የለውጡ የወደፊት ሂደት

የለውጡ የወደፊት ሂደት

አንዱዓለም ተፈራ

ማክሰኞ፣ መስከረም ፰ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፩ ዓ. ም. ( 9/18/2018 )

ከመነሻው፤ ለውጡን የምንፈልግ በብዛት እንደምንገኝ ሁሉ፤ ለውጡን የማይፈልጉ ብቻ ሳይሆን፤ ለውጡን የሚቃወሙ እንዳሉ ማመን አለብን። ባሁኑ ሰዓት ለውጡ እንቅፋቶች ገጥመውታል። እኒህ እንቅፋቶች፤ መሠረታዊ ችግሮች ናቸው? ወይንስ በሂደት የመጡና ሊወገዱ የሚችሉ? ለውጡ የጎደለው እንዳለ ጠቋሚዎች ናቸው? ወይንስ የለውጡ ምንነት ችግር? የለውጡ ሂደት የፈጠራቸው ናቸው? ወይንስ ከለውጡ ምንነት ጋር የተያያዙ? ከምን የመጡ ናቸው? ይሄንን ሳይመለከቱ፤ በደፈናው እንዲህ ሆነ እንዲያ እናድርግ በሚል መጓዙ፤ የእምቧለሌ ሽክርክር ይሆናል።

መጀመሪያ ማድረግ ያለብን፤ ለውጡ ለምን መጣ? በማን ላይ መጣ? ማን አመጣው? እንዴት መጣ? የሚለውን መመለስ ነው። አዎ! ችግር አለ። ይሄን መካድ አይቻልም። አዲስ አበባ ውስጥ ሆነ አርባ ምንጭ፣ ኢትዮጵያ ሶማሊም ሆነ ቤንሻንጉል፤ በየቦታው የተፈናቀሉትም ሆነ፤ ሆን ተብሎ የሚዘመትባቸው ሰዎች፤ መሠረታዊ በሆነ ችግር ምክንያት እንጂ፤ ሰዎቹ ስለተጠሉ ወይንም ወንጀል ስለሠሩ አይደለም።

በአንድ ሀገር የሚከሰተው ለውጥ፤ እንዲህ መሆን አለበት! ወይንም እንዲያ መሆን አለበት! ተብሎ በተቀመጠ ቅምር እንደ ተዘጋጄ እጄ ጠባብ፤ የሚጠለቅ አይደለም። ተጨባጩ የሀገሪቱ ሁኔታ፣ የወቅቱ የፖለቲካ ሀቅና፣ በሂደቱ ያሉት ተሳታፊዎች አሰላለፍ፤ ይወስነዋል። ያም እንኳን ሆኖ፤ ለውጡን በትክክል መተንበይ አይቻልም። የኛን እውነታ ስንመለከት፤ ለውጡ ኢሕአዴግ በፈጠረው በደልና ጥፋት የተነሳ የመጣ ነው። ለውጡ ኢሕአዴግን ለማፍረስና፤ ያራመዳቸውን የፖለቲካ ቀውሶች ለማስተካከል ነው። ለውጡን ኢሕአዴግ ሊመራው አይችልም። የመጀመሪያው ችግር፤ ለውጡ የመጣበት ኢሕአዴግ፤ ለውጡን እየመራ መገኘቱ ነው። ይህ ማለት፤ በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ለውጥ ፈላጊዎች ተሳታፊ አይሆኑም ማለት አይደለም። ነገር ግን፤ እነሱ የለውጡ አካል ይሆናሉ እንጂ፤ የለውጡ ባለቤትና ግለኛ መሪዎች መሆን አይችሉም። ይህ፤ በመፈንቅለ መንግሥት ከሚደረግ የለውጥ ሂደት ጋር ይመሳሰላል። አብዛኛውን ጊዜ፤ የሥርዓቱ ምሰሶ የሆነው ወታደራዊ ክፍል፤ መፈንቅለ መንግሥት ያደርግና፤ “እኔ ባለቤት ነኝ፤ ሌሎቻችሁ አርፋችሁ ተቀመጡ!” ይላል። ይህ ያንን ያስታውሰኛል። ከራሳችን ታሪክ መማር ይገባናል።

ቀጥሎ ደግሞ፤ የለውጡን መሠረታዊ መነሻዎች ወደ ጎን ትቶ፤ ሌሎችን ማስተካከሉ ላይ ነው። ለውጥ ሲደረግ፤ መነሳት ያለባቸው ሰዎች፤ አሁንም አድራጊ ፈጣሪ ሆነው መገኘታቸው ነው። በዐማራው ክልል ሆነ በደቡብ ክልል፣ አሁንም የኢሕአዴግ መሪ የነበሩ ናቸው በማስተዳደርና፤ የለውጡ መሪዎች ነን ብለው ተሰልፈው የሚገኙ። ማገናዘብ ያለብን፤ እኒህ ሰዎች ባሉበት ቦታ ከፍተኛ በደል በሕዝቡ ላይ በደል ፈጻሚ ነበሩ። የተበደሉትና ከፍተኛውን መስዋዕትነት የከፈሉት ናቸው፤ የለውጡ ባለቤቶች። በምንም መለኪያ ቢሆን፤ ለውጡ የመጣባቸው ለውጡን ሊመሩ አይችሉም። አሁን እየታዬ ላለው ሁኔታ፤ ይህ ሀቅ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው።

ከላይ የተቀመጠው አሁን ያለውን መንግሥት አስመልክቶ ነው። ነገር ግን ያ ብቻ አይደለም ችግሩ። ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት የሚንቀሳቀሰው፤ በኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት ነው። ያ ብቻም አይደለም። ባሁኑ ሰዓት፤ በወታደራዊ ክፍሉ፣ በደህንነት መሥሪያ ቤቱና በመንግሥቱ አጠቃላይ መካከለኛ አመራር ላይ ተሰግስገው የሚገኙት የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ሰዎች ወይንም እነሱ በገንዘብ የገዟቸው ሰዎች ናቸው። እኒህ ሰዎች ሕልውናቸውን የተከሉት፤ ለትግሬዎቹ ገዥ ቡድን ጥቅም ነው። ዐማራ ሆኑ ሶማሊ፤ ኦሮሞ ሆኑ የደቡብ ክልል ስዎች፤ የሚወክሉት ሕዝብ ኖሯቸው ሳይሆን፤ ለሆዳቸው ለትግሬዎቹ ገዥዎች ተገዝተው የቆሙ ናቸው። እናም አሁን በትክክል የሚወክሉት ሕዝብ የላቸውም። ስለዚህ፤ የሚያገለግሉት ያንኑ አሳዳሪያቸውን ነው። በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየወሰዱ ያሉትን ትክክለኛ እርምጃዎች፤ ማድነቅ አለብን። ያ ግን መሠረታዊ አይደለም። የግለሰቦች መልካም ፈቃድ፤ የሀገርን ሂደት ወሳኝ መሆን የለበትም። አሰራሩ ነው ወሳኙ። ለውጡን ያመጣውን ክፍል አግልሎ፤ ወደፊት መሄድ አይቻልም። አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወክሉት ኢሕአዴግን እና ኦሕዴድን እንጂ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ አይደለም። ውክልና የሠጣቸው ኢሕአዴግ ነው። አሁንም የኢሕአዴግን መዋቅር ነው እየመሩ ያሉት። ይሄ ሁሉ በገዥው ክፍል ላይ ቢነሳም፤ በአንጻሩ ደግሞ አማራጩ ጨለማ ነው።

በተቃዋሚ በኩል እስከዛሬ የነበረውና አሁን በተፎካካሪነት አለን የሚለው ክፍል፤ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ፤ አንድነት የሌለው፣ ግልጥ ራዕይ ያላስቀመጠ፣ አማራጭ ሆኖ ያልተገኘ ነው። ቁጥሩ መብዛቱ ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ ድርጅት ራሱን ወደላይ ክቦ፤ ከማንም ጋር ላለመሥራት ችግሮችን ደርድሮ፤ “እኔ ነኝ!” እያለ ሲደነፋ ይገኛል። “ሌሎቹ አይረቡም!” የሚል ጉራም አለበት። ይሄ በሆነበት እውነታ፤ ይህ ክፍል፤ በሥልጣን ላይ ያለውን ክፍል፤ በምንም መንገድ ሊወቅስ አይገባውም። ራሱን አያውቅምና! ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ባንድ በኩል፤ ሀገር አቀፍ ነን የሚሉ በሌላ በኩል ተኮልኩለዋል። በጣም አጽናፋዊ አቋም ያላቸው፤ ኢትዮጵያዊነትን እርግፍ አድርገው ጥለዋል። በሀገር አቀፍ ዓላማ የተደራጁትም በመካከላቸው የርዕዩተ ዓላማ ልዩነት ሳይሆን የመሪዎች ልዩነት አንቋቸው፤ መቀራረብ አላሳዩም። መሰባሰብ ይጠቅማቸው ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ፤ ከገዥው ክፍል የሚለዩበትን የርዕዩተ ዓለም ጉዳይ፤ በግልጥ ለሕዝብ አላቀረቡም። የምርጫ ቀን መሆን የለበትም። ከዚያ በፊት፤ ለምን እንደተቋቋሙ መናገር አለባቸው። አማራጭነታቸው የምርጫው ወቅት አይደለም የሚሰመረው። ከዚያ በፊት ከሕዝብ ጋር ሲተዋወቁ፤ ማንነታቸውን መግለጥ አለባቸው። አዎ! የሀገራችን የፖለቲካ ሂደት በየቀኑ እየተለዋወጠ ነው።

ሀገራችን አሁን ካለችበት ወጥታ ወደፊት ለመሄድ፤ ሀገራዊ የሆነ ራዕይ፣ መስማሚያ ጉዳይ፣ አሰባሳቢ መድረክ ያስፈልገናል። ሕዝቡ የኔ የሚለው መንግሥት በቦታው መቀመጥ አለበት። ድክመቱ ያለው በሁሉም ወገን ነው።

አሁን ወዳለንበት ሀቅ ስንመለስ፤ የለውጡ ሂደት እየተካሄደ ያለው፤ የኢሕአዴግ አባል ሆነው፤ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉ ጥቂት ግለሰቦች፤ የሚችሉትን በማድረግ ነው። እንግዲህ የለውጡ ግስጋሴና ጥልቀት፣ የለውጡ ፍጥነቱና ይዘቱ፤ በኒሁ ግለሰቦች ፍላጎት ይመራል ማለት ነው። ይህ በጣም ሊያሳስበን ይገባል። ይሄንን ሊያደርጉ የምችሉት ደግሞ፤ የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት በፈቀደላቸው መሠረት መሆኑን ከላይ አስፍሬያለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታጋዩን ክፍል ልብ ሰልለው፤ “ለውጡ እኔ ነኝ። የማሸጋግርህ እኔ ነኝ። የሽግግር መንግሥቱ እኔ ነኝ! ከፈልግህ ተደራጅና፤ እኔ አስመራጭ፣ ምርጫ አዘጋጅ፣ የምርጫ ሂደቱን ተከታታይ በሆንኩበት ምርጫ፤ የሽግግሩን ዘመን ከጨረስኩ በኋላ ተሳተፍ!” ብለው ቁጭ አሉ።

ወደፊት እንሂድ። አሁን ለውጡን የሚመሩት፤ መጀመሪያ ሕጋዊነት ያግኙ። የኢሕአዴግ ሕጋዊነት በለውጡ እውነትነት ፈርሷል። የሕዝቡን ውክልናን ለማግኘት፤ የፖለቲካ መሠረታቸውን ማስፋት አለባቸው። ይህ ማለት፤ የሕዝቡን ታጋዮች ያካተተ መንግሥት ማለት ነው። ይህ ሰቅዞ ከያዛቸው የኢሕአዴግ ሰንሰለት ነፃ ያወጣቸዋል። ቆራጥ እርምጃ እንዲወስዱ ይፈቅድላቸዋል። ሕዝቡ የኔ ብሎ እንዲከተላቸው በር ይከፍትላቸዋል።

በተፎካካሪው ክፍል ያሉት ደግሞ፤ ትክክለኛ አማራጭ ሆነው መቅረብ አለባቸው። ዓርማ መለጠፍ፣ መርኀ-ግብር ማውለብለብ፣ መሪዎችን ባደባባይ ማዞር ብቁ ድርጅት መኖሩን አያሳይም። መጥቆ የወጣ ራዕይ፣ የተጠናከረ ድርጅትና በዛ ያሉ አባላት፣ የሚመዘን ተልዕኮና በግለሰቦች ፍላጎት ሳይሆን በድርጅታዊ አሰራር የሚመራ የፖለቲካ ድርጅት ሆነው መገኘት አለባቸው። ያ አለ ወይ?

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in እስከመቼ - ESKEMECHE. Bookmark the permalink.

አስተያየት ያስቀምጡ