የኢሕአዴግ አይቀሬ ዕጣ – አስጊው የኢትዮጵያ ጣጣ

የኢሕአዴግ አይቀሬ ዕጣ – አስጊው የኢትዮጵያ ጣጣ
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
ሰኞ፤ መስከረም ፲ ቀን ፳፻፰ ዓመተ ምህረት ( 9/21/2015 )

መከወኛ ሃሳብ፤

ዛሬ ካለንበት የፖለቲካ ሀቅ ላይ ቆመን የነገዋን ኢትዮጵያ በሃሳብ ብንመለከት፤ ሶስት እውነታዎች ገጠው ይታያሉ። የመጀመሪያው፤ አሁን በሥልጣን ላይ ባለው የገዥ ቡድን አስተዳደር፤ ምንም ቢሆን ምንም፤ ኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሊኖራት አለመቻሉ ነው። ሁለተኛው ደግሞ፤ ኢሕአዴግ፤ ውስጡ እየነቀዘ፤ ወደ አንድ ፓርቲነት ከማደግ ይልቅ፤ በየድርጅቶቹ መጎነታተል እየተወጣጠረ፤ ከውስጥ መርቅዞ ወደ መበታተኑ በመሄድ ላይ ያለ መሆኑ ነው። ሶስተኛው ደግሞ፤ አሁን በያዝነው ሂደት፤ ሀገራችን እጅግ ወደ ከፋና ልትወጣበት ወደማትችለው መቀመቅ ውስጥ እየዘቀጠች መሆኗ ነው። እኒህ ፈጠው ያደገደጉ የፖለቲካ ሀቆች፤ በዚህ ጽሑፍ ተተንትነው ቀርበዋል።

መግቢያ፤

በ፳ ፩ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ፤ ዓለም በሥልጣኔ እየገሰገሰ፤ የሳይንስ ስነ-ምርምር የእደ ጥበብ ግኝቶችን በብዛት እያዥጎደጎደና ተዓምር የሚባሉ እምርታዎችን እያስከተለ ባለበት ወቅት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በወገንተኛ አምባገነን አስተዳደር ሥር፤ የኋልዮሽ ስትጓዝ ትገኛለች። የዚህ ገዥ ቡድን ፍላጎትና ተግባር፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ የቆመ በመሆኑ፤ ሰላም፣ ብልፅግናና ዕድገት ከሀገራችን ፍጹም ርቀው ሸሽተዋል። አድልዖና ሙስና አስተዳደሩን አግምተውት፤ አፍንጫ ካስያዘ ውሎ አድሯል። በጣም ጥቂት ምርጥ ዜጎች በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ሲያካብቱ፤ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረው ደሃ ወገናችን፤ በውጪ መንግሥታትና በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ምጽዋት፤ ቀኑን ይገፋል። የፖለቲካ ምኅዳሩ ትርጉም በማይሠጥ መንገድ፤ በገዥው ቡድን ተጠራቆ የተያዘ በመሆኑ፤ የተለዬ አቋም ያላቸው ግለሰቦችና የአስተዳደሩን ተግባር የማይደግፉ ሁሉ፤ ለእስር የተዳረጉበት፣ የሚዳረጉበት፣ የተገደሉበትና የሚገደሉበት ሁኔታ፤ የዕለት ተዕለት የኑሮ ሀቅ ሆኗል። በሕዝቡ ዘንድ፤ በተለይም በወጣቱ ውስጥ ተስፋ መቁረጥ ነግሷል። ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ቀርቷል። ተማሩም አልተማሩም፤ የሥራ አጡ ቁጥር ሀገሪቱን ለውጥረት ዳርጓታል። አሁንም ሀገሪቱን እየጣሉ፣ ከገዥው ክፍል እየሸሹ፣ ሞትን በከበበ አስፈሪና አስጊ መንገድ፤ ወደ ውጪ የሚነጉዱት ወጣቶች ቁጥር ልክ አጥቷል። ይህን ሁሉ ምን አመጣው? ይሄስ ምን ያህል የሚሰነብት እውነታ ነው? ይህ ጉዟችን ወደየት ያመራል? ምን መደረግ አለበት? የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ይሄን ሀቅ በመመርመር፤ በግልጽ ተንትኖ ማቅረብ ነው።

ላለንበት ሀቅ የዳረገን ሂደት፤

በወርሃ የካቲት ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓመተ ምህረት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር እስከዳር፤ ከነበረበት የጉልተኛ ሥርዓት ማነቆ ለመላቀቅ፤ ሆ ብሎ ተነሳ። በነበረው ኋላ ቀርና አፋኝ የፖለቲካ ሥርዓት ምክንያት፤ በዚያ ወቅት ብቁ የሆነና የተዘጋጀ የሕዝቡ የፖለቲካ ድርጅት ባለመኖሩ፤ የፖለቲካ ሥልጣን ክፍተት ተፈጠረ። በወቅቱ ጉልበቱን ያሳየውና የተደራጀው ክፍል የሀገሪቱ የጦር ሠራዊት ነበርና፤ አጋጣሚውን በመጠቀም፤ የወጣት መኮንኖች ስብስብ ቦታውን በጦር ሠራዊቱ ስም ወሰዱት። ይህ የወጣት መኮንኖች ስብስብ፤ ወታደራዊ ደርግን አቋቁሞ፤ በሂደቱ የአንድ ግለሰብ የበላይነትን ፈጠረ። ይህ ሰው በላው አረመኔ መንግሥቱ ኃይለማርያም፤ የግለሰብ አምባገነንነቱን ጨብጦ፤ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ እልቂትን አስከተለ። እንዲያ ያለ አስተዳደር ዘለቄታ የለውምና፤ በሚዘገንን መንገድ አገሪቱን አፋልሶ፤ ወገን ጨርሶ፣ ብሩህና ለወገን ተቆርቋሪ፣ ሀገራቸውን ወዳድና አስተዋይ የሆኑ የአንድ ትውልድ ልጆቿን መትሮ፣ ሀገራችንን አመሰቃቅሎ፤ ለወገንተኛ አምባገነኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በሩን ከፍቶ ለቀቀለት። ሰው በላው መንግሥቱ ኃይለማርያምም ጅራቱን ቆልፎ እንደሚሸሽ ውሻ፤ እግሬ አውጭኝ ብሎ ሾልኮ ጠፋ።

በዚያ በተፈጠረው ሁለተኛ ክፍተት፤ በ ፲ ፱ ፻ ፹ ፫ ዓመተ ምህረት፤ ሰተት ብሎ አዲስ አበባ የገባው ወገንተኛው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ የሀገሪቱን ሥልጣን ከመጨበጡ በፊትና ከጨበጠ በኋላ፤ ሁለት የተለያዩ መሠረታዊ የሆኑ ግልጽ የፖለቲካ እምነቶች ነበሩት። ይህ ድርጅት ሲመሠረት፤ የትግራይን ክፍል ሀገር ነፃ አውጥቶ፤ የራሱን አንድ ሀገር ለመመሥረት ነበር። የሥልጣን ክፍተቱ ተፈጥሮ አመቺ ሁኔታ ሲያጋጥመው፤ ይህን ዓላማውን እንደያዘ፤ “ሌሎች”ን አስተባብሬ ገዥ እሆናለሁ የሚል የፖለቲካ እምነት ገዛ። ለዚህ ዓላማው፤ ከ”ሌሎች” ጋር መተባበሩ ሊያስከትል የሚችለው የባለቤትነትና የበላይነት ጥያቄ ስላላማረው፤ ራሱ ጠፍጥፎ የሚያቋቁማቸውን ድርጅቶች አጋሮቹ በማስመሰል አንኳለለ። እኒህ ድርጅቶች፤ ከ”ሌሎች” ድርጅቶች ከድተው የወጡ፣ ከደርግ በፍርሃት የሸሹ፣ ምርኮኛ እስረኞችና እነዚህን ባንድ ላይ ሰብስበው ከሚቆጣጠሩ የራሱ ድርጅት አባሎች የተዋሀዱ ነበሩ። በዚህ ስሌት የተመሰረቱት ድርጅቶችን ከራሱ ጋር በመቁጠር፤ ኢሕአዴግን አቋቋመ። አሁን ኢትዮጵያዊ ጋቢ ለበሰ። እዚህ ላይ ግን፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ “ሌሎች” እያለ የመደባቸውን ድርጅቶችና “እኔ” በማለት ያጠነጠነውን፤ ራሱን በበላይና “ሌሎች”ን በበታች አድርጎ ነው።

የተነሳበት የፖለቲካ እምነቱ እንደተጠበቀ ነበር። በተለይም ከእምነቱ ውስጥ ሁለት እንደ አንገት ማተብ ያነገታቸው አሉት። የመጀመሪያው፤ “ትግራይ እስከዛሬ የበታች ሆና ተበድላለች። አሁን በኛ አማካኝነት የበላይ ሆና፤ ‘ሌሎችን’ በዳይ መሆን አለባት!” የሚለው ሲሆን፤ ከዚሁ ጋር ጎን ለጎን የሚሄደው ሁለተኛው ደግሞ፤ “አማራ እስከዛሬ የበላይ ሆኖ ሁሉን ሲበድል ነበር። አሁን የበታች ሆኖ፤ በትግሬዎችና በ’ሌሎች’ ተበዳይ መሆን አለበት፤” የሚለው ነው። እንግዲህ እኒህ ከገዥና ተገዥ መደቦች ውጪ ሆነው፤ የአንድን ግለሰብ ነፃነት ለትውልድ ሐረጉ በማስረከብ፤ “የበደለህ አማራ ነው!” “የተበደልከው አማራ ስላልሆንክ ነው!” በሚል እምነቱ፤ የበዳይና ተበዳይ ወገን የሽክርክር አዙሪት አስተዳደሩን መሠረተ። ትናንት አማራ ሁሉን በዳይ፤ ትግሬ ተበዳይ ነበር። ዛሬ ትግሬ በዳይ፤ አማራ በሁሉም ተበዳይ ነው። ነገ ደግሞ . . . እያለ የሚቀጥል የትውልድ ሐረግ ቆጥሮ፤ በደልንና መበደልን የመረካከብ አባዜ ዘፈዘፈበት። ሌላው የፖለቲካ እርምጃ ሁሉ ከዚሁ ምንጭ ተቀዳ።

በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል፤ በጥቂት የገዥው ቡድን አባላት ላይ፤ የአብዛኛው ተገዢ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለነፃነቱ መነሳት ቦታ አጥቶ፤ በኢትዮጵያዊያን አርሶ አደሮች፣ ላብ አደሮች፣ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ነጋዴዎች መካከል ያለው የሙያና የመደብ አንድነት ተሰርዞ፤ የትውልድ ትስስሩ መነሻና መድረሻ ሆነ። ይህ ደግሞ፤ በአንድ በኩል ሰው ሁሉ በየትውልድ መንደሩ ብቻ እንዲሰፍር አስገደደ። በሌላ በኩል ደግሞ፤ አድልዖ፣ ሙስና፣ ምዝበራ፣ ለከት የለሽ ብልግና፤ የሥርዓቱና የሰዎች የርስ በርስ ግንኙነት ወሳኙና መታወቂያዎች እንዲሆኑ አደረገ። በገዥነት አሁን ቢቆናጠጥም፤ እንዳለፈው አረመኔ ገዥ ሁሉ፤ ይሄም ገዥ ቡድን ያልፋል። በርግጥ እስኪያልፍ እያለፋ ነው። አይቀሬ ዕጣው እያንዣበበበት ነው። የነገዋ ኢትዮጵያ ምን ትሆን ይሆን?

ፍሬ ሃሳብ፤

የነገዋን ኢትዮጵያ በሃሳብ ስንመለከት፤ የመጀመሪያው እውነታ፤ አሁን በሥልጣን ላይ ባለው ገዥ ቡድን አስተዳደር፤ ምንም ቢሆን ምንም፤ ኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሊኖራት አለመቻሉ ነው። እንግዲህ ይህ ነጥብ፤ ለምን? የሚል ጥያቄ ማስከተሉ አይቀርም። ለዚህ መልሱ የሚገኘው ከኢሕአዴግ ማንነት ነው። አሁን ያለውን አስተዳደር፤ ማለትም የኢሕአዴግን አስተዳደር ብንመለከት፤ በመንግሥትና በኢሕአዴግ መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም። መንግሥት ማለት ኢሕአዴግ ማለት ነው።  ኢሕአዴግ ማለት መንግሥት ማለት ነው። መንግሥት የተለዬ አካል፤ ገዥ የፖለቲካ ፓርቲ የተለዬ ሌላ አካል፤ መሆኑ ተወርውሮ ተጥሏል። መንግሥታዊ መዋቅሩና የኢሕአዴግ መዋቅር አንድ ሆነዋል። ሕግ አውጪው ክፍል፣ ወሳኙ ክፍል፣ እና ፈጻሚው ክፍል፤ አንድ ሆኗል። አብዮታዊ ዴሞክራሲ፤ ኢሕአዴግን የበላይና ዘለዓለማዊ ያደርገዋል። በኢሕአዴግ እምነት፤ “ተዋግቶና ደሙን አፍስሶ ያገኘው ሥልጣን!” ስለሆነ፤ በምንም መንገድ በሰላም ሥልጣኑን መልቀቅ አይታሰበውም። ደሙን የከፈለው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም። ደሙን ያፈሰሰው ለራሱ ሥልጣን ለመያዝና ዓላማውን በማራመድ ነው። ስለዚህ ከሀገሪቱ መሪ ጀምሮ እስከ ቀበሌ ዘበኛው ድረስ፤ የኢሕአዴግ አባል መሆን ግዴታ ነው። ከኢሕአዴግ ውጪ መንግሥታዊ መዋቅር የለም፤ ከመንግሥታዊ መዋቅሩ ውጪም የኢሕአዴግ አካል የለም፤ ኢሕአዴግ መንግሥት ነውና!

ከዚህ ተነስቶ፤ እንዴት ያለ መንግሥታዊ አካል፤ ከኢሕአዴግ ውጪ ያለ፣ ሕግ ሊያወጣ፣ ፍርድ ሊመለከት፣ ፖሊስ ሆኖ ሥርዓት ሊጠብቅ፣ የሕዝብን አቤቱታ ሊሰማ ይችላል? እንዴትስ ያለ ነፃ የምርጫ ዝግጅት ሊያደርግ ይችላል? እንዴትስ ያለ ሕግ አውጪና ሕግ አስከባሪ ሊኖር ይችላል? ይህ የኢሕአዴግ አወቃቀር፤ ግድ የሚለው፤ ሀገር አቀፍ ድርጅት እንዳይኖር ነው። በየክልሉ ያሉ የኢሕአዴግ አባልና ተቀጥላ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ሌላ የነሱ ተቃዋሚ ድርጅት እንዳይኖር የዕለት ጉዳያቸው ነው። መገንዘብ ያለብን፤ በየክልላቸው የፖለቲካ ድርጅት ለምፍጠር የሚያመለክቱ ሰዎች፤ ፈቃድ ሠጪዎቹና ነሺዎቹ እኒሁ ድርጅቶች ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ፤ እነኚህን በየክልሉ ያሉ ድርጅቶች መቃወም ማለት፤ መንግሥትን መቃወም ማለት ነው። ቀጥሎ ደግሞ፤ መንግሥትን መቃወም፤ ያስከስሳል፣ ያሳስራል፣ ያስደበድባል፣ ንብረት ያስቀማል፣ ካገር ያስባርራል፣ ያስገድላል። በጠቅላላው ኢሕአዴግን ከሥልጣን ለማውረድ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ፤ መንግሥትን ለመገልበጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። ስለዚህ ይህንን ለመቆጣጠርና ለመቅጣት፤ አስፈላጊ ሕጎችን ማርቀቅ፣ ካስፈለገም ያሉትን መሰረዝ፣ በተግባር ላይ ማዋል አለዚያም የማይስማማውን ሕግ አውጥቶ መጣል፤ የኢሕአዴግ ዋና ተግባር ነው።

ታዲያ አሁን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በኢትዮጵያ አሉ አይደል? ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? የሚሉ ጥያቄዎች ሊከተሉ ይችላሉ። አሁን ያሉትን በተቃውሞ የተሰለፉ ድርጅቶች ሕልውና፤ በደንብ መመርመር ያስፈልጋል። አዎ! ተቃዋሚ ድርጅቶች አሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ በኢሕአዴግ እይታ፤ እኒህ አሸባሪ ድርጅቶች እንጂ፤ ተቃዋሚ ድርጅቶች ተብለው አይታመኑም፤ አይታወቁም። ማንኛውም ኢሕአዴግን የሚቃወም ወይንም ኢሕአዴግ ያላቋቋመው ድርጅት በሙሉ፤ ፀረ-ኢሕአዴግ ነው። ፀረ-ኢሕአዴግ ደግሞ፤ ፀረ-ሀገር ማለት ነው። እናም ፀረ-ሕዝብ ነው። እናም፤ አድኀሪ፤ ኋላቀር፣ ትምክህተኛ፣ ጠባብ ብሔርተኛ፣ ሀገር ከፋፋይ ጠላት ነው። ይህ የፖለቲካ ድርጅቶችን ብቻ ሳይሆን፤ የሙያ ማህበራትንና የሃይማኖት ተቋማትን ሁሉ ያጠቃልላል። የኢሕአዴግን ሰበካና ወቀሳ ደጋግሞ ላዳመጠ የፖለቲካ ሂደቱን ተከታታይ፤ እኒህ የተጠቀሱ ውንጀላዎች፤ በተደጋጋሚ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በጋዜጣ፣ በድረገጾችና በየስብሰባ አዳራሾች የሚዥጎደጎዱ ዘለፋዎች ናቸው። ስለዚህ ሌሎች ከኢሕአዴግ ነፃ የሆኑ ድርጅቶች እንዳያድጉ ተብታቢ ማሰሪያዎች ናቸው። ለምን ሲባል፤ ያልተፈለጉ ደንቃራዎች ስለሆኑ ነው። የተፈለገው፤ አጃቢ ሆኖ እሺ ጌታዬ የሚል ድርጅት ብቻ ነው። አጃቢ ያስፈለገውም፤ ለውጭ ሀገሮች መታያና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አለ ማስባያ የጀሮ ጉትቻዎች፣ ያንገት ማስጌጫዎች እንዲሆኑ ብቻ ነው። ያ ከሌለ ብድርም ሆነ እርጥባን አይገኝማ! ከሌሎች ጋር እኩል መሰለፍና መታየት አይገኝማ!

በነገራችን ላይ፤ የዚህ የኢሕአዴግ፤ ዋናው ፈጣሪና መስራቹ አንድ ድርጅት ሆኖ፤ የበላይነቱን በሌሎቹ በፈጠራቸው ላይ ያነገሰና፤ እኒህን ተፈጣሪ ድርጅቶች በአጃቢነት የሚጠቀም መኖሩ ከታች በዝርዝር ቀርቧል። አሁን ያሉትን ተቃዋሚ ደርጅቶች ስንመለከት፤ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፤ የአንድነት ለፍትኅና ለዴሞክራሲ ፓርቲና የሰማያዊ ፓርቲ፤ ቀጥሎም መድረክ ናቸው። እኒህ ደግሞ የራሳቸውን ፈለግ እየተከተሉ ስላስቸገሩ፤ ለምርጫ ሲወዳደሩ ሙሉ እንቅፋት በመፍጠር ሕልውናቸውን ለማሳጣት ከመጣር አልፎ፤ መሪዎቻቸውን መወንጀል፣ ማሰር፣ ማስቃየት፣ ማባረር፣ ከሀገር ማስወጣትና መግደል ተፈጽሞባቸዋል። የጎንዮሽ የስም ተመሳሳይ ተለጣፊ ድርጅቶችን እያቋቋመ እንዲዳከሙና እንዲጠፉ ያላባራ ጥረቱን ቀጥሎበታል።

በተጨማሪ ደግሞ ሌላው ሊከተል የሚችለው፤ ታዲያ እንዲህ ከሆነ፤ ይሄን አምባገነን መንግሥት ምን በሰላም ለመለወጥ ጥረት ይደረጋል? አጉል ድካም አይሆንም ወይ? ከንቱ ከመድከም፤ ገዥው ጠመንጃ አንግቦ ሥልጣኑን እንደነጠቀና ያለጠመንጃ ሌላ የማያውቅና የማይሰማ ስለሆነ፤ ሌሎቹስ ለምን ጠመንጃ አንግበው መታገል ብቻ አማራጫቸው አይሆንም? የሚሉ ጥያቄዎች ናቸው። ይህ ራሱን የቻለ ርዕስ ነው። ጠቆም አድርጎ ለማለፍ ያህል፤ ጠመንጃ አንግቦ ለትግል በመነሳት ሕዝባዊ ድልን ለመቀዳጀት፤ ወሳኝና መኖር ያለባቸው ግዴታዎች አሉ። መፈለግ ለብቻው ወሳኝ አይደለም። በጦርነት ማቸነፍ ይቻላል! የሚለው ብቻውን ወሳኝ አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በሰላም መንገድ እየተደረገ ያለው ትግል፤ በእውነት የሰላም ትግልን መንገድ የተከተለና፤ በትክክል ተተግብሮ ያለቀለት ነው ወይ? የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል። ስለዚህ፤ በሰላም ወይንስ በትጥቅ ትግል የሚለውን፤ በሌላ ጊዜ እንመለከተዋለን። ከዚህ በፊት ይሄው ጸሐፊ ያቀረባቸው ጦማሮች አሉ። እነዚህን (https://nigatu.wordpress.com) ሄዶ መመልከት ይቻላል።  እንግዲህ እዚህ ላይ፤ መድበለ ፓርቲና ኢሕአዴግ ሊቀራረቡና አብረው ሊሄዱ የማይችሉ መሆናቸው በግልጽ ሰፍሯል።

ሁለተኛው እውነታ ደግሞ፤ ምንም እንኳን ለረጅም ጊዜ በተደጋጋሚ በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ወደ አንድ ፓርቲ ለመዋሐድ እየተዘጋጁ ነው ተብሎ ከበሮው ቢደለቅም፤ ይህ ስብስብ፤ በአባል ድርጅቶች መካከል ያለው ትብብር ውስጡ ነቅዞ፤ ወደ አንድ ከመሄድ ይልቅ፤ በየድርጅቶቹ የየግል ፍላጎት መጎነታተሉ የስብስብ ውህደቱን እየወጣጠረው፤ ወደ ውድቀቱ በመሄድ ላይ ያለ መሆኑ ነው።

ከላይ እንደተጠቆመው፤ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢሕአዴግን) የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር (TPLF) ሲመሰርት፤ የአራት “ትልልቅ” የፖለቲካ ድርጅቶች ጥምር አድርጎ ነው። እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን፤ በጽሑፍ ያልሰፈረ ሁለት ክፍል አለ። ይሄም፤ “እኔ” የሚለው ራሱ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና፤ “ሌሎች” የሚላቸው ቀሪውን የኢትዮጵያ ክፍል ይወክላሉ ብሎ የመደባቸው ድርጅቶች ናቸው። በነዚህ ሁለት ክፍሎች መካከል፤ የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አለ። ይህን በአእምሯችን እናስቀምጥና ወደ አራቱ “ትልልቅ” ድርጅቶች እንመለስ። እነሱም፤ ፩ኛ. የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር (TPLF)  ፪ኛ. የአማራዎች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ANDM) ፫ኛ. የኦሮሞዎች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (OPDO) ፬ኛ. የደቡብ ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (SPDM) ናቸው። ሀገሪቱን ማስተዳደር ሲጀምር፤ ለመግዛት እንዲያመቸው፤ ተጨማሪ አምስት አናሳ የፖለቲካ ድርጅቶች አክሎበታል። እነሱም፤ ፩ኛ. የአፋሮች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ANDP) ፪ኛ. የኢትዮጵያ ሶማሊዎች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ESPDP) ፫ኛ. የሐረሬዎች ሊግ (HNL) ፬ኛ. የጋምቤላዎች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (GPDM) እና ፭ኛ. የቤንሻንጉልና ጉምዞች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (BGPDUF) ናቸው። እንግዲህ እኒህ እንዴት ተዋቀሩ? በምን ተገናኙ? እና የመሳሰለውን ለመመለስ፤ ወደ ጀማሪው ድርጅት ፊታችን ማዞር ይኖርብናል።

ከኢትዮጵያ ተገንጥዬ የራሴን መንግሥት እመሰርታለሁ ብሎ የተነሳው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ከተቋቋመ በኋላ፤ በትግራይ ውስጥ ያለኔ ሌላ ድርጅት መኖር የለበትም የሚል ስሌት ይዞ፤ መጀመሪያ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባርን (TLF) ደመሰሰ። ቀጥሎ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊትን (EPRP) ከትግራይ ወግቶ አስወጣ። በመጨረሻም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረትን (EDU) በታተነ። በተጨማሪም የሁለት ነፃ አውጪ ግንባሮች መፋለሚያ ታዛ በነበረችው ኤርትራ ውስጥ በመግባት፤ የኤርትራዊያን ነጫ አውጪ ግንባርን (ሸዓብያ – EPLF) በማገዝ፤ የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባርን (ጀብሃ – ELF) አብሮ ወግቶ ደመሰሰ።

ይህ ነው አሁን ኢሕአዴግ በመባል የሚታወቀው ድርጅት። ኢሕአዴግ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የመግዣ ስሙ ነው። ይህ ድርጅት በፈጠራቸው ድርጅቶችና በራሱ ስም ሀገሪቱን ይገዛል። እያንዳንዱ የተፈጠረ የስብስቡ አባል ድርጅት፤ የራሱ የሆነ ክልል አለው። የራሱ “የተወሰነ” ነፃነት አለው። የራሱ የሆነ “ሕዝብ” አለው። እናም ሊያሳድገው ወይንም ሊያጠፋው የሚችለው፤ ተገዥ ወገን አለው። ታዲያ ይህ ሁሉ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ሥርና ፈቃድ ነው። እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን፤ የኅብረተሰብ ሕልውናና የፖለቲካ ድርጅቶች ክስተት፤ በዕለት ተዕለት ግንኙነትና በፖለቲካ ገበያ ሥምሪት ልውውጥ፤ የራሱ የሆነ የእምርታ ዕድገት ሂደት ያገባና፤ ባልተጠበቀ መንገድ፤ ጉልበት ያበጃል። ትናንት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አዛዥ ናዛዥ የነበረበት እውነታ፤ ሀገሪቱን በማስተዳደር ሂደቱ ላይ፤ ያዝዛቸው የነበሩት የፈጠራቸው ድርጅቶች፤ አንጻራዊ ነፃነት ማበጀታቸውና፤ ጡንቻቸውን ማፈርጠማቸው፤ አይቀሬ የኅብረተሰብ ክንውን ግዴታ ነው። እናም ዛሬ ብቅ ብቅ እያለ የምናየው የዚህን ሂደት ገጽታ ነው።

እኒህ በኢሕአዴግ ስም የተካተቱ ድርጅቶች፤ በመካከላቸው፤ ከሚመሳሰሉብት የሚለያዩበት ጉዳይ ይበልጣል። በመጀመሪያ፤ ሁሉም የሚወክሉት የየራሳቸው የተለያየ ክፍል አላቸው። እናም እያንዳንዳቸው ተጠሪነታቸውም ሆነ ተቆርቋሪነታቸው ለየብቻ ለየራሳቸው ክልል ነው። እያንዳንዳቸው በውስጣቸው የሚያስተዳድሩት፤ ከፌዴራሉ ጣልቃ ገብነት ነፃ የሆነ የራሳቸውን ክልል ነው። እናም የፌዴራል መንግሥቱ፤ በፈቃደኝነት ያሉበት የስብስብ መዋቅር ነው። ይሄ ምን ያህል ሊቆይ እንደሚችል መገመቱ ከባድ አይደለም። አንድ ሆነው ለመቆየት ምክንያቱ የለም። እስካሁን ያቆያቸው ደርግ፤ ማስፈራሪያነቱ አደፈ። አማራን ማጥቃቱ ማሰባሰቢያነቱ ሻገተ። “እኔ የበላይ ልሁን!” “የለም እኔ የበላይ ልሁን!” የሚለውና፤ “እኔ ይሄ አለኝ!” “አንተ ይሄ ይጎድልሃል!” የሚል ፉክክር በቦታው ተተካ። እስካሁን የነበረው የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መፍራትና የታዘዙትን ማድረግ ብቻ የነበረው እውነታ፤ እያደር በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ላይ ጥላቻና ቁጭት ተተክቷል። አንድ ሊሆኑ አይችሉም። በፍርሃት የተወጠረው ረገበ። በቦታው የጥላቻ ጥርስ ተነከሰ። እስካሁን የሚደረገው ማንኛውም የፌዴራል ጉዳይ፤ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የጉልበት የበላይነት ነበር። አሁን ተለወጠ።

የክልሎችን ቦታ ወስኖ ያስቀመጠው ይሄው ፈጣሪና ፈላጭ ቆራጭ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ነበር። በክልል አወቃቀር ላይ፤ ማንኛቸውም ቢሆኑ ደስተኛ አይደሉም። ትናንት የትግራይን ክልል ለማበልጸግ ብሎ በጉልበቱ ከአማራው ክልል ቆርሶ የወሰደውን፤ የወልቃይት፣ የሁመራ፣ የጠለምት፣ የጠገዴ፣ የወሎ መሬት፤ ነገ የአማራው ክልል ገዥ የኔ ነው ቢል፤ ሊገርመን አይገባም። በፍርሃት ፈንታ ድፍረት፣ በመታዘዝ ቦታ ጥላቻ ነግሷልና! ለአዲስ አበባ አስተዳደር ከኦሮሞ ክልል ቆርሶ የወሰደውን መሬት የኦሮሞ ክልል ገዥዎች እንወስዳለን ቢሉ፤ ሊገርመን አይገባም። በደቡቡ ክልል ውስጥ ያሉት የተለያዩ ወገኖች፤ በውስጣዊ የደንበር መካለል ምክንያት ግጭት ማድረጋቸው አይቀሬ ነው። ለምን ቢባል ሁሉን ያደረገው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ በላያቸው ላይ የጫነው የይስሙላ ጥብቆ እንጂ፤ ሕዝባዊ መሠረትና ድጋፍ እንዲኖረው የአካባቢውን ሕዝብ ተሳትፎና ድጋፍ ያልጠየቀ ነበርና! ደግሞም በየክልሉ ያለ አስተዳደር፤ በጉልበት ያፈተተውን በማድረግ በደል ቢፈጽም፤ ለፌዴራሉ ገዥ ክፍል፤ በውስጥ አስተዳደሬ ጣልቃ አትግባብኝ ብሎ አንገቱን ቢያቀና፤ አያስደንቅም። አክሱም ለወላይታው ምኑ ነው ተብሏልና፤ ሞያሌ ላይ የደቡቡ ክልል አስተዳደር ከኬንያ በኩል ችርግ ቢገጥመው፤ ሞያሌ ለፌዴራል መንግሥቱ ምኑ ነው? ይባል ይሆን? በባጀት ቢጣሉ፣ በሕዝብ ቁጥር ቢነታረኩ፣ በክልል ደንበር ቢጋጩ፣ በፌዴራሉ ውክልናቸው፤ “እኔ የበላይ!” “እኔ የበላይ!” ተባብለው መኳረፉ፤ አይቀሬ ነው።

በርግጥ በፌዴራሉ ደረጃ፤ የኔን አባል አትሰሩ፣ የኔን አባል አትክሰሱ መባባሉ ታይቷል። እስከዛሬ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አባላት ብቻ የፈለጋቸውን ሲያደርጉ፤ የሌሎቹ አባላት አንገታቸውን ደፍተው መቀበላቸው ያለ ነበር። ይህ ግን ጧፉ በርቶ፤ ሰፈፉን አቅልጦ ጨርቁን አቃጥሎ ጨርሶ፤ በርሃኑ እየጠፋ ነው። ስለዚህ፤ በፌዴራሉ ለሚደረግ ማንኛውም ውሳኔና ተግባር፤ ተፎካካሪዎች እንጂ ተደጋጋፊዎች አይደሉም። ለፌዴራል ጉዳይ ሲሰለፉም፤ “እኔ ምን አገኛለሁ?” ከሚል እንጂ፤ “እስኪ ‘ሌሎች’ ምን ቸግሯቸዋልና ልርዳቸው!” ከሚል አይደለም። ስለዚህ ተፎካካሪዎች ናቸው። እስካሁን በአንድነት ያሰለፋቸው፤ የደርግ ማስፈራሪያነት ነበር፤ አበቃለት። ቀጥሎ የተተካው ከደርግ ወጥቶ የፀረ-አማራ አቋምቸውና የዚሁ ወገን ፍራቻቸው ነበር፤ ይህን ወገን እስኪቻላቸው ድረስ አጠቁት። አሁን ምን አለ ሊያዋህድ ቀርቶ እንዲተባበሩ የሚያደርጋቸው? ምንም! ስለዚህ እኒህ ተፎካካሪ ድርጅቶች የጥቅም ግጭት ነው በመካከላቸው የተረፈው። እናም አንደኛው ሌላኛውን መወንጀል ይከተላል። ከውስጡ መፈረካከስ ይቀጥላል። በዚህ ላይ፤ ወጣት አባሎቻቸው፤ ፍጹም የየግል ክልላቸውን የበላይነት ለመጠበቅ የሚቆሙ ይሆናሉ። የተማሩት ይሄንኑ ነውና! እናም ጠባብነት ንጉስ ይሆናል። ግጭቱ አይቀሬ ነው። ይሄንን ለማርገብና ጊዜ ለመግዛት፤ አጭር እርምጃ መውሰድ ይቻላል። ነገር ግን፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ነባር አባላት፤ ይህ እንዳይሆን፤ የነሱን የበላይነት ለወጣት አባሎቻቸው እያስተማሩ ያሳደጉበት ሀቅ ስላለ፤ ራሳቸው ራሳቸውን አስረውታል። ወደኋላ ቢሉ በራሳቸው ወጣት አባላት የሚመቱት እነሱ ናቸው። እናም ወደፊት መግፋት ብቻ ነው ያላቸው ምርጫ።

ከዚህ ተነስተው፤ “ሌሎች” ክፍሎች ወታደራዊና የፖሊስ ኃይሎቻቸውን ማቋቁምና የውጭ ግንኙነታቸውን መመሥረት ተከታዩ እድገታቸው ነው። እስከዛሬ ይህ ሁሉ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ፍላጎትና እምነት የሚካሄድ ነበር። የአማራዎች፣ የኦሮሞዎች፣ የደቡብ ኢትዮጵያዊያን ሆነ የሌሎች አናሳ የተባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች መስራች፤ ይሄው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ነው። እናም ምን ጊዜም ቢሆን፤ ማንኛውም መዋቅር ሆነ የሂደት ውሳኔ፤ ለዚህ ወገነተኛ ቡድን ፍላጎት ተገዥ ካልሆነ፤ የመጀመሪያው አኩራፊ፤ ይሄው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ይሆናል። በመጀመሪያ ግጭቱን ፈጣሪ፤ ጥቅሜ ቀረብኝ በማለት፤ ይሄው ድርጅት ይሆናል። የመጀመሪያው ተገንጥሎ ለብቻው የሚሮጠውም ይሄው ድርጅት ነው። ለዚህም ከወዲሁ፤ ፌዴራላዊ የሆኑ ውሳኔዎችን፤ ክልሉን እንዲጠቅሙ አዘጋጅቷል። የዓለም አቀፍ አየር ማረፊያውን በትግራይ አዘጋጅቷል። ወታደራዊ ማዕከሎችን በትግራይ አቋቁሟል። በትምህርት የትግራይ ወገኖቹን በበላይነት አሰልፏል። አሁን ደግሞ የባቡር ሐዲድ ለትግራይ እንዲገባ፤ ፌዴራላዊ ወጪውን አስሸፍኗል። የሱዳን በር እንዲኖረው ከአማራው መሬት ጠቅልሎ ወስዷል። የሀገሪቱን ንብረት፤ በኤፈርት በኩል እጠቃሎ ትግራይ አግብቷል። ወሳኝ የፌዴራል መንግሥቱ ቦታዎች በሙሉ በአባላቱ ቁጥጥር ሥር ናቸው። ለስም እንኳ ከ”ሌሎች” ድርጅቶች የተወከሉ ሰዎች በኃላፊነት ላይ ቢቀመጡም፤ የወሳኝነቱን ሚና የሚጫወቱት፤ የዚሁ ድርጅት አባላት ናቸው። ስለዚህም የተስተካከለ የእኩልነት አሰራር በሌለበት ቦታ፤ አይቀሬው ግጭት ብቅ እያለ ነው። ይህ ከውጪ በሚደረግ ግፊት ሳይሆን፤ በራሱ በአደረጃጀቱና ( ማለትም፤ በዋናው በ”እኔ” ባዩ ድርጅትና በ”ሌሎች” ድርጅቶች መካከል ባለ አደረጃጀት ) በሂደቱ ምክንያት አይቀሬ ሆኖ የሚታይ ሀቅ ነው።

እንግዲህ በክልሎቹ መካከል የሚነሳው ግጭት ለሀገሪቱ ከፍተኛ አደጋ አለው። ይህ ወደ ሶስተኛው ነጥብ ይወስደናል። ሶስተኛው ገጦ የሚታየው እውነታ፤ አሁን በያዝነው ሂደት፤ ሀገራችን እጅግ ወደ ከፋና ልትወጣበት ወደማትችለው መቀመቅ ውስጥ እየዘቀጠች መሆኗ ነው። የክልሎች መጋጨት፤ የማይሰራ የፌዴራል መዋቅር ከላይ ተቀምጦ፤ ጉልበተኛ የክልል ገዥዎች የፈለጉትን የሚያደርጉበትን ሀቅ ያሳየናል። የኢትዮጵያ መንግሥት የሚባለው በኖ ይጠፋል። እኒህ የየክልል ገዥዎች ደግሞ፤ በምንም መንገድ በስምምነት ጎረቤት እንኳን ሆነው የሚኖሩበት ሁኔታ እንዳይኖር፤ በጠላትነት የሚፋረጁ ስለሚሆን፤ በመካከላቸው የማይበርድ ጦርነት አይቀሬ ነው። የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የአካባቢ ንብረት መመንመን ወይንም አዲስ ሀብት በአንዱ አካባቢ መገኘት፣ ከውጪ በሚደረግ የጥቅም ድጋፍ አንዱ ከሌላው በልጦ መገኘት፣ በሃይማኖት ምክንያት በጎረቤት ክልሎች መካከል የሚፈጠረው ልዩነት መስፋት፣ ክልሎችን የበለጠ እንዲራራቁና አክርረው እንዲጋጩ ያደርጋል። ይህ ነው የነገዋ የሀገራችን የኢትዮጵያ ጣጣ። “እኔ የበለጠ ላግኝ፤ የለም እኔ የበለጠ ላግኝ!” በሚል የተጣሉ ክልሎች፤ ከተለያዩ በኋላ ፍርሻው የሚያስከትለው መዘዝ፤ የማይጨበጥ እሳት ነው። ይህ ሁሉ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የፖለቲካ ቀመር ውጤት ነው። ውጤቱ ደግሞ አይቀሬ ነው።

መዝጊያ፤

ውጤቱ ቢያስፈራንም፤ በሀገራችን ላይ ከላይ የተጠቀሰው አደጋ የመከሰት እድሉ ያየለ ነው። በሂደት የዚህ ድርጅት የፖለቲካ ስሌት ሊስተካከል ሲገባው፤ አክራሪ የሆነው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ በጀመረው ጠባብ ዓላማ አሁንም መግዛት ስለያዘ፤ መገራት አቃተው። እናም ለዚህ አይቀሬ እውነታ ዳርጎናል። በርግጥ ስለማንፈልገው፤ ሊሆን አይችልም ብለን ልንሸመጥጥና ልንክደው እንችላለን። ይሄን ጸሐፊም ማብጣልጣል እንችላለን። ያ ግን፤ ሊሆን አደግድጎ የመጣውን ሀቅ፤ አይለውጠውም። ይልቅስ አሁን በቁጥጥራችን ሥር ያለውንና ማድረግ የምንችለውን መጀመር አለብን። በቁጥጥራችን ሥር ያለውና ማድረግ የምንችለው፤ በመጀመሪያ፣ የትግሉን ምንነት በአንድነት መቀበል ነው። ይህ ትግል የነፃነት ትግል ነው። ይህ ትግል የኢትዮጵያዊያን በሙሉ ትግል ነው። ይህ ትግል የዛሬ ነው። ይህ ትግል ከያንዳንዳችን የሚጠብቀው አስተዋፅዖ አለ። በመሳተፍ እናበርክት።

ይህን ትግል በአንድነት የምናደርገው እንጂ፤ እያንዳንዱ ድርጅት ለየራሱ ባፈተተው የሚጋልብበት ሜዳ አይደለም። እናም የትግሉ የመጀመሪያ አጭር ግብ፤ ታጋዮችን በሙሉ ወደ አንድ አሰባስቦ አንድ የትግል ማዕከል መፍጠር ነው። እናም በሀገራዊ ራዕይና ተልዕኮ፣ በጥቂት የመታገያ ዕሴቶች ዙሪያ መደራጀቱ፤ ግዴታ ነው። ይህን ግድ የሚለው፤ ተጨባጩ የሀገራችን የፖለቲካ እውነታ ነው። ዋናዎቹ ታጋዮች ያሉት በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ከፍተኛውን መስዋዕትነት በመክፈል፤ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጋር ሌት ተቀን በኑሯቸው እየተገደዱ፣ እየተሰቃዩ፣ በእስር ቤት እየተንገላቱ፣ መታገያ ሰላማዊ ድርጅቶቻቸውን እየተቀሙ፣ ያሉት ሕዝቡና የሕዝቡ ታጋይ ልጆች ናቸው። ትግላቸው መስተካከል አለበት። ሰላማዊውን ትግል አንድ ድርጅት ብቻ ነው ሊመራው የሚገባ። በአንድ ሀገር ሁለትና ሶስት ሰላማዊ ትግል የለም። ግቡ ውስንና የጊዜው ገደብ ያለው የትግል አንድነትና መታገያ ድርጅት ነው ሊኖረን የሚገባ። አንድ ትግልና አንድ መታገያ ድርጅት ብቻ ነው የሚኖረው። አንድ የትግል ማዕከል እስካልተፈጠረ ድረስ ደግሞ፤ በተናጠል የምናደርገው ትግል፤ በተናጠል መመታትን ነው የሚጋብዘው። ትግሉ አንድ ነው። መታገያ ድርጅቱም አንድ መሆን አለበት። ይሄን እስካልተቀበልን ድረስ፤ የገዥውን እድሜ እያራዘምን ነው።

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in አስተያየቶች - Commentaries. Bookmark the permalink.

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s