የአባይ ግድብና የኢትዮጵያ ፖለቲካ

የአባይ ግድብና የኢትዮጵያ ፖለቲካ
አንዱ ዓለም ተፈራ
የእስከመቼ አዘጋጅ – አሜሪካ
አርብ ጥር ፴ ቀን ፳፻፮ ዓመተ ምህረት
የአሁኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ የሕዝቡን ድምፅ መስረቅ፣ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ማሰር፣ ማባረርና መግደል፣ ሃይማኖቶች የገዥው ክፍል መገልገያ ይሆኑ ዘንድ፤ የእምነቶቹ ተከታዮቹን፤ አቤት! ወዴት! ብለው እንዲሰግዱለት ማስገደድ፣ ደንበራችንን ቆርሶ መሥጠት፣ ለም መሬቶችን ባለቤቶቹን አፈናቅሎ ለባዕዳን መቸርቸር፣ አባይን መገደብ፣ በጠቅላላው ሕዝቡን አፍኖና ረግጦ የመግዛት አስተዳደራዊ ዘይቤ ነው። በአንፃሩ ደግሞ፤ ድህነትን ማጥፋት፣ የመሬቱን ሥሪትና የመሬት ባለቤትን መልስ መሻት፣ የሁሉንም የኅብረተሰቡን የልማት ዘርፍ ተቆጣጣሪነት በማን እጅ ነው ብሎ መጠየቅ፣ ሀገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ናቸው።
ከነዚህ አንዱን ብቻውን ለይቶ በማውጣት፤ ጥቅሙንና ጉዳቱን፣ ችግሩንና መፍትሔውን አንስቶ መፍትሔ ላይ መድረስ አይቻልም። የሀገራችንን ፖለቲካ ውስጡን መመርመር አለብን። እንደማንኛውም አምባገነን መንግሥት ሁሉ፤ በሀገራችን ላይ ያለው ገዢ መንግሥት የሚያቅደው ሆነ በተግባር የሚያውለው ሀገራዊ ድርጊት፤ የራሱን ሕልውና ለማራዘም ብቻ ነው። የወራሪም ዓይነት አስተዳደር ስለሆነ፤ የሀገሪቱን የቅርብ ሆነ የዘለቄታ ጥቅም በማንኛውም መንገድ ያስጠብቃል ማለት፤ የሕልም እንጀራ በልቶ ሲነቁ ጠገብኩ እንደማለት ነው።
ለዚህ ምክንያቱ፤ ሀገራዊ ጉዳዮች አንዳቸው ካንዳቸው የተቆላለፉበት ሀገራዊ ትስስር ስላላቸው ነው። የሀገራችንን ፖለቲካ መረዳት የሚቻለው፤ ከየት ወዴት? ለምን በምን? ብለን ጠይቀን፤ በሀገራችን ያሉትን ዕቅዶችና ተግባራት፤ ዝምድናቸውንና ሂደታቸውን ስንረዳ ነው።
ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከቆመ አስተዳደር፤ ምን ዓይነት ዕቅድና ተግባራዊነት ያለው ምግባር ይጠበቃል? ኢትዮጵያዊያን መንግሥት አለን፣ ለኛ የቆመ ነው፣ የኛ ነው ማለታችንንን አቁመናል። ይልቁንም ይሄ መንግሥት ወድቆ በሀገሪቱ የሕይወት እንቅስቃሴ ለማድረግ በመጠባበቅ ላይ ነን ማለት ይቻላል። በአንፃሩ ደግሞ፤ ገዢው ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጡ መንግሥት፤ ይኼን ባለመረዳት ይሁን በዕብሪት፤ መግደሉንና ሀገር ማፍረሱን ብቻ የወደፊት መራመጃ ሜዳው አድርጓል።
የአባይን መገደብ አስመልክቶ፤
በተናጠልና በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ፤ የአባይ ወንዝ መገደብ በሁለት መንገድ ለኢትዮጵያ ጠቀሜታ አለው። የአባይ ወንዝ መገደብ የለበትም የሚል ካለ፤ ሌላ አጀንዳ ያነገበ ነው። አባይ ለኢትዮጵያ መንግሥታት ደካም ጎን በመሆን፤ ሲያስጠቃን የኖረ ሀብታችን ነው። በአንድ በኩል ሉዓላዊነታችንን አስረክበን፤ በፈሳሹ ውሃም ሆነ በሚጭነው አፈራችን ላይ ባለቤትነታችንን አስምረን፤ ከደካማ ጎንነት ይልቅ መጠቀሚያ መሣሪያ ከማድረግ አኳያ አባይን የመገደቡ ዓላማ ይደገፋል። በሁለተኛው ወገን ደግሞ፤ የአባይ ወንዝ ሲገደብ፤ ሊገኝ ከሚችለው ልማታዊ ጠቀሜታ አንፃር የመገደቡ ዓላማ ይደገፋል።
እንግዲህ ይኼን ካስቀደምን በኋላ ተከታዩ ጥያቄ፤ ከተግባራዊነቱ በፊት፤ ለምን? እንዴት? ማን? መቼ? የሚሉትን ጥያቄዎች ከሀገሪቱ ሌሎች ጉዳዮች ቅደም ተከተል አኳያ መመልከት ግዴታ ይሆናል። እንዲያው ግድቡ ተጀምሯልና ሌላውን ጉዳይ ወደኋላ ትተን፤ ይኼ የተጀመረ ሀገራዊ ጉዳይ እንዴት እንደሚጠቅም ወይንም በምን መንገድ ወደፊት መሄድ እንዳለበት እንወያይ የሚለው የጓዳ በር ሩጫ፤ ሀገራዊ መዘዝ ስላለው፤ ረጋ ማለቱና ከሥሩ ጉዳዩን መመርመሩ አማራጭ የሌለው ግዴታችን ነው።
አሁን በገዢነት የተቀመጠውን ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ይዞ፤ የአልጀርሱን ስምምነት አልቀበልም በማለት ሰርዞ፤ የኤርትራ መንግሥት፤ ለፈፀመው ወረራና ለወደቁት ፹ ሺ ወጣቶች ተጠያቂነት አለበት ብሎ መነሳት አይቻልም።
አሁን በገዢነት የተቀመጠውን ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ይዞ፤ አሰብን በዓለም መንግሥታት ፍርድ ቤት ወስዶ፤ ወደ እናት ሀገሯ ወደ ኢትዮጵያ እናስመልሳለን ማለት አይቻልም። ከአሰብ ወደብ ጥቅም ይልቅ የአባይ ወንዝ መገደብ ጥቅም ይበልጣል የሚል ካለ አእምሮው መመርመር አለበት።
አሁን በገዢነት የተቀመጠውን ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ይዞ፤ የሀገራችንን ደንበር በዓለም አቀፍ አደባባይ አቅርበን ትክክለኛውን ፍርድ እናገኛለን ማለት አይቻልም። ደንበራችን ተቆርሶ ለውጭ ሀገር ከመሠጠቱ ይልቅ፤ የአባይ ወንዝ መገደቡ የበለጠ ይጠቅማል የሚል አእምሮው መመርመር አለበት።
መቀጠል እችላለሁ፤ ነገር ግን የምታውቁትን መደለዙ ጠቀሜታ የለውም። አሁን በገዢነት የተቀመጠውን ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት ይዞ፤ የአባይን ወንዝ ግድብ እንዲህ ይሁን ወይንም እንዲያ ይሁን ለማለት እሞክራለሁ ብሎ መነሳት፤ ራስን መሳቂያ ለመድረግ ባደባባይ መጋለጥ ነው። እናም የአባይን ወንዝ ከገዢው ክፍል ውጪ ውጤቱ ለሀገር እንዲውል ሃሳብ አቅርበን አናስወስናለን ማለት ዘበት ነው። እናም የአባይ ወንዝ ግድብ ከዕቅዱ እስከ አፈፃፀሙ ለፖለቲካ መሣሪያነት የታለመ ስለሆነ፤ በዚህ መሳተፍ የፖለቲካ መሣሪያ ለመሆን በፈቃደኛነት ጀርባን አጉብጦ አንገትን ለሠይፍ መድፋት ነው። ለዚህ ራሳቸውን ያቀረቡ፤ የግል አጀንዳ አላቸውና ማንም ሊያስቀራቸው አይችልም። ለሀገር ጥቅም ነው እያሉ ግን ማንንም አያጃጅሉም።
የተጀመረ ግድብ የሕልውና መሠረቱ ያልተስተካከለ ነውና፤ ሆን ብለው ሊያስቀሩት ሳይሞክሩ፤ በፖለቲካ ክስረቱ የትም አይደርስም ወይንም በፖለቲካውም ሆነ በጥቅሙ ፀረ-ኢትዮጵያ ለሆነ ተግባር የሚውል ይሆናል። መሠረቱ ትክክል ቢሆን ኖሮ፤ ብዙ ፈተና መቋቋም ይችል ነበር። ትክክለኛነት የጎደለውና በእኩይ ተንኮል የተመሠረተ እንደሆነ እያወቅን ወደፊት መሄድ አይኖርብንም። ጉዳቱ እንዳያመዝን ማስላት አለብን። የአባይ ወንዝ መገደቡን ጉዳይ፤ ከላይ እንደጠቀስኩት ሁላችንም እናምንበታለን። ይሄ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያዊያን ጉዳይ። ሌሎች ጉዳዮች አሉን። በርግጥ የአባይ ወንዝ መገደቡ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ታዲያ ዝግጅቱ ደግሞ የበለጠ አንገብጋቢ ነው። አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉና ቅደም ተከተሎችን ማወቅና መከተላችን ደግሞ ግዴታችን ነው።
የአባይ ወንዝ ግድብ የተጀመረው ለምን ሲባል ነው? ይህን ጥያቄ መጠየቅ የግድ አለብን። መልሱ ደግሞ የግንቡ ጉዳይ በተጀመረበት ወቅት ከነበረው የዓለም የፖለቲካ ሁኔታና የሀገራችን ተጨባጭ ሀቅ ጋር የተዛመደ ነው። እናም ያንን ማንሳት አለብን። ለምን እንጠይቃለን ቢባል፤ መልሱ፤ የግድቡን መሠረትና ሕይወት ስለሚነግረን ነው። እንዲያው ማንም ይጀምረው ማንም፣ ለምን ተጀመረ እንዴት፤ ብቻ ተጀመሯልና እንተባበር ማለት፤ ደሮን በመጫኛ ነው። በዚህ መነፅር ስንመለከተው፤ የአባይ ወንዝ አሁን የተገደበው፤ ከላይ በጠቀስኳቸው ሁለት ሀገራዊ ጠቀሜታዎች ተመሥርቶ ሳይሆን፤ ለፖለቲካ ፍጆታ ነው። ለፖለቲካ ፍጆታ የሚተገበሩ ዕቅዶች ደግሞ ዘለቄታ የላቸውም። አሽከርካሪው የወቅቱ ፖለቲካ ነውና!
በአስተዳደሩ ብልሹነትና በኑሮው አስቸጋሪነት ሕዝቡ እንዳይነሳበት የፈራው ወገንተኛ አምባገነን ሕገወጥ መንግሥት፤ የአባይን ወንዝ ግድብ ጀመረ። ታዲያ አሁን የገንዘብ ችግር አለብኝ በማለት፤ ሀገራዊ ስሜት ቀስቅሶ ገንዘብ ማሰባሰብ ያዘ። እንዲህ ያለ ግድብ ሲጀመር ምን ምን መደረግ ያለባቸው ጉዳዮች ነበሩ? እንዴት ነው የገንዘብ ወጪው መታቀድ የነበረበት? ብለን ስንይዝ፤ ብቻ ተጀምሯልና እንርዳ የሚል መልስ ይሠጣል። ይህ ስህተት ነው። የተጀመረ ሁሉ እንዳጀማመሩ ይሳካል ወይንም አይሳካም። በየተፋሰሱ ገና ብዙ የሚገደቡ ወንዞች አሉን። መገደብም እንችላለን። ሀገራችን ብዙ ዕቅዶችና በተግባር መዋል የሚገባቸው ጉዳዮች አሉዋት። ሕዝቡ ተባብሮ ይተገብራቸዋል። ሕዝቡ የኔ ያለው መንግሥት ሲኖርና ሀገራዊ ቅደም ተከተሉን የሚያስተካክል መንግሥት ሲኖር፤ ሕዝቡ በሙሉ ልቡ የሚያንቀሳቅሳቸውና ከግብ የሚያደርሳቸው ጉዳዮች አሉን። ሀገራችን ወደፊት ገፍታ ከዓለም መንግሥታት የዕድገት ደረጃ ትቀመጣለች። ሀገራችንን ደሃና ኋላ ቀር ያደረጋት፤ የአስተዳደር በደል እንጂ፤ የተፈጥሮ ሀብት ወይንም የተማረ ሰው እጥረት አይደለም።

eske.meche@yahoo.com

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in አስተያየቶች - Commentaries. Bookmark the permalink.

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s