ለእርስዎ፤ ጊዜ ወስደው ይኼን ለሚያነቡ ታጋይ ኢትዮጵያዊ፤

በአንድነት ተሰባስበን መታገሉ ግዴታችን ነው።

ውድ ታጋይ ኢትዮጵያዊ፤

በምኞት የምንጋልበው ፈረስ፤ ከፈለግነው ቦታ በፍጥነት የሚያደርሰን፤ በምኞት ዓለም ውስጥ ብቻ ነው። እኛ አሁን በአንድነት ያጋጠመን የምኞት ችግር ሳይሆን፤ የሀገራችን ተጨባጭ ሀቅ ነው። ይህ ደግሞ ተጨባጭ መፍትሔ ይጠይቃል። ሀቁን ተረድተን፣ ማድረግ ያለብንን ለይተን፣ ከትናንት ዛሬ፤ ከዛሬ ደግሞ ነገ የተሻለ ግስጋሴ የምናደርግበት ትግል እንዲሆን መጣር አለብን። በተናጠል በግለሰብና በየራሱ ድርጅት ለየብቻ የሚደረገው ትግል፤ ግስጋሴው አመርቂ እንዳልሆነ ተረድተናል። ስለዚህ አንድ የኢትዮጵያዊያን የነፃነት ንቅናቄ መሥርተን፤ ባንድነት መታገል አለብን።

ይህ ጥሪ፤ ብዙ የትግል ልምድ ላካበቱትና ለአዲስ ታጋዮች፣ ከፍተኛ ትምህርት ላላቸውና የመማር ዕድሉ ላላጋጠማቸው፣ የላቀ ወታደራዊ ሹመት ላላቸውና ውትድርና ላልቀመሱት፣ ለሁሉም “ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ እኔም ያገባኛል!” ለሚሉ ግለሰቦችና በድርጅት የተሰባሰቡ ኢትዮጵያዊያን ነው። የሌሎች ቆርጦ አለመነሳት ራሳቸውን እንዲያገሉ ላደረጋቸው፣ በትግሉ መጓተት ተስፋቸው ለመነመነ፣ የኛን ፖለቲካ ጠልተው ዓይኖቻቸውን ለጊዜው ለጨፈኑ ኢትዮጵያዊያንም ጭምር ነው።

በርግጥ መሰባሰብ ቀናና ቀላል ጉዳይ አይደለም። “ማን ጠራው?” እና “መቼና የት ተጠራ?” የሚሉት ከጥሪው የበለጠ ትክረት ባገኙበት ወቅት፣ ጥሪ ትርጉሙ የጎንዮሽ በተጣለበት ወቅት፤ ተቀባይነት የሚያገኝ ጥሪ ማስተላለፍ ቀላል አይደለም። ሆኖም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሀቅ ከመቼውም በላይ አጣብቂኝ ውስጥ የገባ በመሆኑ፤ የማይቻል የሚባለውን ሁሉ ለማስቻል፤ ጊዜ የምንሻማው ሆኖ፤ ሁሉንም እንድናደርግ ግድ ብሎናል። ይህ የቅንጦት ምርጫችን አይደለም። መሯሯጫ ሰዓት ላይ ነው ያለነው። ስለዚህ፤ የመሰባሰብ ሂደታችንን ከመቼውም ባፈጠነ መንገድ ማራመዱ ግድ ሆኗል። ተግባራዊ ሆነን እስካልተገኘን ድረስ፤ ጊዜ ራሱ መፍትሔ ይዞ የሚመጣበት መንገድ የለውም። እናም ይኼን ቀጥተኛ የመሰባሰቢያ ማመልከቻ፤ ለርስዎ፣ እርስዎን ለመሰሉ ታጋይ ኢትዮጵያዊያንና ለታጋይ ድርጅቶች እንድልክ ኢትዮጵያዊነቴ አስገድዶኛል። እንደሚቀበሉት ሙሉ እምነቴ ነው።

ውድ ታጋይ ኢትዮጵያዊ
በሀገር ውስጥም ሆነ በስደት፤ የሀገራችን ሁኔታ በያለንበት ሁላችንንም የአእምሮ ዕረፍት ነስቶናል። እስከዛሬ በግልዎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት መስዋዕትነት እየከፈሉ ሲታገሉ ነበር። የሀገራችን የፖለቲካ ሀቅም የትግሉን መቀጠል ያለጥርጥር ግድ ይለዋልና፤ አሁንም ትግልዎ ተገቢ ነው። መታገል ግን፤ ከግብ መድረሻ እንጂ ራሱ ግብ አይደለም። ስለዚህ ለምን የሚታገሉለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ከግብ እንዳልደረሰ መፈተሹን እርስዎ ከኔ የበለጠ እያሰቡበት እንደሆነ ተቀብዬ፤ ትግሉ የኢትዮጵያዊያን በሙሉ በመሆኑ፤ እርስዎ ያለሙት ግብ አለመገኘት ለኔም በግሌ የጉዳዩ ባለቤት በመሆኔ፤ አሳስቦኛል። እናም በታጋዮቹ በሁላችን፤ በግለሰብ ባለነውም ሆነ በድርጅት በተሰባሰቡት መካከል ያለውን፤ የምናልመውን የጋራ ግብ በማውጣት፤ በአንድነት የምንሠራበትን መንገድ በዚህ መልዕክቴ ዘርዝሬያሁ። ምርጫ የሌለበት ግዴታ ከፊታችን ላይ ተጋርጧልና፤ አቤት! አለሁ! በማለት በመደጋገፍ ሀገር አድን የሆነ ትግል እንድናደርግ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። ይህ ጊዜ የሚሠጥ ጉዳይ አይደለም። ግዴታችን ነው። እንዴት ይጀመራል እና ማን ይጀምረው በሚል ጥያቄ መጓተቱ ይቅርብን። ይኼው ጀምሬዋለሁ። በኔ በኩል መገናኛ ኢሜሌ ይኸው ነው። (eske.meche@yahoo.com) እርስዎና ሌሎች በሚሠጡት መልስ እንቀጥላለን። አብረን ጀማሪዎች እንሆናለን። ኢትዮጵያዊ ግዴታችንንም እንወጣለን። ለወገንና ለሀገር እንደርሳለን።

የታወቀ ነው፤ መሰባሰብ ቀላል ጉዳይ አይደለም። የሚቻልና ቀላል ቢሆን ኖሮማ፤ ካሁን በፊት ይተገበር ነበር። አልተደረገም። አይደረግም ማለት ግን አይደለም። የአሁኑ የማይቻል የተባለ ቀውጢ ሰዓት የሚጠይቀው ደግሞ፤ የማይቻል የተባለውን ማድረግን ነው። ስለዚህ የማይቻል የሚባል መፍትሔ ማቅረብ አለብን። ተቻለም አልተቻለም፤ በአሁኑ ሰዓት ለማንኛውም ጥረት አጥር አናበጅለትም። ካለም ጥሰን እንቀጥላለን። ይህ አይደረግም! አይቻልም! ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በፍጹም አያደርጉትም! ቢባልም፤ እኔ ይቻላል፤ ይደረጋል፤ በማለት ተነስቻለሁ። እርስዎም እንደሚተባበሩኝ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ የለኝም።

ጥሪዬ በአንድነት ተሰባስበን የኢትዮጵያዊያን የነፃነት ንቅናቄ እንድንመሠርት ነው። ይኼንን በመነጋገር ገሃድ እናደርገዋለን። በመጀመሪያ ይህን ንቅናቄ ፈላጊዎች መገናኘት አለብን። ከዚህ በምን መንገድና እንዴት የሚለውን ተመካክረን እንወስነዋለን። በዚሁ የኢሜል አድራሻ፤ ( eske.meche@yahoo.com ) መልስ ይሥጡኝና ወደፊት መሄዱን አብረን እንጀምር።

በምንም በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት የሆነውን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ አንኳሰንና አሳንሰን ማየት የለብንም። በምኞትም ይወድቃል ብለን መጠበቅ የለብንም። ያ ከሆነ ደግሞ የበለጠ አደጋ ሊከተል እንደሚችል ለርስዎ እኔ አስገንዛቢ ልሆን አይቃጣኝም። ከዚያ ለመዳን፤ በግልጽ በአንድነት መነሳት አለብን። ይህ ቡድን በምንም መንገድ ወዶ ሥልጣኑን እንደማይለቅ ሁሉ፤ የታጋዩ ክፍል አይሎ ትግሉ ሲጠነክር፤ ያለ የሌለ ጉልበቱን በሕዝቡ ላይ እንደሚያፈሰው መገንዘብ አለብን። እናም በትክክል የዚህን ቡድን ጥንካሬና ድክመት ማወቅና ትግሉም በሚያመች መንገድ መመራት አለበት። ይህ ትግል ከግቡ የሚደርሰው፤ በአንድነት ተሰባስበን፣ የአንድነት ራዕይ ኖሮን፤ በአንድ ጠንካራ ድርጅት ሥር፤ በኢትዮጵያዊነታችን ለኢትዮጵያዊነታችን ስንታገል ብቻ ነው።

መሰባሰብ አስፈላጊነቱን ተቀብለን፤ ለመሰባሰብ ለሚደረጉ ጥረቶች ግን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ፤ ታጋይነት አይደለም። መሰባሰቡ ዋና ጉዳያችን ነው ካሉ፣ መሰባሰቡ ለትግሉ መደፊት መቀጠል ወሳኝ ነው ካሉ፣ እስከዛሬ የከፈሉት መስዋዕትነት ዋጋ እንዲኖረው ከፈለጉ፤ የመሰባሰቢያ ጊዜው አሁን ነው። ለትግሉ ያለዎት ጥንካሬ፣ ለስኬቱ ያለዎት ቆራጥነት፣ የታጋይነትዎ ብስለት የሚለካው አሁን ነው። አሁን የትም ማምለጫ የሌለው ትንቅንቅ ውስጥ ነን። በልባችን የያዝነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያቸናፊነት እምነት፤ በሕይወታችን ላይ ሙሉ ቁጥጥሩን ይውሰድ። ቀኑ ሌት፣ ሌቱ ቀን መሆናቸው ትርጉም ይጡ። የሕዝቡን ድል አንግተን፤ ወደፊት መሄድ ብቻ ምርጫ የሌለው ጎዳናችን ይሁን።

የመሰባሰቢያ ዕሴቶቻችን፤

አንደኛ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዥዎቹ ከፍተኛ በደል በየጊዜው ደርሶበታል። በዛም አነሰም ሕዝቡ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል፤ በደል ደርሶበታል። አንደኛው ክፍል ከሌለው የበለጠ በደል ደርሶበታል። ይህ የታሪክ ሀቅ ነው። ማንም ሊክደው አይችልም። ሆኖም ግን ይህ በደል የደረስውና በመድረስ ላይ ያለው፤ በገዥዎቹ የግል የሥልጣን ጥማት እንጂ፤ አንደኛው የሀገራችን ክፍል ሌላኛውን የሀገራችን ክፍል ሊወርና ሊያጠቃ በዶለተበት ሂደት አይደለም። ስለዚህ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተከታታይ ገዥዎች ተጠቂ መሆኑን መቀበል አለብን። አሁንም ወደፊት ስንመለከት፤ የኢትዮጵያን ገዥዎችና ፍላጎት ደምስሰን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነትና ሉዓላዊነት የትግላችን መሠረታዊ ዕሴት አድርገን መነሳት ነው። ካሁን በኋላ ሕዝቡ ወሳኝነቱና የበላይነቱ ከጥያቄ ውስጥ የማይገባ ቋሚ መብቱ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን።

ሁለተኛ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ስትሰፋና ስትጠብ ለዘመናት ኖራለች። በዚህ እንኮራለን። ታሪካችን ሙሉ ለሙሉ ትክክለኛ ተግባራትን ብቻ ያስመዘገበ ነው ብሎ የሚከራከር የዋህ ነው። ገዢዎች፤ ከመንደር እስከ በዙፋኑ ላይ የተቀመጡ ሁሉ፤ ሕዝቡን ባጠቃላይ፤ እስር በርሳቸው ደግሞ በተለይ፤ ሲጣሉና ሲዋጉ፣ አልፎ ተርፎም አንዳንዶቹ ለሥልጣን ሲሉ ከባዕድ እያበሩ የሀገራቸውን መሪዎች መዋጋታቸው ሀቅ ነው። ይህ ሁሉ ታዲያ የታሪካችን አካል ነው። ልንሸመጥጥና ልንክደው አንችልም። በገዥዎቹ ፍላጎት ተመርቶ አንደኛው ክፍል ሌላውን አጥቅቷል። በተመሳሳይ መንገድ ደግሞ በተራው ሌላው ብድሩን መልሷል። ይህም ታሪካችን ነው። ይህ ሁሉ ተደምሮ ነው የአሁኗ፣ የሀገራችን፣ የኢትዮጵያ ታሪክ። ከዚህ የምንማረው፤ ማንም ገዥ ሆኖ ሰነበተ ማንም፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ አንድ ሀገር ሆና፤ ደካማም ይሁን ጠንካራ በየወቅቱ አንድ መንግሥት ኖሯት፣ ለረጅም ጊዜ እንደቆየችው ሁሉ፤ አሁንም በአንድነቷና በአንድ ሀገርነቷ መቀጠሏን ማረጋገጥ አለብን።

ሶስተኛ፤ በሰዎች መካከል ላለ ማናቸውም ግንኙነት፤ በመካከላቸው የሚያስተሳስራቸው፤ በጋር የሚስማሙበት የመተባበሪያ ሕጋቸው ነው። ይህ ሕግ ነው በመካከላቸው የሚኖረውን አብሮ የመቀጠል ሂደት የሚወስነው። እናም ሕጉ ካልተከበረ፤ በመካከላቸው ያለው አብሮነት ትክክለኛ አይደለም ማለት ነው። ስለዚህ በመተማመን አብሮነታቸው እንዲቀጥል፤ ሕጉን ማስከበሩ ግዴታ ነው። ይህ በሁለት ሰዎች መካከልም ሆነ በአንድ ሀገር ሕዝብ መካከል አንድ ነው። ሕጉን፤ ደንብ፣ ስነ ሥርዓት፣ በማለት እንደያስፈላጊ ቦታው ስም ሊሠጠው ይችላል። ሆኖም ግን መሠረታዊ ይዘቱ፤ በሰዎች መካከል፣ አብሮነታቸውን የሚያስረው፤ በመካከላቸው ያለው ሕግ መሆኑ ነው። ስለዚህ በሕግ መገዛትና የሕጉ መከበር፣ ግዴታ መሆኑን መቀበል አለብን። እናም በሀገራችን የሕግ የበላይነት መስፈን መሳኝ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን።

አራተኛ፤ በአንድ ሀገር የሚኖሩ ሰዎች፤ የሀገራቸው ዜጎች በመሆናቸው፤ እያንዳንዳቸው እኩል የሀገሪቱ ባለቤቶች ናቸው። ለዚህም፤ የሀገሪቱ ሕግ ሁሉንም በእኩልነት መመልከት አለበት። ግዴታቸውም ሆነ መብታቸው በዜግነታቸው ላይ የተመሠረተ ነው። የሀገሪቱ ዜጎች በሙሉ፤ እኩል የሆነ መብትና ግዴታ አላቸው። ስለዚህ ከዜግነታቸው የሚመነጨው የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው፤ ያላንዳች መሰናክል መከበር አለበት። በአንድ መንገድ ወይንም በሌላ፤ ሁለት ወይንም አስር ሆነው እኛ ስለተደራጀን የበለጠ መብት ይኑረን የሚባልበት ጨዋታ አይደለም። ማንም ግለሰብ፤ የሀገሪቱ ዜግነት እስካለው ድረስ፤ ሙሉ መብቱ የተከበረ ነው። ይህ፤ ለሁሉም፤ የትም ቦታ የሚሠራ፤ የኢትዮጵያዊ ዜግነት መብታቸው ነው። እናም የግለሰብ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበራቸውን ማረጋገጥ አለብን።

በነዚህ አራት ነጥቦች ዙሪያ፤ ሁላችን ለንቅናቄው እንሰባሰብ። እኒህ መታገያችን ናቸው። እኒህ የኢትዮጵያዊያን መታገያ ዕሴቶቻችን ናቸው። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ፤ እኒህም ሊቀየሩ፣ ሊያንሱ፣ ሊበዙ፣ ሊቀየጡ ይችላሉ። ይኼን በአንድነት በምንሰባሰብበት ጊዜ እንወስነዋለን። አሁን ለመጀመር መንደርደሪያችን እናድርገው። ይህን ወራሪ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ልንጥለው የምንችለው፤ በኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው። እሱ ፀረ-ኢትዮጵያዊያን ነው፤ እኛ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ነን። የምንታገለው ለኢትዮጵያዊነታችን ነው። በዚህ ተደራጅተን መታገል አለብን። የምንደራጀው በየኢትዮጵያዊያን የነፃነት ንቅናቄ ነው።

ይህ ትግል ወደፊት ሊሄድ የሚችለው፤ ይህ የምንመሠርተው ደርጅት፣ አደረጃጀቱና የአባላቱ የትግል ፍላጎት ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ድርጅት ጥንካሬና ጥረት ልቆ ሲገኝ ብቻ ነው። ይህ ትግላችን፤ የተለዩ አርቆ አሳቢ መሪዎችን ይጠይቃል። አሁን በየድርጅቶች የመሪነቱን ኃላፊነት የጨበጡት ሁሉ፤ ከድርጅቶቻቸው በላይ ሀገራቸውንና የሕዝቡን ትግል ተሸክመው፤ ለዚህ ትግል ድልና ለዚህ ትግል ድል ብቻ ድርጅቶቻቸውን ተገዥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ነገና ተነገ ወዲያ የሚመጣውን አስቀድመው በማየት፤ በሥራቸው የተሰባሰቡ ታጋዮችን በትክክለኛው መንገድ ሲያዘጋጇቸውና ሲመሯቸው ነው ትግሉ ወደፊት የሚሄደው። በትግሉ ሂደት፤ እንደሁኔታው መለዋወጥ፤ እነሱም ራሳቸውን እና ደርጅቶቻቸውን፤ ትግሉ በሚጠይቀው መሠረት ማሳደግና ማስተካከል አለባቸው። መሰባሰቡና በአንድነት ሁላችን መታገላችን የዕለቱ ጥያቄ ነው።

ለትግሉ የምንሰለፍንበት የኢትዮጵያዊያን የነፃነት ንቅናቄ የሚጠነክረው፤ በኢትዮጵያዊነታችን አምነንና ሀገራችን ባለችበት አሳዛኝ ሁኔታ ተቆርቁረን፤ የሀገራችንን ነፃነትና ለሕዝቡ ነፃነት የሚሆነውን መፍትሔ በተለያዬ መልክ የምንመለከት ሁሉ፤ በአንድነት ተቀምጠን፤ በመካከላችን ባለው ስምምነት፤ የጋራ የሆነ አቋማችንን ለድርጅቱ ምሰሶ ስናደርገው ነው። አንድ አመለካከት ያለው አንድ ድርጅት ብቻውን ሥልጣን ላይ ባሁኑ ሰዓት ከወጣ፤ መልሰን መደንከር ነው።

ይኼን የኢትዮጵያዊያን የነፃነት ንቅናቄ የሚመሩት፤ ከግለሰብ ማንነታቸው በላይ፤ ኢትዮጵያዊያንን እና ኢትዮጵያን ያስቀደሙና ብቃታቸውንና ችሎታቸውን ያለምንም ስስት ለትግሉ የሚያውሉ መሆን አለባቸው። የትግሉ ስኬት በነዚህ መሪዎች ችሎታና ጥረት ይወሰናል። ከመጀመሪያው በሥራቸው ተተኪ የሚሆኑትን አዘጋጅተው፤ ቀጣይነትን የሚያስተማምኑ መሆን አለባቸው። የሀገሪቱን ምርጥ ታጋይና አታጋይ መሪዎችን፤ ትግሉን ወደፊት የሚገፉ ወጣት ታጋዮችን ማሰባሰብ አለባቸው። እኒህ ደግሞ፤ አሁን በትግሉ በተሠማሩ ድርጅቶችና በትግሉ ዙሪያ ባሉ ግለሰቦች መካከል ነው የሚገኙት። ሌላ ከሰማይ የሚወርዱ መሪዎች የሉንም። እናም በትግሉ ዙሪያ ያለነው በሙሉ መሰባሰብ አለብን።

ባሁኑ ሰዓት ስለያንዳንዱ ሀገራዊ ጉዳዮች ባንድ ላይ መጨነቅ የለብንም። የጉዳዮች ቅደም ተከተል ማድረግ አለብን። መጀመሪያ ሀገራችን እንደመዥገር እየመጠመጠ ያለውን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ማስወገድ ነው። በሂደቱ በሀገር ቤት ያለውና ከሀገር ውጪ ያለው የታጋይ ክፍል በአንድነት የሽግግር መንግሥት ማቋቋምና ህዝቡ ሉዓላዊነቱ፣ ሀገራችን አንድነቷ፣ ሕግ የበላይነቱና የኢትዮጵያዊያን የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩበትን ሁኔታ ማዘጋጀት ነው። ከዚህ በተረፈ፤ የዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ ውሎችና ደንቦች ሊከበሩ የሚገባቸው፤ የኛን ጥቅም የሚያስጠብቁ ሆነው እስከተገኙ ድረስ ብቻ ነው። እኒህ መታሠሪያና መታነቂያ ገመድ ሆነው፤ አንገታችን እንድናስገባ የሚጠብቁ መሆን የለባቸውም። ታሪካችን ብዙ አስተምሮናል። እናም ማንኛውም ስምምነት፣ ውልና ደንብ፤ በዚህ መነፅር ይመረመራል።

አሁን ማድረግ ያለብን፤ ትክክለኛውን የትግል መስመር ተከትለን፤ ትክክለኛ የሆነ የኢትዮጵያዊያን የነፃነት ንቅናቄ መመሥረት ነው። ኢትዮጵያዊው ትግል፤ በሰላምም ሆነ በሌላ መንገድ በትክክለኛ እየተመራ አይደለም። ይኼ የሆነው፤ ታጋዮች ጠፍተው ሳይሆን፤ አንድነትን ያሰመረ የመታገያ ማዕከል በቦታው ኖሮ፤ ትግሉን አቀናጅቶ የሚመራ ንቅናቄ ባለመገኘቱ ነው። መሠረታዊ የሆነውን የትግሉን ምንነት በደንብ ተረድተን፤ ለዚሁ ትግል ተመጣጣኝ የሆነ ትብብርና ድርጅት ስለሌለን ነው። ትግሉን በትክክል ለመምራት ደግሞ፤ የአንድነት ትግል መሆኑን መረዳታችን፤ መቅደም ይገባዋል። እናም ይሄን የማራመድ ኃላፊነቱ አለብን። መሰባሰብ ይገባናል። ለዚህ የርስዎን መልስ እጠብቃለሁ። የርስዎን ሃሳብ እፈልጋለሁ። ይኼው የኔ የኢሜል አድራሻ፤ ( eske.meche@yahoo.com )

አክባሪዎአንዱ ዓለም ተፈራ

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in አስተያየቶች - Commentaries. Bookmark the permalink.

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s