ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን – እኛስ?

እስከመቼ ቅጽ ፳ ቁጥር ፩
ጥር ፳ ፰ ቀን ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህረት

መንደርደሪያ፤
በሀገራችን የፖለቲካ ትግል፤ ብዙዎቻችን አንደምታውን አሁን በደንብ ያልተገነዘብነው፤ በጣም ከፍተኛ ለውጥ ተካሄዷል። ይህ፤ ከጊዜ በኋላ፤ ወደኋላ ዞረው ለሚመለከቱት፤ ትልቅ የታሪክ ክንውኖች የሂደት መወደሪያ አምድ ሆኖ ያገለግላል። እናም የሂደቶች ማዕዘን፣ የሂደቶች ትርጉም፣ የግንዛቤ መሰላል ይሆናል። የዚህን ለውጥ ሚዛንና ከበሬታ አሁን ዓይተን፤ የራሳችንን ድርሻ ቆርሰን መጉረስ አለብን። ለውጡ ምንድን ነው? ድርሻችን ምንድን ነው? የዚህ ጽሑፍ ምርመራና መልዕክት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያጠነጥናል።
ምርመራና መልዕክት፤
በውጭ የምንኖር ታጋይ ኢትዮጵያዊያን፤ ማለትም ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን፤ ዋናው መገናኛ ማዕከላችን የሀገራችን የፖለቲካ ሂደት ነው። ስንገናኝ ሰላምታችን እንኳ፤ “ሰላም ነው?” ሆኗል። ድረገጾችን የምንጎበኘው፣ ሬዲዮዎችን የምናዳምጠው፣ ቴሌቢዥኖችን የምናየው፣ ስብሰባዎችን የምንካፈለው፣ . . . የሀገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ ለማወቅ፣ ውጤቱን ለመረዳት፣ የምንፈልገው መሆኑን ለማረጋገጥ፣ . . . ነው። ይህ፤ በትግሉ ዙሪያ ላለን ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን፤ ከዕለት ተዕለት የኑሯችን ሩጫ ቀጥሎ፤ ዋናውን ቦታ አጣቦ ይዟል ማለት ይቻላል። በዚህ የተጣለ አውድማ ላይ ግን ሁላችን ባንድ ተቀናጅተን እህሉን እያመረትን አይደለንም። አንዳንዶቻችን መንሾ ይዘን ላይ ታች እንላለን። ሌሎቻችን የሚሠሩትን እንመለከታለን። ቀሪዎቹ የሚመረተውን ለመዛቅ ሠፌዳችንን ይዘን አድብተናል። እናም ያንድነት ማምረት ሳይሆን፤ በምርቱ ዙሪያ ላለው ክፍፍል ቦታ ማካለል ይዘናል። የምርቱን ውጤት ባንድ ዓይን ማየት ተስኖናል። ዓይኖች አጥተን አይደለም። ይኼን ለሌላ ጊዜ ልተወውና ወደ ተነሳሁበት ርዕስ ልመለስ።
ዛሬ ባሁኑ ወቅት በኢትዮጵያዊያን ትግልና ታጋዮች ውስጥ፤ በጣም ክፍተኛ የሚያናጋ ለውጥ ተካሂዷል። ለውጡ በአንድነት ፓርቲ አዲስ አመራርና አባላት ባሉ ግለሰቦችና ክፍሎች የተገበረ ነው። እስካሁን ትግሉ የነበረው፤ በኢትዮጵያ ሕዝብና በወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሳይሆን፤ በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችና በትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ነበር። በሰላማዊ ሕዝብ እና በወራሪው መንግሥት መካከል አልነበረም። እያንዳንዱ የፖለቲካ ቡድን ደግሞ የሚታገለው ራሱ በድርጅቱ የመርኀ-ግብር ባሰፈረውና ላሰፈረው ዓላማ እንጂ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አልነበረም። እንዲያ ቢሆንማ ኖሮ ሁሉም ድርጅቶች አንድ በሆኑ ነበር። ይህ የትግል ሂደት ልዩነት ሳይሆን፤ የጠቅላላ የትግል ዓላማና የግብ ልዩነት መኖሩን ያረጋግጣል። ማንም ድርጅት ታግሎና ያለውን መንግሥት ጥሎ፤ ለሕዝቡ ሥልጣኑን የሚሠጥ የለም። ያንን የሚያረጋግጥልን፤ ከወዲሁ ለተመሳሳይ ተግባር ከተሰማሩት ጋር አብረው አለመሆናቸው ነው።
የአንድነት አባላት መልዕክት፤
የአንድነት አመራር አባላት ይኼንን ነውር ሰበሩት። ይህ ከባድና ትልቅ እመርታ ነው። እኒህ ግለሰቦች ያሰመሩት መካለያና የወሰዱት እርምጃ፤ ያይን ጉድፍ ገፋፊ ነው።
“የምንታገለው ለድርጅት ሳይሆን፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ትግላችን የሚካሄደው፤ በምንም ስም ስለተጠራ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሞትና የሽረት ትግል ስለሆነ ነው። መሠረታዊ የሆኑትን የኢትዮጵያ ሕዝብ መታገያ ዕሴቶች እስከያዘ ድረስ፤ ከማንም ጋር መታገል እንችላለን። ትግላችን እኔ መሪ ልሁን የሚል እሽቅድድም የለበትም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገ የትግሉና የድሉ ባለቤት ይሆናል።”
አሉን። ይህ ነበር ትግሉ እስከዛሬ የጎደለው ዋና መያዣ እጅ። እያንዳንዱ ድርጅት ታሪኩን፣ የሰው ኃይሉን፣ ሀብቱን፣ ቆራጥነቱን፣ የመርኀ-ግብሩን ጥራት፣ የመሪዎቹን ትልቅነት፣. . . እያነሳ፤ “እኔን ተከተሉ፣ የኔ አባል ሁኑ፣ እኔ በምጠራው ተሰብሰቡ!” እያለ የራሱ ጥግ ይዞ ነበር። ይህን አጋለጡት። የትግሉ መንገድ በዚህ እንዳልሆነ አሳዩን። ካሁን በኋላ ትግሉ፤ በተለያዩ ድርጅቶችና በወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መካከል ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ሕዝብና በገዥው ወራሪ መካከል መሆኑን በግልጽ ያለሙትን፤ በተግባር አሳዩን። በዚህ ድርጊታቸውና እምነታቸው ያደገው የሰማያዊ ፓርቲ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በትግሉ ላይ ያለው ፍላጎትና እምነት ነው። አሁን የታጋዩን ቁጥር በነሱ ሳይሆን በነሱ ቁጥር በማባዛት አሳደጉት። እናም ትግሉን ችቦ ሆነው አበሩና አጧጧፉት።
እኛስ?
ታዲያ ታጋይ ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን፤ እኛስ? ምን እንማራለን? ምን ማድረግ አለብን? ይህ ነው እኛን ያፈጠጠብን። በርግጥ ትግሉ ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ደግሞ ትግሉ የኛ የኢትዮጵያዊያን ነው። ብሎም ትግሉ የዛሬ ነው። እኛም አዎ ትግሉን እንደግፋለን። በምን መንገድና ሂሳብ እንደግፋለን? እዚህ ላይ በደንብ ልንመረምራቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ፤
፩ኛ. አንድ ድምጽ አለን ወይ? ድምጻችንን አንድ ማድረግ እንችላለን ወይ?
፪ኛ. ግንዛቤያችን ምንድን ነው? አንድ ለሆነው የፖለቲካ ሀቅ፤ አንድ ዕይታ አለን ወይ?
፫ኛ. አንድ ሆነን እንድንሰለፍ የሚያደርገው ኢትዮጵያዊ ራዕያችን ምንድን ነው?
፩ኛ. አንድ ድምጽ አለን ወይ? ድምጻችንን አንድ ማድረግ እንችላለን ወይ?
ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን በውጭ እንድንኖር የተደረግንበት ዋናው ምክንያት፤ የሀገራችን የፖለቲካ ቀውስ ውጤቶች መሆናችን ነው። በርግጥ የወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መልምሎ የላካቸው ቅጥረኛ ስደተኞች፤ ከትግራይ ይመልመሉ ከሌላው ክፍል፤ በውጭ ያለነውን ኢትዮጵያዊያን ኑሮ እንዳያምር፤ ቤተክርስትያኖቻችንና መስጊዶቻችን ነፃ እንዳይሆኑ፣ የስፖርት ድርጅቶቻችን እንዳይስፋፉ፣ የየከተማዎች ኢትዮጵያዊ የአገልግሎት ማኅበሮቻችን ባንድ እንዳያቅፉን መሯሯጥ ተግባራቸው ስለሆነ፤ እኒህ የሕዝቡ ጠላቶች ናቸው። እኒህ የገዥው አካል ናቸው። ታዲያ ሌሎቹ፤ በፖለቲካው ምክንያት ሀገራችን የለቀቅን፤ ወደ ሀገራችን ተመልሰን ለመሄድ በፖለቲካ አመለካከታችን የተከለከልን፤ በሀገራችን የሚካሄደውን የፖለቲካ ክስተት በምን ዓይነት እንመለከተዋለን? አንድ ድምጽ አለን ወይ? ድምጻችን ምን ይላል? በተለይ ከዚህ ነውጠኛ የአንድነት አመራሮች ውሳኔና ተግባር በኋላ፤ የአንድነት ድምጻችን ምንድን ነው? አደጋገፋፍችን እንዴት ነው? ለምን እንደግፋለን? ትግሉ ምን ያህል ከራሳችን ሕልውና ጋር ይዛመዳል? ምን ያህል የያንዳንዳችንን ሕይወት ይነካል? መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች ናቸው።
ትግሉ በግለሰብ ደረጃ ከራሳችን ጋር ካልተዛመደ፤ ትግሉን የኔ ነው ብለን ልንቆምለት አንችልም። የኔ ብለን፤ ሌሎችም የኔ ብለው፣ የኔ የምንለው የጋራችን ሆኖ የማናደርገው ትግል፤ ውጤታማ ሊሆን አይችልም። የኔ ለማለትና ለመተባበር ደግሞ፤ መጀመሪያ አንድ ድምጽ ሊኖረን ይገባል። ይህ ወሳኝ ነው። አንድ ድምጽ ከሌለን መተባበር አይቻለንም። አሁን አንድ ድምጽ የለንም። አንድ ድምጽ ሊኖረን ይገባል። ድምጻችንን አንድ ማድረግ ደግሞ እንችላለን።
፪ኛ. ግንዛቤያችን ምንድን ነው? አንድ ለሆነው የፖለቲካ ሀቅ፤ አንድ ዕይታ አለን ወይ?
ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን አንድ ድምጽ ሳይኖረን፤ ስለትግል ዘዴ፣ ስልትና ሂደት መወያየት ዋጋ የለውም። ስለሰላማዊ ትግል ወይንም ስለትጥቅ ትግል መደምደሚያ ላይ ሊደረስ አይቻልም። ይህ ጉዳይ ትርጉም የሚኖረው፤ አንድ ስብስብ ሆነን፤ አንድ ድምጽ ሲኖረን ነው። ስለ አጭርና ረጅም ጊዜ ዕቅድ ማውራቱ፤ ከንቱ ነው። የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅዶች ትርጉም የሚኖራቸው፤ መሠረታዊ ለዕቅዶቹ መረጃዎች ተሰብስበው ቀርበው፤ አቃጅ አካልና ፈጻሚ አካል ሲኖራቸው ነው። በሕዋ የተንጠለጠለ ዕቅድ የለም። ያለፈጻሚ የሚታቀዱና የሚዘጋጁ ያጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅዶች የሉም። ማነው አቃጁ አካል? ያጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን ስናነሳ፤ እኒህ ዕቅዶች ተወራራሽነት አላቸው። ያጭር ጊዜ ዕቅዶች የመጨረሻውን ግብ የሚያራምዱ መሆን አለባቸው። ይህ ደግሞ በተግባር በሚተረጎሙበት ወቅት የሚታይ ነው። እንዲያው በወረቀት ላይ ስለሠፈሩ፤ በርጥቡ የታሰበው እንዳለ ይሳካል ማለት አይደለም። ሂደታቸው የሚያስከትለውን፤ በሩቁ በርግጠኝነት መግለጽ አይቻልም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሀቅ፤ ወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ ኢትዮጵያዊያንን ኢትዮጵያዊ ነኝ ብለው በመቆማቸው፤ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ እያሰቃየ ያለበት ሀቅ ነው። ይህ ሁላችንን አንድ ስለባና አንድ ታጋይ ያደርገናል። ስለዚህ አንድ ዓይነት ዕይታ መያዛችን፤ የግድ ነው።
፫ኛ. አንድ ሆነን እንድንሰለፍ የሚያደርገው ኢትዮጵያዊ ራዕያችን ምንድን ነው?
አዎ! ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን በእያንዳንዱ የፖለቲካ ጉዳይ፤ ሁላችን አንድ ዓይነት አቋም ሊኖረን አይችልም። የተለያየን ነን። አስተዳደጋችን የሠጠን መመዘኛና አመለካከት፣ አሁን ባለንበት ኑሮ ምክንያት ያሸጋሸግነው የፖለቲካ ቅንብር ዝማሜና፣ ለወደፊት ይጠቅመኛል ብለን ከግል ሕይወታችን ያዛመድነው ቅመራ፤ የተለያየ አቋም ሠጥቶናል። ነገር ግን፤ በኢትዮጵያዊነት ትግላችን ዙሪያ፤ ታጋዮች ነን ብለን ስንሰለፍ፤ ያነገትናቸው ኢትዮጵያዊ ዕሴቶች አሉን። በኔ እምነት፤ እኒህ ዕሴቶቻችን፤
፩ኛ. ኢትዮጵያዊያን፤ በኢትዮጵያዊነታችን አንድ ሕዝብ ነን፣
፪ኛ. የኢትዮጵያ ሀገራችን ዳር ደንበርና ለም መሬት ለኢትዮጵያዊያን ነው፣
፫ኛ. በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት ይስፈን፣ እና
፬ኛ. የያንዳንዷ/ዱ ኢትዮጵያዊ/ት የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ፤ ናቸው።
እኒህ ኢትዮጵያዊ መታገያ ዕሴቶቻችን ናቸው። ለነዚህ በአንድነት መነሳት አለብን። እኒህ ሁላችንን ያስተባብሩናል። እኒህን ይዘን ስንሰለፍ፤ ለቀሪው ወገናችን የምሥራች እንልክለታለን።
ማጠቃለያ፤
የኢትዮጵያ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ የተመሰቃቀለ ነው። የዘሩ ከሃይማኖቱ፣ የጎጡ ከአስተዳደር በድሉ፣ ተመሰቃቅሎና ተናክሶ፤ ታጋዩን መያዣ መጨበጫ እንዳጣ በጎርፍ የሚንሳፈፍ ቅርንጫፍ፤ ወዲያና ወዲህ አከላትሞታል። ነገር ግን፤ ታጋይ ግብ ያለው፤ በመርኅ የሚመራ ግለሰብ ነው። እናም እኛ መርኅ ኖሮን፣ ግባችንን አጥርተን አውቀን፣ ቅደም ተከተላችንን አስፍረን መጓዝ መቻል አለብን። ተግባራዊ መሆን አለብን። ተስፋችን ጣራ መድረስ አለበት። ቁም ነገረኞች መሆን አለብን። መቆጠር አለብን። እናም አንድ ድምጽ ሊኖረን ይገባል – የሕዝቡን ትግል ደጋፊዎች። አንድ ዓይነት ዕይታ ሊኖረን ይገባል – የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ይወድቃል ብለን ማመናችን። በዚህ ጥርጥር የለንም። ይህ የሚሆነው እኛ ስለፈልግን ሳይሆን፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ በተግባሩ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደ መጨረሻው ገደል አፋፍ በመግፋቱ፤ ሕዝቡ የያዘው የሞት የሽረት ትግሉና አይቀሬ ድሉ የሕዝቡ ስለሆነ ነው። በሂደቱ እኛ የራሳችንን ድርሻ ቀርፈን መውሰድ አለብን። ስለዚህ ከአንድነት አባላት ተምረን፤ በንድ ትልቅ የኢትዮጵያዊያን የነፃነት እንቅስቃሴ እንሰባሰብና ለሕዝቡ ትግል እንድረስ። እኔ ለዚህ አባል ሆኛለሁ። እርስዎስ? eske.meche@yahoo.com

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in አስተያየቶች - Commentaries. Bookmark the permalink.

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s