የሰላም ትግሉ በኢትዮጵያ (ክፍል ፪)

የሰላም ትግሉ በኢትዮጵያ (ክፍል ፪)

ረቡዕ፤ ሰኔ ፲ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህቱረት ( 6/17/2015 )

በክፍል አንድ፤ የሰላማዊ ትግሉ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ምን እንደሆነ ገልጫለሁ። በዚሁ ላይ፤ የሰላማዊ ትግሉ ከተወዳዳሪ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ጋር ያለውን ልዩነት አሳይቻለሁ። በተጨማሪ ደግሞ፤ የሰላማዊ ትግሉ የሚካሄደው በአንድ የሕዝባዊ ንቅናቄ ድርጅት ሥር ብቻ መሆኑንና፤ አማራጭና ተለዋጭ እንደሌለው አስምሬበታለሁ። በሂደቱ መሰባሰቢያ የሆኑትን ሀገር አቀፍ የትግል ዕሴቶች አስቀምጫለሁ። በዚህ በክፍል ሁለት ደግሞ፤ ስለተሳሳተው የሰላማዊ ትግሉ ግንዛቤያችን አስረዳለሁ። ባጠቃላይ፤ የሰላም ትግሉ ከትጥቅ ትግሉ አኳያ ለምን እንደሚመረጥ በግልጽ አሰፍራለሁ። በማጉላትም በአሁኑ ሰዓት፤ የሰላማዊ ትግሉ አማራጭ የሌለው ብቸኛ የትግል መንገዳችን እንደሆነ አመላክታለሁ።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ስለሚካሄደው ሰላማዊ ትግሉ ያለን ግንዛቤ ጉድለት አለው። አንዳንዶቻችን፤ ገዥው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ስለሚያስር፣ ስለሚገድል፣ ከሀገር ስለሚያሳድድ የሰላማዊ ትግሉ አይሠራም እንላለን። ሌሎቻችን ደግሞ፣ በምንም መንገድ፤ ገዥው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ወዶ ሥልጣኑን ስለማይለቅ፤ በምርጫ መሳተፉ ዋጋ የለውም፤ ስለዚህ የትጥቅ ትግሉ ብቻ ነው የሚያዋጣ፤ በማለት ሰላማዊ ትግሉን እናዋድቃለን። ይህ በመሠረቱ በሀገራችን ያለውን አስከፊ የፖለቲካ ሁኔታ ከመመልከትና ይህ የገዥ ቡድን ላንዴም ለሁሌም እንዲወገድ ከመፈለግ የተነሳ መሆኑ ግልጽ ነው። ችግሩ ግን ፍላጎት የታሪክን ሞተር አያሽከረክርም። ተጨባጩ የሀገራችን እውነታና ያንን ለመለወጥ በቦታው የዋለው ተግባር ነው፤ ሂደቱን የሚነዳው።

ትግሉ በአምባገነኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ነው። ትግሉ በሀቅ ያለ ነው። ትግሉ አንድ ነው። በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በኢትዮጵያ ካለው ሰላማዊ ትግል ባሻገር ያለውን በማካሄድ ላይ ያሉት፤ አንድም የዚህ ወይንም የዚያ አካባቢ ነፃ አውጪ ግንባር ናቸው፤ አለያም ይህ ወይንም ያ ድርጅት ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ አሰባስቦ በአንድ ያሰለፈ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ድርጅትም ሆነ ጦር የለም። ስለዚህ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ወገን፤ የገዥው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ደግሞ በሌላ ወገን የተሰለፈበት ትግል አልተያዘም። እናም ይህ እስካልሆነ ደረስ፤ ትግሉ የሕዝቡ አይደለም ማለት ነው። በርግጥ ሁሉም ድርጅቶች የሕዝብ ነን ማለታችውና ለሕዝብ ነው የምንታገልው ማለታቸው አይካድም። ለሕዝብ ከሆነ የሚታገሉ ከሆነ፤ ለምን በአንድ አይሰባሰቡም? ይህ የሕዝቡ የነፃነት ትግል የማይሆነው፤ የሚታገሉት ለራሳቸው ጠባብ የግል የድርጅታቸው ዓላማና ግብ ስለሆነ ነው። በራሳቸው ጠባቡ የድርጅት ፍላጎትና በሕዝቡ ፍላጎት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። አለያማ ሁሉም የሕዝቡን ፍላጎት እንከተላለን ካሉ፤ በአንድ ይሆኑ ነበር። እንግዲህ በዚህ ጠባብ የድርጅት መነፅር ሁሉንም ነገር ስለሚመለከቱ፤ የድርጅቶች መፍትሔ ከዚሁ ይመነጫል። ሕዝቡ ነፃ የሚወጣው፤ ራሱ ሕዝቡ በአንድነት ሲታገልና የሕዝቡ የሆነ አንድ ድርጅት ብቻ ሲኖር ነው።

ከሰላም ትግሉ ውጪ ባሉት የሚታገሉ ድርጅቶች እምነት፤ የነሱን ድርጅት የበላይ አድርጎ የማያስቀምጥ የትግል ሂደት ሁሉ፤ “ትክክል” አይደለም። ለዚህ ነው ሰላማዊ ትግሉን የሚኮንኑት። በትክክለኛ መንገድ መኮነንም ተገቢ ይሆናል። ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ መኮነን ግን ተገቢ አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ፤ ገዥውን ክፍል ለማስወገድ የሚደረግ ንቅናቄ እንጂ፤ ገዥውን ለመተካት የሚደረግ ሩጫ አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ፤ ያለው የገዢ ቡድን መወገድ አለበት ብሎ የተነሳ ሕዝብ፤ የሚወስደው የፖለቲካ እርምጃ ነው። ማንኛውም የትግሉ እንቅስቃሴ፤ በመሳተፍ ተወዳድሮ ለማቸነፍ ሳይሆን፤ የውድድሩን መድረክ፤ ሕዝቡን ለመድረሻና ለመቀስቀሻ ለመጠቀም ነው። ሰላማዊ ትግል ሽርሽር አይደለም። መስዋዕትነት ይከፈልበታል። የኛ ታጋዮች በከፍተኛ ደረጃ እየከፈሉበት ነው። ሳሙዔል አወቀ ከፍተኛውን መስዋዕት ከፍሏል። ሌሎች ቀድመዉታል፤ ሌሎችም ይከተሉታል። ለዚህ ነው ይህ ገዥ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መወገድ ያለበት። እና “ምርጫ ተወዳደረን እንድንጥለው ካልፈቀደልን፤ ሰላማዊ ትግሉ አበቃለት!” ማለት፤ ሰላማዊ ትግልን አለማወቅ ሳይሆን፤ ሆን ብሎ ማደናገር ነው። ሰላማዊ ትግል፤ በምርጫ ለማቸነፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ ይደለም። በምንም መንገድ በምርጫ የሚቸነፍና ወዶ ሥልጣኑን የሚለቅ አምባገነን ጠላት የለም። ለዚህም ነው ሰላማዊ ታጋዮችን በበለጠ ጠላት ብሎ ፈርጆ፤ ከሌሎች ታጋዮች በከፋ ሁኔታ የሚጨፋጭፋቸው። ይህ መስዋዕትነት፤ ለትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ሞቱ መቃረቡን የሚያበስረ ደዎል ነው።

እኔ የሰላማዊ ትግሉን የምቀበለው፤ ፍጹማዊ ከሆነ ከትጥቅ ትግሉ ይበልጣል ከሚል ድርቅ ያለ እምነት ተነስቼ አይደለም። በምንም መንገድ ትጥቅ ትግልን አልኮንንም። በአሁኑ የኢትዮጵያ የትግል አሰላለፍ ግን፤ የቅንጣት ታክል ማመነታታት ሳይኖረኝ፤ የሰላማዊ ትግሉ ያላማራጭ ብቸኛ መንገዳችን ነው እላለሁ። ለምን? አሁን አንድ የሆነ የትግል ማዕከል የለንም። እያንዳንዱ ድርጅት፤ ለድርጅቱ ግብ የሚታገልበት ሀቅ ነው ያለው። የታጠቀ ኃይልም ቢኖረው፤ የራሱና ለራሱ ግብ የሚጥር ነው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ለግሉ ታጥቆ፤ ታግሎ ሥልጣን ጨብጧል። የያንዳንዱ ድርጅት ትግል፤ ያንን ለመተካት ነው። ውጪሰው ኢትዮጵያዊ ታጋዮች ደግሞ፤ አንድነት ከመመስረት ይልቅ፤ በመከፋፈልና እርስ በርስ በመነካከስ፤ ቁጥራቸው የበዙ ድርጅቶችን መሥርተን፤ በሕዝቡ ትግልና ድል ላይ ልናደርግ የምንችለው አስተዋፅዖ አመንምነነዋል። ዋናውን ጉዳይ ትተን በጠባብ ዕይታችን ታፍነን፤ ሩቅ ማየት አቅቶን ዓይናችን ስለጨፈን፤ የትግሉ ባቡር፤ ጓዙን ጠቅልሎ ጥሎን እየሄደ ነው። እርስ በርስ መነኳኮሩ ጥሞናል። ከዕለት ዕለት መበጣጠስና መቀናነሱ አልቆረቆረንም።

አሁንም ባለንበት ስናዘግም፤ ትግሉ እኛን ታግሎናል። ይልቁንም ከኛ ተከትለው የትግሉን ችቦ የሚያበሩት ታጋዮች፤ መልሰው መላልሰው እንደኛው በተለመዱት፤ ሀገር ወይስ ድርጅት፣ የሰላማዊ ትግል ወይስ የትጥቅ ትግል፣ ከውጭ መደራጀት ወይስ በሀገር ቤት መንቀሳቀስ፣ ከኤርትራ መነሳት ወይስ ኤርትራን በጠላትነት የትግሉ አካል ማድረግ፣ በየግል ድርጅቶች መታገል ወይስ የትግል ማዕከል መፍጠር፤ በሚሉ አንድ ቦታ ላይ በማይደመደሙ ንትርኮች እንዳይጠመዱ ያሰጋኛል። ከዚህ ወጥተውና የእስከዛሬውን ትግል መርምረው፤ ትምህርት በመውሰድ፤ የአንድነት ትግል የሚያደርጉበትን ሁኔታ ማስተካከል አለብን። ይኼን የማቀርበው፤ በትግሉ ሳይሆን፤ አሁን በውጭ ባለነው ታጋዮች ያለኝ እምነት እየመነመነ በመሄዱ ነው።

ሰላማዊ ትግል፤ ለሚታገሉለት ሕዝብና ሀገር፤ ለኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያ፤ የመጨረሻ ከፍተኛውን ቦታ በመሥጠት፤ ከግለሰብ የኔነት ጋር የተያያዙትን በሙሉ፤ የግል ጥቅም ሆነ የድርጅት ግብ ወደ ኋላ ገፍቶ፤ ቅድሚያ ለወገንና ለሀገር የሚሠጡበት የተባበረ የአንድነት ትግል ነው። ትግሉ፤ ገዥውን ወገንተኛ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አምባገነን መንግሥትን ድል ማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ የሚከተለውን ሥርዓት ወሳኝ የሆነ ነው። ትግላችን ከፍተኛ ጥንካሬን ይጠይቃል። ትግላችን ወሰን የለሽ ትዕግስትን ይጠይቃል። ሞትን መናቅን ይጠይቃል። ይህ ሰላማዊ ትግል፤ የሕዝቡ ትግል ነው። ሰላማዊ ትግል፤ ታጋዮች በሕዝቡ መካከል ተገኝተው፣ የአካባቢው አካል ሆነው፣ የአካባቢው ብሶት የራሳቸው ብሶት ሆኖ፣ ከተባሰው ጎን ተሰልፈው፣ ከፍተኛውን መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚያካሂዱት ትግል ነው። የድርጅቶች ትግል አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ በሕዝቡ የሚደረግ ነው። ሰላማዊ ትግሉ ሁሉን አስተባባሪ ነው። የማንም የግል ድርጅት ንቅናቄ አይደለም። የሰላማዊ ትግሉ ደጋፊ ብዙ ነው። ሰላማዊ ትግል የተወሰነ አባልነትን ብቻ ያነገበ የአንድ ክፍል ጥረት አይደለም። ሰላማዊ ትግሉ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪሰው ኢትዮጵያዊያን ዘንዳ ድጋፍና ተቀባይነትን ይሻል። በዚህ ዓይን ስንመለከተው ነው፤ የኛን አስተዋፅዖ ትርጉም የምናበጅለት።

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in አስተያየቶች - Commentaries. Bookmark the permalink.

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s