እና ዐማራ!

እና ዐማራ!
አንዱዓለም ተፈራ
አርብ፣ ነሐሴ ፬ ቀን፣ ፳፻፲ ዓመተ ምህረት

ለውጡ እስካሁን በጀመረው መንገድ ይሄዳል የሚል ተስፋ ሁላችን ሰንቀናል። ባሁኑ ጊዜ፤ መሠረታዊ የሆኑት የኢሕአዴግ የአስተዳደር መተክሎቹ እንዳሉ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ፤ የዘር ፖለቲካው ባጭር ጊዜ ውስጥ እንደማይለውጥ አስምረውበታል። ከውጪና ከውስጥ የዘር ፖለቲከኞች የሰላ የመቀራመቻ ስንጢያቸውን አሰልስለው “የኔ!” “የኔ!” ታቸውን ተያይዘውታል። በዚህ ሂደት አንድነት የሌለው የዐማራው የድርጅቶች ጋጋታ፤ ቁጥሩ የሚጨምርበት እንጂ፤ ወደ አንድ የሚሰባሰብበት ሁኔታ አይታይም። እና ዐማራ!

የሾህ አጥር በመካከላችን ማበጀቱን ትተን፤ ይሄን ጉዳይ የሁላችን አድርገን መነጋገር እንችላለን። የዐማራው ጉዳይ የእከሌ ወይንም የእከሊት አይደለም። የሁላችንም ነው። የአንድ ድርጅት ወይንም የሌላም አይደለም። የዐማራዎች በሙሉ ነው። ይሄን ጉዳይ ደግሞ ካልተነጋገርንበት፤ ሌላ ከዚህ የከበደ ምን አለ? ሀቁን መመልከትና እውነቱን መነጋገር አለብን። በዐማራው ላይ የተደረገው ጭፍጨፋ፤ በዐማራነት እንጂ፤ ግለሰቦች በሠሩት ተግባር የተመሠረተ አይደለም። ይህ ሆን ተብሎ ታምኖበትና በመምሪያ በተግባር የዋለ በመንግሥት ደረጃ የተከናወነ ጥፋት ነው። እናም ዐማራ የሆን ሁላችን፤ ልንቆረቆርበት ይገባናል። ባሁኑ ሰዓት የዐማራውን የፖለቲካ ምህዳር አጣበው የያዙት፤ የብሔረ ዐማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብዐዴን) እና የዐማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዐብን) ናቸው። የዐማራ ጉዳይ ደግሞ፤ የብዐዴን ወይንም የዐብን ብቻ፤ የግል ጉዳይ አይደለም። የብዐዴን አመራር፤ ከመካከለኛው መንግሥት ጋር ሆኖ፤ ሀገር የመምራትና ሀገር አቀፍ ፓርቲ የመመሥረት ዓላማ ያለው ይመስላል። ዐብን ደግሞ፤ እኔ ነኝ የዐማራ ብሔርተኝነት ማዕከል ብሎ፤ በብቸኝነት ቢሮዎቹን በየቦታው በመክፈት ላይ ነው። የነኝህ የየራሳቸው ሩጫ፤ ዐማራውን ይጎዳዋል። እኒህ ሁለቱ፤ አንዳቸው አንዱን አጽናፍ፤ ሌላቸው ሌላኛውን አጽናፍ ይዘው የሚጓተቱበት መሆን የለበትም። ሁለቱም በየበኩላቸው የየራሳቸው ጥናካሬና ድክመት አላቸው። በኔ በኩል፤ እኒህ ሁለቱ ቢጣመሩ ጥንካሬያቸው አይሎ፤ ሁሉን ዐማራ ሊወክሉ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል እምነት አለኝ።

የዐማራ ሕዝብ አንድ ነው። ለዐማራው የሚቆም ደግሞ ባንድ መሰለፍ አለበት። ይህ ለዐማራው መቆም፣ የርዕዩተ ዓለም ባለቤትነትን አይጠይቅም፣ አያካትትም፣ አያስፈልገውም። ይህ ለአንድ ወገን የመቆርቆር ጉዳይ ነው። ተቆርቋሪዎች ደግሞ፤ በሙሉ በአንድነት ተሰባስበው መመካከር አለባቸው እንጂ፤ ወዲያና ወዲህ ሆነው መጓተት የለባቸውም። ከዚህ በመነሳት፤ ለዐማራው እንቆማለን ያሉት በሙሉ፤ የየድርጅታቸውን ጥንካሬም ይሁን ድክመት ሳይመዝኑ፤ ለዐማራው መቆም አለባቸው። እናም አንድ የዐማራ ጠንካራ ድርጅት ነው የሚያስፈልገው። ብዐዴንና ዐብን ወደ አንድ መምጣት አለባቸው ስል፤ ከዚህ እምነት በመነሳት ነው። ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮነንና ለዐማራው ፕሬዘዳንት ገዱ አንዳርጋቸው፤ ከኦሕዴድ በፊት፤ አብን ይቀርባቸዋል። ከኦሕዴድ ጋር ከመደራደራቸው በፊት፤ በዐማራው በኩል ያለውን በአንድነት ቢመሩት፤ ለራሳቸውም ጥንካሬ፤ ለዐማራውም ትክክለኛ ውክልና ይኖራል።

የሁለቱን ድርጅቶች ድክመት እዚህ ላይ ማተቱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያይል አልሄድበትም። ጥንካሬያችውን ስንመለከት ደግሞ፤ በብዐዴን በኩል፤ መንግሥታዊ መዋቅር፣ ንብረትና ግዝፈት አለው። በዐብን በኩል ደግሞ ወጣቱ፣ የጠነከረ የዐማራነት ብሔርተኝነትና ትኩስነት አላቸው። እኒህ የሁለቱ ወገኖች ጥንካሬዎች ባንድ ላይ ሲጣመሩ፤ ከፍተኛ የሆነ የደቦ ጉልበት ይፈጥራሉ። በሕዝቡ ዘንድ ደግሞ ቀስቃሽ ስሜትን ፈጥሮ፤ ብዙዎችን ያነሳሳል። እስኪ በያላችሁበት ይሄን ምከሩበት።

Advertisements
Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ

ድልድይ የሌለው ተቆርቋሪነት

ድልድይ የሌለው ተቆርቋሪነት
አንዱዓለም ተፈራ
ማክሰኞ፤ ነሐሴ ፩ ቀን ፳ ፲ ዓመተ ምህረት

ድልድይ ሁለት ጎን ለጎን የሆኑ ቦታዎችን ያገናኛል። ድልድይ በሌላቸው ቦታዎች የሚገኙ ሰዎች፤ መገናኘት ያስቸግራቸዋል። ባንጻሩም፤ ከትናንት ወደ ዛሬ የሚያሸጋግር ድልድይ ከሌለ፤ ዛሬ ትናንት የተሠራውን እንደገና እንዳዲስ በመሥራት ይጠመድና፤ ዛሬ ሁልጊዜም ትናንትን እንደሆነ ይቀጥላል። ይህ ነው በኢትዮጵያ፤ ለሕዝብ ተቆርቋሪዎች የእንቅስቃሴ ሂደት፤ በተደጋጋሚ እያየን ያለነው። ከትናንት መማር እያቃተን፤ ዛሬም የትናንቱን መልሰን ስንዳክርበት እንገኛለን። ለምን? መማር ስለማንችል አይደለም። የትናንቱ ስላልተመዘገበም አይደለም። የማስተላለፉ ሥርዓት በትክክል ስላልተከናወነ ነው። የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ይህ ነው።

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፤ “በአቸነፈ እና በአሸነፈ የተላለቃችሁ!” ብለው ያስቀመጡትና አዳራሹን የሞላው ያጨበጨበበት፤ ብዙ ሕይወት ያለፈበትን የሁለት የተለያዩ የፖለቲካ አሰላለፎችን ትግል አቅልለው በማስቀመጣቸው ቢሆንም፤ ይህ የግል ስህተታቸው ሳይሆን፤ በብዙኀኑ ተቀባይነት ያለው መሆኑ ነው። አጨብጫቢዎቹ ስለ ነበረው ትግል ያላቸው ዕውቀት አነስተኛ ነው። በስድሳዎቹ የነበርነው ተማሪዎች፤ ስለ ሀገራችን ታሪክ፣ ስለ አርበኞቻችን ተጋድሎ፣ ስለ መንግሥት ሂደት፣ ስለ ታሪክና ማንነት የነበረንን ዕውቀት በግሌ ስመለከተው፤ ጎደሎ ነበር። እንዲሆን የምንፈልገውን፤ ከሀገራችን ታሪክና ተጨባጭ እውነታ ጋር አላጋባነውም ነበር። እዚህ ላይ፤ እኔ ሁሉን ወክዬ ሳይሆን፤ በግሌ ሁን የማምንበትን ነው የማስቀምጠው። እናም በተማርነው መሠረት፤ ለሁሉም ነገር ፊታችንን ያዞርነው ወደ ውጪ ነበር። ከትናንታችን የወረስነው አጥተን ሳይሆን፤ በቀጣይነት ያስረከበን ድልድይ አልነበረውም። ይህ ትልቅ ስህተት መሆኑን አምናለሁ።

ደርግ፤ ከትናንት የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቆርቋሪዎች ለዛሬዎቹ ምንም ዓይነት መወራረስ እንዳይኖር፤ ትውልዱን ጨረሰው። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አነጋገር፤ በዚያ ወቅት ደርግ ባደረገው የትውልድ መጨረስ፤ በተተካ የፈጠራ ትረካ ውጤት ነው። መተላለቁ፤ በአንድ ቃል ሁለት አጠራር ላይ የተመሠረተ አልነበረም። መግለጫውን እንደ ዋናው ቁም ነገር መውሰድ፤ ስህተት ነው። ከዚያ በኋላ የተከተለው የፖለቲካ ታጋይም ሆነ የተማሪ ተንቀሳቃሽ፤ ሀ ብሎ እንደገና መፍጠር ነበረበት። ልምዱም ሆነ ግኘቶቹ ለቀጣዩ ትውልድ አልተላለፉለትም። ጉድለቶቹም ሆነ ጥንካሬዎቹ በትክክል አልተነገሩትም። በዚያው በደርግ ጊዜ የተደረጉት ግድያዎችና የቀይ ሽብር ዕልቂቶች በትክክል ተመዝግበው አልተላለፉም። የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ዙፋኑን ዘርፎ፤ ራሱ ያደረጋቸው ጭፍጨፋዎችና ግድያዎች፤ አሁንም ሳንማርባቸው ተድበስብሰው ወደፊት መቀጠሉ፤ እየተንደረደርንበት ስለሆነ፤ ትምህርት ሳናገኝ፤ ነገ እንዳይደገም ሰግቻለሁ።

አዲሱ ወጣት፤ አዲስ ትግል ብሎ፤ እንደገና ከ ሀ እየጀመረ መቀጠሉ፤ ወደፊት የሚባል ሳይሆን፤ ባለህበት እርገጥ የሚል ጉዞ ላይ ያስቀምጠናል። ከትናንቶቹ በጎ የሆኑና ግድለቶች አሉ። ያን መርምረን፤ ከዚያ መማር ካልቻልን፤ የዚያ ጊዜ ድከመቶችን ተሸክሞ መጓዝና መድገሙ አይቀሬ ነው። ለምን? የስድሳዎቹ ተማሪዎች እንቅስቃሴ መሪዎች ምን ጥሩ ነገር ሠሩ? ምንስ ድክመት ነበራቸው? ከነሱ በፊት የነበሩት ምሁራንስ? ደርግስ? የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባርስ? ነገ የሚከተለውስ? ያን ማሰብና መመርመር ካልቻልን፤ በድክመቶቻቸው ተዘፍቀን፤ ያንኑ እያሸተትን፣ ከዚያው የማንወጣ እንሆናለን።

Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ

የለውጡን መሠረታዊ ምክንያትና ዓላማ መሳት የለብንም።

የለውጡን መሠረታዊ ምክንያትና ዓላማ መሳት የለብንም።

አንዱዓለም ተፈራ
አርብ፣ ሐምሌ ፳ ፯ ቀን ፳ ፻ ፲ ዓመተ ምህረት ( 8/3/2018 )

አለባብሰው ቢያርሱ፤ ባረም ይመለሱ!

አሁን በሀገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ለውጥ፤ በተለይ በዐማራ፣ በኦሮሞ፣ በኢትዮጵያዊ ሶማሊ ወጣቶች፤ ባጠቃላይም በኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘ ነው። ይህ ለውጥ፤ ኢሕአዴግ መራሽ አይደለም። ይልቁንም ለውጡ በኢሕአዴግ ላይ የተነሳ ነው። የለውጡ ዒላማ፤ ኢሕአዴግና የኢሕአዴግ የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ ናቸው። ኢሕአዴግ፤ የመለስ ዜናዊ፣ የበረከት ስምዖን፣ የሺፈራው ሽጉጤ፣ የአብዲ ኤሊና አሁንም በየቦታው ተሿሹመውና በወታደሩም ውስጥ በጄኔራልነታቸው ብዙውን የሀገራችንን ሀብት እየተቆጣጠሩ ያሉት፤ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎች ድርጅት ነው። ወጣ ካለም ለነሱ ሲያገለግሉ የነበሩ አድር ባዮች የተሸከሙት ድርጅት ነው። ይህ ነው ሕዝብን ያፋጀ፤ በሙስናና በአድልዖ የተሞላ፣ የአንድ ወገኑ የኢሕአዴግ ሥርዓት። ይህን ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቃኝ ያለው። የለውጡ መሠረታዊ ምክንያትና ዓላማ ይህ ነው።

አሁን ፈጠው ያሉት ጥያቄዎች ግልጥ ናቸው። አንደኛ ለውጡን ያልፈለገው አምባገነኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ መቀሌ መሽጎ፤ አሁንም ዘረኛና ለትግራይ ሕዝብ አደገኛ የሆነ ዝግጅት ይዟል። በሌላ በኩል፤ አዲስ አበባ ኢሕአዴግ ለውጥ እያካሄደ ነው። ማለትም ኢሕአዴግ በኢሕአዴግ ላይ ለውጥ እያካሄደ ነው። ዋናው ጠላት መቀሌ ላይ መሽጎ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚችለውን ያህል ሁሉ እየሸረበ ያለው የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ነው። በዚህ ላይ ምንም ዓይነት ብዥታ ሊኖር አይገባም። ይሄን ክፍል ጠላቴ ብሎ የፈረጀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። እናም ለውጡን መምራትም መግፋትም የሚችለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ለውጡን ያመጡትና ከፍተኛውን መስዋዕትነት የከፈሉት ተመካች እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። ማን ባመጣው ለውጥ ነው፤ ማን ተመልካች የሚሆነው? ማን እንዲወገድ ነበር፤ ብዙዎቹ ሕይወታቸውን የገበሩት? ይህ ማለት፤ በትግሉ የተሳተፉትና ግንባር ቀደም ሆነው የተደራጁ ወገኖች፤ ለውጡን ከሚፈልገው የኢሕአዴግ ክፍል ጋር በመሆን፤ ትክክለኛ ለውጥ እንዲመጣ፤ አብረው የሽግግር ወቅቱን መምራት አለባቸው።

መመንጠር ያለበት፤ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው የሕዝብ ጠላት ነው። ይህ ደግሞ በትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፤ በሌሎቹን ይህ ቡድን በመሠረታቸው የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥም ነው። አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ እንዳይሆን! ለኔ እስካሁን ጥሩ ተሠርቷል። በዚህ ግን ብዙ መሄድ አይቻልም። ለውጥ አምጪው ክፍል የተሳተፈበት ብቻ ነው፤ ትክክለኛና ዘለቄታነት ያለው ለውጥ የሚያመጣው። ሀገራችን ደግሞ፤ ላለፉት አርባ አምስት ዓመታት ብዙ ደምታለች። ደሙ ያብቃ። የተወሰኑ ሰዎች ሀገር ቤት ለመግባት በመጓጓት የሀገራችንን የፖለቲካ ማህደር ቢኳኩሉት፤ መልኩ እንጂ ውስጣዊ ይዘቱ አይቀየርም። አሁን መሠረታዊ ለውጥ ሥር እንዲሰድ አመቺ ሁኔታዎች አሉ። ለዚህ የለማ ቡድን ምስጋና ይገባዋል። ነገር ግን የለማ ቡድን እየመራው የሚካሄድ ከሆነ፤ ዘለቄታ የለውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመራውና የሚሳተፍበት መሆን አለበት። ይህ ለውጥ ከዚህ ቡድንና ከኢሕአዴግ በላይ ነው። እናም የሽግግር መንግሥት መቋቋሙ የግድ አስፈላጊ ነው።

Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ

በግለሰብ መተማመን ወይንስ በአሰራር?

በግለሰብ መተማመን ወይንስ በአሰራር?

አንዱዓለም ተፈራ

ረቡዕ፣ ሐምሌ ፳ ፭ ቀን ፳ ፻ ፲ ዓመተ ምህረት ( 8/1/2018 )

ሁላችንም ደስ በሚል ሁኔታ ላይ ነን። በዚህ ሰዓት፤ “ጠንቀቅ እንበል”! ማለቱ የሚያስበረግጋቸው ይኖራሉ። ነገር ግን፤ ዘለቄታ መፍትሔ የሚገኘው፤ ለመፍትሔው አምድና መሠረት የሆነ አሰራር፤ በቦታው ሲኖር ስለሆነ፤ የግድ ጠንቀቅ እንበል። ሰዎች ይመጣሉ፤ ሰዎች ይሄዳሉ። ዛሬ የወደድነውን ግለሰብ፤ የወደድንበት ምክንያት የሚለወጥበት ሁኔታ ሲገኝ፤ ነገ መልሰን ከወዳጅ መዝገባችን እናወጣዋለን። ይህ የኅብረተሰብ ሀቅ ነው። እንግዲህ እዚህ ላይ፤ “በግለሰብ መተማመኑ ነው ወይንስ በአሰራር የተቀመጠ መፍትሔ፤ ዘላቂነት ያለው?” ለሚለው ጥያቄ፤ ምን መልስ እንሠጣለን? ይህ ነው የዚህ ጽሑፍ ማሽከርከሪያ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የያዙት አቅጣጫ በጣም ደስ ይላል። በአሜሪካ ያደረጉት ጉዞም የተሳካ ነበር። ይህ ስኬት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የግል ስኬት፣ ወይንም የለማ ቡድን የግል ስኬት ሳይሆን፤ የመላ ኢትዮጵያዊያን ስኬት ነው። ሁላችን የምንፈልገው፤ ይህ ስኬት፤ ዛሬ ሆነ ነገ፣ በሀገር ውስጥ ሆነ ከሀገር ውጪ፤ ዘለቄታነት እንዲያገኝ ነው። ዘለቄታ የሚኖረው ደግሞ፤ ጉዳዩን ለአንድ ግለሰብ ወይንም ቡድን ፈቃደኝነት በመተው ሳይሆን፤ መደረግ ያለበትን ሁላችን ባንድነት ስናዜመው ነው።  ይህ ዜማችን አሰራርን ይወልዳል። አሰራር ደግሞ ለዘለቄታነት መንገድ ይጠርጋል።

ሀገራችን አሁን ላለችበት ሁኔታ፤ ቀጥተኛ ተጠያቂው ኢሕአደግ እና ኢሕአደግ በቦታው ያስቀመጠው የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያው ነው። ኢሕደግ ቆስሏል። ኢሕደግ ግን አልፈረሰም። ሕይወቱ ብቻ ሳይሆን፤ ፍልስፍናው፣ አስተዳደሩ፣ በሂደቱ ያስቀመጠው ሙስንና የዘር አድልዖ አሰራር፤ በቦታው እንዳለ ነው። የሀገሪቱ ደንበርና ያላግባብ ከሕዝብ የተነጠቀው ለም መሬት፣ በሕዝቡ መካከል የተፈጠረው አለመተማመንና መበላላት፣ የተገደሉ ወገኖቻችን፣ የተፈናቀሉና የተሰደዱ ወገንቾ፣ ተሟጦ የተወሰደው የሕዝብ ንብረት፣ ወዘተ. ብዙ ኢሕአዴግ የሚጠየቅባቸው ጉዳዮች አሉ። በኢሕአደግ ላይ ሕዝቡ ያለው እምነት ራሱ ለጥያቄ የሚቀርብ ነው። ይህ ካልተመለሰ ደግሞ፤ መልካም አስተዳደርና መልካም ተስተዳዳሪ ማሰቡ ያዳግታል። ከሁላችሁም ጋር እስማማለሁ! አሁን ለዚህ ሁሉ መልስ የምንሠጥበት ጊዜ አይደለም። ይህ ጊዜ ይፈጃል። መልካም! ነገር ግን አሁን ካላንበት ወደፊት ለመሄድ፤ መንገዳችን በየት በኩል ነው? ይህ መመለስ አለበት። አቅጣጫና ጉዞው መጀመር ያለበት፤ አስራሩ ዛሬ በትክክል በቦታው ሲቀመጥ ነው።

እዚህ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ቅንነትና በጎ እምነት አይደለም እየተጠየቀ ያለው! በዋሺንግተን ከተደረገው ስብሰባ፤ ጎደለ የምለው ቢኖር፤ በምሁራን እና በጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አሕመድ መካከል የተደረገ ውይይት፤ የሀገራችንን የወደፊት አቅጣጫ የሚያመለክት አለመሆኑ ነው። በርግጥ በዝርዝር ይሄ ይሆናል፤ እንዲህ ይደረጋል የሚል ባልጠብቅም፤ ምን ዓይነት መንግሥት ይቀጥላል? ከምርጫው በፊት፤ የተወዳዳሪዎች ምዝገባና አዘጋጆቹ፣ ይህ የሚካሄድበትን የሚመራው ክፍልና መቼ የሚሉት ጥያቄዎች አለመነሳታቸው ገርሞኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሩህ ተስፋ አላቸው። መልካም! ታዲያ አግዙኝ ሊሉ እኮ በተገባ ነበር። ምሁራኑ ደግሞ፤ ምን ዓይነት መንግሥት ይዘው ሊገፉ ነው? ብሎ መጠይቅ ነበረበት። ያ አልሆነም። በጄ! እንለፈው። ተስፋ የማደርገው፤ ቢያንስ በጽሑፍ ደረጃ፤ ምሁራኑ ለሳቸው፤ መልካም ትንታኔና መንግሥታዊ ሂደቱን በተመለከተ መደረግ ያለባቸውን የሚጠቁም፤ በተለይ ደግሞ በየሙያ መስካቸው፤ ምን ምን መደረግ እንዳለባቸውና ሀገራችንን የሚያሳድጋትን ሰነድና አቅጣጫ ሠጪ ሰነድ አቅርበውላቸዋል የሚል ነው። አሁን ደግሞ፤ ዛሬ ምን ዓይነት መንግሥት ይዘው ሊቀጥሉ ነው? ይህ የኔ ጥያቄ ነው።

በርግጥ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፤ አሁን የሚፈልጉትን እየመረጡ፤ ሀገራችንን እየመሩ ናቸው። እሳቸው፣ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ እና ሌሎች ቅን የሕዝብ አገልጋዮች በሙሉ ከባድ ፈተና ላይ ናቸው። ኢንጅነር ስመኘው በቀለ በሕይወታቸው ከፈሉ። ጠቅላይ ሚንስትር አብይም ተቃጥቶባቸው ነበር። እኒህ ሁሉ ከለውጡ ጋር በተያያዘ ምክንያት ለመሆናቸው ምስክር ጠያቂ አይኖርም። እናውቀዋለን። ታዲያ ይሄኮ የሁላችን ኃላፊነት ነው። የሳቸው የግል ዕዳ አይደለም። እናም ጊዜው፤ ሰፋ ያለና ሕዝቡን ያካተተ የሽግግር መንግሥት የግድ ይላል። ከላይ እስከታች ሕዝቡ የኔ ብሎ የሚጠብቀው መንግሥት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ የሚሆነው፤ ሰፋ ካለው ኅብረተሰብ፤ በተለይም ከተደራጀው ክፍል ውክልናን ሲያገኝ ነው። የሽግግር መንግሥት ማለት፤ አሁን ካለንበት ወደምንፈልገው ለመድረስ መጓጓዣችን ነው። የሚቀጥለውን ምርጫም አካሂያጁ ይሄው ክፍል መሆን አለበት። ኢሕአዴግ መራጭና አስመራጭ የሚሆንበት ሂደት አጓጉል ነው። ይሄ አቸናፊነቴን ከወዲሁ ተቀበሉ ማለት ነው። በርግጥ ኢሕአዴግ የማቸነፍ ዕድሉ ከማንም በላይ ነው። ነገር ግን እኔው ላዘጋጀው፤ ወይንም እኔ አውቅላችኋላሁና እመድባለሁ ማለቱ አያስኬድም።

ብዙዎች ለዚህ ችግር አይኖርባቸውም። በተለይም እስካሁን ከነበረው ጋር በማነጻጸር፤ ይሄ የተሻለ በመሆኑ፤ በዚህ ብቻ በመርካት፤ የለም አታደፍርስብን! ባዮች አሉ። መልካም! ነገና ከተነገ ወዲያ በተወሰኑ ሰዎች ቅንነት ሀገርን ትመራ ማለት፤ ኃላፊንት የጎደለው ሂደት ነው። ከፋም በጄም አብረን ያደረግነው ጉዳይ፤ ሁላችንን ተጠያቂ ስለሚያደርገን፤ ባለቤትነቱ ሁላችንንም የግድ የተስተካከለ ሥራ እንድንሠራ ያስገድደናል። ሌሎች እንዲሠሩት መተው ግን፤ በኋላ “እነሱ!” እያሉ ጣት ለመጠቆም መዘጋጀት ነው።

እናም የሽግግር መንግሥት መቋቋሙ የግድ አስፈላጊ ነው።

Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አውቶቡስና የቅርብ ታሪካችን ትምህርት

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አውቶቡስና የቅርብ ታሪካችን ትምህርት

አንዱዓለም ተፈራ

አርብ፣ ሐምሌ ፳ ቀን ፳ ፻ ፩ ዓመተ ምህረት ( 7/27/2018 )

ትናንት አርብ፣ ሐምሌ ፳ ቀን ፳ ፻ ፩ ዓመተ ምህረት ( 7/27/2018 ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከተቃዋሚ/ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ያደረጉትን ልውውጥ ከድረገጽ ካገኘሁት ቪዲዮ ላይ ተመለከትኩ። ዛሬም በዋሺንግተን ዲ. ሲ. ስብሰባ ያደርጋሉ። ከትናንቱ የተለየ እንደማይናገሩ እገምታለሁ። በአርቡ ስብሰባ፤ ከትንንሽ ድርጅቶች እስከ ትልልቅ ድርጅቶች፣ በዛ ካሉ የብሔር ድርጅቶች እስከ ሀገር አቀፍ ድርጅቶች፣ ከነባር ታጋይ ደርጅት መሪዎች እስከ ነባሮችን ጠይ ድርጅት መሪዋች ድረስ፤ አድናቆት ተቸራቸው። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አውቶቡስ፤ ተሳፋሪዎችን ግራና ቀኝ ሲጠራና ሲያሳፍር ተመለከትኩ። አውቶቡሱ ደምቋል። የአረንጓዴ ብጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ውስጡን ሞልቶታል።  ኢትዮጵያዊ ቃና ያለው ቅኝት አጥኖታል። ባሁኑ ስዓት ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታላቅ አክብሮትና ምስጋና በስተቀር፤ አንዲትም ነጥብ በተቃራኒ ማንሳቱ፤ የትየለሌ ጠላትነት ነው። ይህ አንድም ሰማይ! አለያ መሬት! የሚል ሂደት፤ ትክክል እንዳልሆነ እሳቸው ገልጸውታል። እናም እንኳን መንግሥትና ሕዝቡ የምንሰማማበት ወቅት ላይ ደረስን። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ፤ ብዙዎችን የሚያስደስቱ መልሶች ሠጡ። እኔም ባመዛኙ በመልሶቹ ረካሁ። ከመካከል ግን የቅርብ ታሪካችንን ዞሬ እንድመረምር ያደረጉኝ መልሶችን አገኘሁባቸው። ምንድን ናቸው?

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፤ በጣም ልብ የሚነካ ቅንነትና ሕዝባዊ ፍቅር አላቸው። የፖለቲካ ግንዛቤያቸውም ካሁን በፊት በመሪዎቻችን ያልታየ ነው። በግለሰብ ደረጃ መደነቅ ያለባቸው ናቸው። ሁላችን መርሳት የሌለብን ደግሞ፤ እሳቸው አንድ ግለሰብ ናቸው። የፖለቲካ ተመክሯቸው ደግሞ፤ አሁን ሊያፈርሱት እርዱኝ! እያሉ ካለው የኢሕአዴግ ሥርዓት የተሸመተ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ፤ የሀገራችን ችግር በጣም ጥልቅና ውስብስብ ስለሆነ፤ ጊዜ ወሳጅ ነው። እሳቸውም ይሄንኑ አስምረውበታል። በፖለቲካ ሂደት ደግሞ፤ ቋሚ የሆነ ባህርይ የለም። አሰላለፍ በየጊዜው ይቀያየራል። ፊት ለፊት ላጋጠመው የኅብረተሰብ ሁኔታ፤ መፍትሔ የሚሉትን ማቀንቀን የፖለቲካ ሂደት ማሽከርከሪያ ምሰሶው ነው። ዛሬ ጥሩ ያልነው ነገር፤ በቅጽበት ዋጋ ሊያጣ ይችላል። ምን ጊዜም ቋሚ ሆነው የሚቀጥሉት፤ ሕዝቡና ሀገሪቱ ናቸው። አምባገነን መሪዎች በመልክም ሆነ በቅርጽ ከኔና ከርስዎ የተለዩ አይደሉም። ቀንድ የላቸውም። የተለዩ ያገጠጡ ጥርሶችም የሏቸው። ሲጀምሩም፤ “አምባገነን ነኝ!” እያሉ በማወጅ አይደለም። ይሄንን ለማስረገጥ፤ ሩቅ ሳንሄድ፤ የራሳችንን የቅርብ ታሪክ ዞሮ መመልከቱ ይረዳል።

በ ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓመተ ምህረት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር አደባባይ ወጥቶ፤ የነበረውን መንግሥት “ወጊድልኝ!” ሲል፤ ተደራጅቶና ታጥቆ የነበረው ወታደራዊው ቡድን፤ “ኢትዮጵያ ትቅደም!” “እናንተ በያላችሁበት አርፋችሁ ተቀመጡ! እኔ ሁሉን አደርገዋለሁ!” በማለት መድረኩን ለብቻው ተቆጣጠረ። አስታውሳለሁ፤ አንድ ወዳጄ፤ “እስኪ ተዋቸው! ጥሩ ይዘዋል! አሁእኛ፤ በየሙያ መስካችን ጠንክረን መሥራት ብቻ ነው ያለብን! እነሱ አንድ በአንድ እያሉ፤ ልክ ያስገቡታል!” ብሎ ተከራከረኝ። እውነትም ሁሉንም ልክ አስገቡት! መሬት!!! ደርጋማው ወታደራዊ መንግሥት፤ ላንድ ሰሞን ጋዜጣዎችን ነፃ አደረገ፡ ውይይት ፈቀድኩ አለና ሰውን አንጫጫ። ከዚያ ለቃቅሞ መሬት አገባቸው። ሰው በላውን መንግሥቱ ኃይለማርያም ለዘለዓለም አንግሦ፤ እኔው ነኝ ሽግግር መንግሥት አለና፤ በበነጋታው እኔው ነኝ መንግሥት ብሎን ቁጭ አለ።

በተመሳሳይ መልኩ፤ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር አዲስ አበባ ሲገባ፤ ብሔሮች ነፃ ወጡ አለን። ከሰው በላው መንግሥቱ ኃይለማርያም አዳንኳችሁ አለን። በደርግ ጊዜ የጠፉት ነፍጠኞች፣ ትምክህተኞችና ፊውዳሎች ነፍስ ዘርተው መጥተው፣ ዓይን አፍጥጠው ተገትረው፣ ክንፋቸውን ዘርግተው ሕዝቡን ካሰሩበት ማነቆ፤ ነፃ አውጣኋችሁ ተባልን። ዴሞክራሲ ነገሰ ተባልን። ኢትዮጵያ ያልነበራት ሕገ መንግሥት አገኘች ተባልን። አዲስ ታሪክ ተጻፈልን። ከዐማራና ለተዋሕዶ በኢተክርስትያን ተላቀቃችሁ ተባልን። ወደፊት ልናይ ነው ተብለን፤ ፊታችንን ወደፊት ስናዞር፤ አንኳንስ ዴሞክራሲ ሰፍኖ አዳዲስ ፓርቲዎች ሊፋፉ፤ አብረው ተማክረው የገቡት የትግራይ፣ የኦሮሞና የኤርትራ ነፃ አውጪዎቹም ተለያይተው ተጨራረሱ። የራሳቸው የሚባል ትውልድ ሰለሌላቸው፤ ያው የፈረደብንን ኢትዮጵያዊያንን በነሱው ጦርነት ማገዱን። ብዙዎች አለቁ። ከዚያማ ሀገራችን እንኳንስ ለውጪዎቹ፤ በውስጥ ላሉት ኢትዮጵያዊያን አዲስ እስከትሆን ድረስ ሁለንተናዋ የተለዋወጠ ኢትዮጵያ ተከሰተች። ባህል፤ ወግ፣ ስነ ሥርዓት፣ ታሪክ፣ በሕዝብ መካከል የነበረው መተሳሰብ ቦታ ተነፈገ።

አሁን፤ በሕዝቡ፤ በተለይም በወጣቱ፤ ከፍተኛ መስዋዕትነት፤ ለዚህ በቅተናል። ታዲያ ከዚህ ወደፊት ለመሄድ ሲታሰብ፤ የት ነበርን? እንዴት ለዚህ በቃን? ወደፊት ለመሄድ አሁን በቦታው ምን አለን? የሚለውን መመልከቱ የግድ ነው። ዝርዝር መግባቱ ቀባሪውን ማርዳት ነው። በቀጥታ ወደ ተነሳሁበት እመለሳለሁ። የመጀመሪያው ለሽግግር መንግሥት ጥያቄ የሠጡትን መልስ በሚመለከት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ለዐማራው የሕልውና ጉዳይ የሠጡት ትኩረት ወይንም የትኩረት ማነስ ነው። በየተራ ልሂድባቸው።

የሽግግር ጥያቄ ለምን ተነሳ? ምን ማለትስ ነው?

የሽግግር መንግሥት፤ ከነበረው ወደምንፈልገው ለመሄድ መሸጋገሪያ ድልድዩ ነው። ዛሬ የምንፈልገውን ለማግኘት፤ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ፤ የተወሳሰበና ቀና ባለመሆኑ፤ ያንን ለመደልደል እና ለማዘጋጀት፤ የግድ መንገዱን ለማለሳለስ፤ ሁሉም የሀገሪቱ ተቆርቋሪዎች የሚሳተፍበት ቡድን ማዘጋጀት የግድ ነው። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው፤ የኢሕአዴግ ፓርቲ ነው። ኢሕአዴግ ራሱን እያሻሸለ ለመሆኑ መስካሪ የሚፈልግ የለም። እያየነው ነው። አሁንም ሀገራችን የአንድ ፓርቲ ሀገር ናት። ምንም ይሁን ምንም፤ ሀገራችን የአንድ ፓርቲ ሀገር ሆና፤ ነገ የብዙ ፓርቲዎች ሀገር ትሆናለች በሚል ተስፋ ወደፊት መሄድ ያዳግታል። ዛሬውኑ ዘለን የብዙ ፓርቲዎች ሀገር ማድረግ አንችልም። ነገር ግን ከአንድ ፓርቲ ወደ ብዙ ፓርቲዎች ለመሸጋገር፤ የግድ የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋል። ያ ነው የሽግግር መንግሥት ጥያቄው መሠረቱ። ያንን ዘሎ ማለፍ አይቻልም። ቆዩኝ እኔ አደርገዋለሁ የሚለው ንግግር፣ መንግሥቱ ኃይለማርያምን፣ መለስ ዜናውን ያስታውሱኛል። ያን መስማት ይዘገንናል። የነገዋን ትክክለኛ መንገድ የያዘች ሀገራችን እንድትሆን፤ የግድ የሽግግር ጊዜ ያስፈልገናል። በርግጥ የሽግግሩ መንግሥት አመሠራረትና ይዘት በትክክል መያዝ አለበት። ሆኖም ግን፤ አደጋ አለው! እና ወይንም ሁሉም መንግሥት የሽግግር መንግሥት ነው! የሚለው አያስኬድም። Wንነት ከዚህ ይጀምራል።

የዐማራውን ጥያቄ በሚመለከት፤

ዐማራው እንደሌላው የሀገራችን ሕዝብ ከፍተኛ በደል ተካሂዶበታል። እዚህ ላይ ጥያቄ የለም። የዐማራውን በደል፤ ከጥፋቱ ልክ የለሽነት በላይ፤ ልዩ የሚያደርጉት ግልጽ የሆኑ ኩኔቶች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ፤ ዐማራው በተናጠል፤ “እስከዛሬ በዳይ ሕዝብ ነበር!” በሚል ተፈርጆ ነበር። የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ገና ሲመሠረት፤ “በዐማራው መቃብር ላይ የትግራይ ሩፑብሊክን እመሠርታለሁ!” ብሎ ነበር የተነሳው። በተግባርም ዐማራውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ያላደረገው ነገር የለም። ቀጥሎም ያቋቋማቸው ተቀጥላ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ፤ ብዐዴንን ጨምሮ፤ ይሄን መተከል የኔ ብለው፤ ዐማራን የዘር ማጽዳት ፈጽመውበታል። ዐማራው በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ፤ በመላ ኢትዮጵያ ለምዕተ ዐመታት ኖሯል። ዐማራው ከመላ ኢትዮጵያ እየተፈናቀለ፤ እየተዘረፈ፣ እየተገደለ፣ እየተሰደደ ነበር። ይህ የተለየ በደል፤ አሁንም በግልጽ በራሱ መኖሪያ በሆኑት፤ በወልቃይት፤ በራያ፣ በጠለምት፤ “ትግሬ ነኝ ብለህ ኑር! ወይንም ከዚህ ጥፋ!” ተብሎ ተወጥሯል። መተከል፤ “ያንተ ቦታ አይደለም!” ተብሎ፤ የደረሰበትን በጽሑፍ ማስቀመጡ ይዘገንናል። በዚህ ሁኔታ፤ ሀቁ የሚነግረን ይሄ ሆኖ ሳለ፤ “ሁሉም እኩል ነው!” ብሎ አጨብጭቡና ተደመሩ ብቻ ማለቱ ለኔ አያስኬድም።

ለዐማራው፤ ከሌሎቹ ኢትዮጵያውያን የተለዬ፤ ልዩ የሆነ ሥጦታ ይለገሰው የሚል የለም። ነገር ግን፤ ዐማራው አሁንም የሕልውና ጥያቄ አለው። አሁንም በአደጋ ላይ ነው። በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድና መንግሥታቸው ሊያደርጉ የሚችሉት የተወሰነ ነው። አብላጫው ድርሻ፤ ዐማራው ራሱ ሊያደርገው የሚገባው ነው። በወልቃይት፣ በጠለምት፣ በራያ፣ በመተከል የሚኖረው ዐማራ አሁንም በእስር ቤት ውስጥ ነው። የተፈናቀሉ ዐማራዎች አሁንም በየመንገዱ ተጥለው ነው የሚገኙት። ሌላው በሂደት የሚተገበር ይሆናል። ዋናው ግን፤ ይሄን የዐማራውን የሕልውና አደጋ መገንዘብ ነው።

ይሄን ሁሉ ካሰፈርኩ በኋላ፤ አሁንም ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ያለኝን አክብሮት መግለጽ እፈልጋለሁ። ሁላችንም እስከዛሬ ይሆናል ብለን ያልገመትነው ገሃድ ሆኖ ስናየው፤ በደስታ መጥለቅለቃችን ያለ ነው። ፊታችንን ስንመለከት፤ ጀርባችንን መዳሰስና የነበርንበትን መፈተሹ፤ ትምህርት ይሠጠናል። ወደን የሰቀልነውን ብቅል፤ ኋላ ማውረዱ እንዳይከብደን፤ ካሁኑ አሰቃቀላችንን እንወቅበት። አመሰግናለሁ። eske.meche@yahoo.com

Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ

የሽግግር መንግሥት ማቋቋሙ፤ ግዴታ ነው።

የሽግግር መንግሥት ማቋቋሙ፤ ግዴታ ነው።
አንዱዓለም ተፈራ
ሐሙስ፣ ሐምሌ ፲ ፪ ቀን ፳ ፻ ፲ ዓመተ ምህረት

የተራበች እናት ምግብ ማግኘቷ፤ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው።
ምርጫ የሚሆነው ሰጪና ነሺ ካለ፤ ለዚሁ አካል ብቻ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መሐመድ የኦሕዴድ መሪ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መሐመድ የኢሕአዴግ ወኪል ናቸው። አሁን ኢትዮጵያን እያስተዳደሩ ያሉት፤ በኢሕአዴግ መዋቅርና ሰዎች ነው። በርግጥ የያዙት መንገድ፤ እስከዛሬ በትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ገዥዎቻችን ሲመራ የነበረው ኢሕአዴግ ሲከተለው ከነበረው ለየት ያለ ነው። አሁንም መሠረቱ ግን ኢሕአዴግና ኢሕአዴግ ሲመራበት የነበረው የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ ነው። እናም አንድን ወገን ብቻ ወክለው፣ ነገር ግን በጣም ጥሩ ነገር ለብዙኀን በማድረግ ላይ ያሉ ናቸው። ይህ በጎ ተግባራቸው፤ ከመጡበት አኳያ ስናየው ውስንነት አለበት። በአንድ ሰው ቅንነት ሀገር አትመራም። የሚቀጥለው ምንድን ነው? ብለን ከመጠበቅ በላይ፤ ምን መሆን አለበት የሚለውን ሁላችን በያለንበት መነጋገር አለብን። የሀገራችን ችግር ምስቅልቅል ነው። ይህች ሀገር የሁላችን ናት። ለውጡን ተባብረን ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ፤ ሁላችን መታቀፍ አለብን።

የሀገራችን ችግር ምስቅልቅል ነው። በቀጥታ አንድና አንድን እንደመደመር ሊወሰድ የሚችል አይደለም። ይሄ ምስቅልቅል ችግር፤ መሠረታዊ የሆነ ከሥሩ መንግሎ የሚጥል መፍትሔ ካልተገኘለት፤ እምቧለሌ ዙሪያ የሚሽከረከርና የማይለቅ ይሆናል። የክልል ጉዳይ አንድ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ፤ አከላለሉ፣ አስተዳደሩ፣ “እኛ” እና “ሌሎች” የሚለው ግንዛቤ፣ ርስ በርስ ሕዝቡ እንዲጋደል የተደረገው ሂደት፣ የመፈናቀልና በግፍ የመገደል ጉዳይ ሌላው ነው። አድልዖ፣ ሙስና፣ የመንግሥት ሥልጣንና የተዋረዱ ሂደት ሌላው ጉዳይ ነው። የመንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ የመግባት ሁኔታ፤ ሌላው ጉዳይ ነው። በገፍ ከሀገራቸው የተሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ሌላው ነው። አንዱን አካባቢ ከሌላው አስበልጦ የማሳደግና ዕድሉን ሁሉ በዚያ መንዳት ሌላው ጉዳይ ነው። ብዙ ከዚህ የከፉ ሌሎች ሊዘረዘሩ የሚችሉ እንዳሉ ሁላችን እናውቃለን። የሚከተለው ምንድን ይሆን? ብለን ከመጠበቅ በላይ፤ ምን መከተል አለበት የሚለውን መነጋገር አለብን።

ይህች ሀገር የሁላችን ናት። እናም ሁላችን የኔ ብለን መፍትሔ ማምጣቱ ላይ መረባረብ አለብን። ግዴታውን ለአንድ ግለሰብ ወይንም ክፍል ሠጥተን፤ ሌሎቻችን እጆቻችንን አጣጥፈን መቀመጥ የለብንም። ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የደረሰው ጥፋት፤ በኢትዮጵያዊያን የተፈጸመ በመሆኑ፤ የኛው ታሪክ ነው። እናም አብሮን ለምጥ ሆኖ ለዘለዓለሙ ይኖራል። አሁን እንዲቀጥል የምንፈቅድበት ወይንም በትብብር እንዲቆም የምናደርግበት ዕድል ገጥሞናል። ኋላ ዞረን ያኔ እንዲህ ቢደረግ ኖሮ! ወይንም እኔ እንዲያ ባደርግ ኖሮ! ብለን የመቆጫው ጊዜ፤ ሊመጣ አይገባውም። አሁን ማድረግ ያለብንን፤ አሁን ማድረግ አለብን። እናም ትክክለኛው ጥያቄ፤ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ነው።

የሽግግር መንግሥትን መቋቋም የማይፈልጉ አሉ። እኒህ በሁለት ይከፈላሉ። የመጀመሪያዎቹ፤ አሁን ያለውን የለውጥ ሂደት ስለሚጠሉት፤ እንዲከሽፍና የነበሩበት መንበር እንዲመለስላቸው የሚደክሙት ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ፤ የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል ስለሚፈልጉና ለውጡ ይነጋነጋል ብለው ስለሚፈሩ፤ ሁሉን ነገር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንተውላቸው ባዮች ናቸው። የመጀመሪያዎቹን መነጋገር ያለብን አይመስለኝም። እናም አልፈዋለሁ። ሁለተኛዎቹን በሚመለከት፤ ያንድ ሰው ድካም ይበቃል ወይንስ ሁላችን የምንረባረብበት? በሚል እመልሰዋለሁ።

አንድ ብቻቸውን የሚደክሙት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ባሁኑ ጊዜ፤ ዙሪያቸውን ከከበቡት መካከል ነባር የሕዝቡ ጠላቶች አሉ። በግለሰብ ደረጃ እሳቸውን፤ ያን ካልቻሉ ደግሞ ሥራቸውን ለማደናቀፍ ወደኋላ የማይል ኃይል አለ ማለት ነው። መርሳት የሌለብን፤ ሕይወታቸውን ለማጥፋት ሞክረዋል። እሳቸውን ማጣት ከባድ ውድቀት ነው። ነገር ግን፤ በሳቸው ተማምኖ መጋለብ ኃላፊነት የጎደለው ሂደት ነው። እሳቸውን መንገር ያለብን፤ አሁን ሀገራችን የምትፈልገው፤ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞ፤ ውስብስቡን የሀገራችን ችግር፤ ባገር አቀፍ ጥሪ መፍታት ነው። እንዴት ሊቋቋም ይችላል? እንዲህ አይሆንም ወይ? ያ ችግር አያስኬድም? የመሳሰሉ ምክያቶችን መደርደር ይቻላል። ነገር ግን ከዚህ የቀለለ ሌላ መንገድ የለም። ስለ ሽግግር መንግሥት አቋቋም፤ በሚቀጥለው ጽሑፌ በሠፊው እሄድበታለሁ። ወይንም ሌሎች ሊያቀርቡ ይችላሉ። ዋናው ግን፤ ካለንበት አዘቅት መውጣት የምንችለው፤ ካሁኑ ቦታችን ወደምንፈልገው ቦታ ለመድረስ፤ የሽግግር መንግሥት ግዴታ ነው። ምን ትላላችሁ?

ከታላቅ አክብሮት ጋር
አንዱዓለም ተፈራ

Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ

የቀን ጅቦችና መሰሪ ተግባራቸው፤

የቀን ጅቦችና መሰሪ ተግባራቸው፤

አንዱዓለም ተፈራ

ሰኞ፤ ሐምሌ ፱ ቀን፣ ፳፻፲ ዓመተ ምህረት

በዐማራውና በኦሮሞው ኅብረት ደማቸው የፈላና፤ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ የቀን ጅቦች፤ በዐማራውና በኦሮሞው መካከል ጠብ ለመጫር ያለ የሌለ ጉልበታቸውን እያፈሰሱ ነው። ከዚህ መካከል አንዱ ዘዴያቸው፤ በታሪክ እኒህን ሁለቱ ታላላቅ የኢትዮጵያ አካሎች ማጣላት ነው። ዐማራ ኢትዮጵያን በሚመለከት፤ ሰንደቋን አንግቦ የኖረ ሕዝብ ነው። ኦሮሞም ሀገር ገንቢና ባለቤትም ነው። በሁለቱም ወገን ገዥዎችና ተገዥዎች ነበሩባቸው። በኢትዮጵያ ስም የገዙት ከሁለቱም ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም የተወለዱ ነበሩ።

እኒህ የቀን ጅቦች፤ ኦሮሞዎችን አሳንሰው፤ ተገዥ ብቻ፣ ዐማራው ገዥ ብቻ፣ በማድረግ፤ አንዱ ሌላውን እንዲያጠፋና የዘለዓለም ጠበኞች እንጂ፤ ሊስማሙ የማይችሉ አድርገው እየሳሉ ነው። ታሪኩ ግን ዐማሮችና ኦሮሞዎች፤ ኢትዮጵያዊ ሆነው በነበሩት ነገሥታት፤ ነገሥታቱ በነበራቸው ዕውቀትና ችሎታ፤ ሀገራችንን ጠብቀው ያቆዩ ናቸው። ይሄን ደግሞ የሌለ ታሪክ በመፍጠርና የውሽት ስዕል በመለጠፍ ተያይዘውታል። አክራሪ ኦሮሞ መስለው፤ የኦሮሞን ወጣት በጥላቻ ለመመረዝ ያደረጉትን ላሳያችሁ።

ይህ የምታዩት ፎቶ፤ አንዱ የቀን ጅብ፤ የኦሮሞ ወጣቶችን በዐማራ ጥላቻ ለመሙላት የለጠፈው ነው።

One

ይህ የውሸት ፎቶ ነው። ይሄ ፎቶ፤ ከመጀመሪያው ፎቶ ላይ፤ የአፄ ሚኒልክን የፊት ገጥ ቀዶ በማስቀመጥ፤ ለማወናበድ የተደረገ ነው። የመጀመሪያው ፎቶ ይሄውላችሁ።

Two

ልቀጥል። ይሄው ሁለተኛ ፎቶ፤

Three

ይሄኛውን ደግሞ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ፎቶ ተክተው ለጥፈውታል።

ስድስት

ሌሎችም እንዳሉ ሁላችሁ ታውቃላችሁ። ይሄን ለምን ያደርጋሉ? የሁለቱ ወገኖች መተባበር፤ የትግሬዎች ገዥዎችን ኦድሜ ስላሳጠረ፤ በሀገር ውስጥ ሰላም እንዳይኖርና ብጥብጥ ተፈጥሮ፤ ቢቻሉ በቦታቸው ሊመለሱ፤ ካልቻሉ ደግሞ ሀገር ሰላም እንዳያገኝ ነው። ምን ትላላችሁ?

Posted in እስከመቼ - ESKEMECHE | አስተያየት ያስቀምጡ