የኛ ነገር

የኛ ነገር 

(ክፍል ፩)

አንዱ ዓለም ተፈራ፤  ጥቅምት ፲ ፪ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፬ ዓ. ም.

(ውድ የእስከመቼ አንባቢዎች፤ ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ተከታታይ ወራት፤ አዲስ ትረካ በዚህ ገጽ ላይ አሰፍራለሁ። ቢያንስ በሳምንት ሁለት ጊዜ ትረካውን በማሳደግ፤ የፈተናን ታሪክ እቀጥላለሁ። ፈተና አንድ ገበሬ ነው። ትረካው የሱ የዚህ ሰሞን ሁኔታ ነው። ብቅ እያላችሁ መከታተል ትችላላችሁ። ለታዳሚነታችሁ ከወዲሁ ምስጋና አቀርባለሁ።)

መቼ መወለድ እንደምንችል፤ ውሳኔው የኛ አይደለም። ይህ ቢሆን ኖሮ፤ ዓለም መቼ እንደምትጣበብና መቼ ደግሞ ራቁቷን እንደምትሆን መገመቱ ያስቸግራል። ሀቁ ግን፤ ሁላችንም እኛው ባለቤትነት በሌለን ወቅት ተወልደናል፣ በጊዜያችንም እናልፋለን። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ፤ ገና ከናታቸው ማህፀን ውስጥ ያሉ ፅንሶች፤ ምን የፖለቲካ ግንዛቤ እንደሚኖራቸው ተተልሞላቸዋል። የትኛውን የፖለቲካ ፓርቲ እንደሚደግፉና አባል እንደሚሆኑባቸው ተወስኖላቸዋል። ባጭሩ በትውልድ ማንነታቸው፤ ቀሪው ሕይወታቸው ተተልሞላቸዋል። የራሳቸው የሆነ ነፃ አመለካከት እንዲይዙ መብት የላቸውም። ይህ ነው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ለኢትዮጵያዊያን አውርሶን የሄደው። በቀላሉ የማንላቀቀው አባዜ ሆኖብን፤ ይሄው አጥንቶቻችንን እያስቃጨለ፤ ይነዳናል። በዚህ የታሪክ ወቅት ተረኛ ሰው የሆነውን፤ ወላጆቹ ፈተና ብለው የሰየሙትን ሰው፤ ደባርቅ መንገድ ለመንገድ ሲንከራተት አገኘነው።

ከጥቂት ወራት በፊት፤ ፈተና፤ ካዳርቃይ ወጣ ብሎ፤ ወደ ሃዋዛ በሚወስደው ዳገት ላይ በእርሻ ይተዳደር ነበር። እግሮቹ ብዙ ርቀው አያውቁም። ገበያው አዳርቃይ ነው። አንጋጦ የሚያየውን የስሜን ተራሮች ሰንሰለት፤ የምሥራቅና ደቡብ ግድግዳው አድርጎት ነበር። ቁልቁል እስከ ዋልድባ ገዳም ፈሶ የሚታየውን ቆላ ለም መሬት ደሞ፤ የሰሜንና ምዕራብ የዓይኖቹ ማረፊያ አድርጎት ነበር። ከባለቤቱ ከመታሰቢያ እና ከአንድ ልጁ ከክንዴ ጋር የተደላደለ ኑሮ ነበራቸው። የሚኖሩበት ቦታ፤ ምንም እንኳን አሁን የመንግሥት ጢሰኞች ቢባሉም፤ ካያት ከቅመ አያቶቹ የተረከበው ርስቱ ነው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ “የአማራና የትግሬ!” ብሎ መሬቱን ቡያ አጠገብ ከከፈለው ወዲህ፤ ማይፀብሪን የባዕድ ቦታ፤ አዳርቃይን ደግሞ “የኛ!” ቦታ ማለት ይዟል። ያ ብቻም አይደለም። ከዚያ ጊዜ ወዲህ፤ ጥርጣሬና መጠባበቁ የዕለት ጉዳይ ሆኗል። አርሶ አደር የሚባል ነገር የለም። ሁሉም ነገር አማራ ነህ? ትግሬ ነህ? ሆኗል። ባገሩ ሁሉ ያለው፤ ወይ አማራ ነው፤ ወይ ትግሬ ነው። ከ“እነሱ!”ና ከ “እኛ!” እየተባለ ነው ኑሮን ሰው የሚገፋው። ባላገርና ከተሜ፣ ደገኛና ቆለኛ መባባሉ ሁሉ ቀርቷል።

ታዲያ ባለፈው ጊዜ፤ የተኩሱ ጋጋታ አስደንግጦት ሌት የተነሳው ፈተና፤ ወደ በረቱ ዘልቆ ሲመለከት፤ አንዷ ላሙ ወድቃ ትፈራገጣለች። ደም ከጎኗ ይፍለቀለቃል። ድንጋጤው በረታ። ምንም ዓይነት ዝግጅት አላደረገም። ቶሎ ብሎ፤ መታሰቢያንና የአራት ዓመት ልጁን ክንዴን ቀስቅሶ፤ ላሄን ካለው ያጎቱ የአያ አሸብር ልጅ ሊያደርሳቸው፤ እየተደናበረ መንገድ ጀመረ። ሃዋዛን አልፈው ተራራዎቹን ወደ ምሥራቅ ትተው ሲገሰግሱ፤ ከፊታቸው፤ ታጣቂዎች አስቆሟቸው። የመንግሥት ወታደሮች ናቸው ብለው፤ ሊጠጉ ሲሉ፤ በትግርኛ ሲነጋገሩ ሰማ። ወደ ኋላ እንዲሸሹ መታሰቢያንና ክንዴን ጎተታቸው። መታሰቢያ አደናቅፏት ወደቀች። ሊያነሳት ሲቃጣ፤ የታጠቀው ወጣት፤ ጠመንጃውን ቀስሮ በትግርኛ የስድብ ውርጅብኙን እያከታተለ መጣበት። ዓይኖቹ እንባ እንደያዙ፤ ክንዴን ተሸክሞ ወደ ቁልቁለቱ ተንከባለለ። አምስት ጥይት ለቀቀበት። አልተጎዳም። የወንዙን ፈሰስ ይዞ፤ ሽቅብ ወደ ወንዙ መነሻ በፍጥነት መራመድ ያዘ። እኒህ የምናምንቴውቹ ታጣቂዎች አዳርቃይን አልፈው ዛሪማን ያዙ። መንገዱ እየተዘጋበት ነው። ካዳርቃይ ወደ ዛሪማ የሚወስደው መንገድ በጭነት መኪናዎች ጋጋታ ይናጣል። ገና ሌሊቱ አልገለጠም። አሁን አንዳንድ ጊዜ ከሚሸከመው፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በግሩ ከሚያስሮጠው ልጁ ሌላ፤ የባለቤቱ የመታሰቢያ ነገር በልቡ ከብዶታል። ጨለማውን እንኳ ከጉዳይም አልቆጠረው። ቤቴ፣ ከብቶቼ፣ የሚባል ነገር በጭንቅላቱ ቦታ አላገኙም።

መቼም የባላገር ነገር፤ ምንነቱ ከርሻውና ከከብቶቹ ጋር የተቆራኘ ነው። አሁን ግን ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ስለሆነ፤ የዛሬን መትረፍ እንጂ ሌላ ማሰብ አልቻለም። ገና እሱና ልጁ በዛሪማ አቅጣጫ እንኳን ሳይዘልቁ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ታጣቂዎች ድብ ባሕርን ያዙ። ላሄንና ሻግኔንም እያሰሱ ገቡበት። የሱ መያዝ የጊዜ ጉዳይ ሆነ። “ብያዝ! ከመታሰቢያ ጋር አብረን እንሆናለን!” የሚለውን ልቡን፤ ጭንቅላቱ “አንተ ጅል! እኒህ አረመኖች ምን አዘኔታ አላቸው ብለህ ነው! ልጅህን ጨምረህ ልታስረክብ ከሆነ፤ ድንቅ!” ሲል ገታው። ፀሐይዋ ፈንጥቃለች። እንግዲህ ሁሉ ግልጥ ሊሆን ነው።

ወደ አጎቱ ልጅ ቤት ጉዞው ዋጋ የለውም። እሱም አይኖርም። ቤቱም በኒህ የምናምንቴዎች ታጣቂዎች ተወርሷል። ልጁ ከክንዱ ላይ እንቅልፍ ስለጣለውና እሱም በጣም ስለደከመው፤ በጥሻው ውስጥ ተደብቆ አረፍ አለ። ጥሎት ዘወር ባለበት መንገድ፤ የምናምንቴዎች ታጣቂዎች ይነጉዳሉ። “ለመሆኑ እኒህ ሰዎች ከመሬት ይፈልቃሉ ወይንስ ከሰማይ ይዘንባሉ! ማለቂያ የሌላቸው ምን ጉድ ናቸው!” አለና ለማን እንደሆነ እንኳ የሚጠይቀው ሳያውቀው፤ በጎኑ ኮሽታ ሰማ። ሊሰወር ወደ ጥሻው የበለጠ ተጠጋ። እንደሱው የተሸሸጉ ሽማግሌ ነበሩና፤ “አይዟችሁ ልጆቼ! እኔም እንደናንተው ነኝ። እኒህ መናጢዎች መንደሩን ሲያቃጥሉ አምልጬ ነው! ሰው ተደናብሮ ሲሮጥ፤ ከኋላ እንደቅጠል አረገፉት። እኔ መሮጥ አቅቶኝ፤ ይሄው ተዚሁ ተደበቅሁ። አሁን ግን እርቦኛል! ጠምቶኛል! ደክሞኛል! ጉልበቴም ተሟጦ መንቀሳቀስ ተስኖኛል!” አሉ ዓይኖቻቸው እየተጭለመለሙ። ግራ ገባው። ተጨማሪ አንድ ሽክም ተጣለበት። እሳቸው ቢሞቱ ደግሞ በአዕምሮው ምን እንደሚጫነው ማጤን አልፈለገም።

“አባቴ መንደርዎ የት ነው?” ሲል ጠየቃቸው። በመልሳቸው አጎቱን እንደሚያውቁ ተረዳ። ማንነቱን ነገራቸውና ፊታቸው ፈካ። አዲስ ተስፋ አገኙ። “በል የሱን ቤት አቃጥለውታል። እሱ አምልጧል። የቤተሰቡን ዕጣ አላውቅም።  ሞኝ ሞኙ ሰው፤ እኒህን የሰው ዘር አርጎ፤ ከቤተስኪያኑ ገብቶ ተጠጋ። ገብተው የተጠጋውን ሰው እንዳለ ፈጁት። ስማማ! ወንዙን ተከትለህ ሽቅብ ስትሄድ የረኞች ማማ አለ። ተደብቀህ ተዚያ ውጣና፤ የኛን መንደር ለቀው መሄዳቸውን ሰልል። እረኞቹ ትተውት የሄዱት ካለ ደሞ፤ ያን ይዘህ፤ በግሬራውም ውሃ ልታመጣልን ትችላለህ!” አሉትና አደፋፈሩት። የልጁ መዳከም፣ የሽማግሌው ማደፋፈርና፣ የሱ ሆዱ ባዶ መሆን ተደማምሮ፣ እንዲሄድ ገፋፋው። የልጁን ነገር አደራ ሠጣቸውና፤ ከጥሻው መመርኮዣና በትር የሚሆን ዘንጥሎ፤ ወደ ወንዙ መነሻ አመራ። ቀስ እያለና ዙሪያውን እያዳመጠ፤ ወደ ማማው ተጠጋ። የወዳደቁ ልብሶችና ወተት የሞላው ግሬራ አገኘ። ተንከባሎ ራቅ ያለ አገልግል ዓየና ሄዶ ሲያነሳው፤ እንደሞላ ነው።

ምግቡን ማግኘቱ ቢያስደስተውም፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ወታደሮችን መዳረሻ ማወቁ ወሳኝ ሆነበት። እናም በዝግታ ማማው ላይ ወጣ። እየተንቀጠቀጠ ነበር። የማማውን ሲጢጥታ ወታደሮቹ ከሩቅ ይሰሙብኛል ብሎ ፈርቷል። ምንም ሊታየው ስላልቻለ፤ ቀጥ ብሎ ቆመ። ምንም የሚተነፍስ ነገር በአካባቢው የለም። የተቃጠሉት ጎጆዎች በአመድ ተሸፍነዋል። የወዳደቁ ከብቶችን ተመለከተ። ድንገት ወደ ግራው ሲመለከት፤ የሰው ሬሳ ዓዬ። ባለበት ጉልበቱ መንገድ ሠጠና በርከክ አለ። የእንባ ዘለላዎች በጉንጮቹ ወረዱ። ከወደኋላው የድምድምታ ድምፅ ሰማ። ቀና ብሎ ሲያዳምጥና የሚችለውን ሊያይ ሲጥር፤ ከወደ ሃዋዛ በኩል ጥቅጥቅ ያለ የታጠቀ ሰው ጎርፍ ሲተም ዓዬ። እኒህም የነሱ እንደሆኑ ዕውቅ ነው። እናም ቶ ብሎ ያገኘውን ይዞ ወደ ልጁ ገሠገሠ። ሲደርስ እንደተኙ ናቸው። ምግቡንና ወተቱን አቅርቦላቸው፤ በፍጥነት በሉና፤ ትንሽ ራቅ ብለው ተደበቁ። በጣም ትንንሽ የሆኑ ልጆች እየተንጋጉ ሲሄዱ ዓዩ። እኒህ ናቸው የኒህ ምናምንቴ ታጣቂዎች።

የባለቤቱ የመታሰቢያ ነገር ልቡን ሰቅዞ ይዞታል። ሽማግሌውን ሰውዬ ተመለከታቸው። እሳቸውም፤ “የኔን ነገር ተወው። ሰው በመሆኔ ውሎ ማደሩን ብፈልገውም፤ ከልጅህ በተጨማሪ ዕዳ ልሆንብህ አልፈልግም። ለወትሮው ካንዱ ገዳም ገብቼ እተርፋለሁ እል ነበር። እኒህ ዕርጉሞች ገዳሙንም አያከብሩት! እናም አውሬ ከሚበላኝ፤ ዝም ብዬ ወደ ቆላ ወገራ እየተሽሎከለክሁ ያቅሜን እሞክራለሁ። እዚያ ከደረስኩ ብዙ ዘመዶች አሉኝ። አንተ ግን፤ ልጅህን ይዘህ በጎበዝ አቅምህ ገስግስ። ፈጣሪህ ይርዳህ!” አሉት። እሱ ግን፤ “አባቴ! የሁላችን ዕጣ አንድ ነው። እኔም ቢሆን ዋናውን የመኪና መንገድ ቆርጬ ወደ ቆላ ወገራ መሄዱ ነው ያለኝ ምርጫ! እናም አብረን ዕድላችን እንሞክር!” አላቸው። “የለም! አንተ ልጅ ይዘሃል። ከኔ ትሻላለህ! አንዳችን እንኳ እንትረፍ! ሂድ ግዴለህም! የሚያናግረኝ ሰው ማግኘቱ ለኔ ተስፋ ሠጥቶኛል! እኔ ጎታታ ነኝ። ሂድ ልጅህን አትርፍ!” ብለው ያሰናብቱታል። የምናምንቴዎች ታጣቂዎቹ ነጉደው እስኪጨርሱና ካካባቢው እስኪሰወሩ ድረስ ባሉበት ቆዩ። መሄዳቸውን እስኪመሽ ድረስ አላረጋገጡም ነበር። ሲመሽ በለመዳት ተሽሎክሉኮ ወደ ማማው ሄደ። ወጥቶ ሲያዳምጥ፤ ምንም ድምፅ የለም። እናም ሰውዬውን ተሰናብቶ፤ ቀድሟቸው ወደ ቆላ ወገራ ጉዞውን ጀመረ።

በዛሬማና በድብባሕር መካከል አውራ ጎዳናውን አቋርጦ ወደ አጅሬ በሚወስድ አቅጣጫ፤ የጨረቃዋን ብርሃን ተጠቅሞ አመራ። ቦዛን ወደ ግራ በመተው፤ ፍጥነቱን ጨምሮ ገሰገሰ። አሁን ደከመኝ የለም። አሁን ራበኝ የለም። አሁን ጠማኝ የለም። አንዳንድ ያልተነኩ ጎጆዎች ዓይቷል። አብዛኛው ግን ተቃጥሏል። በጥይት ተመትተው የወዳደቁ ከብቶችም ዓይቷል። እህሉም የከብት መንጋ የተነዳበት ይመስል አጉል ሆኗል። ካልተቃጠሉት ቤቶችና አንዳንድ ታጥቀን ቤታችንን እንጠብቃለን ካሉ ቆላ ወገሬዎች ቤት ዕርዳታ እያገኘ፤ በአራተኛው ቀን ዳባት ገባ። ከዚያ ሆኖ፤ ጎንደር ላለችው የባለቤቱ እህት መልዕክት ላከ። እየበረረች የደረሰችው ዋርሳው፤ ሁሉን ነገር ሲነግራት፤ ምጥ እንደያዛት ሁሉ በርከክ አለች። ስትረጋጋ፤ እሱ የባለቤቱን ጉዳይ እንዲከታተልና ተመልሶ የሚሄድበትን መንገድ እንዲፈልግ፤ እሷ ደሞ ልጁን ይዛ ጎንደር እንድትሄድና ሲረጋጋ መጥቶ ሊወስደው እንደሚችል መከረችው። እሱ አውጥቶ አውርዶ፤ ሌላ ምርጫ እንደሌለው አውቆታልና፤ ሃሳቧን ተቀበለ። የመንግሥት ሰዎች እርዳታ እንዲያደርጉለትና ሚስቱን እንዲያፋልጉለት ጠየቃቸው። እነሱም ይሄ የነሱ ሥራ እንዳልሆነና ባሁኑ ጊዜ ዋና ተግባራቸው፤ ተዋጊውን መርዳት ስለሆነ፤ እሱም አብሯቸው እንዲዘምት ይመክሩታል። ቀጥለውም ስለምናምንቴዎቹ ታጣቂዎች መረጃ እንዲሠጣቸው ጠየቁት። እነሱ መረጃ እንዲሠጣቸው ነው የሚፈልጉት። እሱ ደግሞ የሚያውቀው ነገር የለም። ቢኖርም ውስንና ጠቃሚነት የሌለው ነበር። እነሱ ከሱ የሚፈልጉትና እሱ ከነሱ የሚፈልገው አልተገናኘም። ወታደራዊ ስልት ዕውቀትም ሆነ የምናምንቴዎችን እንቅስቃሴ ሚስጢር የሚረዳበት ግንዛቤ የለውም። የመንግሥቱ ሰዎች የሱን ሁኔታ አላጤኑለትም። እናም ተለያዩ። እሱ በመንገድ እየተንከራተተ ከሰነበተ በኋላ፤ ሲርበውና ሲጠማው፤ “ቀሪውን ሕይወቴን ሚስቴን ስፈልግ አሳልፈዋለሁ!” በማለት፤ ታጣዎች ከሚሰለጥኑበት ቦታ ሄዶ የፋኖ ሠልጣኝ ሆነ።

(ሁለተኛው ክፍል ይቀጥላል)