ዐማራው ያለበት ሁኔታና የወደፊት ጉዞው አቅጣጫ ( ክፍል ፩ )

ዐማራው ያለበት ሁኔታና የወደፊት ጉዞው አቅጣጫ ( ክፍል ፩ )
አንዱዓለም ተፈራ
ነሐሴ ፰ ቀን ፳ ፻ ፲ ዓ. ም.

ከምን ተነሳን? ( የመጀመሪያው ጉዳይ )

ዐማራው አሁን ያለበት ሁኔታ፤ እስከዛሬ ከደረሰበት በደል የተነሳ የወደቀበት አዘቅት ነው። ይሄን ረግጦ በመነሳት፤ ወደፊት ጥሶ መሄድ ያስፈልጋል። ስለፈለጉ ብቻ ግን፤ ወዳሰቡት ቦታ መሄድ አይቻልም። መመርመር አለ። ማቀድ አለ። ማመቻቸት አለ። መተግበር አለ። ይህን ሂደት፤ መመርመሩን እና ማቀዱን፣ ማመቻቸቱን እና መተግበሩን፤ ከኛ ውጪ ላሉ፤ ለሌሎች መሥጠት አንችልም። እኛው ራሳችን፤ የኛ የራሳችን ጉዳይ ነው ብለን፤ ባለቤትነቱን ወስደን፤ ተግባር ላይማዋል አለብን። በኔ በኩል፤ ከዚህ በማከታተል፤ የነበረውን ተመልክቼ፣ አሁን ያለንበትን አካትቼ፣ ወደፊት ልንጓዝ ወደ ምንፈልገው ግባችን የሚወስደንን መንገድ ተልሜ፤ አሁን ማድረግ ያለብንን እጠቁማለሁ።

የዐማራው የሕልውና ጉዳይ መልክ ያበጀው፤ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ገና ሲመሠረት፤ “በዐማራው መቃብር ላይ፤ የትግራይን ሩፑብሊክ እመሠርታለሁ!” ብሎ በወረቀቱ ላይ ያሰፈረ ጊዜ ነው። ከዚያ ቀጥሎም በ፲ ፱ ፻ ፸ ፪ ዓ. ም. ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይት ሲገባ፤ ሕዝቡን ስብስቦ፤ “ከዛሬ ጀምሮ እናንተ ትግሬዎች ናችሁ! የምትናገሩት በትግርኛ ብቻ ነው! የምታለቅሱት በትግርኛ ብቻ ነው! የምትዘፍኑት በትግርኛ ብቻ ነው! አቤቱታችሁን የምትጽፉት በትግርኛ ብቻ ነው። የምትጽፉትም ለኛ ብቻ ነው!” የሚል አወጀ። ወልቃይትን ከ፲ ፱ ፻ ፸ ፪ ዓ. ም. ጀምሮ፤ በአዋጅ ትግራይ አደረጋት። አውራ ላይ ከኢሕአፓና ከሕዝቡ ትልቅ ጦርነት ገጠመው። ወጣት የትግራይ ልጆችን ማገደ። ነገር ግን፤ ኃላፊነቱ ለወጣቱ ነፍስ ሳይሆን፤ ለዓላማቸው ነበርና፤ የማገደውን ማግዶ ወልቃይትን ተቆጣጠረ። ወደ ጠለምት አመራ።

በዚህ ጊዜ፤ የጠለምት፣ የብራ ዋስያ፣ የወልቃይትና የጠገዴ አርበኞች፤ “እኛ አርሶ አደሮች ነን። መንግሥት ከሆናችሁ፤ ዋና ከተማውን ያዙና፣ ከዚያ ሆናችሁ ስትጠይቁን፣ ግብራችን እንልካለን። በዚህ በቦታችን ግን ተውን! እኛ ማንነታችንን ራሳችን እናውቃለን! ሌላ ሰው ማንነታችን አይነግረንም! እኛ ትግሬዎች አይደለንም! እኛ ዐማራዎች ነን!” በማለት፤ “ከፋኝ!” ን አቋቁመው፤ ትግላቸውን ጀመሩ። በቀጥታ ማጥፋት ስላልቻለ፤ በካህናት ልመናና ሽምግልና በማባበል፤ የመጀመሪያውን መሪ፤ ገብረመድሕንን በዕርቅ አባብሎ አስገብቶ ገደል። በመቀጠል፤ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ መንግሥት የሚያደርገውን ግፍና በደል በመቃወም፤ ሕዝቡን መቀሰቀስ ሲይዙ፤ ኢትዮጵያ የብሔርና ብሔረሰቦች ስብስብ እንጂ፤ ኢትዮጵያዊ የሚባል ሕዝብ የለም ስለተባሉ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያሰቡትን ተገደው፤ የመላ ዐማራ ሕዝብ ድርጅትን በማቋቋም፤ ትግላቸውን ገፉ። ነገር ግን፤ ከሁሉም በላይ ዐማራውን ይፈራ የነበረው የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ የዐማራውን ትግል ለማጥፋት እሳቸውን መግደል አስፈላጊ ነው ብሎ በማመን፤ እሳቸውን ለሞት ዳረጋቸው።

የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር፤ በመርኀ-ግብሩ እንዳሰፈረው፤ ዐማራውን ማጥፋት ዋና ጉዳዩ ነበርና፤ ባቋቋማቸው ተቀጥላ የብሔር ድርጅቶቹ አማካኝነት፤ የራሱን መንግሥት ሲያቋቁም፤ ዐማራው ያላተሳተፈበት ሕገ-መንግሥት አረቀቀ። በሕገ-መንግሥቱም ዐማራው ስፍራ እንዳይኖረው ተደረገ። ዐማራው በዐማራነቱ የሕዝብ ጠላት ተደረገ። ከየመሥሪያ ቤቱ ተባረረ። የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር በአጠራቸው ክልሎች ውስጥ፤ ዐማራው እንዲጨረስ፤ በአሽከሮቹ በነ ታምራት ላይኔ አማካኝነት፣ ተገደለ፣ ተፈናቀለ፣ ተሰደደ፣ ተዘረፈ፣ ታሰረ፣ የሁለተኛና የሶስተኛ ደረጃ ዜግነት እንኳን ተነፈገው። ከ “ደቡብ ኢትዮጵያ” ከ “ኦሮሚያ” ከ “ኢትዮጵያ ሶማሊያ” ከ “ትግራይ” የዐማራ ሰው እንዳይገኝ ተገፋ። ይብስ ብሎ፤ በራሱ በ “ዐማራ” ክልልም የትግሬዎቹ የበላይነት ነገሠበት። ዐማራው ቤት የሌለው ሆነ። በደል ምን ጊዜም በደሉን የሚቃወም ያፈራልና፤ ዐማራው በእምቢተኝነት ትግሉን ሳያባራ ቀጠለ።

በከፋኝ የጀመርነው ሰዎች፤ በራሳችን ድክመትና በሁኔታው አለመመቸት፤ ስንከፋፈልና ስንነቃቀፍ፤ መሸናሸንና መበታተን ተከተለን። ፕሮፌሰር አስራትም ከዕረፍታቸው በኋላ፤ ትክክለኛ መሪና ትክክለኛ መርኅ ባለመኖሩ፤ መዐሕድ ተዳከመ። ይሄም ሆኖ፤ ባንድ መልኩም ሆነ በሌላ፤ የዐማራው ትግል አልቆመም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ ክስተት ተፈጠረ። በወያኔ አገዛዝ ውስጥ ያደጉ ትንታግ የዐማራ ወጣቶች፤ የዐማራ ብሔርተኝነትን በማንገት፤ ቤተ ዐማራ ብለው ብቅ አሉ። እኒህ ወጣቶች፤ አዲስ ፈር ቀደው፣ ወጣቱን በራሱ እንዲተማመን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። የኛው አባዜ አልለቃቸው ብሎ፤ ባንድነት እንደጀመሩት መቀጠል አቅቷቸው፤ እነሱም በመከፋፈል ተዳከሙ። የጀመሩት የዐማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ግን አልበረደም።

እንግዲህ በዚህ ሁሉ አልፈን ነው እዚህ የደረስነው።
እዚህ አሁን ያለንበትን ሁኔታ በሚቀጥለው በክፍል ፪ አቀርባለሁ።

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in እስከመቼ - ESKEMECHE. Bookmark the permalink.

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s