ይኼም ያልፋል – ካወቅንበት!

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ           ይኼም ያልፋል – ክፍል ፩

ይኼም ያልፋል  –  ካወቅንበት!  ( ክፍል ፩ )

የእስከመቼ አዘጋጅ – አንዱ ዓለም ተፈራ

ሕዳር ፲ ፱ ቀን ፳ ፻ ፷ ዓመተ ምህረት፤         November 28, 2013

የካቲት ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓመተ ምህረት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ይዘትና መልክ ለመቼውም እንዳይመለስ አድርጎ ለውጦታል። የሕዝቡን አመለካከት ለውጧል። የፖለቲካ ምኅዳሩን ቀይሮታል። የገዥዎችን ምንነት ከመሠረቱ፤ በጎም ሆነ ዕርግምት፤ እንዳይመጣ አስናብቶታል። ከዚያ በፊት የነበረው፤ ጊዜው ያለፈበት፣ የዓለምን የዕድገት ግሥጋሤ ደረጃ ያልተከተለ፣ ባለበት የበሰበሰና የአዲሱን ትውልድ ሕልውና እንኳን ለማውቅ ያልፈለገ ነበር። እናም ደህና ሁን ተብሏል። ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓ. ም. ፵ኛ ዓመቱ ሊከበር በራችንን አንኳኳቷል። ምን ተፈጠረ? ምን ተደረገ? ምን ተከተለ? እኛስ ማንነታችንና ሚናችን ምንድን ነው? ራሳችንን ለማወቅ፤ ከየት መጣን፣ አሁን ላለንበት ሁኔታ እንዴት በቃን? ለሚሉት መልስ ማግኘት አለብን። ታሪካችን ስናጠና፤ የአሁን ማንነታችንን እናውቃለን። ታሪካችንን ስናጠና፤ የስብስብ ትናንትናችንን ስናውቅ፤ የዛሬው ማንነታችንን ለመረዳት በር ይከፍትልናል። ታሪካችንን ስናጠና፤ ከሌሎች የተለየንበትን በመገንዘብ፤ የራሳችንን ማንነት እናውቃለን። ታሪካችንን ስናጠና፤ ለነገው ጉዟችን ግራ ቀኙን በመመርመር፤ ስንቅ እንቋጥራለን። ታሪካችንን ስናጠና፤ የፖለቲካ አስተሳሰባችን ይዳብራል፤ ከሰማይ በተዘረፈ ርዕዩተ ዓለም መነፅር ረዳትነት ሳይሆን፤ በኅብረተሰባችን በተመሠረተ ግንዛቤ። የፖለቲካ ፍልስፍና መሠረቱ በኅብረተሰባችን ውስጥ ያለው ሀቅና ተጨባጩ የሕዝቡ የአመለካከት እውነታ ነው። እናም የራሱ የወገኑ የሆነ መሠረት በመያዙ፤ በሕዝቡ መካከል ለሚኖረው የፖለቲከኞች እንቅስቃሴ፤ ድልድዩ ጠንካራ ይሆናል። በመካከላቸው ለሚኖረው ልውውጥም የሠላ መንገድ ይፈጠራል። ታሪክን ማጥናቱ ከሁሉም በላይ በፖለቲካው መስክ ለተሰማሩት፤ ወሳኝ ነው።

ያለፉት ፵ ዓመታት፤ ከ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ አንስቶ እስከ አሁን ፳ ፻ ፮ ዓ. ም. ድረስ ያሉት፤ በኢትዮጵያችን ታሪክ ውስጥ፤ የተለየ ቦታ አላቸው። ልዩ ቦታቸው፤ የጨለማ ዘመን የነበረው ዘመን መሳፍንት ካለበት መቀመጫ ጎን ነው። ልዩ ቦታቸው፤ በፋሽስቱ የጣሊያን ወረራ ያለፉት የ፭ ዓመታት የግፍ ዘመን ካለበት ቦታ ነው። በነዚህ ዓመታት ያሳለፍነውና ያለንበት ይህ የፖለቲካ ሀቅ፤ እንደዘመነ መሳፍንቱና እንደ ፋሽስቱ ዘመን ሁሉ ያልፍና፤ ከታሪክ መጽሐፍ ውስጥ አንዱን ገፅ ይይዛል። ከዚህ የጨለማ ዘመን ቀጥሎ የሚመጣው፤ በነጠላው ሲታይ፤ ከነበረው ተቃራኒ ይሆናል። ይህም፤ ከጨለማው የዘመነ መሳፍንት ተከትሎ በአፄ ቴዎድሮስ አማካኝነት፤ የተባበረችና መንግሥታዊ መዋቅር ያላት አዲስ ኢትዮጵያ እንደተከተለች ሁሉ፤ ከፋሽስቱ የጣሊያን ወረራ ዘመንም ተከትሎ ኋላ ቀርም ቢሆን፤ መልክ ያለው ነፃ መንግሥት እንደተመሠረተ ሁሉ፤ ከአረመኔዎቹ የደርግና የወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ ቡድን ውድመት የሚከተለው፤ ተቃራኒ መሆኑ ነው። በዚህ ዘመን በሥልጣኑ ቁንጮ የነበሩትና ያሉት፤ እርስ በርሳችን እንድንናቆር ሲያሠልፉን፣ ራሳችንን እንድንጠላና ሌላ ገፅታ እንዲኖረን ሲያስገድዱን፣ በታሪካችን ሳይሆን ራሳቸው በፈጠሩት ታሪክ ሲያጠምቁን ኖረዋል። ከነሱ የሚከተለው፤ የተለየ ይሆናል። የመጪው ምንነት፤ በነበርነውና ባለነው የኅብረተሰቡ አባላት የአስተሳሰብ ይዘት መስመር ይገነባል። ግንዛቤያችን ግድግዳና ጣራው ይሆናል። በርግጥ ያለንበት የዓለም አቀፍ ሁኔታ ይገዛናል። አሁን ያለንበት ደንባራው የጨለማ ዘመን ተቀያሪነቱ ግን አይቀሬ ሀቅ ነው። በዚህ ዘመን ያለነው፤ ስላደረግነው፣ ስላላደረግነው፣ ማድረግ ስለነበረብን፣ ሳናደርገው ስለቀረነውና ለምን ማድረግ የነበረብንን አለማድረጋችን ብዙ መጻፍ ይቻላል። ለወደፊቱ ብዙ እንደሚጻፍ አምናለሁ። በዚህ ተከታታይ ጽሑፍ፤ እኔ አሁን ካለንበት በመነሳት፤ ምን ማድረግ እንዳለብን በመጠቆም የወደፊቱን ሂደት እቃኛለሁ። በመጀመሪያው መግቢያና አጠቃላይ የጨረፍታ ጉዞ አደርጋለሁ። በተከታዮቹ ደግሞ፤ የያንዳንዳችንን ድርሻ አመላክታለሁ።

ደርግም ሆነ በሥልጣን ላይ ያለው ወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ ቡድን፤ በኢትዮጵያዊያን፣ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ብዙ በደል ፈፅመዋል። ሀገራችን የሁለት መቶ ዓመታት ወደ ኋላ ጉዞ እንድታደርግ ሆናለች። ሰዎች ሕልምና ተስፋቸው ተነጥቋል። ማንነታቸው ተጠይቋል። ታስረዋል። ተሰደዋል። ተገድለዋል። ንብረታቸው ተዘርፏል። ወድሟል። ጠፍቷል። ኢትዮጵያዊነታቸው በመጋዝ ሊተለተል ተጋድሟል። ያሳለፍናቸው ፵ ዓመታት፤ የመናኮር፣ የመተላለቅ፣ የኢኢትዮጵያዊነት ዘመን ነበር፤ ነውም። ግፉ ግና አላለቀም፤ አልተጻፈም። ብዙ ጸሐፊዎችና ብዙ መጽሐፍቶች ያስፈልጉታል። ያም ሆኖ መሉ በሙሉ ይገልፁታል ማለት ዘበት ነው። መጠናት አለበት። ያለፍንበትን፤ እኛ እንኳን ያለፍንበት በደንብ አናውቀውም። በዚህ አንድነት ባልፈጠርንበት ያለፈ ታሪካችን፤ አንድ የሆነ የወደፊት ልናልም አንችልም። ምን መሆን አለበት? በሚለው ልንስማማ አንችልም። እናም፤ ለወደፊት መጪዎችም፤ በደንብ የተስተካከለ ያለፈ ታሪክ ልናቀረብላቸው አንችልም።

ታሪካችንን ማጥናት፤ እንደ ኢትዮጵያዊነታችን ግዴታችን ነው። አሁን ያለነውና ወደፊትም የሚመጡት፤ ትክክለኛ የሆነ አመለካከት ኖሮን፣ ግልፅ የሆነ የጋራ ተግባሮቻችንን ተገንዝበን፤ የተደረጉትን ጥሩና ጥሩ ያልሆኑ ተግባራት መርምረን፤ የተሻለ የወደፊት እንዲኖረን፤ የትናንቱን ማወቅ አለብን። ከኛ በፊት የነበሩት፤ ትዝታዎች ነበሩዋቸው። አሁን ያለነው ደግሞ እያንዳንዳችን ያጠራቀምነው የየራሳችን ትዝታዎች አሉን። ያለነዚያ ትዝታዎች ማንነታችን በኖ ይጠፋል። እናም እኒህ የያንዳንዳችን ትዝታዎች በአንድ ላይ ተጠራቅመው፤ ሲገጣጠሙና አንድ ሲሆኑ፤ የጋራችን ይሆናሉ። የአዘዞው ከሞያሌው ጋር፣ የጎዴው ከአሶሳው ጋር፣ ያዲስ አባው ከጋምቤላው ጋር መሰብሰብ አለባቸው። ያለፉት ፵ ዓመታት ኑሯችን ከዚያ በፊት ለዘመናት ከነበረው የኢትዮጵያዊያን ኑሮ ጋር መታየት አለበት። በረጅሙ ታሪካችን፤ እያንዳንዱ የኅብረተሰባችን የሂደት ክፍል፤ ካለፈውና ከነበረው የተያያዘ ነው። የምናጠናው ታሪክ የአንድ የተወሰነ ክፍል ታሪክ አይደለም። ይህ ታሪክ ከዳር እስከዳር በሀገራችን ያሉት ዜጎቿ ታሪክ ነው። የተጻፈውን ካልተጻፈው፣ የመጽሐፉን ከአፈታሪኩ፣ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ከአኗኗሩ፣ የጎጆውን ከበረቱ፣ የርሻውን ከንግዱ፣ የመንደሩን ከሀገራችን አጣምረን ማጥናት አለብን። ያለፉት ፵ ዓመታት ሁኔታችን፤ ከዚያ በፊት በነበረው ሀቅ የተፈለፈና የተመሠረተ ጉዳይ ነው። የተነጠለና የተለየ አድርገን መውሰድ የለብንም። ለተፈፀመው ግፍ ተጠያቂ ነው ለማለት ሳይሆን፤ ለተከተለው እውነታ፤ የነበረው ሀቅ አዘጋጅቶታል። በወቅቱ ደግሞ የነበሩት፤ የተለያየ አማራጭ እያላቸው፤ ያንን የወሰዱትን መንገድ መምረጣቸው፤ ተጠያቂዎቹ፤ የወቅቱ ባለጉዳዮች ናቸው። ለዚህም ነው ደርግና ወገንተኛው አምባገነኑ ሕገወጥ መንግሥት ተጠያቂነታቸው።

እዚህ ላይ፤ ከጥንት ጀምሮ በዚህ ሁሉ የሕልውና ሰውነት፤ አጥንት ሆኖ ካንዱ ዘመን ወዳሌላው ዘመን የተላለፈ ኢትዮጵያዊነት አለን። ያ ደግሞ ከጥሩውም ከመጥፎውም ዘንቆ የያዘ ነው። ያ ነው ያሳለፍነው፤ ጥሩ ጎኑ እንዲበረታና አስቀያሚ ጎኑ እንዳይደገም የምንፈልገው። ያን ማጥናታችን፤ እጃችን ጠምዝዞ ለወደፊቱ የምናደርገውን ያስገድደናል ወይንም የሚሆነውን ይነግረናል ሳይሆን፤ እኛን የበሰልን፣ የጠነከርን፣ ያወቅን አርቆ አስተዋዮች ያደርገንና፤ ለምንወስደው ዕርምጃ መንገድ ይከፍትልናል ነው። የወደፊቶቻችን ወደኋላችን ዞረው፤ ያሳለፍነውን ታሪካችንን ያጠኑታል። እየተለዋወጠ የመጣውን ሂደታችንን በደንብ መርምረው፣ ለተግባራችን ትርጉም ፈልገው፣ መልካሙን ከመጥፎው ለይተው ትምህርት ይወስዱበታል። የወደፊታቸውን ጉዞ ለማስተካከል የበሰሉ፣ የጠነከሩ፣ ያወቁ አርቆ አስተዋዮች ያደርጋቸዋል።

ከዚህ ታሪካችን መማር ካልቻልን፤ ጨለማው ዘመን እንዲቀጥል እናደርገዋለን። ባንድ በኩል የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ትምህርቱን ስለወሰዱ፤ የድርጅት መሪዎች ብቻ ስላወቁ፤ ጥሩ አስተዳደር አይኖረንም። የዴሞክራሲያዊ አሠራር፤ በተወሰኑ ሰዎች ፍላጎትና ፈቃድ የሚተገበር አይደለም። የኅብረተሰቡ የአስተሳሰብ ደረጃ፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉት ሕዝባዊ መዋቅሮች፣ መሪዎቹ ለሕግ ያላቸው ከበሬታና ሕግን ለማስከበር ሽንጣቸውን ገትረው፤ የራሳቸውን ፍላጎትና ምኞት ለሕዝቡ ሕልውናና ደህንነት አሳልፈው የሠጡ ታታሪ የኅብረተሰቡ አባላት ሲኖሩ ነው። የዴሞክራሲን መበልፀግ ሊያረጋግጡልን የሚችሉት፤ ሕግ፣ ለሕግ ያለን ከበሬታና ሕጉን ለማስከበር ከመንግሥታዊ መዋቅሩ ሌላ፤ በሕዝቡ ውስጥ ያለው ዝግጅት ነው። ይኼን ደግሞ ለማራመድ የሚችሉ በሕዝቡ ውስጥ ያሉ ሕዝባዊ ድርጅቶች ወሳኝ ቦታ አላቸው።

ከሕገወጡ አምባገነን ወገንተኛ ቡድን አንፃር ደግሞ፤ ይህን ለመቋቋም የተሠለፉት፤ በቂና አጥጋቢ ውጤት አላሳዩም። ይህ ከጥረት ጉድለት ሳይሆን፤ ታሪክን በድንብ ተረድቶ ኢትዮጵያዊ የሆነ የጠራ ራዕይ ካለመያዝ የተነሳ ነው። እናም መቀጠል የለበትም። ባጭር ጊዜ እንኳን ብዙ ጥሩ አጋጣሚዎች በከንቱ ታልፈዋል። ወገንተኛው አምባገነን ሕገወጥ ቡድን በተደጋጋሚ ብዙ አጋጣሚዎችን በየጊዜው እየፈጠረ ለታጋዩ ክፍል ስጦታ አቅርቦልን ነበር። በሚያስገርምና በሚያሳፍር ሁኔታ እያንዳንዳቸውን አሳልፈናቸዋል። በመካከላችን መፈጠር የነበረበት ትብብር በኖ ጠፍቷል። ትንሿ ጉዳይ በአስገራሚ መንገድ መከፋፈያ በመሆን መራራቅን በመካከላችን እንድትደነቅር ተደርጓል። ከሀገር ይልቅ መታገያ መሳሪያ የሆኑት ድርጅቶች መመለኪያ ጣዖቶች ሆነዋል። መገንዘብ ያለብን፤ አሁን በአባላቱ ዘንድ ዴሞክራሲያዊ አሠራርን ተቀብሎ ያላረጋገጠ ድርጅት፤ በሥልጣን ላይ ሲወጣ ዴሞክራሲያዊ አሠራርን ሊከተል አይፈልግም፤ አይችልምም።

ድርጅቶችና በድርጅት ውስጥ ያሉ አባላት ብቻ የሀገር ተቆርቋሪዎችና የትግሉ ባለቤቶች እንደሆኑ ተደርጎ፤ በድርጅቶቹ ሆነ በውጭ ባለነው ባልተደራጀነው ግለሰቦች ተወሰዷል። ይህ በትግሉ የመሳተፍን ጉዳይ፤ ለድርጅቶች የመተው ዝንባሌን አጎለበተው። ከትግሉ ለመራቅ ያሰቡት፤ ስበብ በመፈለግና በመፍጠር፤ የድርጅቶቹ ጉዳይ አድርገው እራሳቸውን አስመለጡ። በድርጅቱ ያሉት፤ የትግሉ የግል ባለቤት እኛ ብቻ ነን በማለት፤ ትግሉን የራሳቸው የግል ንብረት አድርገው ወሰዱ። እናም በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ያለው ክፍፍል አልበቃ ብሎ፤ በውጭ ያለነው ደግሞ፣ በድርጅቶች ውስጥ ያሉትና ከድርጅቶቹ ውጪ ያሉት በመባባል ተከፋፈልን። ቀጥሎ በያንዳንዱ ድርጅት ደግሞ አንዱ ካንዱ እኔ እበልጣለሁ፣ የኔ ታሪክ ይበልጣል፣ እኔ የበለጠ ተቀባይነት አለኝ፣ እኔ ብዙ ታጋዮች አሉኝና የመሳሰሉትን በመቁጠር ተራራቁ። ቀጥሎ ደግሞ፤ በሰላም ነው የምንታገለው፤ የለም በትጥቅ ትግል ነው መንግሥቱን የምንገለብጠው በመባባል የበለጠ ተራራቁ። እንዲህ ያለው መበጣጠስ፤ የታጋዩን ወገን በማዳከም የሕገወጡን ቡድን የሥልጣን እድሜ አራዘመው። በድርጅት ውስጥ ላሉት፤ በድርጅቶች እምነትና ፍላጎት ብቻ ሆኗል ትግሉ የሚታሰበው። ካለድርጅቶች ሀገር እንደሌለ ተደርጓል። በጣም ያሳዝናል።

በዚህ ወቅት ብዙ ኢትዮጵያዊያን ሕይወታቸውን አጥተዋል። ለጋ ሕፃናት ወላጆቻቸውን አጥተዋል፤ ወይንም ራሳቸው ተገድለዋል። አባቶችና እናቶች ልጆቻቸው ቀድመዋቸዋል። ያ ግን እኛን አላቆመንም። እኛን የሱ ተገዥ አላደረገንም። እኛን አልገታንም። የወደፊቱን ብርሃን ከማየት አለገደንም። ለዚህም ነው የትግሉን ሠፈር አጥብቀን የያዝነው። በኛ እምነት የተሻለ፣ የበለጠና ግሩም የወደፊት ይጠብቀናል። ያን ለማምጣት ብስለታችንና ፈቃደኝነታችንን መፈተሽ አለብን። ካወቅንበት፤ ይኼ ያለንበት ሀቅ በቶሎ ያልፋል። ልናፋጥነው ወይንም ልናዘገየው የምንችለው እኛው ነን። ኃላፊነቱም እኛው ላይ ነው። ጥሩነቱ እንችላለን። ማፋጠን እንችላለን። የተቀመረ፣ የተፈተነና የቀረበ የመፍትሔ መንገድ የለንም። ሊኖረንም አይችልም። ሆኖም ግን በጃችን ያለውን በማመዛዘን በቀና መንገድ ከተነሳን፤ መፍትሔው ከፊታችን ግልፅ ሆኖ ይቀርብልናል። ሀገር ወዳዶች ተቆጠሩ! ይኼም ያልፋል – ካወቅንበት! በተከታታይ ጽሑፎች፤ የቀድሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የቀድሞ የጦር ሠራዊት አባሎች፣ መምህሮች፣ ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የክርስትና እምነት ተከታዮች፣ የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ የሴቶች ማኅበር አባሎች፣ በማኅበራቸውና አሁን ባሉበት እውነታ፤ በወቅቱ ያልፈፀምነውን ትግል፤ አሁን ምን ማድረግ እንዳለብን መልስ እሠጣለሁ።

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in አስተያየቶች - Commentaries. Bookmark the permalink.

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s