አበራ ነጋሣ

አበራ ነጋሣ ( ከአንዱዓለም ተፈራ )

የልጁን ፊት አተኩሮ እየተመለከተ፤ በልቡ በጣም ሩቅ ወደሆነ የማያውቀው ሀገር ዘመተ። ልጁ የአስራ ስድስት ዓመት ወጣት ነው። አባቱን አስታውሶ ነጋሳ ብሎ ስይሞታል። እናም የልጁ ስም ነጋሳ አበራ፤ የሱ ስም አበራ ነጋሳ ነው። አበራ ነጋሳ የተወለደው አዘዞ ከተማ ነበር። አዘዞ፤ ከጎንደር ከተማ ወደ አየር ማረፊያው ሲሄዱ፤ ከከተማው አስራ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፤ አየር ማረፍያው ከመድረሱ በፊት ደግሞ፤ ሶስት ኪሎ ሜትር ቀድማ ትገኛለች። አዘዞ የወታደር ሰፈር ነበረች። ባለፈው የ፳ኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ አካባቢ፤ የሰሜኑን ሀገራችንን ለመከላከል የተቋቋመው የ፪ኛ ክፍል ጦር፤ ከሶስቱ ብርጌዶች አንዱ፤ የ፰ ብርጌድ፤ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ያለውን ደንበር ለመጠበቅ አዘዞ ሰፍሮ ነበር። ይህ የ፰ ብርጌድ፤ ሶስት የሻለቃ ጦሮችና አባሪ የከባድ መሳሪያ፤ የሕክምና፣ የመገናኛና የዋናው መስሪያ ቤት ከፍል ሲኖሩት፤ አንዱ ፩ኛ ሻለቃ ጦር ጎርጎራ፤ ሁለቱ ደግሞ፤ ከአባሪ ክፍሎቹ ጋር አዘዞና አየር ማረፊያው ነበሩ። እኒህ የሻለቃ ጦሮች ፍጹም ተደላድለው የተቀመጡ አልነበሩም። ከአካባቢው ተወላጆች በተመለመሉ ወታደሮች የተሞላው የጎርጎራው የሻለቃ ጦር፤ በ፲ ፱ ፻ ፶ ፮ ዓመተ ምህረት ገደማ፤ በሶማሊያ የተቃጣውን አደጋ አስመልክቶ፤ የሶስተኛውን ክፍለ ጦር ሊረዳ ወደ ኦጋዴን ሄዶ፤ በዚያው ተመድቦ ቀርቷል። አዘዞ የነበረውም የ፬ኛው ሻለቃ ጦር ከኮንጎ ከተመለሰ በኋላ ኤርትራ ተልኮ፤ የምዕራባዊ ቆላውን፤ አቆርደትን፣ ከረንንና ተሰነይን ከ፲ ፱ ፻ ፶ ፯ ዓመተ ምህረት ጀምሮ ቤቱ አድርጓል። በዚያ ምትክ ደግሞ፤ አየር ማረፊያው ላይ አዲስ ሁለት የ፳ ፬ኛና የ፴ ፩ኛ የሻለቃ ጦሮች ተመስርተው ነበር።

የአበራ ነጋሳ አባት ወደ አዘዞ የመጡት፤ ከ፲ ፱ ፻ ፶ ፫ቱ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ነበር። ወታደር ነጋሳ ኦላና፤ በጣም ረጅምና ቀጥ ያሉ፤ በወቅቱ አዲስ አበባ በክብር ዘበኛነት ተመልምለው ያገለግሉ የነበሩ የጦር ሠራዊቱ አባል ነበሩ። በመፈንቅለ መንግሥቱ ጊዜ ምን እንደተደረገ ፍጹም አያውቁም። ብቻ አብረው ከምድብ ወታደሮቻቸው ጋር ባንድ ጎራ ሆነው ተኩስ እንደተጀመረ ያስታውሳሉ። ሆኖም የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ከከሸፈ በኋላ፤ ተሸናፊ ሆነው መማረካቸውን ያውቃሉ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከብዙ ወታደሮች ጋር አዘዞ ካለው የ፰ኛ ብርጌድ ተመድበው ተቀላቅለዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከዚህ ዓለም እስከ ተለዩ ድረስ፤ አዘዞን ቤታቸው አድርገዋል። በመጡ በሶስተኛው ዓመት፤ የጠገዴ ተወላጅ የሆኑትን ወይዘሮ አልጠገብን አግብተው ሙሽሪትን፣ ፋሲካንና አበራን ወልደዋል። አበራ የተወለደው መስከረም ፲ ፮ ቀን ፲ ፱ ፻ ፷ ፩ ዓመተ ምህርት ነው። አባቱ አበራን ሰላሌ ስለሚገኙት ዘመዶቻቸው ብዙ አስተምረዉታል። ዘመዶቹን አንድ ቀን ሄዶ እንዲገናኝ ሲያስቡ፤ ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የወታደር ደሞዝና የመጓጓዣው ወጪ አልጣጣም ብሏቸው፤ ዛሬ ነገ ሲሉ በርጅና ዘመናቸው ድንገት ታመው ተለዩት። የቀብር ስነ ሥርዓታቸው የተፈጸመው ሎዛ ማርያም ቤተ ክርስትያን ነው። ከአዘዞ ሰው ሌላ የሚዛመዱት ሰው አልተገኘም። እናቱም ወይዘሮ አትጠገብ፤ አዘዞ ተክለሃይማኖት ነው የተቀበሩት።

ወታደር ነጋሳ ልጃቸውን አበራን በደንብ አስተምረው፤ በሀገራቸው ታላቅ ሰው እንዲሆንላቸው ጥረዋል። ሴቶቹን ብዙም ለትምህርታቸው አልተጨነቁም ነበርና ለወታደሮች ዳሯቸው። አበራም አዘዞ ሲያድግ፤ ከአፄ ፋሲል ትምህርት ቤት ጓደኞቹ ከነአበራ ደለሳ፣ ተረፈ ነጋሳ፣ አበራ ወልደየስ፣ ቢራራ ተስፋሚካዔል፣ ይሁኔ ጌታሁን፣ ሙሉዬ መኮንን፡ ሰለሞን ሻንካ ጋር ሆኖ፤ የሎዛ ማርያም አስተሮዬ ሲከበር፤ የኦሮሞኛ፣ የወላይትኛ፣ የትግርኛ፣ የአማርኛ፣ የጉራግኛ፣ የአፋርኛ፣ የሶማልኛ ዘፈኖችን ይጨፍር ነበር። አበራ እንዳባቱ ሎጋና ቀጥ ያለ ወታደራዊ አቋቋም ስለነበረው፤ ጓደኞቹ ሽምበቆው የሚል ስም ሠጥተውታል። ጓደኛሞች የሆኑ ያዘዞ ልጆች፤ ስም መሠጣጠት ያውቁበታል። ቁራ፣ ድምቢጥ፣ ድንች፣ ሱዘንድ፣ ዋንዛ፣ ድኩሌ፣ ቡሊት፣ ሰማይ ዳሱ፣ ኳስ ፊደሉ፣ ቁንን ከስሞቹ ጥቂቶቹ ነበሩ። በአስተሮዬ የጥምቀት ዘፈን ጊዜ፤ ምንም እንኳ ዜማ አውጪዎቹና ትክክለኛ ጨፋሪዎቹ ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆኑም፤ አብረው የሚጨፍሩት ወጣቶችና ሌሎች ወታደሮች በሙሉ፤ የዘፈኑ የጋራ ባለቤት ነበሩ። በየዓመቱ የማይለዩት ገብሬ ሽበሺ ከጎንደር እና አለቃ አድማሱ ከአዘዞ፤ ገብሬ ሽበሽ እማማ ውብ ናት ደማም ናትን ሲያወርድ፤ አለቃ አድማሱ በዘነዘና ቁመናቸው እስክስታውን ሲያወርዱት ለጉድ ነበር።

አዘዞ የሁሉም ቤት ነበረች። ዘፈኑ ሁሉ የኢትዮጵያ ዘፈን፣ ቋንቋው ሁሉ የኢትዮጵያ ቋንቋ ይባሉ ነበር። የትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ለመጣ ኢትዮጵያዊ፤ አዘዞ ቤቱ ነበረች። አዘዞ አንድ ዓመት አፄ ፋሲል ትምህርት ቤት የተማረ ወጣት፤ የአዘዞ ልጅ ተብሎ ይታወቃል። ወታደሮች፤ ሁሉም ከወታደሩ ሰፈር (ካምቦ) የድማዛ ድልድይን ተሻግረው፤ የሲቪሉ ሰፈር (ብላጆ) ቤት ገዝተው፤ የጡሮታ ጊዜያቸውን ያሳልፉ ነበር። ከአስመራ የመጡት አዘዞ ያገኙዋቸውን አግብተው ወልደው ከብደው አዘዞን ቤታቸው አድርገዋል። ከሐረር ጀምሮ እስከ ወለጋ፤ ከሲዳማ እስከ ትግራይ የመጡትም እንዲሁ። ከአዘዞ ተቀይረው የሄዱም በዚያው አግብተው ከትመዋል። አንዳንዶቹ ተመልሰው አዘዞ በመመደብ ቤተሰባቸውን ይዘው መጥተዋል። መጋባቱ፣ ክርስትና መነሳሳቱ፣ ማኅበሩና እድሩ፣ ቁቡና ስንበቴው ድብልቅልቅ ያለ ነበር።

ያች የአስተሮዬ ቀን፤ በወታደሮችና በአዘዞ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን፤ በድፍን ጎንደርና በአካባቢው ባሉ ትንንሽ ከተሞች በናፍቆት የምትጠበቅ ነበረች። ላብ በላብ እስኪሆኑ የሚጨፍሩት እድምተኞች፤ መብላት ረስተው ተጎትተው እስኪወሰዱ ድረስ መድረኩን አይለቁም ነበር። በአዘዞ የአስተሮዬን በዓል ለማክበር የሚታረደው ዳንግሌ በግ፣ ዳጉሳ አውራ ደሮ፣ የሚጎዘጎዘው ግጫ ሣርና የሚጤሰው ጠጅ ሳር ለጉድ ነበር። ብሉልኝ ጠጡልኝ እየተባሉ በየመንገዱ የሚጎተቱት እንግዶች ብዙዎች ነበሩ። በአስተሮዬ አዘዞ የድግስ ከተማ ነበረች። አዘዞ በአፄ ቴዎድሮስ ጊዜ የጦራቸው ማሳረፊያ እንደነበረች ይነገራል። ቀድሞ በተክለሃይማኖት ደብሩ ዙሪያ ያለው የመጀመሪያው የነዋሪዎች መንደር፤ ደብረዘይት ተብሎ ይታወቅ እንደነበር ተክለሃይማኖት ያለው መጽሐፍ ያትታል።

ከወታደር ሰፈሩ አልፎ የድማዛን ድልድይ ተሻግሮ ያለው ነዋሪ፤ እንደ የጦር ሰፈሩ ሁሉ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ነበሩ። እንዲያውም በሚያስገርም ሁኔታ ከውጪ ሀገር የመጡ ሁሉ ቤታቸው ያደረጉበት ሰፈር ነበር። ከሁለቱ የሰሜንና የደቡብ የመኖች የመጡ ነጋዴዎች፤ ኢትዮጵያዊያን ሚስቶችን ከዚሁ አግብተው፤ ሱቆችን በሙሉ ይዘው ነበር። ሀጅ አሊ፤ አሊ ዞማ፣ መረጡ፣ መሐመድ አሊ፣ አሊ በርሚል፣ ጥቂቶቹ ነበሩ። ሰፈሩ መስጊድ ሲኖረው፤ ቤተ ክርስትያን ግን አልነበረበትም። የሎዛና የተክለሃይማኖት ደብሮች ያሉት በወታደሩ ሰፈር ወገን ነው። የሲቪሉ ሰፈር፤ እንደ ወታደሩ ሰፈር በጣሊያን ፋሽስቱ አጭር ጊዜ ወረራ የተሰሩ ቤቶች ብዙ ባይኖሩትም፤ ከድማዛ ጥግ የነበረው አስተዳዳሪው የነበሩበት ቤትና መሐል ገበያው ላይ ያለው ወፍጮ የተተከለበት ቤት፤ የፋሽስቱ ጣሊያ ቅሪት ነበሩ። የብርጌዱ መኪና ጠጋኝ አብደል ራህማን እድሪስ፣ ጠንቋዮች እነ የማነ ብርሃን፣ አለቃ አድማሱ፣ የከተማው አድማቂዎች ነበሩ። ግርማይ “ደንጊያ ወርዋሪው”፣ ዋንዛዬ “ጠጠው በል!” ማማ አዋጉ እብዲቱ፤ ከማል ዱክየው፡ አበባው ዘላኔ እብዱ፣ የከተማዋ ትክሎች ነበሩ። አባ መልኬም የሠራዊቱ ቄስ ነበሩ። ቀደም ብሎ ጁዳ የሚባል ሕንድ፤ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ሆኖ እዚያው ትምህርት ቤቱ ውስጥ ከባለቤቱና ከልጆቹ ጋር ይኖር ነበር።

አበራ ነጋሣ አዘዞ አፄ ፋሲል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን አጠናቆ፤ ወደ ጎንደር የቀዳማዊ ኋይለ ስላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሄደ። የአስረኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት፤ ለመምህርነት ሙያ ሥልጠና ፈተና አልፎ፤ ወደ ሐረር ተጓዘ። ሐረር በትምህርት ላይ ሳለ፤ አዘዞ አብራው ከተማረችውና ወደዚሁ አብራው ከመጣችው ከፀሐይ ተስፋእግዚ ጋር ጓደኝነቱን አጠበቀ። ፀሐይ ተሰፋእዝጊ የመቶ አለቃ ተስፋእግዚ ልጅ ናት። አባቷ የመቶ አለቃ ተስፋእዝጊ ከአስመራ ወደ አዘዞው የ፰ኛ ብርጌድ ተዛውረው የመጡ ነበሩ። የፀሐይ አባትና እናት ወደ አዘዞ ከመምጣታቸው በፊት፤ ከአስመራ ውጪ ፍፁም ተንቀሳቅሰው አያውቁም ነበር። ሁለቱም ወላጆቿ ተወልደው ያደጉት አስመራ ነበር። እናቷ ትምህርት ቤት የመግባትና የመማር ዕድል አልነበራቸውምና፤ አዘዞም መጥተው አማርኛ መናገር ይቸግራቸው ነበር። አባቷ ወታደርነት ተቀጥረው የመቶ አለቅነት እስኪያገኙ ድረስ፤ ያገለገሉት አስመራ በነበረው የ፪ኛ ክፍለ ጦር ውስጥ፤ በአንዱ ብርጌድ፤ በአንዱ የሻለቃ ጦር ተመድበው ነበር። አዲሱን ማዕረግ እንዳገኙ፤ አዘዞ ተመደቡና መጡ። አበራና ፀሐይ የክፍል ጓደኝነታቸው የጀመረው፤ ፀሐይ ከአስመራ እንደመጣች ነበር። ፀሐይ ከክፍል ጓደኞቿ ከነማሚቱ ደለሳ፣ ፀሐይ ጤናው፣ ፀሐይ እቁባይ፣ እናኑ ተገኝ፣ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበራት። የአዘዞ ልጆች አብረው ከመማርና አብረው ከትምህርት ቤት ውጪም ጓደኝነት ስለነበራቸው፤ ግንኙነታቸው ዘለቄታ ያለውና አብሮ ከመወለድ ያልተለየ ነበር። ከፊሎቹ ወላጆቻቸው ከሸዋ፣ ከፊሎቹ ደግሞ ከኤርትራ፣ ከሐረር፣ ከትግራይ፣ ከከፋ፣ ከአርሲ፣ ከሲዳማ የመጡ ነበሩ። አዘዞን ትንሿ ኢትዮጵያ ይሏት ነበር ነዋሪዎቿ። አበራና ፀሐይ ሐረር ሲገቡ፤ አብረው ከማደጋቸውና ከወላጆቻቸው በዚህ ርቀት አብረው በመገኘታቸው፤ አዘውትረው ሲገናኙ ወደ ከንፈር ጓደኝነት አመሩ።

አበራና ፀሐይ ከመምህርነት ሥልጠናው ሲመረቁ፤ አብረው እንዲመደቡ ብዙ ጥረት አደረጉ። ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ መጋባታቸውን ለትምህርት ቤታቸው አስታወቁ። እናም አብረው አርሲ ውስጥ፤ ከአሰላ ራቅ ባለች ገጠር ቦታ ተመደቡ። ከሶስት ዓመት በኋላ ወደ አዘዞ ተዛወሩ። በዚያን ጊዜ፤ የፀሐይ አባት ጡሮታ ወጥተው፤ ወላጆቿ ወደ አስመራ ተመልሰው ሄደዋል። አዘዞም በሚያውቋቸው ሰዎች መካከል፤ ደግሰው ጋብቻቸውን አሰመሩበት። የአዘዞ ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ዳሩ። ፀሐይ አስመራ እየተመላለሰች ወላጆቿን ትጠይቅ ነበር። አበራና ፀሐይ የፖለቲካ ሰው ስላልነበሩ፤ ለ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ቱም ሆነ ለ፲ ፱ ፻ ፹ ፫ቱ የመንግሥት ሥልጣን ቅይይር ምንም ዓይነት ትኩረት አልሠጡትም። “ፖለቲካ የሌሎች ጉዳይ ነው። እኛ መምህራን ነን። የመንግሥት ጉዳ እኛን አያገባንም።” ይሉ ነበር። በ”የዕድገት ኅብረት ዘመቻ” ተብሎ ወጣቶቹ ሲበታተኑም ሆነ በቀይ ሽብር ጭፍጨፋ፤ አልተነኩም። ያ ሁሉ አልፎ አዲስ ገዢ መጥቶ፤ ኤርትራውያን ወደ ሀገራቸው ይመለሱ ተብሎ ሕዝቡ ሁሉ ሲተራመስ፤ ፀሐይ ምንም አልመሰላትም ነበር። ነገር ግን፤ ጉዳዩን በደንብ የተረዱ ጓደኞቿ፤ በቤታቸው ደብቀው አተረፏት። በዚህ ላይ ደግሞ አበራ በባለቤቴ የመጣ የኔ ጉዳይ ነው ብሎ ስለተነሳ፤ የሚችለውን ሁሉ በማድረግ አተረፋት። ፀሀይ ኤርትራዊ ነኝ አላለችም። የድምጽ መስጠቱም ጉዳይ አልነካትም። አሁንም በኢትዮጵያዊነቷ፤ ከኢትዮጵያዊ ባለቤቷና ልጆቿ ጋር ነው የምትኖረው። ፖላቲካን አታምጡብኝ ብላ እንደ ኮረንቲ የምትፈራው ጉዳይ ነው።

አሁን ግን ጊዜው ተለውጧል። አበራና ፀሐይ ችግር ውስጥ ናቸው። ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሀገር መሆኗ ቀርቷል። ኢትዮጵያ የብሔሮችና የብሔረሰቦች ክልሎች ጥርቅም ስለሆነች፤ ግለሰቦች በየብሔሮቻቸው ክልሎች ሲሆኑ ብቻ ነው፤ በክልል አባልነታቸው ኢትዮጵያዊነታቸው የሚታወቀው። ከብሔር ከልሉ የወጣ ግለሰብ፤ እንደውጪ ሀገር ሰው ተባራሪ ነው። እንዲያውም የውጪ ሀገር ግለሰብ የበለጠ ይከበራል። ይህን ደግሞ አስከባሪዎቹ የመንግሥት ካድሬዎች ናቸው። ይህ የገዥዎችን አባሎችና ዘመዶች አይነካም። ለነሱ የተለየ ሕግ አላቸው። ለሕዝቡ የሚያገለግል አንድ ሕግ፤ ለገዥዎቹ የሚያገለግል ደግሞ የተለየ ሕግ፤ በሀገራችን አለ። ያካባቢው ሕዝብ መብት የለውም። መንግሥት የሚለውን መስማትና መንግሥት ያዘዘውን ማድረግ ብቻ ነው ሕዝቡ ያለበት። ምንም እንኳ አብረው ያደጓቸውና የሚያውቃቸው ሁሉ፤ የኛ ናቸው ስለሚል፤ በሕዝቡ በኩል ችግር ባይኖርባቸውም፤ በመንግሥቱ በኩል የሚደርስባቸውን በደል መገመት አይቻልም። አዘዞ ማለት አበራና ፀሐይ፤ አበራና ፀሐይ ማለት አዘዞ ናቸው! ብለው ነው ሁሉም የሚያምኑ። ኤርትራዊያን ይውጡ በተባለበት ጊዜ እንደተደረገው ሁሉ፤ ሕዝቡ እንደሚከላከልላቸው ያውቃሉ። ከመንግሥቱ በኩል ያሉት አዲስ የመጡ ወጣት የኮር አባሎች ግን ሌላ ናቸው። ዛሬ ጊዜ ባለሥልጣኖቹና ወጣቶቹ፤ ቀድሞ ለነበረው የሕዝቡ ግንኙነትና ለቆዬው አስተሳሳሪ ባህል ደንታ የላቸውም። ደንታ የላቸውም ብቻ ሳይሆን፤ አያውቁትም፤ ማወቅም አይፈልጉም። መሪ ድርጅታቸው ከሚነግራቸው ነገር ውጪ፤ ሌላ ትክክል ሆነ ሀቅ የሚባል ሰውም ሆነ ነገር የለም፤ ካለም መኖር ስለሌለበት ይታሰራል፣ ይሰደዳል ወይንም ይገደላል። በፓርቲያቸው የሚነገራቸውን እንደ ቅዱስ ቃል ይዘው ከመብረር በስተቀር፤ ጭንቅላታቸውን ተጠቅመው ሁኔታዎች መመርመርና ውሳኔ መሥጠት ምን እንደሆነ አያውቁም፤ አልሠለጠኒበትም፤ አይፈቀድላቸውም።

በተጨማሪም፤ ሁሉም ለራሱ የሚል መመሪያ ያለ ይመስል፤ እኒህ የገዥው ቡድን አባላት፤ ራሳቸውን ለማበልጸግ፤ መንግሥታዊ መዋቅሩን ለጥጠው ይጠቀሙበታል። ይህ ነው አበራን ያስጨነቀው። “ለምን የልጄን ስም ነጋሳ አልኩት!” ብሎ አሰበ። “እንኳንም አንድ እሱን ብቻ ነጋሳ አልኩት! ሴቶቹን እንኳን የአካባቢውን ስም ሠጠኋቸው!” ብሎ ልቡ በሌሎቹ ላይ ሊደርስ ይችል የነበረውን አስቦ ተረጋጋ። ሴቶቹ ልጆቻቸው፤ ከወታደሮች ባሎቻቸውና ልጆቻቸው ጋር ሆነው፤ ማንነታቸውንም ሆነ የወላጆቻቸውን ማንነት ረስተዋል። ኢትዮጵያዊነታቸውን ብቻ ነው የሚያውቁት። “ሴቶቹን ፀሐዬ የኤርትራ ስም ብትሠጣቸው ኖሮ፤ ምን ይበላን ነበር!” በማለት አሰበ። አባቱ ለኢትዮጵያ ብለው ነበር ወታደር ሆነው ያገለገሉት። እዚህ ሲመደቡም “ሀገሬ ኢትዮጵያ!” ብለው ነበር እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ የኖሩት። “አሁን ሕዝቡ የኔ ነህ እያለኝ፤ እንዴት የመንግሥት ካድሬ ጭንቀት ይፈጥርብኛል!” ብሎ አዘነ። ሕዝቡ ደግሞ ጉልበት የሌለው በሆነበትና መንግሥቱ ያፈተተውን በሚያደግበት ወቅት፤ “ምን ይውጠኝ ይሆን?” የሚለው ልቡን ሰቅዞ ይዞታል። መንግሥቱ የሕዝቡን ድምጽ የሚሰማና ለሕዝቡ የሚያገለግል ሳይሆን፤ ሕዝቡ ለመንግሥቱ አገልጋይና መንግሥቱን ብቻ እንዲሰማ የተገደደ ሆኗል። ጥቂት ያካባቢው ተወላጆች የሆኑ የኮር አባላት ቢኖሩም፤ ለሆዳቸው ያደሩ ስለሆኑ፤ “ደደብ አማራ!” እያሉ ገዥዎቻቸው ሲሰድቧቸው እንኳ፤ ግድ የላቸውም። ሆዳም ማተብ የለውም። ቤቱም ሆዱ ነው።

“የኔስ የኔ ነው። አርጅቻለሁ። ከተወለድኩበት ቀን ይልቅ የመቃብሬ ቀን ይቀርባል። አሳቤ ለልጄ ነው። እኔ የአባቴን የትውልድ ቦታ እንኳን አላውቅ። ያባቴን ቋንቋ አላውቅ። እትብቴ የተቀበረው አዘዞ። ያዘዞ ሰው ደግሞ የኔ ነህ ብሎኛል። አዘዞ የኢትዮጵያ ክፍል ናት። በኢትዮጵያዊነቴ ደግሞ፤ እንኳንስ ተወልጄ የኔ ብዬ ባደግሁበት ቦታ ይቅርና፤ የትም የኢትዮጵያ ክፍል መኖር እችላለሁ። እኔ ደግሞ ያዘዞን የድማዛ ውሃ ጠጥቼ ያደግሁ ያዘዞ ልጅ ነኝ። እንዴት ብዬ ነው ያዘዞ ልጅ አይደለሁም የምለው? ለምን ካዘዞ እባረራለሁ? ተባርሬስ የት ነው የምሄደው? በመንግሥት ፍላጎት የተነሳ እንዲህ ያለ ጣጣ ውስጥ ለምን ገባሁ! አንተ ፈጣሪ ምን በደልኩህ!” በማለት አምላኩን አማረረ። “የሰውን ነገርና ተግባር በአምላክህ አታሳብብ!” የሚለው ከጎኑ ጠፋ።

አበራን ምን ሊውጠው ይሆን? ይህ የአበራ ብቻ ጥያቄ አይደለም። የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነኝ ባይ ጥያቄ ነው። ዛሬ ያዲስ አበባ ልጅ ነኝ በማለት እግሩን አፈራግጦ የተቀመጠ ሰው፤ ነገ አዲስ አበባ አልተወለድክም ወይንም ዘርህ አዲስ አበባን አይሸትም፤ የናትህ ዓይንም የተለዬ ነው፤ ተብሎ እንደሚባረር ማወቅ አለበት። መቼ ነው ኢትዮጵያዊነት ማለት በሁሉም መልኩ የኢትዮጵያ ዜጋ መሆንና መብቱም ከዚያ የሚመነጭ የሚሆነው? አበራስ ምን ማድረግ አለበት? ፀሐይስ? ልጆቻቸውስ? በሌሎች ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንስ? እስካሁንስ የት ገቡ!