በኢትዮጵያ ምን ዓይነት መንግሥት አለ? ( መንደርደሪያ ሃሳብ )

በኢትዮጵያ ምን ዓይነት መንግሥት አለ? ( መንደርደሪያ ሃሳብ )

እስከመቼ ቅፅ ፲፯ ቁጥር ፲

ሰኞ፤ ነሐሴ ፳፮ ቀን ፳፻፮ ዓመተ ምህረት ( 09/01/2014 )

ይህ መሠረታዊ ጥያቄ ነው። በተለይ በትግሉ ላይ የተሰማራነው ኢትዮጵያዊያን፤ ለዚህ ትክክለኛ መልስ መሥጠት አለብን። ለዚህ የምንሠጠው መልስ፤ ትብብሮችን ወይንም ውህደቶችን፣ ልዩነቶችን ወይንም መራራቆችን ያስከትላል። ከዚህ መሠረታዊ ጥያቄና ለዚህ ጥያቄ ከምንሠጠው መልስ፤ ማንነታችንን ብሎም የተሰባሰብንበትን ድርጅት ማንነት ማወቅ ይቻላል። እንግዲህ ሀገራችን ባለችበት ቀውጢ ሰዓት፣ የታጋዩ ክፍል ባለበት የተበታተነ ሀቅ፣ የተበታተነ ትግል በመከተል ትግሉ ማዕከል ባልያዘበት ሁኔታ፣ ትግሉን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ ካልፈለግን፤ ድርጅቶችን መመሥረትና በትግል ላይ ነኝ ከማለት አልፈን፤ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መልስ መሥጠትና ይህን ግልጽ ማድረግ አለብን። የዚህ ጽሑፍ መልዕክት ይህ ነው። እናም በኢትዮጵያ ስላለው የመንግሥት ዓይነት ለውይይታችን መንደርደሪያ አቀርባለሁ።

የትግላችን ማውጠንጠኛ በሀገራችን ያለው የፖለቲካ ሀቅ ነው። የትግላችን ምንነትና ሂደትም በዚሁ ሀቅ ይመሠረታል። በኢትዮጵያ መንግሥት አለ። ይህን መንግሥት የተለያየ ስም በመሥጠት ማንነቱን የሚገልፁ አሉ። አንዳንዶች ቅጥረኛ ሲሉ ይገልፁታል። አንዳንዶች ደግሞ አምባገነን ይሉታል። እንዲሁም ሌሎች ጠባብ የትግሬዎች መንግሥት ይሉታል። ጥቂቶችም የዘመነ መሣፍንት ኋላ ቀር መንግሥት ይላሉ። አንዳንዶቹ ከግራው ሲወግኑት፤ ሌሎች የምዕራባዊያን መሣሪያ አድርገው ከቀኙ ያዛምዱታል። በዛ ያሉት ደግሞ የተዘበራረቀበት ነው ይላሉ። ለኔ ይህ ሁሉ በበቂና ትክክል አይገልፀውም ባይ ነኝ።

ይህ መንግሥት፤ የኢትዮጵያን ጥቅም እያስጠበቀ የሚገኝ መንግሥት አይደለም። ይህ መንግሥት፤ ኢትዮጵያን ወደ መጥፎ የወደፊት እየወሰዳት ነው። ይህ መንግሥት ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ እየገዛ ያለ መንግሥት አይደለም። በተጨማሪ አሁንም የነፃ አውጪ ግንባር ነኝ ብሎ እየገዛ ያለ መንግሥት ነው። ነፃ አውጪነቱ፤ ኢትዮጵያ የኔ አይደለችም ከማለት አልፎ፤ ከኢትዮጵያ ነፃ መውጣት እፈልጋለሁ ብሎ የተነሳ በመሆኑ ነው። የግለሰቦቹን ኢትዮጵያዊነት መቀበል አንድ ነገር ነው። ተሰባስበው የመሠረቱትን ድርጅትና የዚህን ድርጅት ምንነት በሚመለከት የሚኖረን ግንዛቤ ደግሞ የተለዬ ነው። እኔ ኢሳያስ አፈወርቂና በሻዕቢያ የተኮለኮሉት ኢትዮጵያዊያን ናቸው ብዬ ባምን፤ እነሱ የመሠረቱትና አሁን በኤርትራ ወገኖቻችንን የሚያሰቃየው መንግሥት ኢትዮጵያዊ ነው ብዬ መቀበል የለብኝም። ስለዚህ ግለሰቦች ሌላ፤ አድራጎታቸውና ድርጅታቸው ሌላ ነው እላለሁ። በአምስተኛ ዘርፍ ሙሉ በሙሉ በአስካሪሶች የተሰልፈው የጣሊያን ጦር፤ ኢትዮጵያዊ ነበር ብሎ መቀበል፤ አሳሳች ነው። ያ ጦር የፋሽስቱ የጣሊያን ጦር አካል ነበር። ከዚህ ተነስቼ፤ መለሰ ዜናዊና በረከት ስምዖን፣ ስብሃት ነጋና ስዩም መስፍን ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ እየተቀበልኩ፤ የመሠረቱት ድርጅት ግን ኢትዮጵያዊ አይደለም እላለሁ።

በመነሻዬ ከላይ ሌሎች ለዚህ መንግሥት የሠጡትን መግለጫ ለምን እንደማልቀበል ላስረዳ። እንዲያው የኢትዮጵያን ጥቅም ጎጂ በመሆኑ ብቻ ቅጥረኛ ነው የሚለው አያስኬደኝም። ይህ መንግሥት ቅጥረኛ ነው ለሚለው፤ ማን ቀጥሮት? ለሚለው መልስ የለንም። የቅጥረኛ ባህሪያትን በቅጡ አያሟላም። እናም ቅጥረኛ የሚለውን አልቀበለውም።

አምባገነን የሚሉትን የማልቀበልበት ተግባሩን እንጂ ምንነቱን አይገልፅምና ነው። የሰው በላው የመንግሥቱ ኃይለማርያም መንግሥት ኢትዮጵያዊ ነበር። አምባገነን ነበር። አረመኔ ነበር። ይህ ያሁኑ መንግሥት ግን ኢትዮጵያዊ አይደለም። እናም ከተግባሩ አረመኔነት ብቻ ተነስተን አምባገነን መንግሥት ብንለው ሀቁን ይሸፍነዋል። እናም ማንኛውም ቅኝ ወራሪ አምባገነን ነው። ያ ግን ቅኝ ገዥነቱን አይገልፀውም። ስለዚህም አልቀበለውም።

የትግሬዎች መንግሥት የሚለው ፍጹም የተሳሳተ ነው። ትግሬዎች ተሰባስበው መርጠው ያስቀመጡት መንግሥት አይደለም። በስማቸው መጠቀሙ ሳይሆን፤ ትግሬዎች ቀሪውን ኢትዮጵያን እንግዛ ብለው ተነስተው የዘመቱበት ሀቅ አይደለም። እናም አሁን በሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ያልታቀፈው ብዙው የትግራይ ተወላጅ ወገናችን፤ ከቀሪው የኢትዮጵያ ወገኑ ጋር አብሮ በሚሰቃይበትና አብሮ በቆመበት ባሁኑ ሰዓት፤ ይኼን መንግሥት የትግሬዎች መንግሥት ማለቱ ስህተት ነው። ያን ካልን፤ ትግሬዎች ኢትዮጵያን ወረዋታል ማለታችን ነው። ይህ ትክክል አይደለም። እናም አልቀበለውም።

ጥቂቶችም የዘመነ መሣፍንት ኋላ ቀር መንግሥት ይሉታል። በርግጥ አመሠራረቱ፣ አመለካከቱና ተግባሩ ወደ ሁለት መቶ ዓመት ያለፈውን የመሣፍንት ዘመን ያዘለ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ የተነሳውም በዚያ ዘመን ከነበረው የጎጥ ግዛት መንፈስ ነው። እናም ሰዎች የዘመነ መሣፍንት ኋላ ቀር መንግሥት ቢሉት አይገርመኝም። ነገር ግን መንግሥታዊ ምንነቱን አይገልፀውም። በርግጥ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሲጀመር፤ ሁለት ነጥቦችን አዝሎ ነበር። የመጀመሪያው ሥልጣን ከአፄ ዮሐንስ በኋላ ለትግራይ ተወላጆች እየተላለፈ “እኛ” መግዛት ሲኖርብን፤ በአፄ ሚኒልክ ተነጥቆ ከትግራይ ወደ መካክል ኢትዮጵያ ሄደ የሚለው ነው። ሌላው ደግሞ፤ በአፄ ሚኒሊክ ጊዜ የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ለመዋጋት የዘመተው ወታደር፤ በትግራይ ገበሬዎች ጫንቃ ላይ ተመግቧል የሚለው ነው። እንግዲህ መሠረታዊ መነሻው እኒህ ሁለት ነጥቦች ናቸው። በሌላ ጽሑፌ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ከስድሳዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ጋር ምንም ዝምድና የሌለው መሆኑንና፤ ይህ በዚህ ላይ የገለፅኩት ብቻ መሠረቱ እንደሆነ ያሳየሁበት ስላለ፤ በሌላ ጊዜ እንዲወጣ አደርጋለሁ።

እዚህ ላይ በትግራይ የነበሩና ያሉ ወገኖቻችን በምንም መንገድ ይሄን አመለካከት እንደማይጋሯቸው መግለፅ እወዳለሁ። በርግጥ እንዳሁኖቹ ገዥዎቻችን ሁሉ፤ የኢትዮጵያን ጥቅም በመጻረርና ለፋሽስቱ የጣሊያን ወራሪ በማፈንደድ፤ መስቀላቸውን ይዘው ያረገረጉ፣ ጠመንጃ ተቀብለው ኢትዮጵያዊያን አርበኞችን የተዋጉ፣ ለፋሽስቱ ምግብ ያቀረቡ፣ መሪ ሆነው የዘመቱ ብዙ ባዳዎች ነበሩ። ይህ ግን የትግራይ ተወላጆችን ብቻ የያዘ ሳይሆን፤ በባንዳነት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ጣሊያንን ያገለገሉ ነበሩ። ከኤርትራ አስካሪሶች አስከ በየቦታው የነበሩ አምባሳደሮቻችን፣ ከመሣፍንት እስከ ምሁራን ድረስ ሞልተዋል። በተቃራኒው፤ ከአብቹ አራት ጀኔራሎች አንዱ፤ የትግራይ ወገኖቹን አሰልፎ የተዋጋ የትግራይ ተወላጅ ነበር። ከአርበኞቻችን ቀንደኞች ውስጥ የትግራይ ተወላጆች ብዙ ናቸው። አሁንም አብዛኛው የትግራይ ተወላጅ የገዥዎቹ ሰለባ ነው። በርግጥ ከቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል ሲነፃጸር፤ የትግራይ ክፍል የለማ ነው። ይህ ማለት ግን፤ እያንዳንዱ የትግራይ ተወላጅ የዚህ ልማት ባለቤት ነው ማለት አይደለም። እናም ብዙው የትግራይ ተወላጅ ወገኖቻችን ተጠቂዎች ናቸው። ስለዚህም የትግሉ አካል ናቸው። ኢትዮጵያዊ ናቸው። ደጋፊም ሆነ ተጠቃሚ አይደሉም። ስለዚህ የዘመነ መሣፍንት ኋላ ቀር መንግሥት የሚለው አመለካከቱን ቢገልፅም፤ የመንግሥቱን ምንነት አይገልፅም። አናም አልቀበለውም።

አነሳሱን ከግራው ዘመም ፖለቲካ ጋር በማያያዝ ኮምኒስት፣ ሶሽያሊስት፣ የግራ ፖለቲካ አቀንቃኝ የሚሉት አሉ። ትክክለኛ ተግባሩንና ከምዕራባዊያን ጋር የሚያደርገውን ሽርጉድ ተመልክተው የቀኝ ፖለቲካ አራማጅ የሚሉትም አሉ። ከእውነቱ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። አዎ የማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ኦፍ ትግራይ ፓርቲን አቋቁመው፤ ይህ ጠባብ ሚስጢረኛ ቡድን ሁሉን አካሂያጅ እንደሆነ ሁላችን እናውቃለን። ነገር ግን የግራውን የፖለቲካ ፍልስፍና ትንሽም የምናውቅ ሁሉ፤ ይህ መሸፈኛ ሆኖ በተግባር ፍፁም የማይገናኙ ለመሆናቸው ምስክር አይስፈልገንም። በተቃራኒው ደግሞ ትናንት ማርክሲስት፤ ዛሬ ደግሞ ዴሞክራቶች ነን ብለው፤ ያንኑ ድርጅት ይዘው፤ ትናንትም ዛሬም ከኮንግሬስ በር እውቁን ልመና ቀጥለዋል። ያንን ስም ይዘው ዕርዳት ለማግኘት ትናንትም ዛሬም የአውሮፓን ከተሞች ዳር እስከዳር ይዞራሉ። ያንን ስም ይዘው የትግራይ ተወላጆችን ትናንትም ዛሬም ያሰባስባሉ። በዚያ ስም ነው የሀገሪቱን ንብረት ባደራጁት የንግድ ድርጅት ያካበቱት። ለዚህ ቡድን ግን፤ የራሱን ጥቅም ከመከተል ሌላ፤ የፖለቲካ ፍልስፍናም ሆነ የአስተዳደር መመሪያ ማነቆ የለውም። ጥቅሙን እስካስጠበቀለት ድረስ፤ የራሱን ጥላ ለመሸጥ የተነሳ ቡድን ነው። እናም ከግራም ሆነ ከቀኝ ማዘመዱ፤ ይሄን መንግሥት አይገልፀውም። ስለዚህ በፖለቲካ መስመር የግራ ወይንም የቀኝ የሚለው ትክክለኛ ገላጩ አይደለም። እናም አልቀበለውም።

በዛ ያሉት ኢትዮጵያዊያን ይሄን መንግሥት የተዘበራረቀበት ነው ይላሉ። ይህን መንግሥት በፖለቲካ መስመር ለመፈረጅ፤ የፖለቲካ መስመሮች መግለጫዎችን አሟልቶ መገኘት አለበት። በትክክል ከላይ እንዳሳየሁት፤ ከግራውም ሆነ ከቀኙ የፖለቲካ መስመሮች ጋር ያለው ዝምድና፤ የሱን ፍላጎት እስካሟሉለት ድረስ ብቻ ነው። እናም አዎ ግራና ቀኝ ረግጧል። ያንን ተከትለን ግን አብረን ዘጭ ዘጭ እያልን፤ ዛሬ ግራ ነገ ቀኝ ነው እያልን ልንጓዝ አንችልም። ይህ አካሄድ በትክክል አይገልፀውም። እናም አልቀበለውም።

እንግዲህ ይሄን ካልኩ በኋላ፤ እኔ የምገልፅበትን ከማስፈሬ በፊት፤ ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ፤ አንድን መንግሥት ወራሪ የሚያስብሉ ብዬ ያወጣኋቸውን አስር መመዘኛ ነጥቦች ላስፍር፤

፩ኛ.      ወራሪ መንግሥት ያለበትን ሀገር በኃይል አጥቅቶ የገባ ነው።

፪ኛ.      ወራሪ መንግሥት ያለበትን ሀገር ምንነት አይቀበልም።

፫ኛ.      ወራሪ መንግሥት ያለበትን ሀገር ሕዝብ መብት አያውቅም።

፬ኛ.      ወራሪ መንግሥት በሕዝቡ ዘንድ የራስ መንግሥት ሳይሆን የሌላ መንግሥት ተደርጎ ይወሰዳል።

፭ኛ.      ወራሪ መንግሥት ያለበትን ሀገር ሕዝብ የሁለተኛ ደረጃ ዜጎች አድርጎ ያስተዳድራል።

፮ኛ.      ወራሪ መንግሥት ያለበትን ሀገር ንብረት ዘርፎ ይወስዳል።

፯ኛ.      ወራሪ መንግሥት መሠረታዊ የሆኑትን፤ ያለበትን ሀገር የምንነት ዕሴቶች ያጠፋል።

፰ኛ.     ወራሪ መንግሥት ላለበት ሀገር ባዕድ የሆኑትን የምንነት መግለጫዎች በሕዝቡ ላይ ይጭናል።

፱ኛ.      ወራሪ መንግሥት በጉልበት ይገዛል።

፲ኛ.      ወራሪ መንግሥት ከሚገዛው ሕዝብ ታሪክና ሥርዓት ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የለውም።

ምናልባት ሌሎች ተጨማሪ ሊያደርጉ የሚፈልጓቸው ነጥቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ለኔ እነዚህ በበቂ አመልካቾች ናቸው። ወራሪው ከየት መጣ? ወይንም ንብረቱን ወደየት ወሰደው? የሚሉ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። የነዚህ መልስ ግን የወራሪውን ምንነት በመግለፅ በኩል አስተዋፆዖዋቸው ደካማ ነው። በተጨማሪ ለተወራሪ፤ የወራሪው ከየት መሆን፤ ወረራውን ወረራ ከመሆን አይቀይረውም። ወራሪው ከየትም ይሁን ከየት፣ ከላይ ከሠፈሩት አኳያ፤ በሕዝቡ ላይ ከሚያደርስበት በደልና የዕለት ተዕለት ተግባሩ ነው፤ የወራሪነት መገለጫው። በዚህ ረገድ፤ የወረራን ምንነት ለማወቅ፤ የወራሪውን መምጫና መዳረሻ መመዘኛ አናደርግም። ከላይ የዘረዘርኳቸው አስር ነጥቦች፣ ይህ ወራሪ የሚፈጸመውና ይህ ወራሪ እየፈጸመ ያለው ግብር ብቻ ነው መታየት ያለባቸው። በሀገሩ ላይ በግልፅ ያለውን ሀቅ ከላይ ከተዘረዘሩት አስር ነጥቦች አኳያ እንመልከት፤

አንደኛ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በኃይል ሀገሪቱን አጥቅቶ ገባ። ይኼ የሚያጠያይቅ አይደለም።

ሁለተኛ፤ እንደገባም ሀገሪቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳትሆን፤ ራሱ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የተጠፈጠፋቸው ንቅናቄዎችና የኒሁ ስብስብ “ሕዝቦች” ሀገር ናት አለ። ማለትም፤ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያኖች ሳትሆን፤ የ”ብሔር ብሔረሰቦች” እና “ሕዝቦች” መሬት ናት አለ። እናም የኢትዮጵያዊነትን ምንነት ራሱ በሚፈልገው ቅያሬ ተካው። በዚህም ኢትዮጵያዊነት የሚባል ዜጋ የለም አለ። ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የተነሳበትን ዓላማ፤ በምድሯ ላይ አስቀመጠ። ገዥዎቹ እኒህ ሆኑ።

ሶስተኛ፤ ይህ ግንባር የኢትዮጵያን ሕዝብ መብት አያውቅም፣ አይቀበልም። ድምጻቸውን ሠጥተው የመረጡትን ( ፲ ፱ ፻ ፺ ፯ ምርጫ እንዳየነው ) ሆነ በኢትዮጵያዊ ዜግነታቸው በሕግ የሚገባቸውን ( አሁን በእስልምና ተከታዮች እንዳየነው ) አይቀበልም። የሚያውቀው ሕግ ቢኖር፤ ዛሬ ራሱ ፈልጎ ለዛሬ የፖለቲካ ቀመሩ የሚያወጣውን ሕግ ብቻ ነው።

አራተኛ፤ ኢትዮጵያዊያን “እነዚህ” እርኩሶች እያለ፤ የራሱ እንዳልሆኑ የሚገልፅበት ሀቅ መኖሩን ነጋሪ አይስፈልገንም። “እነሱ” እና “እኛ” የሚለው ገለፃ፤ የውስጥና የውጪ፣ የሀገርና የባዕድ፣ የራስና የሌላ የሆነ ክፍፍል መኖሩን ለመግላጽ መጠቀሚያ ስለሆነ፤ “እነዚህ” የሚለው ቃል በሕዝቡ ዘንድ፤ የኛ ያልሆኑ በማለት፤ ባዕድነታቸውን ያመለክታል።

አምስተኛ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የራሱን አባላት አንደኛ ዜጋ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሁለተኛ ዜጋ አድርጎ እየገዛ ነው። በሹመትም ሆነ በንግድ ፈቃድ፣ በቤት ንብረትም ሆነ በትምህርት ዕድል፤ ኢትዮጵያዊያን መተዳደሪያቸው ሁለተኛ ዜጋ የሆኑበት ሀቅ በሀገሪቱ ሰፍኗል።

ስድስተኛ፤ ይህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ከተመሠረተበት ዕለት ጀምሮ፤ የኢትዮጵያን ንብረት በመንጠቅ የራሱ ያደረገና አሁንም በማድረግ ላይ ያለ ነው። በረሃብ ምክንያት የተገኘን ስጦታ፤ በየከተማው የነበረውን የሀገሪቷ ንብረት፣ በልመና የተገኘውን ድጎማ፤ መንግሥታዊ ንብረት የነበረውን ዕቃ በሙሉ በራሱ ድርጅት ቁጥጥር ሥር በማዋል ዘርፏል።

ሰባተኛ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የኢትዮጵያዊነት ዕሴቶችን አጥፍቷል፤ እያጠፋም ነው። ይህ ከመሬቷ አንስቶ ሕዝቡ በምሬት እየጣላት እንዲወጣ የሚያደርግ ፀረ-ኢትዮጵያዊ ተግባሩ ምስክር ነው። በእምነት ተቋማት ላይ ያደረሰው በደልና አሁንም በማድረስ ላይ ያለው አንዱ ነው። በጋዜጠኞች ላይ ያደረሰው ውርጅብኝ ሌላው ነው። የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ማባረሩ፤ በየመሥሪያ ቤቱ የነበሩትን፤ የፖለቲካ ሰዎች ሳይሆኑ የመንግሥት ቋሚ ሠራተኞች የነበሩትን ማባረሩ ሌላው ነው። እኒህ ከጥቂቶቹ መሠረታዊ የኢትዮጵያ ዕሴቶች መካከል የሆኑት መውደማቸው፤ ለወራሪነቱ መግለጫዎች ናቸው።

ስምንተኛ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ኢትዮጵያዊያንን “ኢትዮጵያዊያን አይደላችሁም። ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም” በማለት፤ ሌላ ማንነት ጭኗል። በኢትዮጵያ ማንም ግለሰብ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ተሳትፎው፤ በኢትዮጵያዊ ዜግነቱ እንጂ፤ ትግሬ ወንም ኦሮሞ፣ አማራ ወይንም ሶማሊ ስለሆነ አይደለም። ይህን ቀየረው። ትግሬ ኢትዮጵያዊ፣ ጋምቤላ ኢትዮጵያዊ ነህ አለ። ፓትሪያርክህን የምሾምልህ እኔ ነኝ አለ። የፋሽስቱ ጣሊያን ወራሪ አቡነ ጴጥሮስን ለኔ ካልታዘዝክ ብሎ እንደረሸናቸው ሁሉ፤ ይሄም የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትሪያርኩን ሽሮ አባረረ። የእስልምና እውነተኛ ተወካዮችን በራሱ ካድሬዎች ተክቶ፤ ሕዝቡ ለአቤቱታ ትክክለኛ ወካዮቹን ቢልክ፤ እስር ቤት አጎራቸው። እኒህን የምንነት መግለጫዎች ሆን ብሎ ያጠቃቸው ያለምክንያት አይደለም። ኢትዮጵያዊያን ርስ በርሳቸው እንዲጣሉና ለወደፊት በመካከላቸው ምንም ዓይነት ስምምነት እንዳይኖር ነው። ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ሌት ተቀን እየጣረ ያለ ነው።

ዘጠነኛ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ራሱ የሚያወጣቸውን ሕጎች እንኳን የማያከብር ነው። እንዳመቸው ሕግ ያወጣል ይሽራል። የሚገዛው በጉልበት ነው። ዋናው ግቡ ሕዝቡን ዝም ማሰኘትና ረግጦ መግዛት እንጂ፤ ማስተዳደር አይደለም።

አስረኛ፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ፣ የሕዝቡ ባህልና ስነ ሥርዓት ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የለውም። ኢትዮጵያዊ ነን ብለው አይዋሹም። የሚገዙት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ነን ብለው ነው። ምነንልባት አሁንም ያ ዝግጅታቸው፤ ማለትም ነፃ የማውጣት ዓላማቸው እንዳለ የተቀመጠ ይመስለኛል። ዛሬም የራሳቸውን ጦር ከማደራጀትና ከማጠናከር ወደ ኋላ አላሉም። ዛሬም የራሳቸውን ዳር ደንበር ከማጎልበት ወደ ኋላ አላሉም። ዛሬም የራሳቸውን ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ጣቢያ ከማዘጋጀት ወደ ኋላ አላሉም። ዛሬም የራሳቸውን ሰዎች በኢትዮጵያ ንብረት ውጪ ሀገር ሰዶ ከማስተማር ወደ ኋላ አላሉም። ዛሬም በማንኛውም መንግሥታዊ ዘርፍ የበላይነቱን በመያዝ ትምህርቱንና ልምዱ ከመሽመት ወደ ኋላ አላሉም። ዛሬም ቀሪው ኢትዮጵያዊ እነኝህን ዕድሎች እንዳያገኝ ወደ ኋላ ከማስቀረት አልቦዘኑም። ኢትዮጵያዊነትን አለመቀበላቸው ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ላለመታረቅ ሆን ብለው የሚጥሩ ናቸው። እብሪትና ኩራት ደረታቸውን የነፋው ይመስለኛል። ነገ ኢትዮጵያዊ ይሆናሉ ማለት ዘበት ነው። ምንአልባት ጠላት!

በዚህ እደመድማለሁ። የለም ተሳስተሃል የሚልና ትክክለኛው ይህ ነው የሚል ቀረቤታ ካለ ለመመልከት ዝግጁ ነኝ። ዋናው ይኼ ሀገራዊ ውይይት አስፈላጊ ነው ብለን የምናምን ታጋዮች፤ ሃሳባችንን ወደፊት ማቅረብ ነው።

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in እስከመቼ - ESKEMECHE. Bookmark the permalink.

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s