የኛ ነገር ክፍል ፫

አንዱ ዓለም ተፈራ፤  ቅዳሜ፣ ጥቅምት ፳ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፬ ዓ. ም.

“ዓያችሁ፤ እነሱ ሲመጡ፤ ተጠንቅቀው ነው። ዙሪያቸውን እያዳመጡና ሸፋኝ ከኋላቸው አስቀምጠው ነው። ደሞ  እኛ እዚህ ብናጠቃቸው፤ ሽማግሌውንና አሮጊቶችን ሴቶች፤ ከኛ ጋር እንደተባበሩ ሲለሚጠረጥሩ ይፈጇቸዋል። ዓይናችን እናጣለን።እናም እኛን ሊከቡና በረሃውን እየደመሰሱ፤ መዳረሻ ሊያሳጡን ይችላሉ። ወደ ላይ ሲመለሱ ግን፤ ምግባቸውን ይዘው፣ አቸነፍን ብለው፣ ተዝናንተው፣ መንገዱ ሲመታቸው፤ ጠመንጃቸውንም በደንቡ ሳይይዙት እናገኝና፤ የልባችንን እናደርሳለን! ሽማግሌውና ሴቶቹ ከኛ ጋር የሚያብሩት፤ እስካልተጋለጡ ድረስ ነው። እኛን ለመርዳት ብለው ነው ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ያሰለፉት!” ብሎ በተደጋጋሚ ይማጸናቸዋል።

ያየሽና ወንድሞቹ፤ “የተናገርኸው ትክክል ነው። ካልክ እሺ!” አሉና ተስማሙ።

እነሱም፤ ፈተና በሚያውቀው አገር እየተሹለከለኩ፤ የምናምንቴዎችን መመለሻ አደቡ። ጥሩ ቦታ መርጠው መሸጉ። ከዚያ ቦታ ዋሉ። ምግብ አልበሉም። ጠምቷቸዋል። ንቅንቅ ግን አላሉም። ፀሐዩዋ ማዘቅዘቅ ስትጀምር፤ የታጣቂዎችን ድምጽ ሰሙ። ያልነበራቸው ጉልበት ልባቸውን ሞላው። አንዳቸው በሌላቸው ውስጥ ከፍ ያለ እምነት አገቡ። ከወንድማማችነት የበለጠ፤ አብሮ ለመሞት የመሰለፍ ጉዳይ፤ ስሜታቸውን ከፍ አደረገው። አሁን የሞትና የአለመሞት ጉዳይ ነው የበላይነቱን የያዘው። ድምጻቸውን አጥፍተው ጠበቁ። ፈተና እንዳለውም፤ በጣም ተዝናንተው፣ እየተሳሳቁ፣ ምግብ በሠጧቸው ሰዎች እየተሳለቁ፣ ጠመንጃቸውን ከትከሾቻቸው ላይ እንዳነገቱ፣ መንገዳቸውን እየተመለከቱ ቀረቡ። እነ ፈተና በጣም ከመንገዱ ቀርበው ይጠብቃሉ። ከላይ የምናምንቴዎቹ ሸፋኞች፤ ምንም እንደሌለ ስለቆጠሩ መሆን አለበት፤ ቦታቸውን ጥለው ወደ ሰፈራቸው ተመልሰዋል፤ ዓይታዩም።

ልክ የምናምንቴዎቹ ታጣቂዎች ከነሱ አጠገብ ሲደርሱ፤ ባቀባበሏቸው የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎቻቸው ሶስቱን ገደሉ። ፈተና ቶሎ ብሎ ጠመንጃዎቹን ለያየሽና ወንድሞቹ ሠጣቸው። ምናምንቴዎች አስገድደው ያመጡትን ምግብና ወተት ተከፋፍለው ያዙ። ወድ አጅሬ አቅጣጫ በፍጥነት ገሰገሱ። የምናምንቴዎች ታጣቂዎች፤ ጥይት እንደ ዝናብ እያወረዱ ተኩስ ወደ ተደመጠበት መጡ። ተኩሱ ከተደመጠበት ብቻ ሳይሆን፤ ዙሪያውን ሁሉ አርከፈከፉበት። ፈተናም፤ “መልስ መሥጠት የለም! ዝም ብለን መገስገስ ነው ያለብን!” የሚል ትዕዛዝ የመሰለ መልዕክት ነገራቸውና፤ ፈረጠጡ። የምናምንቴዎች ተኩስ በሁሉም አቅጣጫ ሆኖ፤ እየቀረባቸው ሄደ። ምናምንቴዎቹ ቆርጠዋል። በሁሉም አቅጣጫ እየሄዱ ናቸው።

የምናምንቴዎቹ ታጣቂዎች ብዙ ዓይነት ናቸው። ጠንካራ የቡድኑ አባላትና በዓላማቸው በደንብ የሚያምኑ አሉ። እኒህ ጠንካራ ተዋጊዎቻቸው ናቸው። ከዚያ ቀጥለው ደግሞ፤ በመላ ትግራይ፤ ወላጆችን እያስገደዱ ያሰለፏቸው ወጣቶች አሉ። እኒህ የምናምንቴዉን ዓላማ አያውቁም። ነገር ግን፤ “አማራ ሰው አይደለም! አማራ ዋና ጠላትህ ነው። አማራ ካለ ትግሬ አይኖርም! አማራ ታሪክህን ቀምቶሃል! አማራ ትግሬን አይወድም! መጥቶ ከሚያጠፋህ፤ ሄደህ ጨርሰው!” እየተባሉ የተሰበኩ ወጣቶች ናቸው። ለጦርነት መሰለፍ የሌለባቸው ገና ለጋ ወጣቶች ናቸው። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ፤ መከላከያ ከትግራይ ሲወጣ፤ ወደ ጎንደርና ወሎ ዘምቶ፤ በደረሰባቸው ቦታዎች በሙሉ፤ የሚፈራውን እየገደለ፣ ያገሩን ንብረት እየዘረፈ፣ ከብቱን እየነዳ፣ የባለ አገሩን ቤቶች እያቃጠለ፣ ከብቶቻቸውን፤ የሚፈልገውን ወደ ትግራይ ነድቶ፣ የፈለገውን በልቶና ያልቻለውን በጥይት ዘርሮ፣ እህሉን ከትግራይ ማጭድ አስይዞ ባመጣቸው ደጋፊዎቹ አሳጭዶና ጭኖ ከወሰደ ባኋላ፤ ተራፊ ያካባቢ ነዋሪዎችን፤ የሱ ባሪያዎች ከማድረጉ በላይ፤ ልጆቻቸውን ለያዘው ጦርነት እንዲያስረክቡት በማስገደድ ያሰለፋቸው ናቸው። እኒህ ጭዳ ናቸው። ደንበኛ መሳሪያ አልያዙም። ቀደም ብለው ከፊት የሚሰለፉ ናቸው። በምናምንቴዎቹ አይታመኑም።

እኒህ ያገኟቸው ሶስቱ፤ ከመጀመሪያው ክፍል ናቸው። ታማኝና ጥሩ ትጥቅ የያዙ ናቸው። ቆራጥና አረመኔዎች ናቸው። የኒህ መውደቅ ለምናምንቴዎቹ የልብ ቁስል ነው። እናም ገዳዮቻቸውን ማሰደድ ቀጠሉ። እነ ፈተና የአጅሬ መንገዳቸውን ትተው፤ ወደ አዴት አቀኑ። ምናምንቴዎች ከማይደፍሩት ቦታ ደረሱ። የጃኖራ ታጣቂዎች ተቀበሏቸው። ደስታቸው ጣራ መታ። አምስቱ ዘለው ከነሱ ጋር ለመሰለፍ ቀረቡ። እነ ፈተና፤ ትግላቸው መሳሪያ ለመቀማት ብቻ እንዳልሆነ ገለጡ። ዋናው ምናምንቴዎችን ከተከዜ ወዲያ ማሻገርና ከሆነም ማጥፋት እንደሆነ ገለጡ። በበየዳ በኩል እንደነሱው ራስ ደጀንን ትራስ አድርገው እያጠቁ ያሉ ቆራጥ የበየዳ ልጆች እንደሉ ሰሙ። ያየሽም፤ “እኛ ለመሞት ተዘጋጅተናል። አሁን አንድ ወይንም ሁለት ምናምንቴ ለመግደልና ለመፎከር አይደለም የወሰነው! ከኛ ጋር መሰለፍ፤ ዓለም በቃኝ እንዳለ መናኝ መሆን ነው!” አለ።

አምስቱን የሚቀበሏቸው፤ የሚታገሉት ለምን እንደሆነ በግልጥ ሲያውቁ መሆኑን ተናገሩ። እናም ካገሩ ሽማግሌዎች ሶስት፣ አምስቱ ራሳቸውን ያጩት ጃኖሬዎች፣ ፈተና፣ ያየሽና ሁለቱ ወንድሞቹ ዘወር ካለ ቦታ ተቀምጠው ምክር ያዙ። ወደ ሠራዊቱ ተመለሱና የያዛችሁትን ትጥቅ አስመዝግባችሁ፣ ጀግና ተብላችሁ ታወቁ የሚል ሃሳብ ሲሰነዘርላቸው፤ ፈተና፤ “እኛኮ ዕውቅና ፍለጋ አልወጣንም። ከምናምንቴዎች የነጠቅነውን መሳሪያ ደግሞ ማንም አያዝበትም! ባለቤቶቹ እኛው ነን። እኛው መርቀነዋል። ገና የበለጠ ነጥቀን እንታጠቃለን። ወደ ሠራዊቱ አንመለስም። ድል ሆኖ ላላበቃ ጉዳይ፤ ከመሓል ላይ መደንፋቱ፤ ዋጋ የለውም። በሕይወት ከተረፍን፤ ምናምንቴዎች ሲያልቁና አገራችን ስንመለስ፤ ያን ጊዜ ፉከራ ያምራል። ከዚያ በፊት ግን ድንፋታ ነው!” አለ።

እንዲህ መቁረጣቸውን ካዩ በኋላ፤ ሽማግሌዎቹ፤ “እንግዲህ እናንተ ናችሁ ታጥቃችሁ እየተዋጋችሁ ያላችሁ! እስቲ ዓላማችሁን አስረዱን!” አሉ።

ያየሽም፤ “እኔና ወንድሞቼ፤ አገራችን ኢትዮጵያ ናት ብለን ነው ያደግነው። የምንዋጋውም ለኢትዮጵያ ነው። እኒህ ምናምንቴዎች የኢትዮጵያ ጠላቶች ናቸው። እኛ እነሱን ከተከዜ ወዲያ ለማባረር አይደለም የምንፈልገው። ከተከዜ ወዲያ ያለውን አገራችን ለነሱ ማን ሠጣቸው! የትግራይ ሕዝብን እነሱ እንደፈለጉት ባሪያ አድርገው እንዲገዙት አንፈልግም። እናም እስካገራችን ጫፍ ድረስ ነው የምንዋጋው። ይሄ ትግል ደግሞ የመከላከያ አይደለም። ይሄ የራሳችን ነው። ግፉ በኛ ላይ ነው። በደሉ በኛ ላይ ነው። እናም የምንዋጋው እኛው ነን። ይሄው ሶስት የነፍስ ወከፍ መሳሪያ አለንና ውሰዱ። በነኚህ ነው አሁን የያዝነውን የማረክን። በዚህ ካመናችሁ ከኛ ጋር መሆን ትችላላችሁ። አንድ ምናምንቴ ገድሎ ለመፎከር እንዳልሆነ እወቁት!” አለና ጨረሰ።

በሽማግሌዎቹ ፊት ተማምለው ተቀላቀሏቸው። ሽማግሌዎችም እስከሞት መሆኑን አውቀው፤ በእንባ ተሰናበቷቸው። አሁን አምስት ሆነው፣ ስንቅም ይዘው፣ ወደፊት ገሰገሱ። ከመንግዳቸው አንዲት ሴት አገኙ። ከየት እንደመጣች ጠየቋት። አምልጣ እንደመጣችና አብረዋት የነበሩትን ሴቶች ሲደፍሩና ባሪያ አድርገው ሲያስቀሩዋቸው፤ እሷ አመመኝ ብላ ተኛች። በኋላ ግን እሷን አንጎትትም ብለው ሊገድላት ወሰኑ። ከተቀመጠችበት ጥለዋት መንገድ ጀመሩ። አንድ ብቻውን ቀርቶ፤ ሊገድላት ጠመንጃዉን ሲያቀባብል፤ አፈር ዓይኖቹ ላይ ጨምራ ሲደነባበር፤ ጠመንጃውን ቀምታ ወደ ገደሉ በረረች። ብዙ ከሄደች በኋላ፤ ከሩቁ ቁጥቋጦውን መሸሸጊያ አድርጋ ስትመለከት፤ እሷን ፍለጋ ሲተራመሱ ዓየች። ቀሚሷን ከጉልበቷ ላይ አስራ፤ ጠመንጃውን ደረቷ ላይ አቅፋ፤ ነፍሴ አውጭኝ ሩጫ ያዘች። ብዙም ሳትርቅ ደከማት። ተደብቆ ማምለጥ የሚባል ነገር ስላልተመቻት፤ ባላት ጉልበት ሁሉ ገፋች። የዱሩን ፍራፍሬ እየበላች ገሰገሰች።

“እናም ይሄው የናንተን ድምጽ ስሰማ በጥሻው ጠመንጃውን አኖርኩት። የኛ መሆናችሁን አውቄያለሁና አመጣዋለሁ!” ብላ በጥሻው የደበቀችውን ጠመንጃ አወጣችው። አዲስና ዘመናዊ ነው። ኮሩባት። ምግብና ወተት ሠጧት። “አይዞሽ ደርሰሻል! እንግዲህ ጥሩ መንገድ ነው የያዝሺው! ይሄንኑ ይዘሽ ሂጂ። መንደር ትገቢያለሽ!” እያሉ ሲያበረታቷት፤ “እናንተ ወዴት እየሄዳችሁ ነው?” ስትል ጠየቀች። “እኛማ ምናምንቴዎችን ፍለጋ ነው የምንሄደው! እኛ ቆርጠን እነሱን ለማጥፋት ነው ዓላማችን!” ሲሏት፤ “ታዲያ እኔስ ምን ጣጣ አለኝ ብላችሁ ነው! እንደናንተው ተሰልፌ፤ ዘመድ አዝማዴን የፈጀብኝን፣ ቤት ንብረቴን የቀማኝን፣ ከቦታዬ ያፈናቀለኝን፣ በያዝኩት ጠመንጃ እዋጋዋለሁ እንጂ፤ ከእንግዲህ ምን አገር አለኝ! ምን ቤት አለኝ! ምን ዘመድ አለኝ! ብላችሁ ነው። አብሬያችሁ ነው የምዘምት!” ብላ ሽንቀጥ አለች። የማመነታታት ነገር አላሳየችም። እሺ ብለው ተቀበሏት።

የቦዛን ሥር ይዘው ተጠጉ። ደክሟቸው ስለነበር አረፉ። ወግ ጀመሩ። “አንቺ ጀግና! ስምሽ ማን ነው?” አላት ፈተና። “የኔን ነው!” አለችው። “አዎ! ያንቺን እንጂ!” አላት። “ስሜማ በለጠች ነው። በለጠች አዳነ።” ብላ መለሰችለት። “እኒህ እርኩሶች ሲመጡ የት ነበርሽ!” አላት። “ዛሪማ ነበርኩ። ያባት የናቴ ቤት ነበረኝ። እነሱ ሲሞቱ ያወረሱኝ። ትንሽ ሱቅ ቀልሼ እነግድ ነበር። ምን ያደርጋል፤ እንኳን ንግዱ ነፍስ ማትረፉም የግዜር እጅ ታክሎበት ነው!” አለች። ሁሉም አንገታቸውን ደፉ። ፀሐዩዋ ገባች። እነሱም ባሉበት፤ በየተራ ጠባቂ እየሆኑ ተኙ። ጎኅ ሲቀድ በደጋው የቀለጠ ተኩስ አየለ። ምናምንቴዎቹ ክፉኛ ተጎድተው፤ ወደ ኋላ እያፈገፈጉ መሆኑ ገባቸው። ደባርቅን እንይዛለን ብለው፣ ያለ የሌላችውን ኃይል አሟጠው አሰልፈው፣ በወደቀው ላይ አዲሱ እየተረማመደ፣ እስከሚችሉት ተዋግተው ተቸነፉ። እናም ደጋውን ለቀው ወደ ቆላው ወረዱ። ይሄ ለነሱ አልተመቻቸውምና አሳለፉት። አሁን ድብባሕርንም ለቀው ወደ ዛሬማ ሸሹ። መከላከያው፣ የአማራው ኃይልና ፋኖ ተከትሎ መጣ። እነፈተና ዱሩን ታከው ወደ ዋልድባ መቃብሩ ሮጡ። ተዋጊውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ቀድመው፤ ምናምንቴዎችን ማድባትና መግደል ነው የፈለጉት። ሠራዊቱ ዛሪማን ይዞ ቆመ። ፈተና አሁን በሚያውቀው ቦታ ላይ ነው። ወደ አዳርቃይ አቀኑ። ሠርዊቱና ምናምንቴዎቹ ተፋጠዋል።

ፈተና፤ በለጠች አዳነን መልዕክት አስይዞ ወደ አንድ መንደር ላካት። “ሂጅና አኒት አሮጊት ታገኛለሽ። እሷን፤

‘አህያዬ ደክማ፣ ሽክሟን ልታራግፍ

በርከክ በርከክ አለች፤ ከጎጆዬ ደጃፍ! በያት!” አላት።

(አራተኛው ክፍል ይቀጥላል)