የሽግግር መንግሥት ማቋቋሙ፤ ግዴታ ነው።

የሽግግር መንግሥት ማቋቋሙ፤ ግዴታ ነው።
አንዱዓለም ተፈራ
ሐሙስ፣ ሐምሌ ፲ ፪ ቀን ፳ ፻ ፲ ዓመተ ምህረት

የተራበች እናት ምግብ ማግኘቷ፤ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው።
ምርጫ የሚሆነው ሰጪና ነሺ ካለ፤ ለዚሁ አካል ብቻ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መሐመድ የኦሕዴድ መሪ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መሐመድ የኢሕአዴግ ወኪል ናቸው። አሁን ኢትዮጵያን እያስተዳደሩ ያሉት፤ በኢሕአዴግ መዋቅርና ሰዎች ነው። በርግጥ የያዙት መንገድ፤ እስከዛሬ በትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ገዥዎቻችን ሲመራ የነበረው ኢሕአዴግ ሲከተለው ከነበረው ለየት ያለ ነው። አሁንም መሠረቱ ግን ኢሕአዴግና ኢሕአዴግ ሲመራበት የነበረው የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ ነው። እናም አንድን ወገን ብቻ ወክለው፣ ነገር ግን በጣም ጥሩ ነገር ለብዙኀን በማድረግ ላይ ያሉ ናቸው። ይህ በጎ ተግባራቸው፤ ከመጡበት አኳያ ስናየው ውስንነት አለበት። በአንድ ሰው ቅንነት ሀገር አትመራም። የሚቀጥለው ምንድን ነው? ብለን ከመጠበቅ በላይ፤ ምን መሆን አለበት የሚለውን ሁላችን በያለንበት መነጋገር አለብን። የሀገራችን ችግር ምስቅልቅል ነው። ይህች ሀገር የሁላችን ናት። ለውጡን ተባብረን ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ፤ ሁላችን መታቀፍ አለብን።

የሀገራችን ችግር ምስቅልቅል ነው። በቀጥታ አንድና አንድን እንደመደመር ሊወሰድ የሚችል አይደለም። ይሄ ምስቅልቅል ችግር፤ መሠረታዊ የሆነ ከሥሩ መንግሎ የሚጥል መፍትሔ ካልተገኘለት፤ እምቧለሌ ዙሪያ የሚሽከረከርና የማይለቅ ይሆናል። የክልል ጉዳይ አንድ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ፤ አከላለሉ፣ አስተዳደሩ፣ “እኛ” እና “ሌሎች” የሚለው ግንዛቤ፣ ርስ በርስ ሕዝቡ እንዲጋደል የተደረገው ሂደት፣ የመፈናቀልና በግፍ የመገደል ጉዳይ ሌላው ነው። አድልዖ፣ ሙስና፣ የመንግሥት ሥልጣንና የተዋረዱ ሂደት ሌላው ጉዳይ ነው። የመንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ የመግባት ሁኔታ፤ ሌላው ጉዳይ ነው። በገፍ ከሀገራቸው የተሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ሌላው ነው። አንዱን አካባቢ ከሌላው አስበልጦ የማሳደግና ዕድሉን ሁሉ በዚያ መንዳት ሌላው ጉዳይ ነው። ብዙ ከዚህ የከፉ ሌሎች ሊዘረዘሩ የሚችሉ እንዳሉ ሁላችን እናውቃለን። የሚከተለው ምንድን ይሆን? ብለን ከመጠበቅ በላይ፤ ምን መከተል አለበት የሚለውን መነጋገር አለብን።

ይህች ሀገር የሁላችን ናት። እናም ሁላችን የኔ ብለን መፍትሔ ማምጣቱ ላይ መረባረብ አለብን። ግዴታውን ለአንድ ግለሰብ ወይንም ክፍል ሠጥተን፤ ሌሎቻችን እጆቻችንን አጣጥፈን መቀመጥ የለብንም። ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የደረሰው ጥፋት፤ በኢትዮጵያዊያን የተፈጸመ በመሆኑ፤ የኛው ታሪክ ነው። እናም አብሮን ለምጥ ሆኖ ለዘለዓለሙ ይኖራል። አሁን እንዲቀጥል የምንፈቅድበት ወይንም በትብብር እንዲቆም የምናደርግበት ዕድል ገጥሞናል። ኋላ ዞረን ያኔ እንዲህ ቢደረግ ኖሮ! ወይንም እኔ እንዲያ ባደርግ ኖሮ! ብለን የመቆጫው ጊዜ፤ ሊመጣ አይገባውም። አሁን ማድረግ ያለብንን፤ አሁን ማድረግ አለብን። እናም ትክክለኛው ጥያቄ፤ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ነው።

የሽግግር መንግሥትን መቋቋም የማይፈልጉ አሉ። እኒህ በሁለት ይከፈላሉ። የመጀመሪያዎቹ፤ አሁን ያለውን የለውጥ ሂደት ስለሚጠሉት፤ እንዲከሽፍና የነበሩበት መንበር እንዲመለስላቸው የሚደክሙት ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ፤ የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል ስለሚፈልጉና ለውጡ ይነጋነጋል ብለው ስለሚፈሩ፤ ሁሉን ነገር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንተውላቸው ባዮች ናቸው። የመጀመሪያዎቹን መነጋገር ያለብን አይመስለኝም። እናም አልፈዋለሁ። ሁለተኛዎቹን በሚመለከት፤ ያንድ ሰው ድካም ይበቃል ወይንስ ሁላችን የምንረባረብበት? በሚል እመልሰዋለሁ።

አንድ ብቻቸውን የሚደክሙት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ባሁኑ ጊዜ፤ ዙሪያቸውን ከከበቡት መካከል ነባር የሕዝቡ ጠላቶች አሉ። በግለሰብ ደረጃ እሳቸውን፤ ያን ካልቻሉ ደግሞ ሥራቸውን ለማደናቀፍ ወደኋላ የማይል ኃይል አለ ማለት ነው። መርሳት የሌለብን፤ ሕይወታቸውን ለማጥፋት ሞክረዋል። እሳቸውን ማጣት ከባድ ውድቀት ነው። ነገር ግን፤ በሳቸው ተማምኖ መጋለብ ኃላፊነት የጎደለው ሂደት ነው። እሳቸውን መንገር ያለብን፤ አሁን ሀገራችን የምትፈልገው፤ የሽግግር መንግሥት ተቋቁሞ፤ ውስብስቡን የሀገራችን ችግር፤ ባገር አቀፍ ጥሪ መፍታት ነው። እንዴት ሊቋቋም ይችላል? እንዲህ አይሆንም ወይ? ያ ችግር አያስኬድም? የመሳሰሉ ምክያቶችን መደርደር ይቻላል። ነገር ግን ከዚህ የቀለለ ሌላ መንገድ የለም። ስለ ሽግግር መንግሥት አቋቋም፤ በሚቀጥለው ጽሑፌ በሠፊው እሄድበታለሁ። ወይንም ሌሎች ሊያቀርቡ ይችላሉ። ዋናው ግን፤ ካለንበት አዘቅት መውጣት የምንችለው፤ ካሁኑ ቦታችን ወደምንፈልገው ቦታ ለመድረስ፤ የሽግግር መንግሥት ግዴታ ነው። ምን ትላላችሁ?

ከታላቅ አክብሮት ጋር
አንዱዓለም ተፈራ

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in እስከመቼ - ESKEMECHE. Bookmark the permalink.

አስተያየት ያስቀምጡ