዲያ አንድ ቀን፤ “ሚስተር ቲ እስኪ ይኼን እንዴት አድርገኽ ትሠራዋለህ?” አለና ጠየቀኝ። እኔም፤ “ሚስተር ጂ፤ አሱንማ እንዲህ አድርጌ እሠራዋለሁ።” አልኩና መልሴን አቀረብኩ። በጣም ተናደደ። “ግሬኔል ማለት አትችልም?” አለኝ። መቸም መብትን ማወቅና መረዳት ጥሩ ነገር ነው። ለመብት መታገል ምን እንደሆነ በጥብቅ ስለማውቅ፤ “እርስውስ ተፈራ ማለት አይችሉም?” ብዬ ጥያቄውን በጥያቄ መለስኩለት። ወዲያው ርዕሱን ቀይሮ አለፈ። የትምህርት ሰዓቱ ሲያልቅ ወደ ቢሮው ጠራኝ። “አንተ ጎበዝ ተማሪ ነህ። በድሜህ ደግሞ ቀሪዎቹን ተማሪዎች እጥፍ ትሆናለህ። እኔን ልትፈታተነኝ ትፈልጋለህ?” በማለት ሊያፋጥጠኝ ሞከረ። ይቺን ይወዳል አልኩና፤ “እርስዎ ለራስዎና ለስምዎ ክብር የሚፈልጉትን ያህል እኔም ራሴን ማስከበር እፈልጋለሁ። በስሜ ሲጠሩኝ፤ በስምዎ እጠራዎታለሁ። በአንድ ፊደል ሲጠሩኝ ደግሞ በአንድ ፊደል እጠራዎታለሁ።” አልኩና፤ ከዚያ ወዲህ አንዲትም ቀን ጥያቄ ለኔ ሳያቀርቡልኝ፤ የትምህርት ዓመቱ ተጠናቀቀ።

ወደ ርዕሴ ልመለስ። የኢትዮጵያ ክፍተኛ ተራራ ራስ ደጀን ይባለል። ደጀን ብለን የሰው ስም እንደምንሠጠው። ጎጃም ውስጥ፤ በሸዋና በጎጃም መካከል በሚያልፈው የአባይ ወንዝ አጠገብ ያለችው ከተማ ደጀን እንደምትባለው። ደጀን መከታ ማለት ነው። በግዙፍነቱ የታወቀው ተራራ ራስ ደጀን ይባላል። ደጀንን ካናቱ ላይ ቆሜበታለሁ። ከዚያው ላይ ተኝቼ አድሬበታለሁ። ካካባቢው ነዋሬዎች ጋር ራስ ደጀን ብዬ ጠርቼዋለሁ። “እናንተ ከፈረንጅ ቀድታችሁ ተራራችንን ራስ ዳሸን ትሉታላችሁ አሉ1” ሲሉ ቀልደውብናል። “ያው የፈረንጅ አሽከር ተዚያው ባለበት ይንደሻደሽበት እንጂ፤ እዚህ መጥታችሁ ራስ ደሸን አትበሉብን!” በማለት፤ ከኔ ጋር የነበሩትን ያዲሳባ ልጆች አርመዋቸዋል። ታዲያ ያካባቢው ተወላጅ ስለሆንኩ፤ በኩራት የዘመዶቼን አጠራር አጥብቄ ይዣለሁ። በየሄድኩበት አጥብቄ የዘመዶቼን አጠራር አራምዳለሁ። ከናንተ እኔ አውቃለሁ ብሎ የሚሟገት ካለ፤ ከዳኛ ፊት እንቅረብ። አለበለዚያ ግን፤ በሕግ አምላክ ራስ ደጀን ነው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራራ ስሙ! ፈረንጅ መጥራት አቅቶት ወይንም ስለሚቀለው የሠጠውን ስም፤ በተገላቢጦሽ እኛ ከነሱ ተቀብለን የመጥራት አሽከርነቱ ይቅርብን። አይበጀንም።

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in አስተያየቶች - Commentaries. Bookmark the permalink.

4 Responses to ራስ ዳሸን ምን ማለት ነው?

  1. wirelesszone ይላሉ:

    አስደሳች ነው። በእራሳችን መተማመን እና የአካባቢያችንን ቋንቋ እና ወግ ሌሎች እንዲዳኙት ወይም እንዲቀይሩት በአጭሩ እጅ መስጠት የለብንም። የዚህ የእራስ ደጀን ጉዳይ ግን እንዲህ በቀላሉ መታለፍ የለበትም። የተሳሳተ ራሱን ያርም። መፅሃፍ የፃፈ፣ ይቅርታ ጠይቆ መፅሃፉን እርትዕ (edit) ያድርግ። Thanks

    Like

    • Eskemeche ይላሉ:

      አመሰግናለሁ ይበልጣል፤
      ራስ ደጀን ማለት ፈረንጅ አቅቶት ራስ ዳሸን ሲል ተክትለን ራስ ዳሸን ስንል፤ መሠልጠን ሳይሆን፤ ለባርነት ማደር ነው። ደጀን – መከታ፣ መጠለያ፣ መመኪያ ነው። እናም ታላቁ የሀገራችን ተራራ ራስ ደጀን፤ የተራራዎች ሁሉ የበላይ እና ለሕዝቡ መከታ የሆነ ብለው ቀደምቶቻችን ስም ሠጥተውታል። እናም ያካባቢው ነዋሪ በዚሁ በትክክለኛ ስሙ ይጠራዋል። ከተራራው ላይ ተኝቼ አድሬበታለሁ። አከብረዋለሁ። ሁላችንም ልናከብረው ይገባናል።

      Like

  2. ወርቁ ይላሉ:

    ሰላም ወንድም አንዱዓለም::

    በጽሁፍህ በጣም ተደሰትኩ ምንም እንኳን በጣም ዘግይቸ ባነበውም:: ኧረ ሌላም ተመሳሳይ ነገሮች አሉ:: ለምሳሌ “እንኳን ደስ አላችሁ” መባሉ ቀርቶ “እንኳን ደስ ያላችሁ” ሲባል እንሰማለን:: በኔ ግምት አማርኛ ሁለተኛ ቋንቋቸው የሆኑ ተናጋሪወች አበላሽተው የሚናገሩትን የቋንቋው በለቤቶችም እንደትክክለኛ ቋንቋ ይቀበሉታል::

    ከሱ የበለጠ ደግሞ የሚገርመው በሆስፒታሎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በመዘጋጃ ቤት መስሪያቤቶች ድረ-ገጾች እና በመሳሰሉት የህዝብ መገናኛወች ሆን ተብሎ በተደረገ መንገድ ይመስለኛል ጽሆፎች በተበላሸ አቀራረብ ተጽፈው አይቻለሁ:: አማራን የሚጠሉ አማርኛ አስተርጓሚወች አማሮችን ለመጉዳት የተሳሳተ ትርጉም ሆን ብለው እንዳይነግሯቸውም እሰጋለሁ::

    መልካም ቀን::

    Like

    • ትክክል ነህ ወንድሜ ወርቁ፤ አሁን ደግሞ በጣም በሚዘገንን ሁኔታ፤ ቋንቋውን ሳይሆን ራሳችንን በሙሉ የሸጥንበት ሀቅ ባገራችን ነግሷል። በእንግሊዝኛ ተጽፎ እንዳለ እንግሊዝኛው በአማርኛ ተገልብጦ በየቦታው ዓይቼ ራሴን ይዣለሁ። ራሳችንን ሳናከብር የሌሎችን ማንነት የራሳችን አድርገን ለመቅዳት ስንጣድፍ፤ ምንኛ ሕልውናችንን ትርጉም እንዳሳጣነው ባወቅን!

      Like

አስተያየት ያስቀምጡ