የአቶ አለምነው መኮነን ጭንቅላት ወይንም ጭንቅላት አልባነት !

አለምነው መኮነን

የአቶ አለምነው መኮነን ጭንቅላት ወይንም ጭንቅላት አልባነት !
ጥር ፳ ፬ ቀን ፳ ፻ ፮ ዓመተ ምህረት  – 2/1/2014

በዕርግጥ የአንድን የሀገራችን ክፍል ነዋሪዎች ጉዳይ አንስቶ በአንድ መንገድ ወይንም በሌላ መንገድ መነጋገር፤ ወደድንም ጠላንም፤ ያለንበት ዘመን ግዴታ ሆኗል። ትናንት አኝዋኮች ተረሸኑ፣ የኦጋዴን ወገኖቻችን ተከበው ተሰቃዩ፣ ኦሮሞዎች በእስር ቤት ታጎሩ እያልን እንደጮህን ሁሉ፤ ዛሬ ደግሞ በአማራዎች ላይ የሚደርሰውን በደል አንስተን መነጋገር ግዴታችን ሆኗል። የክርስትና እምነት ተከታዮች እንዲህ ሆኑ፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንዲያ ሆኑ ስንል ብዙ ዓመታት ቆጠርን።በማይዘነጋ መንገድ ደግሞ እያንዳንዱን ለይተን እያነሳን፤ ይኼኛውን ብቻ የሚያደርጉ የዚህኛው ክፍል ብቻ ተወላጆችና ለዚያ ክፍል ብቻ ተቆርቋሪዎች ተደርጎ ስለሚወሰድ፤ እያንዳንዱን ጉዳይ “ለሌሎች” መተውና ጠቅላላ ኢትዮጵያዊንን በሚነኩ ጉዳዮች ላይ ብቻ መቆም፤ የታጋይነት ምልክት ተደርጎ የተወሰደ ፈሊጥ ሆኗል። እኔ ይኼን ትክክል ብዬ አልወስደውም። ለእያንዳንዱ ጉዳይ ቆሜ እቆጠራለሁ። በኢትዮጵያዊነቴ የምኮራና በዚያ ብቻ ሀገራዊ የፖለቲካ ተሳትፎዬን የምለካ ስለሆነ፤ ይህ ጉዳይ ከአእምሮዪ ውጪ ነው። አማራው አማራ በመሆኑ ብቻ ለሚደርስበት በደል መቆርቆር፤ የግድ ከአማራ መወለድ አለበት የሚል ካለ፤ ዘረኛ ነው። በኢትዮጵያዊነቱ አያምንም። ለአማራው የሚቆረቆረውን ሁሉ ደግሞ ትምክህተኛ አማራ የሚል ሁሉ፤ ዘረኛ ነው። አማራን ይጠላል። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ላይ የሚደርሰውን በደል የኔ ብሎ ያልተነሳ ታጋይ ነኝ ባይ፤ ባይ እንጂ ኢትዮጵያዊ ታጋይ ነኝ ሊል አይገባውም። በአኝዋኩ ወገናችን፣ በኦሮሞው ወገናችን፣ በአማራው ወገናችን፣ በኦጋዴኑ ወገናችን የሚደርሰው በደል፤ የእያንዳንዳችን በደል ነው ብለን መውሰድ ካልቻልንና፤ የአንዱን ወገን በደል ብቻ ይዘን የምናቅራራ ከሆነ፤ ውሸታምና ዘረኛ ለመሆናችን ሌላ መረጃ አያስፈልግም። በዚህ ጽሑፍ፤ የአማራ ክልል ም/ፕሬዚዳንት እና የብሔራዊ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን የተናገሩት፤ ምን ያህል ፀረ-ኢትዮጵያና፤ ውሃው የተቀዳበት ምንጭ የወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ ፓርቲና መንግሥት የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ እንደሆነ አሰምራለሁ። እናም ደግሞ ይህ አደገኛ መርዝ፤ ጠንከኛነቱን አሳያለሁ።

በወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ ገዢ ቡድን የፖለቲካ ስሌት፥ አማራውን ማጥቃት፤ ከሥር መሠረቱ ሲፈጠር ምሰሶዬ ብሎ የያዘው የትግል ምሰሶው ነው። ቀጥሎም የመንግትነቱን ካባ ካጠለቀ ወዲህ፤ ከራሱ አልፎ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሥልጣን መቆናጠጫ ዋና መሰላሉ፤ ይኼን መቀበልና መተግበር ሆኗል። ይህ ደግሞ ከአማራው ወገን ተወለድን ለሚሉትም ሆነ ከአማራው ወገን አልተወለድንም ለሚሉት ሁሉ የሚሠራ መለኪያ ሚዛን ነው። አንድ ጭንቅላት ብቻ ነው ያለው፤ የገዢው ቡድን ጭንቅላት። ስለዚህ አቶ አለምነው መኮነን ተናገሩት ወይንም አቶ ደሳለኝ ሀይለ ማርያም ተናገሩት ለውጥ የለውም። ሁሉም አፋቸው እንጂ ጭንቅላታቸው የነሱ አይደለምና! እናም የግለሰቡን የአቶ አለምነውን ሰውነት ሳይሆን፤ የአቶ አለምነው መኮነንን ጭንቅላት ነው ማስመዘን የምፈልገው። ቀደም አድርጎ ግን አቶ አለምነው ጭንቅላት አላቸው ወይ? ወይንስ ጭንቅላት የላቸውም? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። በዕርግጥ በዚህ ወራሪ በመሰለ አስተዳደር ለመዘፈቅ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ማንነትን ሽጦ መቆም ግዴታ ነው። ይህ በአእምሯቸው ሳይሆን በሆዳቸው የሚመሩ ሰዎች ብቻ የሚሰበሰቡበት አስተዳደር ለመሆኑ ማስረጃ፤ የራሳቸውን ነፃነት አለማግኘታቸው ነው። ወይንም በትክክለኛው አነጋገር፤ ራሳቸውን መሸጣቸው ነው። አእምሮ ማጣታቸው ማለቱ ይቀላል።

ወንጀል ከተፈፀመ፤ እከሌ ወይንም እከሌና እከሌ ይኼን ሠሩ ወይንም ያንን ሳይሠሩ ቀሩ ብሎ አንድን ወይንም የተወሰኑ ግለሰቦችን መወንጀል፤ ተገቢ ነው። በአንድ ሀገር ያሉትን የአንድ የኅብረተሰብ ክፍል አባላትን ግን ለይቶ ይኼን አደረጉ በተለይም እንዲህ ናቸው ብሎ መወንጀል፤ ከግልብነቱ በላይ የኅብረተሰብን ምንነት አለማወቅን የሚያሳይ አጉሊ መነፅር ነው። ከዚህ ተነስቼ ነው የአቶ አለምነው መኮነንን ንግግር የምረዳው። እስኪ ከአቶ አለምነው መኮነን ንግግር ጠቀስ አድርጌ፤ ጭንቅላት አላቸው ወይንስ የላቸውም? ያስባለኝን ላሳያችሁ፤

፩ኛ፤ “ የአማራው ህዝብ በቅድሚያ እንዳይሰደድ ለማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፣ ነገር ግን ከተሰደደ በሁዋላም ቢሆንም ሰንፋጭ የሆነውን ትምክህተኝነቱን በመተው ከሌላው ጋር ለመኖር መልመድ አለበት። ”

፪ኛ፤ “ የአማራው ህዝብ ሰንፋጭ የሆነ ትምክተኝነት የተጠናወተው በመሆኑ በቤንሻንጉልና በሌሎችም ቦታዎች ለመሰደዱ ምክንያት ሆኖታል። ”

፫ኛ፤ “ በባዶ እግሩ እየሄደ የሚናገረው ንግግር ግን መርዝ ነው። ይሄ መርዝ ንግግሩ አንድ የሚያደርግ አይደለም። ”

፬ኛ፤ “ ከኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ለመኖር አማራው  የትምክህት ለሃጩን ማራገፍ አለበት። ይሄ ለሃጭ ሳይራገፍ በጋራ መኖር አይቻልም። ”

፭ኛ፤ “ ማንኛውም ስም ያወጣ ሙትቻ ፓርቲ ሁሉ መንገሻው አማራ ክልል ነው። ትምክህትን እንደ ምግብ ስለሚመገበው ነው። ያንን ምግብ እየተመገበ ያቅራራል። ”

እዚህ ላይ አቶ አለምነው መኮነን ሁለት መልዕክት ባንድ ላይ አስተላልፈዋል። የመጀመሪያው፤ የአማራውን ጠባየ ቢስነት አመልክቶ፤ አማራውን መኮነን ሲሆን፤ በሥር አስደግፎ ደግሞ፤ አማራው ከሌሎች ቦታዎች በተሰደደበት ምክንያት መንግሥታዊ አካላት ተጠያቂ አይደሉም ብሎ ለማሳመን የተቀመመ መርዝ ነው። ለመሆኑ አቶ አለምነው መኮነን ኢሕአዴግ ራሱ፤ የአማራውን ከሌሎች መፈናቀል ትክክል አልነበረም ሲል፤ የት ነበሩ? መንግሥት በየደረጃው፤ “ደን ስለጨፈጨፉ ነው” ሲል፤ የት ነበሩ? ይኼ የናንተ ቦታ አይደለም ሲባሉ፤ የት ነበሩ? ወይንስ ኢሕአዴግ የአቶ አለምነው መኮነንን ጭንቅላት በመጠቀም፤ ያመነበትን ባደባባይ ተናግሮ በጓሮ በር ራሱን ነፃ ለማውጣት የለከካት መልዕክት ናት? የተፈናቀሉት በትምክህተኛነታቸው ሳይሆን በአማራነታቸው ነው። ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ አዛውነት፣ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ደሃዎች፣ ባለፀጎች፣ ሁሉም ታታሪ ሠራተኞች ተባረዋል። ያካባቢው ሰዎች በተቻላቸውና መንግሥታዊ መዋቅሩ በማያውቀው መንገድ ድጋፍና ሐዘኔታ ሠጥተዋቸዋል። ይህ መንግሥታዊ ተግባር ትክክል ስላልሆነ ወደ መጡበት ይመለሱ ሲል ኢሕአዴግ ራሱ ወስኗል። አቶ አለምነው መኮነን! በኢሕአዴግኛ አነጋገር ወንጀለኛው እርስዎና እንደርስዎ ያሉት አፈናቃዮች ናቸው። ተራዎ ደርሶ፤ እርስዎም መጠቀሚያነትዎ አብቅቶ፤ እስኪባረሩ ወይንም ዘብጥያ እስኪወረወሩ ድረስ፤ ከወገብዎ በደንብ ልምጥ ይበሉ!

አማራው እንዲህ ነው ብሎ መጮህ፤ አማራውን ሌሎች እንዲበድሉት ፍቃድ ፈርሞና ታርጋ ለጥፎ መሥጠት ብቻ ሳይሆን፤ አማራው በተፈጥሮ ጎደሎ ስላለበት፤ ከአማራ የተገኘ ሁሉ፤ አብሮ ለመኖር አይመችምና፤ ከያለበት አባሩት ማለት ነው፤ ከኢትዮጵያዊነትም! ይህ ፀረ-ኢትዮጵያዊነትና ፀረ-ሰብዓዊነት ነው። ለነገሩ በዚህ ሹመት ከተመደበ በሆዱ ተንፏቆ በሆዱ ከሚያድር ሹም ሌላ ምን ይጠበቃል? አቶ አለምነው መኮነን ከአማራው ወገን ተወላጅ መሆናቸው ዋጋ የለውም። የአቶ በረከት ስምዖንም የአማራው ተወላጅነትና ተወካይነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ! እንዲህ ነው በአማራው ላይ መሾም ማለት!

በሌላ በኩል ስለ አንቀጽ 39 ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። እስኪ ለምን ቀረበላቸው የሚለውን እናጢን! አንቀጽ 39 አማራውን ለብቻው እንደ አማራነቱ የሚጎዳው ነው ወይ? አማራውን ማጥቂያ መሣሪያ በመሆኑ ነው ወይ? የአማራ ክልል ሰዎች እንዲጠይቁ የተገደዱት? ጥያቄውን ማንሳታቸው የሚያመለክተው፤ አንድም አማራን ማጥቂያ መሣሪያ በመሆኑ፤ ወይንም የኢትዮጵያን አንድነት አማራው አጥብቆ ስለያዘ ነው። ከዚህ ሌላ ምንም ምክንያት የለውም። ታዲያ አማራው የሚጠቃበት መንገድ፤ በኢትዮጵያዊነቱ ነው ማለት ነው። በተለይም ኢትዮጵያዊነትን ስላጠበቀና በመላ ኢትዮጵያ ተበትኖ ስለኖረ። እናም አንቀጽ 39፤ “ኢትዮጵያን ለመጉዳት የታሰበ ወይንም አማራን ከማጥቃት ጋር የተያያዘ ነው።” ብለው ቢያንስ በአማራው ክልል ያሉት የራሱ የገዥው ካድሬዎች ያምናሉ ማለት ነው። ይኼ ራሱን ችሎ የሚታይ በመሆኑ እዚህ ላይ አስተያየት አልሠጥበትም። ለዚህ ጥያቄ የአቶ አለምነው መኮነን መልስ ደግሞ፤

፮ኛ፤ “ አንቀጽ 39 ባይኖር ኖሮ ኢትዮጵያ  ደቡብ ሱዳን እንደሆነቸው ትሆን ነበር። አንቀጽ 39 በህዝቦች ዘንድ መተማመን መፍጠሩን፣ አቶ መለስ ዜናዊ በሞቱበት ጊዜ በገሃድ ታይቷል። ”

በዚህ መልስ የምረዳው፤ አቶ አለምነው መኮነን እንደ አቶ ደሳለኝ ሀይለማርያም የራሳቸውን ጭንቅላት ተጠቅመው የሚሠሩ ሳይሆን፤ በሟቹ “ባለራዕይ” መሪያቸው የሚጎተት መሆኑን ነው። ሟቹ ቢኖሩ ከዚህ የተለዬ እንደማይናገሩ ስለምናውቅ፤ አቶ አለምነው መኮነን ማስተላለፊያ ቀፎ መሆናቸውን ተረዳሁ። ታዲያ የአቶ መለስ ዜናዊን ቀሚስ ለምን አያጠልቁም? አዎ አምባገነኖች ከነሱ ሌላ በራሱ ጭንቅላት አስቦ የሚሠራ እንዲኖር አይፈልጉም። ታሪክም ይኼንኑ ነው የሚያስረዳን።

እንግዲህ አንደኛ፤ አቶ አለምነው መኮነን የራሳቸው ጭንቅላት የላቸውም ወይንም አከላቱ እንደ ግንድ በድኖ ከራሳቸው ውስጥ ቢኖርም፤ የገደል ማሚቶ ሆኖ ከማስተጋባት ሌላ ሙያ የለውም ማለት ነው። ሁለተኛ፤ ፀረ-ኢትዮጵያዊ የሆነን ተግባር፤ በአማራው ትምክህነት ማመካኘት፤ አደገኛና ለወደፊቱ የአማራውን ኢትዮጵያዊነት ብቻ ሳይሆን፤ የአማራውን የኅብረተሰብ አካልነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ መርዝ ነው። በሶስተኛ ደረጃ ልጠቁም የምፈልገው፤ ራሱ ኢሕአዴግ ሳይወድ ተገዶ ያመነበትን የአማራውን የማፈናቀል ወንጀል፤ ከኢሕአዴግ አሳልፎ በአማራው ላይ ለመለከክ የተደረገ የብልጠት ቅሌት ነው። ማሳረጊያው ግን፤ ይኼን መዘርዘሩ ሳይሆን፤ ይኼን ማውገዙ ሳይሆን፤ ይህ እንዳይደገም ሆነ ለዚህ ተጠያቂዎችን በሕግ ፊት ለማቅረብ፤ የታጋዩ ወገን ምን እያደረገ ነው? ነው። ይህ ትግል የኢትዮጵያዊያን፤ በኢትዮጵያዊነታችን አንድ ራዕይ ኖሮን በአንድ ድርጅት ተሰባስበን የምንነሳበት ትግል ነው። ይህ የአማራው ብቻ እንጂ፣ የትግሬው፣ የኦሮሞው፣ የደቡቡ፣ የኦጋዴኑ፣ የአኙዋኩ የግል ጉዳይ ያልሆነ አይደለም። የኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያዊያን የኔ ብለን በአንድነት እስካልተነሳን ደረስ፤ መፍትሔው የውሃ ውቀጥ መፍትሔ ነው፤ ውሃን ቢወቅጡት መልሶ እምቦጭ ነውና! ከነአቶ አለምነው መኮነን ሆነ ከአሽከርካሪዎቻቸው ተወግዘውም ሆነ ተለምነው መፍትሔ እንዲሠጡን መጠበቅ፤ ላም አለኝ በሰማይ ነው።

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in አስተያየቶች - Commentaries. Bookmark the permalink.

4 Responses to የአቶ አለምነው መኮነን ጭንቅላት ወይንም ጭንቅላት አልባነት !

 1. Gashaw ይላሉ:

  ውድ ንጋቱ ይሄ ሊገርምህ አይገባም አለምነው መኮንን አያቶቹ ከማይጨው እየተመለሱ የነበሩትን አርበኞች በጥይት የደበደቡ ናቸው፡፡ አለምነው በህቡእ አማራም አይደለንም ትግራይም አይደለንም የሚሉ የባንዳ ጥርቅም ስብስብ የሆነው ቡድን አባል ነው፡፡ ንጋቱ በአማራ ክልል እገሌ ተብሎ የሚጠራ ስም ያለው ኃላፊ የለም፡፡በአብዛኛው ህላዌ ዮሴፍ እና ታደሰ ጥንቅሹ ከሻይ ቤት የሰበሰቧቸው ዱርዬዎች ጥርቃሞ ቡድን ነው፡፡ ኅላዌ ዮሴፍ በአንድ ወቅት አንድ የትምህርት ሚኒስቴር የጥበቃ ሰራተኛን አላውቅህም አላስገባህም በማለቱ በሚስቱ ትእዛዝ እዚሁ ባህርዳር ላይ በጥይት የጥበቃ ሰራተኛን መምታቱን ብተሰማ ምን ትላለህ? የአለምነው የአሁኑ ንግግር እነ ሌንጮን እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት በብአዴን በኩል የቀረበ የእጅ መንሻ ስጦታ ነው፡፡ ሞት ለአለምነው መኮንን

  Like

  • nigatu ይላሉ:

   ውድ ጋሻው፤
   በትክክል አስቀምጠኸዋል። አጻጻፌም የመልዕክቱን አመጣጥ ለመጠቆም እንጂ፤ እንደዚህ ያለውን ሰው ለማጋለጥና አዲስ የመረጃ ፍንጭ በሱ ላይ ለመስጠት አልነበረም። ሆኖም ግን፤ ይኼንን እየሰማን ዝም እንዳንል መሠረታዊ የሆነውን የመልዕክቱን ጥሬ ሃሳብ ለማሳየት ነው። ትክክለኛ ትንታኔ ነው ያቀረብከው። አመሰግናለሁ።

   Like

 2. የተሰደበው በወሳኘኝነት የጎጃም ህዝብ ነው!!!!

  Like

  • nigatu ይላሉ:

   አየህ አበጀ፤ የተሰደበው ራሱ ሰዳቢው ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፤ የጎጃም፣ የጎንደር፣ የወሎ ወይንም የሸዋ ብለን ራሳችንን አንከፍልም። ቀጥሎ ደግሞ፤ ሰዳቢውን በማጋለጥ በኩል የስድቡን አመጣጥና ምንነት እንጂ፤ በማን ላይ ተቃጣ የሚለው፤ ለኛ ፋይዳ የለውም። ምክንያቱም፤ ራሱ ስድቡ ትክክል እንዳልሆነ እንጂ የስድቡ መዳረሻ የት እንደሆነ መመልከቻ መነፅር የለንም። ስለዚህ፤ የተሰደበው እከሌ ነው፤ አይደለም የሚለው ንትርክ ጠቃሚ ስላልሆነ፤ ወንድሜ ተወው።

   Like

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s