ምን ዓይነት ትግል በኢትዮጵያ? ( መንደርደሪያ ሃሳብ )

እስከመቼ ቅፅ ፲ ቁጥር ፲፰
አንዱ ዓለም ተፈራ
ማክሰኞ፤ መስከረም ፩ ቀን ፳ ፻፯ ዓመተ ምህረት ( 09/11/2014 )

በእንቁጣጣሽ ፈንታ ይኼው በትግሉ ዙሪያ መልዕክት ይዤ መጥቻለሁ። ዛሬ መስከረም አንድ ጠብቷል። እንቁጣጣሽ ባይ ሕጻናት በያሉበት እነሱም የዛሬ ልምድ በሆነው፤ ይኼኑ በሺዎች የሚቆጠር ዘመን ያለውን ባህላችን ያከብሩታል። እኔም ባለሁበት የፖለቲካ ሀቅ፤ ኢትዮጵያዊ የሆነውን እውነታ ይዤ ቀርቤያለሁ። እንኳን ለ፳ ፻ ፯ ዓመተ ምህረት አደረሳችሁ።

ባለፉት ተከታታይ ጽሑፎቼ፤ ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን እንደሆነና በኢትዮጵያ ምን ዓይነት መንግሥት እንዳለ፤ መንደርደሪያ ሃሳቦች አቅርቤያለሁ። ያንን እንዳደርግ የገፋፋኝ፤ እንደብዙዎቻችሁ ያገሬ ሕዝብ ያለበት የኑሮ ሀቅና የዚህ እውነታ የሚያስከትለው ነገ ስላሳሰበኝ ነው። አሳስቦኝም መፍትሔ ብዬ ያመንኩበትን ለመግለፅ ነው። በመሠረቱ አሁን አፍዝ አደንዝዝ የያዘው የሕዝቡ ወገን ትግል፤ ባለበት ከተቀመጠበት ተነስቶ ወደፊት እንዲንቀሳቀስ፤ አውታር የሆኑትን ሀገራዊ የትግል ሀ ሁ ጥያቄዎች የመመለስ ግዴታ አለብን። አሁን በሀገራዊ ደረጃ፤ በትግሉ አውታር ጥያቄዎች ላይ በድፍረትና በግልፅነት መወያየት ካልቻልን፤ ትግላችን በተስተካከለ መንገድ ተጉዞ፤ ሕዝባዊ ድሉ ከግቡ ይደርሳል የሚለውን መቀበል ያዳግተኛል። በርግጥ ያለውን ወራሪ መንግሥት አውርዶ በራሱ ድርጅት ለመተካት የሚሯሯጥ ካለ፤ የወራሪውን መንግሥት መውደቅ ብቻ ስለሚፈልግ፤ ሆይ ሆይታው ሁሉ ይጠቅመዋልና፤ ይኼኑ ያርገበግባል። አብዛኛዎቻችን የምንፈልገው ይኼን ሳይሆን፤ ላንዴና ለሁሌም የሕዝባዊ ድልና የሰላም የወደፊትን ስለሆነ፤ ይኼ አያረካንም። የምንፈልገው፤ ያለሕግና ስነ ሥርዓት በመንግሥት እጅ ኢትዮጵያዊያን እንደ እንሰሳ የማይታረዱበት፣ የሰላምና የአብሮነት ጎዳና የሚጠረግበት ሂደትና በኢትዮጵያ ብልፅግና የሚጀምርበትን መንገድ ነው።

ዛሬ ሁላችን በየዕለቱ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርን ተግባር መዘርዘሩ፤ በራሱ ትግል አድርገን አጥብቀን ይዘነዋል። ከዚህ ለመራቅና መፍትሔ በመሻቱ መንገድ እንድናቀና ነው በኛ ኃላፊነት ላይ ያተኮረ ጽሑፍ ላይ የተሠማራሁት። እንግዲህ የኛንና የጠላታችንን ምንነት ግልፅ በሆነ መስፈርት ካስቀመጥን፤ ( ማለትም እኛ ኢትዮጵያዊያን፤ ጠላታችን ደግሞ ወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ) ምን ዓይነት ትግል መከተል አለብን? የሚለውን መመለስ ቀጣዩ ሥራ ነው። እነሆ የኔው መልስ።

ምን ዓይነት ትግል በሀገራችን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው? ምን ዓይነት ትግል መካሄድ አለበት? የያዝነው ጎዳና ትክክለኛ ነው ወይ? ትግሉ ማዕከል አለው ወይ? የሚሉትን ሁሌ መጠየቅ ያለብን ጉዳዮች ናቸው። እነኚህን ለመመለስ ደግሞ፤ በሀገራችን ያለውን የፖለቲካ ሀቅ የግድ መተንተንና መረዳት ያስፈልጋል። መቼም ያለንበት የፖለቲካ ሀቅ ለማናችንም ቢሆን ባዕድ አይደለም። በሕዝቡ ወገን የተሠለፈውንና በወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ወገን የተሠለፈውን ለይቶ ማወቁ ከባድ አይደለም። ታዲይ እንደኔ ላለ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወገን ሆኖ ሕዝቡ በሚያደርገው ትግል አስተዋፅዖ ማድረግ የሚፈልግ ግለሰብ፤ ሀገራችን በተወረረችበት ባሁኑ ወቅት፤ ትግሉ ለወገን ደራሽነትና የሀገር ነፃነት ነው። ይህ ማለት፤ የአሁኑ ትግል በድርጅቶች መካከል የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ውድድር ሳይሆን፤ በሕዝቡ ሉዓላዊነትና አንድነት አምኖ፤ በአንድ መለስተኛ አስተባባሪ መርኅ ዙሪያ መሰባሰብና ከሕዝቡ ጎን መቆም ነው።

ይህ ማለት ድርጅት አያስፈልግም ማለት አይደለም። ድርጅት መሣሪያ ነው። ድርጅት ጣዖት አይደለም። አይሰገድለትም። ድርጅት የሚመሠረተው፤ ወቅቱ ለሚጠይቀው የሕዝቡ ተሳትፎ፣ መሣሪያ በመሆን ያንን ግብ ለማስገኘት መጠቀሚያ እንዲሆን ነው። ይሄን በሕዝቡ መካከል የሚኖር ትብብር መልክ ለማስያዝ እንጂ፤ ራሱ ድርጅት መመሥረቱ ግብ መሆን የለበትም። እናም ባሁኑ ሰዓት ወቅቱ ለሚጠይቀው ለወገን ደራሽና የሀገር ነፃነት ትግል፤ መልሱ፤ በመለስተኛ መርኀ-ግብር ዙሪያ ሁሉን ለማሰባሰብና ሕዝባዊ እንቅስቃሴውን የሚመራ ድርጅት መመሥረት ነው። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ብቻ የሚሰባሰቡበት ድርጅት ነው። እናም የርዕዩተ ዓለም ጥራት ወይንም የፖለቲካ ፍልስፍና መራቀቅን አይጠይቅም። የሚጠይቀው፤ ወገን አፍቃሪና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መገኘትን ብቻ ነው። ባሁኑ ሰዓት ደግሞ እነኚህ ኃላፊነታቸውን ያወቁና ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን፤ በያሉበት ተነስተዋል። የጎደለው የመሪና አስተባባሪ ኢትዮጵያዊ ድርጅት ነው። ይህ የሁላችንም ኃላፊነት ነው። ሕዝባዊ ንቅናቄው በኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው። ትክክለኛ ማዕከል ግን የለውም። በርግጥ አንዳንድ ድርጅቶች ለመቀራረባና የትግሉን ማዕከል ለመበጀት መሠረት ለመጣል እየተሯሯጡ ነው። እሰየው ያስብላል። ነገር ግን ባለባቸው የወራሪው መንግሥት ተጽዕኖ ምክንያት፤ ባሉበት ሁኔታ ወደፊት ይሄዳሉ ማለት ምኞት ብቻ ነው።

በወራሪው መንግሥት ምክንያት ሀገራችን ለቀን በውጭ ተሰደን ያለን ኢትዮጵያዊያን የትግሉ አካል ነን። እናም ይህ የስደተኛ ክፍል፤ ሀገር ቤት እንደሚታገሉት ወገኖቻችን እኩል ግዴታውና ኃላፊነቱ አለብን። ስለዚህ ሀገር ቤት ያሉትና ውጭ ሀገር ያለነው በአንድነት የምንሠለፍበት ድርጅት ያስፈልገናል። ራዕዩም ሆነ ተልዕኮው አንድ መሆን አለበት። እነኚህን ሁለት ክፍሎች ባንድ አጣምሮ የማይጓዝ ትግል፤ ከመፍትሔነቱ ይልቅ ችግር ፈጣሪነቱ ይጎላል። ይህ ትግል፤ መሸጎጫ ድብቅ ቦታ አይፈልግም። ትግሉ የጠቅላላ ሕዝቡ ነው። ትግሉ ሕዝብ ነው። ስለዚህ መደበቅ አይስፈልገውም። መፈክሮቹ በየጊዜው በሕዝቡ ላይ የሚደርሱት ግፍና ሰቆቃዎች ናቸው። መፈክሩ ወራሪው መንግሥት ይወገድ ነው። ስለዚህ ሕዝቡ ሲነሳ፤ መደበቂያ መፈለግ ያለበት ወራሪው ነው። ትግሉ በሀገራችን ውስጥ ነው። ትግሉ የራሳችን እንጂ የሌላ መንግሥት ወይንም ግለሰብ አይደለም። ማንም የውጭ መንግሥት ይረዳናል ብሎ፤ የራሳችንን ኃላፊነት በሌሎች እጅ ላይ መጣል፤ በቀላሉ ሲታይ የዋህነት፤ አለያ ደግሞ ለሌሎች መሣሪያ ለመሆን ዝግጁነት ነው።

ትግል ስለመኖሩ ያልተረዳ የለም። ትግል ማስፈለጉ የጥያቄና መልስ ጉዳይ ሳይሆን፤ በሀገራችን ውስጥ ያለ ሀቅ ስለሆነ፤ ትግል የለም ወይንም አያስፈልግም የሚል ቢኖር፤ በወራሪው ወገን ያለ ብቻ ነው። ትግሉ ማስፈለጉ ብቻ ሳይሆን ዕለት ተዕለት በሀገራችን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለ ሀቅ ነው። ነገር ግን ትግል አለ የሚለው ብቻ በቂ አይደለም። ከላይ እንደጠቀስኩት፤ ምን ዓይነት ትግል በሀገራችን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው? ምን ዓይነት ትግል መካሄድ አለበት? የያዝነው ጎዳና ትክክለኛ ነው ወይ? ትግሉ ማዕከል አለው ወይ? ብለን መጠየቅ አለብን። ይህ የሀገር ጉዳይ ስለሆነ፤ ሀገራዊ ውይይት አድርገን ቢቻል መተማመን አለያም ጎራችንን ለይተን መነሳት አለብን። የተማመነው ወደ ሀገራዊ ተግባር እንሰማራለን። ከዚያ በፊት ግን አስቀድመን፤ ትግሉ የሰላማዊ ነው ወይንስ የትጥቅ? በኤርትራ ነው ወይስ በሌላ? ይኼኛውን ድርጅት በመደገፍ ነው ወይንስ ያኛውን እያልን የምናደርገው የጉንጭ አልፋ ትንታግነት፤ ወደ ሀገራዊ ስምምነት ሳይሆን ወደዬ ድርጅቶች የግል ምርጫ የሚያስገባን ጎጂ ንትርክ ነው። ስለዚህ ትግሉ የወገን ደራሽና የሀገር አድን ነውና፤ በአንድነት መነሳታችን ግዴታ ነው። በጣም መለስተኛ በሆነው ሕዝባዊ ንቅናቄው ለመግፋት፤ የትግሉ መርኆዎች የሚከተሉት ናቸው፤

፩ኛ.      የኢትዮጵያን ሕዝብ ሉዓላዊነት መቀበል
፪ኛ.      የኢትዮጵያን አንድ ሀገር፤ ዳር ድንበሯ የተጠበቀ መሆኑን መቀበል
፫ኛ.      የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብት መቀበል
፬ኛ.      በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት መስፈን እንዳለበት መቀበል                    ናቸው።

አሁን ያለንበት የትግል ሁኔታ በትክክለኛ መነጽር ሲታይ፤ ዝብርቅርቅ ነው። ሁላችን እንደምንረዳው በአሸዋ ላይ የተሠራ ቤት፤ ቆይታው እስከሚዘንብ ድረስ ብቻ ነው። እናም ባለንበት እንቀጥል ማለት፤ የሚቀጥለውን ቤት በአሸዋ ላይ እንሥራ ብሎ መነሳት ነው። መሠረቱ አይረጋም። ሁላችንም ለውጥ መደረግ እንዳለበት እናምናለን። ለውጡ የሚጀምረው ከኔና ከርስዎ ነው። የትግሉን ምንነት፣ የአደረጃጀቱን ዓይነት፣ የአሠላለፉን ወጥነት የሚወስነው በሀገራችን ያለው የፖለቲካ ሀቅ ነው ብለናል። ሀገራችን ተወራለች። ኢትዮጵያዊነታቸውን ያልተቀበሉ ሰዎች በፀረ-ኢትዮጵያ ነፃ አውጪ ግንባር ተደራጅተው ሀገራችን ወረዋል። ስለዚህ በአንድነት እንነሳ። ትግሉ ለወገን ደራሽ ለመሆንና የሀገርን ነፃነት ለማስገኘት ነው። ይህ የትግላችን መርኅ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ንቅናቄ፤ አመሠራረቱ፣ ሂደቱ፣ የመጨረሻ ግቡ፣ ፍጻሜው በደንብ መዘርዘር አለበት። ይህ ግን የመሥራቾቹ ኃላፊነት ነው። ይህ ንቅናቄ ዘለዓለማዊ አይደለም። በኃላፊነት የሚቀመጡትም ግቡ እስከሚመታ ድረስ ብቻ ነው። ቋሚ ሹሞች አይሆኑም።

እንግዲህ እስካሁን ለሶስቱ የትግሉ አውታር ነጥቦች፤ ሀ) ኢትዮጵያዊነታችንን በሚመለከት፣ ለ) ጠላታችን የሆነውን ወራሪ መንግሥት በሚመለከት፣ እና በዚህ ጽሑፍ ደግሞ ሐ) የትግሉን ዓይነት በሚመለከት መንደርደሪያ አቅርቤያለሁ። የሚቀጥለው ጽሑፌ ተግባርን የተመለከተ ይሆናል። ባቀርብኳቸው መንደርደሪያ ጽሑፎች ሃሳባችሁን ለለገሳችሁኝ፤ ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ። አብዛኛው የደረሰኝ ግን ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ክፍል ሲሆን፤ የስድብ ውርጅብኛና ከፅሑፉ ጋር ምንም ያልተዛመደ ዘለፋ ስለሆነ፤ አመሰግናለሁ ብቻ በማለት መልሴን ሠጥቻቸዋለሁ። ስለተግባርና ስለድርጅት እኔን ቀድማችሁ በመገኘት ለጠየቃችሁኝ ደግሞ፤ በየግል ከሠጠኋችሁ መልሶች በተጨማሪ፤ በሚቀጥለው ጽሑፌ የበለጠ ተግባር ተኮር የሆነ መልስ ለመሥጠት ዝግጁ ነው። እንደገና መልካም እንቁጣጣሽ!

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in እስከመቼ ቅፅ ፲፯. Bookmark the permalink.

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s