እና ዐማራ!

እና ዐማራ!
አንዱዓለም ተፈራ
አርብ፣ ነሐሴ ፬ ቀን፣ ፳፻፲ ዓመተ ምህረት

ለውጡ እስካሁን በጀመረው መንገድ ይሄዳል የሚል ተስፋ ሁላችን ሰንቀናል። ባሁኑ ጊዜ፤ መሠረታዊ የሆኑት የኢሕአዴግ የአስተዳደር መተክሎቹ እንዳሉ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ፤ የዘር ፖለቲካው ባጭር ጊዜ ውስጥ እንደማይለውጥ አስምረውበታል። ከውጪና ከውስጥ የዘር ፖለቲከኞች የሰላ የመቀራመቻ ስንጢያቸውን አሰልስለው “የኔ!” “የኔ!” ታቸውን ተያይዘውታል። በዚህ ሂደት አንድነት የሌለው የዐማራው የድርጅቶች ጋጋታ፤ ቁጥሩ የሚጨምርበት እንጂ፤ ወደ አንድ የሚሰባሰብበት ሁኔታ አይታይም። እና ዐማራ!

የሾህ አጥር በመካከላችን ማበጀቱን ትተን፤ ይሄን ጉዳይ የሁላችን አድርገን መነጋገር እንችላለን። የዐማራው ጉዳይ የእከሌ ወይንም የእከሊት አይደለም። የሁላችንም ነው። የአንድ ድርጅት ወይንም የሌላም አይደለም። የዐማራዎች በሙሉ ነው። ይሄን ጉዳይ ደግሞ ካልተነጋገርንበት፤ ሌላ ከዚህ የከበደ ምን አለ? ሀቁን መመልከትና እውነቱን መነጋገር አለብን። በዐማራው ላይ የተደረገው ጭፍጨፋ፤ በዐማራነት እንጂ፤ ግለሰቦች በሠሩት ተግባር የተመሠረተ አይደለም። ይህ ሆን ተብሎ ታምኖበትና በመምሪያ በተግባር የዋለ በመንግሥት ደረጃ የተከናወነ ጥፋት ነው። እናም ዐማራ የሆን ሁላችን፤ ልንቆረቆርበት ይገባናል። ባሁኑ ሰዓት የዐማራውን የፖለቲካ ምህዳር አጣበው የያዙት፤ የብሔረ ዐማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብዐዴን) እና የዐማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዐብን) ናቸው። የዐማራ ጉዳይ ደግሞ፤ የብዐዴን ወይንም የዐብን ብቻ፤ የግል ጉዳይ አይደለም። የብዐዴን አመራር፤ ከመካከለኛው መንግሥት ጋር ሆኖ፤ ሀገር የመምራትና ሀገር አቀፍ ፓርቲ የመመሥረት ዓላማ ያለው ይመስላል። ዐብን ደግሞ፤ እኔ ነኝ የዐማራ ብሔርተኝነት ማዕከል ብሎ፤ በብቸኝነት ቢሮዎቹን በየቦታው በመክፈት ላይ ነው። የነኝህ የየራሳቸው ሩጫ፤ ዐማራውን ይጎዳዋል። እኒህ ሁለቱ፤ አንዳቸው አንዱን አጽናፍ፤ ሌላቸው ሌላኛውን አጽናፍ ይዘው የሚጓተቱበት መሆን የለበትም። ሁለቱም በየበኩላቸው የየራሳቸው ጥናካሬና ድክመት አላቸው። በኔ በኩል፤ እኒህ ሁለቱ ቢጣመሩ ጥንካሬያቸው አይሎ፤ ሁሉን ዐማራ ሊወክሉ የሚችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል እምነት አለኝ።

የዐማራ ሕዝብ አንድ ነው። ለዐማራው የሚቆም ደግሞ ባንድ መሰለፍ አለበት። ይህ ለዐማራው መቆም፣ የርዕዩተ ዓለም ባለቤትነትን አይጠይቅም፣ አያካትትም፣ አያስፈልገውም። ይህ ለአንድ ወገን የመቆርቆር ጉዳይ ነው። ተቆርቋሪዎች ደግሞ፤ በሙሉ በአንድነት ተሰባስበው መመካከር አለባቸው እንጂ፤ ወዲያና ወዲህ ሆነው መጓተት የለባቸውም። ከዚህ በመነሳት፤ ለዐማራው እንቆማለን ያሉት በሙሉ፤ የየድርጅታቸውን ጥንካሬም ይሁን ድክመት ሳይመዝኑ፤ ለዐማራው መቆም አለባቸው። እናም አንድ የዐማራ ጠንካራ ድርጅት ነው የሚያስፈልገው። ብዐዴንና ዐብን ወደ አንድ መምጣት አለባቸው ስል፤ ከዚህ እምነት በመነሳት ነው። ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮነንና ለዐማራው ፕሬዘዳንት ገዱ አንዳርጋቸው፤ ከኦሕዴድ በፊት፤ አብን ይቀርባቸዋል። ከኦሕዴድ ጋር ከመደራደራቸው በፊት፤ በዐማራው በኩል ያለውን በአንድነት ቢመሩት፤ ለራሳቸውም ጥንካሬ፤ ለዐማራውም ትክክለኛ ውክልና ይኖራል።

የሁለቱን ድርጅቶች ድክመት እዚህ ላይ ማተቱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያይል አልሄድበትም። ጥንካሬያችውን ስንመለከት ደግሞ፤ በብዐዴን በኩል፤ መንግሥታዊ መዋቅር፣ ንብረትና ግዝፈት አለው። በዐብን በኩል ደግሞ ወጣቱ፣ የጠነከረ የዐማራነት ብሔርተኝነትና ትኩስነት አላቸው። እኒህ የሁለቱ ወገኖች ጥንካሬዎች ባንድ ላይ ሲጣመሩ፤ ከፍተኛ የሆነ የደቦ ጉልበት ይፈጥራሉ። በሕዝቡ ዘንድ ደግሞ ቀስቃሽ ስሜትን ፈጥሮ፤ ብዙዎችን ያነሳሳል። እስኪ በያላችሁበት ይሄን ምከሩበት።

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in እስከመቼ - ESKEMECHE. Bookmark the permalink.

አስተያየት ያስቀምጡ