ለፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ምስክርነት

ለፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ምስክርነት
አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ
ሐሙስ፤ ግንቦት ፲፫ ቀን፤ ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህረት ( 5/21/2015 )

ሰሞኑን በታጋዩ ወገን ስለ ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ብዙ እየተወራ ነው። ገና ብዙ እንደሚወራም አጠያያቂ አይደለም። ለምን ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ በኛ ትግል ሂደት፤ ይሄን የመሰለ ቦታ ይዘው እንደተገኙ፤ ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው። ነገር ግን፤ ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸው ስለኢትዮጵያና ስለሚደረገው ትግል ያላቸው ሃሳብ ተዘግቧል። በአንጻሩ ደግሞ ስላሳቸው የኢትዮጵያ ጠላትነትና የትግሉ እንቅፋትነት ምስክርነት የሠጡ አሉ። በዚህ ሂሳብ፤ እስኪ እኔም በውል የማውቀውን ላቅርብ።

የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ለመጀመሪያ ጊዜ ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይት በገባ ጊዜ፤ ሸረላ ላይ ጦርነት ገጥመን ክፉኛ ቆስዬ ነበር። በዚህም ምክንያት፤ የነበርኩበት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት በጣም ተመናምኖ፤ ሕልውናው አስጊ በሆነበት ሰዓት፤ ለመሰባሰብ፤ የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር – ጀብሃ – ወደሚቆጣጠረው የኤርትራ ምዕራባዊ ቆላ ክፍል – ባርትያ – ሄደን። ከዚያ መጠናከሪያ የሚሆኑ ዝግጅቶች ከተደረጉ በኋላ፤ አዲስ ዕቅድ ወጥቶ፤ ወደ አዲስ አካባቢ ለመንቀሳቀስ ውሳኔ ላይ ተደረሰ። እኔ በነበርኩበት ሁኔታ፤ እዚያው በቦታው ላይም ተደራቢ በጥይት የመቁሰል አደጋ ስለደረሰብኝ፤ ለሕክምና ወደ ከሰላ ተላክሁ። ሠራዊቱ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በሚቆጣጠረው የወልቃይት በረሃማ ክፍል አቋርጦ፤ ወደ ቆላ ወገራ ሲሄድ፤ እኔ በጅብሃ የጭነት መጓጓዣ፤ በሀይኮታ በኩል አልፈን ወደ ከሰላ ተጓዝኩ።

እዚያ በሕክምና ላይ ወደ ስምንት ወራት ቆየሁ። በወቅቱ ሐኪሞቹ፤ በችኮላ የተጠገነው ስብራቴን መልሰው አፍርሰው ለመጠገን ብቃቱና መሣሪያው ስላልነበራቸውና ባለበት ሁኔታ ሊያስከትል የሚችለውን የጤንነት አደጋ አስመልክተው፤ ወደ አውሮፓ መሄድ ይኖርብሃል አሉኝ። ለኔ አውሮፓ መሄዱ ቀርቶ፤ ሱዳን ያን ያህል ጊዜ መቆዬቴ በጣም አሳስቦኝ ስለነበር፤ ምልከታቸውን አልተቀበልኩትም። በርግጥ ይሄን ጉዳይ እኔም ሆነ የጀብሃ ሐኪሞች የምንወስነው ሳይሆን፤ የኢሕአፓ አመራር የሚወስነው ጉዳይ ነበር። በዚህ ወቅት ብዙ የጀብሃ ታጋዮችን ተዋወቅሁ። በጎልዳፋ ትግርኛዬና በእንግሊዝኛ ነበር ልውውጣችን። አንድ ቀን፤ ከቀይ መስቀል ሐኪም ቤት ቆይቼ፤ ወደ መሐል ከተማው ስጓዝ፤ አንድ የጀብሃ የነበረ ታጋይ፤ ከሩቅ ተከተለኝ። ሻሂ ቤት ገብቼ ሻሂ አዘዝኩ። ይህ ሰው በቀጥታ ወደኔ መጣና፤ በትግርኛ፤ አውቅሃለሁ አለኝ። መቼም ሁሉን ከትግል ጋር የተያያዘ መተዋወቅ አስቀድሜ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ የተመሠረተ አድርጌ ሰለምወስደው፤ “ዩኒቨርሲቲ ነው?” አልኩት። “ አይኮነን!” አለኝ። የሁለተኛ ደረጃ መምህር ሆኜ ለጥቂት ዓመታት ሠርቼ ነበርና፤ “አስተማሪ ሆኜ ብዙ ቦታ ሠርቻለሁ።” አልኩት። በአረብኛ እሱም አይደለም አለኝ። በትግርኛውም ሆነ በአረብኛው ከጥቂት የመተዋወቂያ ቃላቶች የበለጠ የሚያስኬድ እውቀት አልነበረኝምና፤ ባጭሩ “ታዲያ የት ነው የምንተዋወቀው?” በማለት በአማርኛ መልሼ እሱኑ ጠየቅሁት። “አነ ወዲ ትኳበዬ!” አለኝ። ይሄም ብዙ አላስኬደኝም። በመጨረሻ፤ “የአየር ማረፊያ ልጅ ነኝ! የታናሽ እህትህ የክፍል ጓደኛ ነኝ! አዘዞ የወታደር ልጅ ነኝ!” ሲለኝ፤ ፊቱ በቀጥታ ታወሰኝ። “ፍስሃ! ምነው በአማርኛ አታናግረኝም!” አልኩና ተቃቅፈን ተሳሳምን። “ከላስ አማርና ጠፊኡ!” አለኝና አረፈ።

ለረጅም ጊዜ አማርኛን ተጠቅሞ ስለማያውቅና፤ ከትግርኛው ባሻገር አረብኛ የመነጋገሪያ ቋንቋው ስለነበር፤ አማርኛ ፍጹም እንደረሳ ነገረኝ። ወሬያችን አላልቅ ብሎ፤ ዓይን እስኪይዝ ድረስ አብረን አመሸን። በመጨረሻም አንድ በጣም ከበድ ያለ ጉዳይ እንዳለውና መገናኘት እንደሚያስፈልገን ነገረኝ። እኔም ጥሩ ነው፤ እንዲያውም ጊዜዬን የማሳልፍበት አጥቼ፤ መጽሀፍ ሳገኝ፤ በማንበብ፤ አለዚያ ደግሞ፤ ከጥላ ሥር ተቀምጨ እንደማሳልፍ ገልጨለት፤ በበነጋታው ልንገናኝ ወሰን። በበነጋታው ሙሉ ቀኑን አብረን ዋልን። ከባድ ያለውን ጉዳይም አስረዳኝ። እሱ መንክዓ ተብሎ ከጀብሃ እንደተባረረ ገለጸልኝ። ጊዜው በፈረንጆቹ 1980 ሲሆን፤ በኛ አቆጣጠር ደግሞ ፲፱፻፯፫ ዓመተ ምህረት ነበር። እኔም በተባራሪ ካልሆነ በስተቀር፤ ስለ መንክዓ ብዙም አላውቅም ነበርና፤ በደንብ እንዲያብራራልኝ ጠየቅሁት። እሱም እስክጠግብ መገበኝ። ቀጥሎ ይህ የጀብሃ ብቻ ሳይሆን፤ የሸዓቢያም ጉዳይ እንደሆነ አስረዳኝ። እንዴት እሱ ወደ መንክዓው ክፍል እንደገባ ጠየቅሁት። እሱም ከሥር ጀምሮ አጫወተኝ።

ከአስመራ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ በነፃ አውጪ ግንባሮች ቅስቀሳና በደርግ ላይ የነበራቸው ተስፋ መጨለም፤ ብዙ ወጣቶች ወደ የኤርትራ ነፃ አውጪዎቹ ጎራ ተሰማሩ። ስለ ጀብሃና ሸዓቢያ የነበራቸው ግምት ግን የተሳሳተ ነበር። ሁለቱ የወንድማማቾች ድርጅት ይመስሏቸው ነበር። እናም ወንድማማቾች ሳይቀሩ፤ አንተ ጀብሃ ሂድ፤ እኜ ሸዓቢያ ልሂድ፤ በቅርብ አስመራ እንገባና እንገናኛለን! በመባባል ነበር ከአንዱ ወይም ከሌላው ድርጅት የተቀላቀሉት። በደስታና በተስፋ የነጎደው ወጣት፤ አስመራን ለመያዝ ጥቂት የቀራቸው የነፃነት ግንባሮች፤ እርስ በርሳቸው ግብ ግብ ገጥመው፤ ወጣቱ ሲታረድ ተመለከቱ። አንዳንዶቹም ከተማረኩት ወይንም ከሞቱት መካከል ዘመዶቻቸውንና ጓደኞቻቸውን ሲያዩ ግራ ተጋቡ። አመራሩ የሚሰብካቸውና እነሱ በልባቸው አምነው የተቀበሉት አልጋጠም አለ። እናም ውስጥ ውስጡን መነጋገር ጀመሩ። ያኔ ነበር እሱም በአካባባቢው ያሉትን ማሰባሰብ የያዘው። ባጭር ጊዜ ሙያዬ ብሎ ይዞት ብቅ አለ። ታዲያ ወዲያ ወዲህ ሲሯሯጥ፤ የጀብሃ ፀጥታ አነቀው። ከእስራት በኋላ፤ ሱዳን ደንበር አውጥተው ወረወሩት። እየተከላተመ ከሰላ ሲገባ፤ ብዙ የጀብሃ መንክዓ ጓደኞቹን አገኘ። ቀጥሎም ከሸዓቢያ በኩል ተመሳሳይ ዕጣ የደረሳቸው የቀድሞ የከተማ ጓደኞቹን አገኘ። ሲነጋገሩም በሁለቱም ድርጅቶች ተመሳሳይ ሁኔታ እንደነበር ተረዱ። ይሄን ታሪክ በዝርዝር ሲያጫውተኝ፤ የልበወልድ ታሪክ የማነብ እስኪመስለኝ ድረስ አላመንኩትም ነበር።

በሶስተኛው ቀን፤ ከሸዓቢያ በኩል፤ የመንክዓዎች ተወካይ ጋር ሆኖ መጣ። ፍስሃ ትኳበ ለጓደኞቹ ስለኔ፤ ባልፈለግሁት ደረጃ፤ በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በኢሕአፓ ስለነበረኝ ሚና፤ አጋኖ ነግሯቸዋል። እናም በዕቅዳቸው ውስጥ አስገብተውኛል። እኒህ በጀብሃና በሻዓቢያ መንክዓ ተብለው የተባረሩ ታጋዮች፤ አሁንም ለኤርትራ ያላቸው የትግል ፍላጎት አለበረደም። እናም ተገናኝተው አዲስ ድርጅት ለመፍጠር የኔን እርዳታ ፈልገዋል። ስለዚህም እኔ፤ መተዳደሪያ ደንቡንና ለድርጅታቸው መርኀ-ግብር እንድጽፍላቸው ጠየቁኝ። ይሄን ኃላፊነት ከመቀበሌ በፊት፤ አንደኛ የነበርኩበት ድርጅት የሚያምነውን፤ የኤርትራ ጉዳይ የቅኝ ግዛት አለመሆኑን ከልቤ እንደማምን ገለጽኩላቸው። እነሱ ይህ ጉዳይ እንደማያግዳቸውና፤ ይልቁንስ በጀብሃና በሸዓቢያ ውስጥ ያሉ ወጣቶች አደጋ ላይ እንዳሉ ስለሚያውቁ፤ ባስቸኳይ ድርጅት ፈጥረው፤ ወጣቶቹን ማሰባሰብ እንደሚፈልጉ ነገሩኝ። በነሱ ግምት፤ በጣም ወጣቱን ጨራሽ የሆነ ጦርነት በመካከላቸው በቅርብ ሊካሄድ ይችላል ብለው ማመናቸውን ገለጹልኝ። እናም ያንን የመስለ አደገኛ ስዕል ስላስጨበጡኝ፤ ተስማምቼ፤ ማርቀቁን ቀጥልኩ።

በዚህ መካከል ድንገት አዲስ ነገር ተፈጠረ። ብዙ የጀብሃ ወጣቶች ወደ ከሰላ መጉረፍ ጀመሩ። በሆስፒታሉም ሆነ በከሰላ ሻሂ ቤቶች፣ አዳዲስ ፊቶችን ማየት የተለመደ የዕለት ጉዳይ ሆነ። እነ ፍስሃ አንድ ቀጠሮ ሳይነግሩኝ፤ ሳይመጡ ቀሩ። ምን ተፈጠረ የሚለው ችግር አልነበረም፤ ምክንያቱም የነዚህ አዳዲስ ወጣቶች ወደከሰላ መጉረፍ ያስከተለው ጉዳይ አለ ማለት ነው ብዬ፤ በሚቀጥለው ቀጠሯችን እስካገኛቸው ዝም አልኩ። በሚቀጥለው ቀጠሮ አምስት ሆነው መጡ። ከዚህ በፊት ያላገኘኋቸው ታጋዮች መኖራቸው እንድቆጠብ አደረገኝ። እናም ዝም ብዬ ማዳመጥ ያዝኩ። ሸዓቢያ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርን ወታደሮች አስከትሎ፤ ጀብሃን ጠራርጎ ከኤርትራ ምድር አስወጥቶ እንዳባረረ ነገሩኝ። አሁን በዚህ ሰዓት፤ ደንበሩ ላይ የሱዳን መንግሥት እንዳስቀመጣቸው ተረዳሁ። በመሐል ቤት፤ ከጀብሃ አመራር መካከል፤ መላከ ተክሌን እንደሚወዱትና እሱ ሊተባበራቸው የሚችል መሆኑን ሲነጋገሩ ሰማሁ። “መላከ ተክሌ ማለት፤ ቀይ ረዘም ያለ የከረን ሰው ነው?” ስል ጥያቄ አቀረብኩላቸው። በፍጥነት፤ “እዎ! ትፈልጠው ዲሃ!” አሉኝ። እኔም አብረን የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች እንደነበርንና አብረን አንድ የመኝታ ክፍል ውስጥ እንደተጋራን ነገርኳቸው። አንደኛው ታጋይ፤ የሱ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነ ሲነግረኝ፤ ላገኘው እችል እንደሆነ ጠየቅሁት። እሱም ችግር የለም አለኝ። ቀጠሮ እንዲይዝልኝ ጠይቄው ወደ ጉዳያችን ዞርን። በሶስተኛው ቀን ቀጠሮ ከመላከ ተክሌ ይዞልኝ መጣ። ደስ አለኝ።

እነዚህ ዛሬ ከኛ ጋር የተቀመጡት፤ ታጋዩ ከታጎረበት ቦታ፤ ተወክለው ይሄን ስብስብ ለማነጋገር እንደተላኩ ሰማሁ። የጀብሃ አመራር ላይ ታጋዩ ተስፋ መቁረጡናን፤ ከሥር ያሉት ተሰባስበው የራሳቸውን ድርጅት መስርተው፤ ከሸዓቢያ ወጣቱን በመደባለቅ፤ አንድ የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር መመሥረት ዓላማቸው እንደሆነ ተረዳሁ። በዚህ መካከል፤ ከሸዓቢያ መንክዓዎች ከመጡት በኩል፤ በድርጅቱ ውስጥ ስለነበረው የኢሳያስ ሚስጢራዊ የመረጃ ክፍል በደል ዝርዝር ሰማን። የተማሩ ሰዎችና የነፃ አስተሳሳብ የነበራቸውን ታጋዮች ምን ያህል እንደሚፈራና እንደሚጠላ ሰማሁ። እግረ መንገዴን ስለመንክዓዎች ሲወራ፤ መሪ ናቸው ከተባሉት መካከል፤ የጎይቶምን የአበራሽ መልኬንና የተስፉ ኪዳኔን ስም ሰማሁ። እንደማውቃቸውና ዩኒቨርሲቲ አብሬያቸው እንደነበርኩ ገለጽኩላቸው። በተጨማሪም አደንቃቸው የነበርኩ መሆኔን፤ አበራሽ መልኬ አብሮ አደጌ እንደሆነች፤ አባቷ ሻለቃ መልኬ ያባቴ አዛዥ መሆናቸውን ነገርኳቸው። ኢሳያስ እንዴት እንዳስገደላቸው ሲነግሩኝ፤ ዘገነነኝ። ምን ያህል አረመኔ እንደሆነ ተረዳሁ። በአንጻሩ ጀብሃ የነበሩት መንክዓዎች ሽርሽር የገቡ ነበር ያስመሰላቸው። የሸዓቢያ መንክዓና የጀብሃ መንክዓ የደረሰባቸው ጭካኔ የተሞላበት በደል፤ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ነበር። ኢሳያስ ራሱን ኢሳያስን ለማመን የሚቸገር ሰው መሆኑን ነገሩኝ። አድራጎቱ ያሳደረባቸው የአእምሮ ተጽዕኖ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ፤ አሁንም የሱ መዋቅር ያሉበት ድረስ ይኖራል ብለው ፍርሃት ነበራቸው። ያን ያህል ሁሉን ነገር የሚቆጣጠርና አስሮ የሚይዝ ባህሪና መዋቅር ነበረው።

ይህ ነው ኢሳያስ አፈወርቂ። ይህ ነው ለራሱ አብሮ ታጋዮች እንኳን ቅንጣት ታክል አዘኔታ የሌለው አረመኔ። ለኔ ሌላው መንግሥቱ ኃይለማርያም ነው። የሰው ደም የሚጠማውና የሚያረካው ሰው። ይህ ሰው የሚከተለው የራሱን ፍላጎት ሊያሟላላት የሚችለውን ሕግ ብቻ ነው። ከዚህ ሰው ጋር ድርድር ወይንም ምንም ዓይነት ስምምነት ማድረግ አይቻልም። የሚሠራው፤ ለሱ አገልጋይ ሆኖ እስከተገኘ ድረስ ብቻ ነው። ለኢትዮጵያዊያን ያለው ጥላቻ፤ ከሥልጣን ጥማቱ በላይ ነው። በትግሉ ዙሪያ ለነበሩት ሕፃናት፤ አውሮፕላን በሰማይ ጽምጿ ሲሰማ፤ ኢትዮጵያ መጣች! እያለ ነበር ወደዛፍ ሥር እንዲከለሉ ያስተማራቸው። ለኢትዮጵያ ያለው ጠላትነት ልክ የለውም። ኢትዮጵያ የኤርትራ አገልጋይ መሆን አለባት የሚል ጽኑ እምነት አለው። ይህ ነው የኔ ምስክርነት።

ስብሰባው ሲያልቅ፤ አዲስ ታጋይ መጣ። አብደላ እድሪስ መላከ ተክሌን ገደለው ብሎ ነገረን። በኢኮኖሚ ጉዳይ ኃላፊው፣ በጸጥታ ክፍል ኃላፊው በመላከ ተክሌና በዋናው የበላይ በአብደላ እድሪስ መካከል ግጭት ነበር። አብደላ እድሪስ ከኢሳያስ የባሰ የሥልጣን ጥማት ያለበት መሪ ነበር። በወቅቱ ፈላጭ ቆራጩ እሱ ነበር። መላከ ተክሌ በታጋዩ ዘንድ ተወዳጅ ነበር። ይሄ ያለተዋጠለት አብደላ፤ መላከን ገደለው። በዚያ ታጋዩ ብትንትኑ ወጣ አለን። በዚያ ወቅት ተሰባስበው የነበሩት ወጣቶች፤ መተዳደሪያ ደንቡንና የድርጅታቸውን መርኀ-ግብር በማርቀቅ ላይ ሳለን፤ የኔ የሕክምና ጉዳይ አለቀና ወደ ትግል ሜዳው ለመመለስ የገዳሪፍ ጉዞዬ ሰዓቱ ደረሰ። የምችለውን በመጣደፍ ከረዳኋቸው በኋላ፤ ተሰናበትኳቸው።

ከሶስት ዓመት በኋላ፤ እኔና ኢሕአፓ በማያዳግም ሁኔታ ተለያየን። አሰናብተው ገዳሪፍ አስቀመጡኝ። ወዲያው ራሴን ችዬ ጎጆ ወጣሁ። ፍስሃን አገኘሁት። በወቅቱ ስደተኞችን ማስተማር ሥራ ይዤ ነበር። ወደ አሜሪካ ፈተናውን አልፈው የሚያሄዱትን ስደተኞች ከሚያከናውነው ድርጅት ተወካይ ጋር ግንኙነት እንዳለኝ ሰምቶ፤ እንድረዳው መጣ። ከተለያየንበት ቀን ጀምሮ የተከተለውን እንዲያጫውተኝ ጠየቅሁት። ጀብሃ ያለምንም ጥርጥር በአብደላ እድሪስ እብሪት በማያደግም ሁኔታ ተበታተነ። እኛም ያደረግነው ጥረት፤ አንድም በገንዘብ እጥረት፣ ሌላም በሸዓቢያ እንቅፋትነት፣ በተጨማሪም በታጋዩ ተስፋ መቁረጥ ሳይገፋ ቀረ። እናም ታጋዩ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው እንኳ አስተማማኝ ያልነበረ በመሆኑና የሚያውቁት ትግሉ ብቻ በመሆኑ፤ የወደፊት ዕጣቸው ጨለማ ነበር። አብዛኛዎቹ በሱዳን ገጠሮች ለጉልበት ሥራ መሄዳቸውን፣ ጀብሃ የነበሩት አንዳንዶቹ ወደ ሸዓቢያ መሄዳቸውን፣ ሌሎቹ ደግሞ ወደ አውሮፓና አሜሪካ በዘመዶቻቸው በኩል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ነገረኝ። እሱ ወደ አሜሪካ ሞክሮ እንዳልተሳካለት፤ አግብቶ ያንድ ልጅ አባት መሆኑን ገለጸልኝ። ያ ነበር የነበራቸው ጥረት መጨረሻው።

ከሁሉ በላይ የተማርኩት፤ ኢሳያስ አፈወርቂ ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ነው። በርግጥ ቀደም ብሎ በኢሕአፓ ላይ የፈጸመው በደል በውል የተመዘገበ ነው። ባጠቃላይ ግን ለኢትዮጵያ ያለው ጠንካራ ጥላቻ፤ ጊዜ የማይሽረው፣ ምንም ዓይነት ድርድር የማያረግበው፣ እና በደም ሥሩ የተተከለ ስለሆነ፤ ከዚህ ግለሰብ ጋር የሚደረግ ቃለ መጠየቅም ሆነ ከሱ የሚደመጥ በጎ ንግግር ዋጋ የለውም። በርግጥ ከአንድ ድርጅት የግል ፍላጎት ተነስቶ፤ ኢሳያስን እንደጣዖት ማጋነን ይቻላል። ተሸክሞ ማተለቅም ይቻላል። ምሽግ ሠጠኝ፣ ማሰልጠኛ ቦታ አቀረበልኝ፣ ገንዘብ ረዳኝ ብሎ ከሱ መጠጋት፤ የወደፊትን የሀገር አደጋ አለማጤን ስለሆነ፤ እንዲህ ባለ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ተው! ተብለው እንዲሰሙ ማድረግ ተገቢ ነው። እምቢ ካሉ ግን፤ ሀገራችንን ሊሸጡ ተነስተዋል ብሎ መኮነን ያስፈልጋል። ከጠላት ጋር አብረዋል ብሎ መወንጀል ያስፈልጋል።

የኔ ምስከርነት ይሄ ነው።

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in አስተያየቶች - Commentaries. Bookmark the permalink.

2 Responses to ለፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ምስክርነት

 1. MINILIK SALSAWI ይላሉ:

  Reblogged this on MINILIK SALSAWI (ምንሊክ ሳልሳዊ) and commented:
  ለፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ምስክርነት – አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ

  Like

  • Eskemeche ይላሉ:

   ውድ ሚኒሊክ፤
   በየጊዜው በአቡጊዳ የምታወጣቸውን አስተማሪ ጽሑፎች እከታተላልሁ። በራስህ ብሎግም ይሄን ጽሑፍ ስላወጣኸው አመሰግናለሁ። በርታ፤ የሀገር ኃላፊነት የወደቀው፤ ኃላፊ ነኝ ብለው በተሸከሙት ላይ ነው።

   Like

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s