ኢትዮጵያ፤ ሙስናና በእምቢተኝነት ቅሬታ የሚያሰሙት ንብረት ማቃጠላቸው።

 ኢትዮጵያ፤ ሙስናና በእምቢተኝነት ቅሬታ የሚያሰሙት ንብረት ማቃጠላቸው። ድርጊቱን እናውግዝ ወይስን ይበል እንበል? ተጠያቂው ማነው? በፕሮፌሰር ሰዒድ ሃሰን፣ መሪ ስቴት ዪኒቨርሲቲ፤
( ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ አንዱዓለም ተፈራ እንደተረጎመው )

ቅዳሜ፣ የካቲት ፭ ቀን፣ ፳ ፻ ፰ ዓመተ ምህረት 

(ይህን ጽሑፍ ወደ አማርኛ እንድተረጉመው የገፋፋኝ፤ ይዘቱ በጣም ጠቃሚና አስተማሪ መሆኑ ነው። እናም እርስዎ፤ አንባቢው፤ ቀድተው በርስዎ ኮምፒተር በማስቀመጥ፤ ጊዜ ወስደው ቢያጠኑት መልካም ነው። እንደ ታሪክ የሚያነቡት ሳይሆን፤ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት፤ በአዕምሮው ዘንድ እንዲቀረጽ፤ ደጋግመው እንዲያነቡት ሃሳብ አቀርብልዎታለሁ። ጽሐፊው እንዳስገነዘቡት፤ ተጭእባጩን ሁኔታ በደንብ መረዳት፤ ሊከተል የሚችለውን ለመገመትና፤ እንዲከተል የምንፈልገው እንዲመጣ፤ እቅድ እንድናደርግ ይረዳለን። መልካም ንባብ። አንዱዓለም ተፈራ )

መግቢያ

ትርጉም ከማይሠጠው በእምቢተኝነት ቅሬታቸውን ለማሰማት በተነሳሱት ላይ የገዥው ፓርቲ ከፈጸማቸው ግድያዎች በተጨማሪ፤ አሁን በቅርብ የወጡት ቁንፅል የቪዲዮ ቅንብሮችና የዜና ዘገባዎች፤ እኒሁ በኦሮሚያ አካባቢ በእምቢታ ቅሬታቸውን ለማሰማት የተነሱት፤ ንብረትና ተቋሞችን ወደ ማጥፋት/ማቃጠል እንዳመሩ ያመለክታል። በዚህ ቀውስ ዙሪያ፤ በውጪ ሀገራትና በሀገር ውስጥ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መካከል፤ የጎደራ ውይይት በመካሄድ ላይ ነው። በውጪ ሀገር በሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን መካከል የሚገኙ ጥቂቶቹ፤ የማቃጠሉን/ማውደሙን ተግባር፤ በገዥው ፓርቲ ከሚፈጸሙት ጽንፍ የለሽ አረመኔያዊ ምግባርና ሥር ከሰደደው ሙስናቸው ጋር (በዚህ ረገድ በትክክል) ያዛምዱታል። ለኒህ በውጪ ላሉት ኢትዮጵያዊያን፤ ተግባሩን ይበል ለማለታቸው መሠረት የሚመስለው፤ አያሌዎቹ የወደሙት ንብረቶች፤ ባለቤቶቻቸው በሥልጣናቸው የባለጉ ልሂቆችና የውጪ ሀገር ኩባንያዎች መሆናቸው ነው። የኒህ ንብረቶችና ሕንፃዎች ባለቤቶች፤ የዘሩትን ነው እያጨዱ ያሉ በማለት አቋማቸውን ያቀርባሉ። ይሄን ግንዛቤ የሚያስተጋቡ ወገኖች፤ በእምቢተኝነት ቅሬታን ለማሰማት መነሳሳት፤ ለለከት የለሽ ምዝበራና ግድ ብሎ የመጣ አደገኛ ክፋት፤ ማሻሪያ ነው ብለው ይወስዱታል። ሌሎች፤ በተለይም ራሳቸውን የሰላማዊ ትግሉ ዘበኛ ብለው የሚቆጥሩ፤ በእምቢተኝነት ቅሬታቸውን በማሰማት የተሳተፉትንና ዝግጅቱን ያቀናበሩትን የሚያካትት ክፍል፤ የንብረት ማቃጠሉንና ማውደሙን በመቃወም ይከራከራሉ። የታየው ውድመትና ቃጠሎ፤ የሰላማዊ ትግሉና በሰላማዊ ታጋዮች ላይ የገዥው ፓርቲ እያደረሰ ላለው አጥር ዘለል አረመኔያዊ ተግባር የተከተለውን አጸፋ በማይወዱ ተንኮለኛ ጠምጣሚዎች፤ የተከናወነ ነው ይላሉ። ውድመቱና ቃጠሎው ቁጥራቸው በዛ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን፤ አወዛጋቢና የከረረ አጣብቂኝ ውስጥ የከተታቸው ይመስላል። ምርጫ የለሽ አረንቋ ውስጥ የገቡ በሚመስል ሁኔታ ተጠምደዋል – (ማለትም ጥፋቱን ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም በማይችሉበት ወጥመድ ውስጥ መገኘታቸው)።

እንደ የሰላማዊ እምቢተኝነት ዘበኝነቴ አግባብ ደግሞ፤ የተስተዋለውን ቃጠሎና ውድመት ይበል አልልም። ከምኞታችን በተጻራሪ ግን፤ በጣም የከፋ ቃጠሎና ውድመት ተግባራዊ የመሆን ችሎታ አይቀሬ ሀቁን፤ አውቃለሁ፤ አሳስቦኛልም። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ይህ ቀውስ እንደሚከተል ቀደም አድርጌ፤ ተገንዝቤ ነበር። እናም፤ ከጓደኞቼ ከነፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ፣ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደና ፕሮፌሰር ብርሃኑ መንግሥቱ ጋር በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን ሙስና ከንካኝ ባህሪ ባነሳንባቸው ወቅቶች ሁሉ፤ የዚህ መከሰት ችሎታ እንዳለ ጠቁሜያለሁ። በኢትዮጵያ ያለውን የሙስና ክፋትና ክብደት ስንወያይ፤ ሚዛኑ ይኼ ነው በማይባል ደረጃ ሊከተል የሚችለውን ጥልቀቱ የማይደረስበት ጥፋት በማሰብ፤ ልክ ጭንቅላቶቻችን የተውገረገሩ፣ ድምፆቻችን የተሽመደመዱ መሰሉ። ለምንድን ነው ኢትዮጵያዊያን በመንግሥት የተደገፉ መዋዕለ ተቋማትና ንብረቶች፤ የነሱ ያልሆኑና በተቃራኒው “የውጭ” ዕሴቶችና አልፎ ተርፎም የመበዝበዣና የመጨቆኛ መሳሪያዎች አድርገው የሚወስዷቸው?

እንግዲህ፤ ለምን የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ (ውቀመን) ብልጽግናን እንደሚያስከትል በእምቢተኝነት ቅሬታቸውን ለማሰማት የተነሳሱት ሊረዱት እንዳልቻሉ፣ ነገር ግን በግልባጩ እነሱ ከዚያ አልፎ “የሀገር በቀል” (ማለትም በፖለቲካ ፓርቲና በልሂቃን ባለቤትነት የተያዙት) “መዋዕለ ንዋይ” እንኳ የማይጨበጥ/የውጭ ባለቤትነት ያለው ንብረት ብለው መወሰዳቸው፣ ለምን የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ (ውቀመን) የስርቆት ማንቆለጳጰሻ ቃል እና የከፋ በዝባዥና ለመጥፎ ምግባር አባሪ በር ከፋች ተደርጎ እንደተወሰደ . . . ወዘተ. እናም እነሱ እኒህን ሁሉ ለማውደም ለምን እንዳቀኑ መረዳት ከፈለጉ፣ ንባብዎን እንዲቀጥሉ አበረታታዎታለሁ። በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን ሙስና ሁለተናዊ ባህሪ፣ የሚያስከትለውን ጉዳት፣ እንዴት የሀገሪቱን ተቋማዊ መስተሳሰሮች ተመልሶ በማይጠገን ሁኔታ እየጎዳ እንደነበርና አሁንም እንደቀጠለ መረዳት  የሚፈልጉ ከሆነ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ይህን ተግባር ለመዋጋት ዕቅድ ለማውጣት ማሰብ በዕውነት የምትፈልጉ ከሆነና ልክ የለሽ የማጥፋት አደጋውን ለማዘግየት በዕውነት የምትሹ ከሆነ፤ እባክዎን ለማብራራት ይፍቀዱልኝ።

ይህ ሐተታ የተሰናዳው፤ እርስዎ (አንባቢው) በኢትዮጵያ የነገሰውን ሙስና አልገታ ባይ ባህሪይ ተረድተው፤ ከዚያ በኋላ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ “መፍትሔዎችን” እንዲያስቡባቸው ለመማጸን ነው። ይህ እንዲሆን የተደረገበት ምክንያት፤ ዕቅዶችን መቀየስና “መፍትሔዎችን” መሻት፤ በታሰበበት ሀገር፤ እዚህ ላይ ኢትዮጵያ፤ የሚገኘውን ሙስና ዓይነትና ምንነት በደንብ አድርጎ መረዳት ስለሚጠይቅ ነው።

የገዥዎች ንጥቂያ፤ የታላቅ ሙስና ቅርጽ የያዘው የችግሩ መሠረታዊ መንስዔነቱ

ከዚህ በፊት በተለያዩ ወቅቶች እንዳሳየሁት፤ በኢትዮጵያ ነግሦ እየተገነዘብን ያለነው፤ የገዥዎች ንጥቂያ ተብሎ የሚታወቅ፤ ከሙስናዎች ሁሉ በጣም ሰርሳሪና የማይገታ ዓይነቱ ነው። የዚህ ዓይነቱ ሙስና፤ በሙስና ስነ-ጽሑፍ ውስጥ የአስተዳደር (መዋቅራዊ ውጣ ውረድ – ቢሮክራሲያዊ) ሙስና ከሚባለው ተለይቶ መታወቅ አለበት። የገዥዎች ንጥቂያ፤ በተለምዶ ሁኔታ፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም ሀገሮች፤ ድኅረ-ኮምኒስት (የሽግግር) ሀገሮችን በመተው፤ የተመዘገበውና የተስተዋለበት ዓይነት ሙስና ነው። አስተዳዳራዊ (መዋቅራዊ ውጣ ውረድ) ሙስና በተለይ፤ ጉቦ ከፋዩ፤ በሀገሩ ያሉ ሕጎችን፣ ደንቦችን፣ እና መተዳደሪያዎችን በመለጠጥ፤ ለራሱ ሚዛናቸው እንዲደፋ በማድረግ ማካሄድ ነው። ባጠቃላይ የአስተዳደር (መዋቅራዊ ውጣ ውረድ) ሙስና፤ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች መዋቅራዊ ውጣ ውረድ ተግባራዊ ሂደቱ ላይ የሚፈጸም ሲሆን፤ የፖለቲካ ( ታላቁ ) ሙስናው የሚካሄደው፤ ከፍተኛውን መንግሥታዊ ሥልጣን በያዙት ደረጃ ነው። የተለያዩ የአስተዳደራዊ ሙስና ምሳሌዎች ሊሆኑ ከሚችሉት መካከል ለመጥቀስ፤ የተወሰነ ብያኔን እንዳይተገበር የማደናቀፍ፣ መዝገቦችን የማጥፋት፣ ወይንም መዝገቦችን አስመስሎ የመቅዳት ተግባር ተባባሪ መሆን፤ በከፍተኛ ደረጃ ሕጋዊ የሆኑ (እንዲተገበሩ የተመሩትን) የማስተጓጎል ወይንም/እናም እንዲዘገዩ የማድረግ፣ የተመደቡበትን የመሥሪያ ቤት የሥራ ሰዓት ለግል ጥቅም ማከናወኛ ሰዓት የማድረግ፣ ያልያዙትን ሥልጣን እንደያዙ በማስመሰል የመቅረብ፣ ጣልቃ የመግባትና ለዘመድ ጥቅምን የማስገኘት (የሥልጣን ብልግና)፣ የሕዝብን ንብረት ያላግባብ የመጠቀም፣ ከሥራ ምድብ ቦታ ያለመገኘት፣ ለልማት ከሚውሉ የአገልግሎት ዝግጅቶች መላሾ መውሰድ ላይ የመጠመድ፣ የሕግ ስነ-ሥርዓቱ ላይ ድጋፍ ለመሥጠት ገንዘብ የመቀበል፣ የሕዝብን ንብረት ወደ ግል መጠቀሚያነት የመምራት፣ ሕገ-ወጥ የሆኑ ተግባራትን እንዳላዩ ዓይቶ የማለፍ፣ ተራ ሌብነትና ንብረት የማባከን፣ ከዋጋ በላይ የመጫን፣ ሕልውና የሌላቸውን የሥራ ዝግጅቶች የማካሄድ፣ ቀረጥ የመሰብሰብ፣ የቀረጥ ፍተሻ ማወናበጃ የማድረግ፣ …ወዘተ።

ምንም እንኳ ከሥሩ መንግሎ ማጥፋት ባይቻልም፤ ደግነቱ፤ መንግሥታት የአስተዳደር (መዋቅራዊ ውጣ ውረድ) ሙስና የሚያደርሰውን ጉዳት፤ መንግሥታዊ ተግባራትን በታወቀ ይፋ መዋቅራዊ ሂደት፣ በተጠያቂነት እና በግልጽነት ሊያሳንሱት ይችላሉ። ይህ የሚሆነው፤ ለምሳሌ የሚከተሉትን በማድረግ፤

ሀ)  ከመንግሥታዊ መዋቅሩ ውጪ ሥልጣን ያለው አካል በማቋቋም
ለ)  ነፃ የምርጫ ቦርዶችን በማቋቋምና ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመፍቀድና በማሳደግ
ሐ) ነፃ የዜና ሥርጭት ተቋማትን በመጠቀም፣ ይህ ደግሞ በተራው ተቆርቋሪ ቡድኖችን፣ የኅብረተሰቡ የትብብር ማኅበሮችን፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንና፣ … ወዘተ እየረዳ
መ) የፓርላማውን የምርመራ ሥልጣን በመጠቀም
ሠ)  ነፃ የሆኑ ፀረ-ሙስና ቦርዶችን እና የተልዕኮ አካሎችን መፍጠር
ረ)  ነፃ የሆነውን የፍትህ ሥርዓት በመጠቀም

ይሁንና፤ በኢትዮጵያ የተገነዘብነው የገዥዎች ነጠቃ በመባል የሚታወቀው፣ በሽግግር ባሉ (በፊት ሶሺያሊስት የነበሩ) ሀገሮች የተከሰተው ነው። ይህ፤ ጉልበተኛ ቡድኖች፤ ተቋሞችና መመሪያዎች፣ ሕጎችና ማዘዣዎች በሚያመቻቸው መንገድ እንዲገነቡላቸው ተገቢ ያልሆነና የተበላሽ ተጽዕኗቸውን በመጫን፤ ለሕዝቡ በጎ ተግባር ከማዋል ይልቅ፤ ለራሳቸው ጥቅም የሚያስጠብቁበት ክስተት ነው። የገዥዎች ነጠቃ በተለያየ መንገድ ሊነሳና ሊተገበር ይችላል፤ ማለትም ጉልበተኛ ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይንም የጥቅም ትስስር ያላቸው ስብስቦች፤ ባንድ በኩል ሚስጢራዊ የሆኑ መንገዶችን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሕጋዊና ተገቢ መዋቅሮችን በመጠቀም፤ ተፎካካሪዎቻቸው በኃላፊነት የተቀመጡትን ባለሥልጣኖችን እንዳይገናኙና የአገልግሎት በሮች እንዳይከፈቱላቸው በማገድ የሚከሰት ነው። የተለዩ ቡድኖችና የመንግሥት ባለሥልጣናት፤ “የመንግሥት ባለሥልጣናትን የፖለቲካ ኃላፊነትና የግል የንግድ ፍላጎት የደበዘዘ መለያያ አጥር” በመለጠጥ አሸዋረው፤ ከኅብረተሰቡ ይልቅ ለራሳቸው የጋራ ጥቅም በማዋላቸው ሊነሳ ይችላል (ከሄልማን፤ 1998፡3  የተወሰደ አስተሳሰብ)። እንደ የብሮድማን እና ሬካናቲኒ (2001) አስተሳሰብ)፤ የገዥዎች ነጠቃ፤ ለተለዩ ቡድኖችና የንግድ ጥቅሞች የሚረዱ መመሪያዎችና ደንቦች ማስፈጸሚያ በመቀየስ፤ ጠቅላላ የፖለቲካ ሂደቱን ድምጥማጡን የሚያጠፋ ጎጂ ሙስና ነው።

የገዥዎች ንጥቂያ ከሀገር ሀገር ሊለያይ ይችላል። በአንዳንድ ሀገሮች፤ የገዥዎች ንጥቂያ፤ በብልግና የላሸቀ ምግባር ተብሎ በሚታወቀው ስር የሰደደ መሰሪ ካፒታሊስታዊ ግዛት፤ አንድ ገጹ ሆኖ ሊታይ ይችላል። በዚህ ክት፤ ጉልበተኛ ቡድኖች፣ ግለሰቦች እና በጣት የሚቆጠሩ ገዥዎች ባሉበት ሀገር፤ እኒሁ ገዥዎች አዳዲስ መንግሥታዊ መመሪያዎች ሲወጡ፤ ሆን ብለው በመጠምዘዝና ቅርጹን በማሳመር “የጨዋታ ሕጎችን” ለራሳቸው እንዲያጋድል የሚያደርጉበት ነው። ይህን፤ በኃላፊነት የተቀመጡ ባለሥልጣናት፤ የተደራጁ የንግድ ቡድኖች፣ ጥቂቶቹ ገዥዎች ወይንም ጉልበተኛ ግለሰቦች እንዲጠቀሙ፤ ድንጋጌዎችን ሲያውጁ እና/ወይም በሚወጡ ሕጎች ላይ ድምጻቸውን ሲሠጡ መገንዘብ ይቻላል። በተጨማሪ ደግሞ ግዙፍ የሆነ “የምጣኔ ሀብት ሥምሪትና የፖለቲካ ሥልጣን በአንድነት በአንድ ክፍል መያዝ እና ጥቅም አሳዳጆች በሀገሪቱ የግዛት ልጓምና በሀገሪቱ ሀብት የበላይነቱን መጨበጥ በሚከተለው የሀብት አለመመጣጠን ይታያል። የገዥዎች ንጥቂያ ክስተት፤ በኃይለኛ መሪዎች (ማለትም የአካባቢ ወይንም የሀገር አቀፍ የሆኑ)፣ ሚኒስትሮች፣ ሕግ መወሰኛና የፍትኅ ሚኒስትር ሥራ አስኪያጆች፣ የመንግሥታዊ ተቋማትና/ትልልቅ ድርጅቶች፣ የገዥው ፓርቲ ባለቤትነት ያለባቸው ኩባንያዎች ሥራ አስኪያጆች በሚያደርጉት ድብቅ ሻጥር ሊታይ ይችላል። በአንዳንድ በኩል የገዥዎች ንጥቂያ፤ የሕጋዊና የፖለቲካ ተቋማት መዳከም ውጤት ነው። በሌሎች አንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ፤ ነጣቂዎቹ፤ ለንጥቂያቸውና ለብዝበዛቸው እንዲያመችላቸው የሀገሪቱን ሕጋዊና ፖለቲካዊ ተቋማት ሆን ብለው ያዳክሟቸዋል። በተጨማሪም፤ በምጣኔ ሀብት ሥምሪቱ እደሳ መክሸፍ እና ጉልበተኛ ግለሰቦች ወይንም የተደራጁ ቡድኖች፤ ከ“መንግሥት ይዞታ ወደ ግለሰብ ባለቤትነት” የሚደረገውን የሽግግር ሂደት በመጠቀም፤ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለውን የሕዝብ ንብረት፤ በመመንተፋቸው ይከሰታል። በአንዳንድ ሁኔታዎች የገዥዎች ንጥቂያ፤ የተደራጁ ቡድኖች፤ እነሱ የፈለጉትን ያደርጉ ዘንድ፤ ግዛታዊ መዋቅሩን፣ ፍርድ ቤቶችን፣ መረጃ ክፍሉን፣ ጦር ሰራዊቱን፣ ሕዝብ መገናኛ መስመሮችን ጭምር፤ ተጽዕኖ ለማድረግ በሚስጥር፤ በግዛቱ ውስጥ የድብቅ ግዛት (“ጎድናዊ ግዛት) ሲፈጥሩ ሊታይ ይችላል። የገዥዎች ንጥቂያ በነገሰባቸው አንዳንድ ሀገሮች፤ የመንግሥት በሆነውና የግለሰብ በሆነው፣ ይፋ በሆነውና ይፋ ባልሆነው፤ የግዛት ክፍልና የገበያ ክፍል በሆነው መካከል ያለው የመለያያ መስመር አካቶ ድብዝዟል። ከላይ በተሠጠው ገለጻ እንደምትረዱት፤ በገዥዎች ንጥቂያ ሥር፤ የአንድ ሀገር ሕጎች፣ ደንቦች፣ ሕጋዊነቶች እናም በመጨረሻም አጠቃሎ ተቋማቱ እንዳሉ የሙስናው አካል ናቸው። እኒህን የመሰሉ የሙስና ገጾች፤ ቀደም ብሎ ከላይ ከተገለጸው አስተዳደራዊ/መዋቅራዊ ውጣ ውረድ ሙስና ፍጹም የተለዩ ናቸው።

በአንዳንድ ኢትዮጵያን በመሰሉ ሀገሮች፤ (ሃሰን፤ 2013) (በተወሰነ ደረጃ ደግሞ፤ እንደ ዩጋንዳ እና ሩዋንዳ የመሳሰሉ ሀገሮች) ጠቅላላ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብት ሥምሪቱ፣ ሕጋዊና ወታደራዊ መዋቅሮች በሙሉ እንዳሉ በጉልበተኛ የተቧደኑ ክፍሎች ወይንም በትውልድ ሐረግ የተሰባሰቡ ቡድኖች እጅ ገብቷል። ይኼን የመሰለው ሙስና፤ አደገኛና መርዛማ ነው። ምክንያቱም፤ እኒሁ የተዋቀሩ ቡድኖች፤ ከታላላቅ ድርጅቶች ባለቤቶች እና/ወይም በጣት የሚቆጠሩ ገዥዎች ጋር በመተባበር፤ የሁሉም ተቋማትን ወሳኝ የሆነ የደም ሥር (የምጣኔ ሀብት ሥምሪት፣ የኅብረተሰቡ ትስስር፣ የጦር ሰራዊት) እየተቆጣጠሩ በመገኘታቸው ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎች፤ እንደ ሩስያ በ1990ዎቹ እና በአንዳንድ የአፍሪቃ ሀገሮች፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ እንደታየው፤ የንጥቂያው ተግባራዊነት፤ በጣም የተደራጀና ዘሎ ገባ ገፋፊ ነው። ነጣቂዎቹ፤ አመጽና ማስፈራራት፤ ከሌሎች መገልገያ መሣሪያዎቻቸው መካከል እንደተጠቀሙ ታውቀዋል። የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት ሥምሪት ሥርዓት ወሳኝ የደም ሥር በበላይነት ለመቆጣጠር፤ የራሳቸውን ሁሉን ከላይ አንቆ ያዥ የንግድ ተቋም (ሞኖፖሊ/ ኦሊጋርኪ) እና ወሳኝ የተጣመረ የንግድ ቡድን (ካርቴል) በማቋቋም፤ እግረ መንገዳቸውን በሥራ ላይ እየዋለ ያለውን የገበያ ማሻሻያ ሂደት ባንድ በኩል በማሰናከል ታውቀዋል። ባጭሩ፤ ይኼን የመሰለው ሙስና፤ የአዲሱ ዘመናችን የተደራጀ የወንጀል ምግባር ይመስላል።

የያንዳንዱ ሀገር ልዩ የሆነ የሙስና ባህርያት

የነጣቂዎች ብልሹ ተግባራት በሁሉም ዘንድ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ናቸው። ነገር ግን፤ ከሀገር ሀገር ወይም የንጥቂያው አጀማመር እና የነጣቂዎች ዓይነት ሊለያይ ይችላል። በድኅረ-ኮምኒስት ሀገሮች፤ ሄልማን እና ተባባሪዎቹ እንዳሉት፤ (2003) በየግል “ነጣቂ ድርጅቶች (ማለትም ለባለሥልጣናት የጨዋታውን ሕግ እንዲመቻችለት የግል ክፍያ የሚያካሂድ) እና በተደማጭ ድርጅቶች (ማለትም ለባለሥልጣናት ክፍያ ሳይቸገር፤ በሕጎቹ ላይ ተደማጭነት ያላቸው ድርጅቶች)” መካከል ልዩነት ያደርጋሉ። በጥቅሉ ነጣቂዎቹ፤ ስርዎ ስሙ የተሠጠው (ኖሜንክላቱራ)፤ በቀድሞው የሶቪየት ሥርዓትና የምሥራቅ አውሮፓ ፈርጅ ሀገሮች ሥር፤ መንግሥት ይቆጣጠራቸው በነበሩት የምርትና የንግድ ድርጅቶች፤ የቀድሞ ሥራ አስኪያጆችና በመዋቅሩ ተሰግስገው የነበሩ ኃላፊዎች ቡድን፣ (ቁጥራቸው በግምት ከሕዝቡ ከመቶ አንድ ነጥብ አምስት የሚሆኑ) ናቸው። እኒህ “ከሌሎች በተለየ የተከበሩ ባለመብት ሆነው፤ ፍጹማዊ የሥልጣን ልጓሙን ጨብጠው፤ እርስ በርሳቸው የማያልቅ የፖለቲካ ቁማር በመጫወት ተጠምደው” ነበር። በተጨማሪም “የተሠጣቸውን የኃላፊነት ቦታ በመጠቀም፤ የንግድ ተቋሞችን ነጣቂ” ባለሥልጣናት ሊሆኑ ይችላሉ። አለያም የተሰባሰቡ የፓርላማ አባላት፣ ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ ሚኒስትሮች፣ ዳኞች በመተባበር ሊሆኑ ይችላሉ (የራሱ የገዥው ፓርቲ መሪዎች፣ ከሳሽ፣ ዳኛና ጠበቃ በመሆን)። የገዥዎች ንጥቂያ በሁሉም ቦታ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ሆኖ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ውስጥ፤ በድኅረ-ኮምኒስት ካሉት ሀገሮች በአንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮች ይለያያሉ።

አንድ ሲሉ፤ እኒህ የኢትዮጵያ ነጣቂዎች፤ እንደ ሩሲያዊያን እና የምሥራቅ አውሮፓ አጓዳኞቻቸው ስርዎ ስሙ በተሠጠው (ኖሜንክላቱራ)(የኮምኒስት ፓርቲው ከፍተኛ ባለሥልጣናት) አባል አይደሉም። ከኒህ ከኛዎቹ፤ ብዙው አባሎቻቸው ሥልጣን ለመውሰድና ራሳቸውን ለማበልጸግ ብጥስጣሽ ልብሶቻቸውን ጣጥፈው ለብሰው ከበርሃ የመጡ ሽምቅ ተዋጊዎች ነበሩና።

ሁለተኛ ደግሞ፤ እንደ ኢትዮጵያ በመሰሉ ሀገሮች፤ የገዥዎች ንጥቂያ ክስተት፤ በተፈጥሮው በጣም ውስን ነው (ባላባታዊ አስተዳደር ቀመስ እና በጎሳ ትስስር የተያዘ)። አለመታደል ሆኖ፤ በትስስር ተቀፍድዶ የተያዘው የኢትዮጵያ ሙስና፤ ለቅናትና መቻቻል አመቺ ይሆናል። ሙስናው የረዳቸው የአንድ ወገን ሊሂቃን ሀብታቸውን ሲያበዙ፤ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍል ያሉት ቅናት ይይዛቸዋል። በተገላቢጦሹ፤ በገዥው ቡድን ወገኖች በኩል፤ ይኼን መርዛማ ተግባር ችላ ብሎ የማለፉ አቀቤታ ሊከሰት ይችላል። ይህ ዝንባሌ የኬንያን ኅብረተሰብ ሠርጾ መግባቱ ታውቋል (የሚሸላ ሮንግን,የ 2009. “አሁን መብላቱ የኛ ተራ ነው።” የሚለውን መጽሐፍ ይመልከቱ) የመጨረሻው ውጤት፤ እያንዳንዱ (በአብዛኛው ኃይለኛ) የጎሳ ቡድን ተራቸውን እየተቀባበሉ ሌሎችን በመጠቅጠቅ ራሳቸውን በሀብት የሚያደልቡበት እሾካማ ተናካሽ የሙስና እሽክርክሪት ነው። በነዚህ ሀገሮች (በተለይም ኢትዮጵያ) አንድ ሽንጡን ገትሮ የሚያደባ ጠንካራ መዘዝ እንዳለ ይታዘቧል – ይሄውም ለሙስና የደንበኝነት እና የዘመናዊ – ወራሽነት ባህሪ ነው።

በሶስተኛ ደረጃ፤ የቀድሞ አንቆ ያዥ ገዥዎች ከፖለቲካ ሥልጣናቸው ከተወገዱበት ከአንዳንድ የድኅረ-ኮምኒስት ሀገሮች፤ ለምሳሌ እንደ ምሥራቅ አውሮፓ በተጻራሪነት መልኩ፤ የኢትዮጵያ ነጣቂዎች የፖለቲካውንም የምጣኔ ሀብት ሥርጭቱንም ጠቅልለው ይዘውታል። የሩስያ እፍኝ ገዥ ባለጸጎች፤ ሀብት ያግበሰበሱት፤ ከዚያም ከዚህም በማምታታት እና ሁሉንም ዓይነት የሀብት ማጠራቀም ወንጀሎችን በማካሄድ፤ የሀገራቸውን ንብረት በጣም በርካሽ ዋጋ በማግበስበስ ጭምር ነበር (የኢትዮጵያ አጓዳኞቻቸውም ይሄኑ ተግብረዋል)። አቶ ፑቲን ታዲያ የአንዳንዶቹን የሥልጣን ጥመኝነት አልወደደውም ነበርና የመንጥር ዘመቻውን አካሄደና አንዳንዶቹን ወደ ዘብጥያ አወረደ። አንዳንዶቹን ደግሞ ለስደት ዳረጋቸው። ይሄን ሲያደርግ በጎን ንብረታቸውን ጋፍፎ ባዶ አስቀርቶ ነው (ለሱ የፖለቲካ ተቀናቃኝ ለመሆን ያልቃጣቸውን ትቶ)። የምሥራቅና የመካከለኛው አውሮፓ ነጣቂዎች፤ በከፊል እነዚህ ሀገሮች የአውሮፓ ኅብረትን መቀላቀል ስለፈለጉና ስለጣሩ፤ እናም የአውሮፓው ኅብረት ያስቀመጠውን ቅድመ-ሁኔታ ማሟላት ስለነበረባቸው፤ ኅብረቱም የገዥዎችን ነጣቃ በመታገልና በማጥፋት ስለረዳቸው፤ ቀስ በቀስ የፖለቲካ ተደማጭነታቸውን አጡ።

በአራተኛ ደረጃ፤ ኢትዮጵያን በመሰሉ ሀገሮች፤ የገዥዎች ነጠቃ አቻ የለውም፤ ማለትም በሌሎች ሀገሮች ከሚገኘው በተለየ መንገድ ጠንካራ ነው። ይህም፤ ሁሉን የፖለቲካ ሂደቱን ማከናወኛ መስሪያ ቤቶችና የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት ሥርጭት ቁንጮ ያጠቃለለ መሆኑ ነው። እዚህ ላይ ንጥቂያው የጦር ሠራዊቱን፣ የጸጥታ ክፍሉን፣ የውጭ ጉዳይ መመሪያውን፣ እና የፍትኅ ሥርዓቱን አልፎ ተርፎም የሕዝብ ግንኙነት መስመሮችን በሙሉ ያካትታል። በኢትዮጵያ፤ የጉልበተኛ ዘራፊዎቹ የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት ሥርጭት ቁንጮ አንቀው መያዛቸው፣ የሀብት ምንጩን ያላግባብ መውሰድ፣ በዘረጉት የፖለቲካ ሥልጣን ትስስር ተጠቅመው ሀብት ማካበት አልጠግብ ባይነት፤ በደሃና በሀብታሞች መካከል ያለውን የአጥር ልዩነት ከመቼውም በላይ እያሰፋ፤ አሁንም ያለምንም ገደብ እየጎደራ ነው። የልሂቃኑ ዝርፊያ እንዲያው በደፈናው፤ ራሱን መንግሥታዊ ሥርዓቱን በወንጀል የተጨማለቀ ስላደረገው፤ አልፎ አልፎ የተደራጀ ወንጀለኛ ቡድን (ማፊያ) የሚያከናውናቸው ድርጊቶች ብቅ ይላሉ። የገዥዎች ንጥቂያ በኢትዮጵያ ሌላው የተለየ መገለጫው፤ በጣም የከፋ የአንድ ጎሳ ወገንተኝነት ተፈጥሮው ነው። በዚህም የተነሳ፤ የመንግሥት የሚባለውና የግል የሚባለው፤ መለያ መስመራቸው ደብዝዟል፤ ፓርቲው ከመንግሥቱ ተለይቶ የማይታይ አካል ሆኗል። ለዚህም ነው ብዙዎቹ፤ የኢትዮጵያን የሙስና ቅንብር፤ በጣም የጋለ ዝርፊያ ነው ወደ ማለት የተፈታተኑት። እኒሁ ወገኖች፤ በዚህ የተነሳ፤ ይህ የተነጠቀ የምጣኔ ሀብት ሥምሪት በክፉ አዟሪት ውስጥ በመጠመዱ፤ ማንኛውም የአስተዳደሩን ሂደት ለማሻሻል የተወጠነ መመሪያ፤ ከወዲሁ ለውድቀት ተዳርጓል ይላሉ። ከመንግሥት አካል ውጪ ሆነው በሚንቀሳቀሱት እና በመንግሥቱ ውስጥ ባሉ ጉልበተኛ ቡድኖች መካከል የማያቋርጥ ፍጥጫና ግጭትን ያያሉ።

በኢትዮጵያ ምን ተፈጠረ?

በኢትዮጵያ የተከሰተው ከሀገሪቱ የንግድ ማከናወኛ ደንብ በተጻራሪ፤ የባዶ ቀፎ ኩባንያዎች መቋቋም ነው። እነዚህ ባዶ ቀፎ ኩባንያዎች የተቋቋሙት፤ ከሁለት እስከ አምስት የሚሆኑ “የአክሲዮኑ ተቋሯጮች”፤ እኒህ “የአክሲዮኑ ተቋሯጮች” የፖርቲ መሪዎች ሆነው፤ በመሰየም ነው። ገነት መርሻ እንደገለጹት፤ የፖለቲካ ፓርቲ የሆኑ የንግድ ክፍሎች በሀገሪቱ የንግድ ሥምሪት ሂደት ጎን ለጎን መሰለፍ፤ ለ ሀ) “የጥሬ ገንዘብ ተጋፎ ወደ ውጪ በመንጎዱ የሀገሪቱ የብልጽግና ምንጭ ሊሆን የሚችለው መንጠፉ፤ ለ) የፍቃድ አሠጣጡን እና ማምታታቱ ሐ) የመንገድ ሥራን፣ የሕንፃዎች መቆምን፣ እና ሌሎች የእነፃ ተቋራጭነትን በሚመለከት ለሚወጡ የመንግሥት ጨረታዎች፤ የውስጥ መረጃን በሚመለከት የቅድሚያ ጥቆማን ማግኘት፤ መ) የተወዳዳሪዎች እጥረት እና የመጨረሻው ደግሞ ሠ) የንግድ ሥምሪቱንና ባለሙያተኞችን በሰላ የአድልዖ ዘዴ የማግለል መንገድ ከፍቷል።

የታዘብነው፤ “የመንግሥት ንብረት የሆኑ የንግድ ድርጅቶችን ለግለሰቦች ለመሸጥ በተቋቋሙ አስፈጻሚ ክፍሎች፤ አድልዖና በጥቅም የተቆራኙ ቡድኖች ፈጠራ ሲፋፋም ነው (ሚንጋ ነጋሽ)። የኢትዮጵያ ሕዝብ የታዘበው፤ የመንግሥት ንብረት የሆኑ የንግድ ድርጅቶችን፤ ለግለሰቦች ለመሸጥ የተደረገው ሂደት፤ በትክክል አለመካሄዱ ነበር ((የገነት መርሻን፤ 2010)፣ የያንግን (1998)የቬስታልን (2009)፣ እና የሚንጋ ነጋሽን (2010) ጥናቶችና ጽሑፎች ይመልከቱ)። ኢትዮጵያዊያን የታዘቡት፤ ፈጥርቀው በሚይዙ የፖለቲካ ፓርቲ ኩባንያዎች (“የችሮታ ተቋሞች”) እንደ የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ችሮታ – ትመማች (ኢፈርት – በእንግሊዝኛ፤ ትእምት – በትግርኛ ) እና በሥሩ በተጠቃለሉ ከመጠን በላይ የበዙ ኩባንያዎች፤ ከአጥናፍ አጥናፍ ተዘርግቶ የተዋቀረ የገዥዎች ንጥቂያ ነበር። የተረዳነው፤ የገዥው ሤረኛ ቡድን አባላት፤ የሽምቅ ተዋጊዎች በነበሩበት ወቅት የዘረፉትን የሀገር ሀብት ለመመለስ፤ እምቢተኝነታቸው ነው። የምናውቀው፤ “በፓርቲያቸውና  በመንግሥት የንግድ ድርጅቶች፤ ባንኮችን ጨምሮ፤” አጥር ዘለል የፓርቲ አባሎቻቸው “በከፍተኛ ደረጃ ባሉ ቦርዶች በበላይነት” መቀመጣቸውና፤ በአካባቢያቸው ላሉ የፓርቲ ኩባንያዎች፤ በቀላሉ የባንክ ብድር ማንዶልዶላቸው ነው። የሥራ ተቋራጭ ጨረታውን፤ “ሌሎች” የተባሉ ኢትዮጵያዊያንን በማግለል፤ ከፓርቲው ጋር ትስስር ላላቸው መሥጠቱና ውድድር ማምከኑ፤ ልክ በሕንጻ ግንባታ ውስጥ በጣም አይሎ እንዳለው፤ ወገንተኝነቱ፤ (የዓለም ባንክ ሙስናን በኢትዮጵያ ምርመራ፤ ምዕራፍ 6ን ይመልከቱ) ተቀጣጠለ። ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታትና አሁንም በመቀጠል፤ ዕለት ተዕለት እየታዘብን ያለነው፤ ለኒሁ ግዙፍ የተጠራቀሙ የንግድ ድርጅቶች ኅብረቶችና ካድሬዎቻቸው ለያዟቸውና የሚወዷቸው ኩባንያዎች ውለታ ማመቻቸቱ ነው። የዚህ ውጤት፤ የውድድር ሂደቱን ማምታታትና የውድድር የገበያ ሁኔታውን ባዶ ማስቀረት ሆኗል። የታዘብነው፤ ልክ በሶቪየት ኅብረት ጥላ ሥር እንደነበሩት ሀገሮች፤ የገንዘብ ነክ ጉዳይ በሙሉ፤ በተወሰነ ቡድን መያዙና በቁጥጥር ሥር መዋሉ ነው። በኢትዮጵያ እየታዘብን ያለነው፤ አዲስ የዜና ማሰራጨትን እና ፀረ-ሽብር በሚባሉ የይስሙላ ሕጎች ታንቆ መያዝን ነው። በኢትዮጵያ የተመከትነው፤ የአዳዲስ ሕጎች – ልክ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከውጪ ሀገሮች እርዳታ እንዳያገኙ የሚያግደው ሕግ ዓይነት፤ በዚያኑ ወቅት የገዥው ፓርቲ በሕጉ ሳይታሰር፤ ከውጪ በሚያገኘው እርዳታ ያለ ልክ በመጠቀም ላይ እያለ፤  – መረቀቃቸውና መታወጃቸው ነው። ያደገው፤ ጀሯችን ዳባ ይልበስ ያሉ ጉልበተኛ መሪዎች “አጉል ግትር፣ እብሪተኛና ከሀቁ የራቁ የዜሮ ድምር አስተሳሰብ ባህላቸው ነው። ኢትዮጵያዊያን የታዘቡት፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማያቋርጥ ሁኔታ ሲጨፈጨፉና ድራሻቸው ሲጠፋ፣ የሀገሪቱ ተቋማትን፤ ነፃ የኅብረተሰቡ ማህበራትን በመበጣጠስም ሆነ የትምህርቱን ጥራት በማላሸቅ፣ በየጊዜው ራሳቸው ያወጧቸውን ሕጎችን በመጣስ፤ … ወዘተ. ሲያዳክሟቸው ነው። እየተገነዘበ ያለው፤ የውጪ እርዳታ ሠጪ መንግሥታትን ለመሸወድ፤ (ድርጅቱ እራሱ በሙስና የተነከረ መሆኑ የሚታማው) የተኮላሸ የፀረ-ሙስና መርማሪ ኮሚሽን መቋቋሙና፤ ይኼንኑ ሙስናን ለመዋጋት የሚደረግ ጥረት፤ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት እስከመጠቀም ድረስ መጥለፋቸው ነው። ልክ እንደ ሩስያና ሌሎች ቦታዎች፤ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ፤ የሕግ አውጪውን፣ ሕግ አስፈጻሚውን፣ የፍትኅና ሁሉን የሕግ ማውጫና ማስከበሪያ መንግሥታዊ ክፍሎችን ነጥቆ ይዟል። እኒህ፤ ለዝርፊያ መቀራመት የተመራ (ለኪራይ ሰብሳቢነት)” ከሁሉም በላይ በጣም የከፋው ሙስና፤ የገዥዎች ንጥቂያ ሙሉ ገጸ-ባህሪ ማሳያ ምስሎች ናቸው።

እኒህ ጥቂቶቹ ናቸው፤

የተከተለው ውጤት፤

የገዥዎች ንጥቂያ (የማፊያን ተግባር ዓይነቱ) እና ወንጀለኛው ገዢ ቡድን፣ ከማይታመን እብሪትና ጭቆና ጋር ተዳብሎ፤ በሀገሪቱ ውስጥ የጠለቀ ጨለምተኝነትን፣ ሁሉም ለራሱ ብቻ የሚስገበገብበትና፣ ጥግ ጥጉን ይዞ ተከፋፍሎ የተፋጠጠበትን ሀቅ አስከትሏል። ይህም በአንድ ምሽት፤ በፈጠራ ችሎታቸውም ሆነ ይኼ ነው በሚባል ጥሩ ነገር የማይታወቁ የትናንት ቁምጣ ለባሽ የሽምቅ ተዋጊዎችና ደሃ ታክሲ ነጅዎች፤ በማይታሰብ ደረጃ የተለጠጡ ቱጃሮች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይህ፤ ያገሬው ትንንሽ ባለሀብቶች፤ የጥፋቱን አቦል የተቋደሱበት የንብረትን መጋየት አስከትሏል። ግብታዊ መነሳሳት ግብታዊ አይደለም – ማለትም፤ ያለ ምክንያት ከመሬት ተነስቶ የሚካሄድ አይደለም። ምክንያቶቹ፤ በገዥው ፓርቲ በኩል ያለው የሚያቅለሸልሸው ስግብግብነት፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ባለሀገር ነዋሪዎቹ፤ ለዘመናት ቀደምቶቻቸው ከኖሩበት ባድማቸው መፈናቀላቸውና፣ ይሄ ነው በማይባል ወይንም ያለምንም ማካካሻ፤ እኒሁ የተነጠቁ መሬቶች፤ የገዥው ፓርቲ ንብረት ለሆኑት ኩባንያዎች፣ ለገዥው ፓርቲ ልሂቃንና፣ ለውጪ ሀገር ሰዎች፤ ባለቤትነታቸው መዘዋወሩና መሠጠታቸው ነው። የግብታዊ መነሳሳቶች ምክንያቶች፤ ያለምንም ጥርጥር፤ የገዥው ክፍል መሪዎች ጭፍን ወገንተኝነትና በዚሁ ክፍል ልሂቃን በኩል የተደራጀ የቡድን ወንጀል መፈጸሙ ናቸው። ሙስና የጋለበበት የመሬት ልውውጡ፤ የሀገሪቱን የብልጽግና ምንጮች ባለቤትነት፤ ከተራው ሕዝብ ወደ በጣም ጥቂት ግለሰቦች እንዲዛወር አድርጓል። መሬታቸው በግዳጅ ተነጥቆ የተፈናቀሉትና የተጨቆኑት፤ ግፉ መጋቱ በቃን ያሉበት ሁኔታ ታየ። እንደ የምጣኔ ሀብት ሥምሪት ባለሙያነቴ፤ የገዥው ሤረኛ ቡድን ያልተገራ ቁንጠጣ (አስገድዶ ማፈናቀል፣) እብሪት፣ የማይረካ ስግብግብነት፣ አፍኖ ያዡ ሙስና ) የማያባራ የሚነቅዝ ቁርሾ ትቶ ማለፉ ይታየኛል። ለገዥው ያልተገራ ቁንጠጣና ለፓርቲው ልሂቃን ወንጀለኛ ተግባር ምስጋና ይግባውና፤ አሁን የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ፤ ለማጭበርበርና ለምዝበራ የጌጥ ስም ሆኖ ተወስዷል። በርግጥ፤ ሕዝብን ማዕከል የሚያደረጉና በትክክል ድጎማቸው የሚካሄዱ የከተማ ልማት ውጥኖች፤ ሁሉንም ባለጉዳዮች በአቸናፊነት የሚያስቀምጡ በሆኑ ነበር። መሬት ቀመስ ለሆነው ለከት አልባ ሙስና ምስጋና ይግባውና፤ የገዥው ሤረኛ ቡድን የገማ ተንኮል ሽረባ፤ የወደፊት ሕጋዊ የልማት ውጥኖችን የመካሄድ ዕድልን ሽርሽሮታል። ያለ ጥርጥር እኒህ ያልተገሩ የገዥው ሤረኛ ቡድን ቁንጠጣዎች፤ ለወደፊት ልማት ከፍተኛ ደንቃራ ይሆናሉ።

በሻጥር የገማውንና በዝርፊያ የተለወሰውን፤ ብዙ አለመረጋጋቶችን ያቀጣጠለውን የመሬት ነጠቃ ትንሽ ጨምሬ እንዳብራራ ይፍቀዱልኝ። ልክ እንደ ቻይናና ሰሜን ኮርያ፤ መሬት የኢትዮጵያ መንግሥት ንብረት ነው። ይህ በተራው፤ መሬትን ያለምንም ማካካሻ ለመንጠቅ ሩጫን፣ ባገኙበት ለማግበስበስና ለአድልዎ የተመቸ ሁኔታን ፈጠረ። ከሚሽጎደጎደው የማያልቅ የመሬት አዋጆች ጥቂቶቹን መገልገያ መሣሪያቸው አድርገው በመጠቀም፤ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና መሬት ነጣቂዎች፤ የቻይናን አስገድዶ መሬትን መውረሱን ቀድተውት ይሆናል። የኢትዮጵያ መሬት ነጣቂዎች፤ ከእንዲህ ዓይነቱ ተግባር ጋር የተያያዙትን ችግሮች መረዳት የተሳናቸው ይመስላል።

አንደኛ፤ በማስገደድ ማፈናቀሉ፤ የሰብዓዊ መብቶችን ረገጣና ቻይና የፈረመችውን አስገድዶ ከመሬት የማፈናቀል ዓለም አቀፍ ውልን ድፍረቶች ማስከተል ብቻ ሳይሆን፤ የተንኮል ጥንሰሳው፤ እያደገ ለመጣው የገቢ ልዩነት ማሻቀብ አስተዋጽዖ አድርጓል እያደገ የሚሄድ የኑሮ ልዩነት የሚያስከትለው ጣጣ እንዳለ፤ የኢትዮጵያ ፈላጭ ቆራጭ ገዥዎች መረዳት ነበረባቸው።

ሁለተኛ፤ በቻይና፤ አብዛኛው የመፈናቀሉ ተግባር የተፈጸመው፤ ከማዕከላዊው መንግሥት ፍላጎት ውጪ፤ በአብላጫው በአካባቢው ባሉ የክልል ባለሥልጣናት ነበር። በኢትዮጵያ፤ ሁለቱም መሬት የማካለሉ እቅድና በሥራ ላይ መዋል የተከናወኑት፤ በማዕከላዊው መንግሥት ባለሥልጣናት ዕዝና መመሪያዎች ነው። ይህም ላደጉት ቁርሾዎች አስተዋፅዖ አድርጓል።

ሶስተኛ፤ ሁለቱም የቻይና ማዕከላዊና የአካባቢ መንግሥታዊ አካሎች፤ ለብዙኀን የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች በር የከፈተ የፋብሪካ የሥራ ቦታዎችን መፍጠር ችለዋል። በዚህም በተዘዋዋሪ መንገድ ንብረታቸውን ላጡና ለተፈናቀሉ ሰዎች፤ የፋብሪካ ሥራው፤ ከፊል ማካካሻ እንዲሆንላቸው አድርጓል።

አራተኛ፤ በኢትዮጵያ በስፋት ከተስተዋለው በተጻራሪ፤ ምንም እንኳ የተሠጣቸው ማካካሻ መሬታቸው በወቅቱ ሊያስገኝ ከሚችለው ዋጋ ፍጹም የማይስተካከል ቢሆንም፤ የቻይና የአካባቢ ባለሥልጣናትና አልሚዎቹ፤ የተፈናቀሉትን የካሷቸው ይመስላል።

አምስተኛ፤ በኢትዮጵያው ሁኔታ፤ ከመሬት ጋር የተያያዘው ሙስና ተጠቃሚዎቹ (በማስገደድ ማፈናቀሉንና የንብረት መውደሙን በሚያካትተው) የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሆነው ተገኝተዋል።

ስድስተኛ፤ ከቻይናው በተለየ ሁኔታ፤ የራሱ የገዥው መመሪያዎች ክፍፍሉን እያባባሱት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ በጎሳ መስመሮች የተከፋፈለ ነው። በዚህም የተለሳ፤ ዘውገ-ነኩ የሙስና ነቀዛው ግጭቱንና ብጥብጡን ያባብሰዋል።

በመጨረሻም፤ ከኢትዮጵያ መሬት ነጣቂዎች በተለየ መልክ፤ የቻይና በለሥልጣናት፤ መሬታቸው ያለአግባብ በተነጠቁ ሰላማዊ ተቃውሞ አሰሚዎች ላይ የጥይት ውርጅብኝ አላሰፈሩም። ለዚህ ይሆናል ሌሎች በኢትዮጵያ የሚገኙ ጎሳዎች፤ በተለይም ኦሮሞዎች፤ የፌዴራል ፖሊሱን (በተደጋጋሚ ተማሪዎችን አረመኔያዊ በሆነ መንገድ ሲደበድብ የተስተዋለው) እና የጦር ሠራዊቱን፤ ንብረትነቱና መጠቀሚያነቱ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አጥፊ ጦር-ቀመስ የታጠቀ የሕዝብ መጨፍጨፊያ ቡድን አድርገው የሚወስዱት። የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ገዥው ፓርቲ ለፈጸማቸው ግፎች ተጠያቂነት እንደሌለው፤ በተደጋጋሚ አስተውለዋል። በጥቂቱ ለመጠቆም፤ በ 19952005/62014፣ አና አሁን 2015/6 ገዥው ክፍል እያደረሰ ያለውን ስቃይ፣ ግለስቦችን ከምድረ-ገጽ መሰወሩን፣ ጋፎ ማሰሩን፣ እና መጨፍጨፉን፤ በ2003 በአኝዎክ ወገኖቻችን ላይ ያደረሰውን የሕዝብ ዕልቂት፣ በ2001 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን መግደሉን ያስተውሏል። የኢትዮጵያን ሕዝብ የማያልቀው ግፍ አንገሽግሾታል። እኒህና ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሌሎች ስቃዮች ናቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ፤ በሥልጣን ላይ ያለው የነሱ መንግሥት እንዳልሆነ እንዲያስቡ ያደረጋቸው። የሕዝብ ብልጽግና ምንጮቹን ጥቂቶቹ መቀራመታቸውና የኒህ ጥቂቶች ለከት የለሽ የሙስና ተግባር ነው የኢትዮጵያን ሕዝብ፤ ንብረቶቹና መዋዕለ ንዋዮቹ ከነሱ የማይወግነው የመዥገሩ ቡድን ናቸው፤ ብሎ እንዲያስብ ያደረገው። እናም ከዚህ ተከትሎ፣ “ከሌሎች” የሚመነጨውን ሙስና መገመቱ ከባድ አይደለም (በብዙዎች እንደወራሪ የተወሰዱ) በብዙ ሁኔታዎች ላይም፤ አንድን ጎሳ እንወክላለን በሚሉት እየተራገበ – በከፍተኛ ቅናትና ቁጣ እየተስተዋለ እያደረገ፤ ብሎም ተከፋፍሎ፤ ሁሉም ወደ ጥጉ መፈርጠጡን እያከረረው ሄደ።

የገዥዎች ንጥቂያ፤ ከጭቆናው፣ ከእብሪቱና፣ ከአረመኔ ተግባሩ ጋር ተዳምሮ፤ ሀገሪቱን እየተመነደገ ለሄደ የኅብረተሰብ-የፖለቲካ-የምጣኔ ሀብት ሥምሪት ምስቅልቅል በሩን ፍንትው አድርጎ ከፍቶ፤ ለወደፊቱ የጎሳ/የጠባብ ወገንተኝነት ግጭቶች መካሄድ በማመቻቸት፤ እየበሰበሰ የመጣው ሥርዓት ወደ የሚጋለጥበትና የሚፍረከረክበት ሁኔታ አምርቷል። አለመታደል ሆኖ፤ እየሟሸሸ በመሄድ ላይ ያለው ሥርዓት፤ የአጓዳኝና የንጹኀን ሰለባዎች ይኖሩታል።

“መፍትሔዎች”፤ አሁን ካለንበት ወዴት እንሄዳለን?

ከላይ እንዳመለከትኩት፤ ለገዥዎች ንጥቂያ፤ መሻሻል ማድረግ ዕርሙ ነው። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፤ በየጊዜው፤ በሕግ የመተዳደር ሥርዓት፤ በከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዳሻቸው ሲለሚሽከረከር፤ የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር ነፃ የሆነ የፍትኅ ሥርዓትን አስከባሪ አካል የለም። በተለያዩት የመንግሥት አካሎችም ምንም ዓይነት የሥልጣን ድርሻ ክፍፍል፣ መከባበርና መጠባበቅ የለም። ያለን ነገር ቢኖር፤ የተሽመደመደ ፋይዳ ቢስ ፓርላማ ነው። አለን ብለን የምንቆጥረው፤ በአጥንት የለሽነትና ደካማነት ታስሮ የተያዘ፤ ሥልጣን አልባው የፀረ-ሙስናው ድርጅት ነው። ከሞላ ጎደል ሁሉም የነፃና በግል ባለቤትነት የተያዙ ጋዜጦች ተገደው ድምጥማጣቸው ጠፍቷል፤ ብዙዎቹ ጋዜጠኞችም ታስረዋል፤ አለያም ተሰደዋል። እኒህ አረመኔያዊ እርምጃዎች፤ ሀገሪቱ (ራሱ የገዥው ሤረኛ ቡድንም) ነፃ የዜና አገልግሎትን በመጠቀም፤ ሥር የሰደደውን ሙስና የማጋለጥ ችሎታውን ነፍጓታል። በሀገሪቱ ያሉ የኅብረተሰቡ ድርጅቶች፤ አንድም ድርሻቸው ጠፍቷል አልያም የገዥዎቹ መገልገያ እንዲሆኑ ተደርገዋል። ያለን፤ የመርማሪ መሥሪያ ቤቱ ሙስናን እና የቢሊየን ብሮች መሰወርን ሲያጋልጥየምርመራ ሹሞቹን አሽቀንጥሮ የሚያባርር የሀገራችን ዋና የሥራ አስኪያጅ አካል ነው። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፤ እያንዳንዱ የቁጥጥር ድርጅት፤ አልፎ ተርፎ መሥራች፣ አቋቋሚ ፈትፋቹና አሁን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ቁንጮው ላይ በክብር የተቀመጡት አቶ ስብሃት ነጋ፤ በድፍረትና ያለዕፍረት፤ ሙስና በኢትዮጵያ ቅጥ አጥቶ ከመስፋፋቱ የተነሳ፤ የሃይማኖት ተቋማትን ሳይቀር ሰርፆ ገብቶባቸዋል እስኪሉ ድረስ፤ የገዥዎቹ ሤረኛ ቡድን መገልገያ ነው። የኢትዮጵያ ሤረኛ ገዥ ቡድን፤ የፀረ-ሙስና አለቃ ሆኖ የማይስተካከል ሥልጣኑንና ማኪያቬሊያዊ ስልቱን በመጠቀም፤ የሚያስቸግሩትን ለማጥመድና ጭጭ ለማሰኘትና ከተቻለም የሤራ ግዛታቸውን ሕይወት ለማርዘም የሚያገለግል ቭላድሚር ፑትንን (ማለትም መለስ ዜናዊን) የመሰለ አጥቷል። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎችና ግብረ አበሮቻቸው፤ (ወይም ባጠቃላይ መላ ሀገሪቱ) (የአሜሪካን ዘራፊ ባላባቶችን የተቋቋመ) ስግብግብ የሤረኛ ገዥ ቡድኑን የሚገታ ወይም የሚያፈራርስ፤ ቴዎድሮስ ሮዝቬልት የላቸውም፤ የኢትዮጵያ ሤረኛ ገዥ ቡድን ከኢትዮጵያ መንግሥት ተለይቶ መታየት አይችልምና። ሄዶ ሄዶ፤ በኦሮሞዎች ላይ የሤረኛ ገዥ ቡድን የተወሰዳቸው የድንብርብርና አይምሬ የጭካኔ እርምጃዎች በግልጽ የሚያመለክቱት፤ የገዥው ክፍል አንድ ፈላጭ ቆራጭ ቁንጮ መሪ ማጣቱን ብቻ ሳይሆን፤ ሀገር አቀፍ ማዕከላዊ ዕዝና ቁጥጥር እንዳነስው ጭምር ያመለክታል።

የቀሩልን፤ ሶስት በንፅፅር ሲታዩ ጠናካራ የሚባሉ ቡድኖች ሲሆኑ፤ እኒህ ቡድኖች፤ ሀገሪቱን ሁሉ ያበሻቀጠው ሙስና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ስቆቃ ሊያረግቡት ሲችሉ፤ የሚወስዷቸውት እርምጃዎች፤ እግረ መንገዳቸውን፤ ያልተገራ ዘራፊውን ገዥ መንግሥት ዕድሜ የማርዘም ዕድል አላቸው። ምንም እንኳ እኒህ ሶስት ቡድኖች የሤረኛ ቡድኑን መንግሥት የፖለቲካ ሕልውና ማርዘም ቢችሉም፤ በዚህ ደረጃ ያለ ሙስና በባለቤቶቹ ሊድን ስለማይችል፤ ከአይቀሬው ውድቀቱ  ሊያተርፉት አይችሉም። እኔ በማቅማማት ላይ ያለሁት፤ ሀ) አህጉራት አቀፍ ተቋማት፤ ለማሳሌ እንደ አይ. ኤም. ኤፍ፣ የዓለም ባንክ፣ እና ሌሎችም፤ ለ) ዕርዳታ ሠጪ ሀገሮች፤ ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት (በተለይም እንግሊዝ) እና ሐ) የገዥው አካል የሆኑና ከገዥው አካል ጋር ቅርበት ያላቸው ጉዳዩ የሚያገባቸው፤ ማለትም፤ “ላለው ሥርዓት ጥብቅና ቆመው የሚጠብቁት”ን (ብርሃኑ መንግሥቱ, 2016 – “ለፖለቲካ ሠፈሩ ምልጃ . . .”) በማጤን ነው። የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ፤ በመንግሥቱ ላይ ከባድ ጫና ማድረግ የሚችል ፈርጠም ያለ ጉልበት አላቸው። እኒህ ተቋማትና ዕርዳታ ሠጪ ሀገሮች፤ ይህ መንግሥት ምን ያህል የዕርዳታ ጥገኛ – ዕልም ብሎ የዕርዳታ ጥገኛነቱ “[ልክ] በሕመም ማስተገሻ ከኒና እንደተለከፈ በሺተኛ፣” እንደሆነ ያውቃሉ። በተለይ ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገሮች፣ ዩናይትድ ኪንግደም፤ ከርዳታ ሠጪ ተቋሞች ጋር በመሆን፤ የሚሠጡት ዕርዳታ፤ ገዥዎቹ ለኒሁ  ክፍያ የሚያደርጉላቸው፣ በግዳጅ ሰውን ወደ አንድ አካባቢ የሚያሰፍሩበት ወይንም በሌሎች መንገዶች የሚያፈሱት፤ የሙስናው ምንጫቸው መሆኑን ግጥም አድርገው ያውቃሉ። ሌሎች ቦታዎች ላይ እንዳሳየሁት ዕርዳታ ሠጪ መንግሥታት፤ የፓርቲው ስብስብ የተዋቀሩ ግዙፍ የንግድ ድርጅቶች መነሻ ገንዘባቸው፤ የሚሠጡት ዕርዳታ መሆኑን ያውቃሉ። እኒህ ዕርዳታ ሠጪ መንግሥታት ከፈለጉ፤ የትግሬዎች ነጫ አውጪ ግንባር መሪዎችን፤ ከውጪ የተሠጠን ዕርዳታ ማባከንና ገንዘቡን ያለአግባብ ወዳልተገባ ቦታ ማዛወር በሚል ክስ መስርተው፤ አንገታቸውን ሊያስደፏቸው ይችላሉ። ሶስተኛውን ቡድን በተመለከተ፤ ፕሮፌሰር ብርሃኑ መንግሥቱ (2016) እንዳቀረበው፤ “ላለው ሥርዓት ጥብቅና ቆመው የሚጠብቁት” የሚሳካላቸው፤ “ከመካከላቸው ጥቂት አክራሪ የሆኑ ባለጉዳዮችን”፤ ለውጡ ለነሱ ዘላቂ ፍላጎት በጣም ጠቅሚነቱን በማግባባትና፤ ለውጡንም ተቀብለው በመምራትም ነው። እዚህ ላይ ትክክለኛ ጥያቄ ማስቀመጥ ይቻላል። እኒህ የሥርዓቱ ዘብ ቋሚዎች፤ ከላይ እስከታች ሁሉም የፓርቲ አባላት በሚገማ መልኩ ሙስኞች ሆነው፤ የራሳቸውን ስግብግብነትና ግለኝነት መቆጣጠር ይችላሉ ወይ? የሚለውን ነው። ታዲያማ ይኼን ካላደረጉ፤ እስካሁን ያካበቱትን ሁሉ ያጣሏ!

እሺ፤ ታዲያ በእምቢተኝነት ተቃውሟቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማሰማት የተነሱት ኦሮሞዎች ንብረቶችን እና የመዋዕለ ንዋይ ሕንጻዎችን ለምን አቃጠሉ? ይኼማ ባንድ ሌሊት እልም ያሉ ቱጃሮች ያደረጋቸውን የራሳቸው ያልሆነን መሬት፤ እንዳሻቸው በሚዘርፉ ሁሉን ለኔ የፓርቲ ልሂቃን ላይ፤ ሥር የሰደደው ምሬት ያስከተለው ነው። ሕዝቡ ያየው፤ ጥሮ ግሮ ሀብት ማግኘት፤ ወይንም በአያት የቅድመ አያት ባድማ ላይ ለማረስ ቅድሚያን ማግኘት ሳይሆን፤ ሀብት ማካበቱ፤ ቅጥ ያጣ ሙስናን፤ አፍቃሪ ፓርቲ መሆንን፣ የደም ትስስርን ተከትሎ ሲነጉድ ነው። በእምቢተኝነት ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማሰማት የተነሱት፤ ከትውልድ ቦታቸው ላይ በአስገዳጅ መፈናቀላቸው ብቻ ሳይሆን፤ ሥራ የላቸውም፤ ገንዘብ የላቸውም፣ ተስፋውም እንኳ የላቸውም። የኒህ ተነሳሺዎች የተለዩ ይዞታዎችን እየለዩ ማጥቃቱ እንደሚያመለከተው፤ ማቃጠሉ/ ማውደሙ እና የእምቢታ ዕቀባው ያተኮረ የሚመስለው፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና የደጋፊዎቹ በሆኑት ላይ ነው። አለመታደል ሆኖ፤ እኒህን የመሰሉ ቅሬታዎች፤ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍል ነዋሪዎች ዘንድ ተረግዟል። ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ብዙ የሚቃጠልና የሚጠፋ የሀብት ምንጭ ባይኖራትም፤ በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ድርጊት ሊደገም ይችላል።

አለመታደል ሆኖ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የምጣኔ ሀብት ሥምሪት አጉራ ዘለል ጉልበተኝነት እና መንግሥት የሚመራው የስቃይ ናዳ፤ አንጀቱ ቆስሏል። ያንጀት መቁሰል ወደ ተስፋብሲነት፣ አክራሪ ቁጠኝነት፣ እና የዛለ መንፈስ መያዝ ያመራል። ከዚያም በላይ ራስን ጎጂ እስከመሆን ያደርሳል። ስለዚህ፤ የንብረት ቃጠሎዎች፤ ኦሮሞዎች ከደረሰባቸው በደል የተነሳ ያንጀታቸው መቁሰል ተከታይ ውጤቶች ናቸው። አንድ ቀን እኒህን የመሰሉ ጥፋቶች፤ ምንአልባትም በከፋ ሁኔታ፤ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ይደገሙ ይሆናል የሚል የሚቀነቅን ፍርሃት አለኝ። በላያችን ያንዣበበውን አደጋ እንዳይከሰት የሚያደርጉ ተገቢ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለን ፀሎትና ተስፋ እናደርግ።

ጸሐፊው፣ ሰዒድ ሃሰን፣ በመሪ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ሥምሪት (ኢኮኖሚክስ) ፕሮፌሰር ናቸው። ሊያገኟቸው ከፈለጉ፤የኢሜል አድራሻቸው፤ shassan@murraystate.edu ነው።

Advertisements

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in እስከመቼ - ESKEMECHE. Bookmark the permalink.

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s