የዊሊ ሊንች ደብዳቤ፤ ባሪያን መግራት

የዊሊ ሊንች ደብዳቤ፤ ባሪያን መግራት

ይህ በዊሊ ሊንች፤ በቨርጂኒያ ቅኝ ግዛት በሚገኘው የጀምስ ወንዝ፤ በ1712 ( እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ) የተደረገ ንግግር ነው። ዊሊ ሊንች በዌስት ኢንዲስ የባሪያዎች ጌታ ነበር። ወደ ቨርጂኒያ ቅኝ ግዛት፤ በዚሁ በ1712( እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ) ፤ ለባሪያ ባለቤቶች፤ እሱ ያሰላዉን መንገድ ሊያስተምራቸው ተጋብዞ ነበር የመጣው። በእንግሊዝኛ ቋንቋ “ሊንችንግ” የሚለው ቃል የተቀመረው፤ ከዚሁ ሰው የቤተሰብ ስም ነው። ሊንችንግ ማለት፤ ያለፍርድ መግደል ማነቅና ማንጠልጠል ማለት ነው። ንግግሩ ከዚህ ይቀጥላል።

ጥር 25 ቀን 1712

ክቡራን መኳንንት፤

ጌታችን በተወለደ በአንድ ሺ ሰባት መቶ አሥራ ሁለት ዓመቱ፤ በጀምስ ወንዝ ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ። በመጀመሪያ፤ የቨርጂኒያ ቅኝ ግዛት መኳንንቶችን፤ እዚህ ጋብዛችሁ ስላመጣችሁኝ ላመሰግናችሁ ይገባኛል። እዚህ ያለሁት በባሮቻችሁ በኩል ያለባችሁን አንዳንድ ችግር በማቃለሉ በኩል ልረዳችሁ ነው። ዌስት ኢንዲስ ውስጥ፤ አንዳንድ የተለያዩ አዳዲስ ሆነው ግን አሁንም የጥንት የሚባሉ ባሮችን የመግራያ መንገዶችን በሞከርኩበት፤ ራሴን ሳላሞካሽ መካከለኛ በምለው የአዝመራ ተክሌ ላይ፤ ግብዣችሁ ደረሰኝ። ይህ የባሪያ መግሪያ መንገዴ በተገባር ከተተረጎመና በሥራ ላይ ከዋለ፤ የቀድሞ ባሪያ ገዢ ሮማዊያን ይቀኑብናል።

የምንጓዝበት መርከብ፤ የዘመኑን የመጽሐፍ ቅዱስ ዝግጅት በምናወድስለት፤ በተደናቂውና አኩሪ ንጉሣችን ስም በተሰየመው በጀምስ ወንዝ ደቡብ ሲያቀና፤ ችግራችሁ የናንተ የብቻችሁና የተለዬ አለመሆኑን በቂ ማስረጃ ዓየሁ። የሮማ ግዛት፤ ምልምል እንጨቶችን በማመሣቀል አዋግሮ፤ በየአዉራ ጎዳናዎቹ በብዛት ሰዎችን ማንጠልጠያ አድርጎ ሲጠቀም፤ እዚህ እናንተ ዛፎችንና አንዳንዴ ደግሞ ገመዶችን እየተጠቀማችሁ ነው። አንድ ሁለት ማይሎች ከዚህ ራቅ ብሎ፤ አንድ ዛፍ ላይ የተንጠለጠለ ባሪያ፤ የሬሣው ግማት በጨረፍታ ወላፈኑ አዉዶኛል። በማንጠልጠል፤ ንጥር ንብረታችሁን ማጣት ብቻ አይደለም፤ አመፅ እየተነሣባችሁ ነው፤ ባሮች እየኮበለሉባችሁ ነው፤ አንዳንዴ ሰብላችሁ ለረጅም ጊዜ ሳይሰበሰብ፤ በማሳው እንዳለ ወቅቱ እያለፈበት፤ አፍላ የትርፍ ስልባቦቱን ሳይሻማና ሳያገኝ ለረጅም ጊዜ ይቆያል። አልፎ፣ አልፎ የሣት ቃጠሎ ያጋጥማችኋል፤ ከብቶቻችሁም ይገደሉባችኋል።

ክቡራን መኳንንት ሆይ!  ችግሮቻችሁን ታውቋቸዋላችሁ፤ እኔ ማብራራት አያስፈልገኝም። እኔ እዚህ ያለሁት ችግሮቻችሁን ልዘረዝር አይደለም፤ እኔ እዚህ ያለሁት ለችግሮቻችሁ ማቃለያ ዘዴ ላስተዋዉቃችሁ ነው። እዚህ ከጎኔ ባለኝ ኮሮጆ ዉስጥ፤ ጥቁር ባሮቻችሁን መግሪያ ፍቱን ዘዴ ይዣለሁ። በትክክለኛ መንገድ በሥራ ላይ ከዋለ፤ ባሪያዎችን ቢያንስ ለሚቀጥለው  ሶስት መቶ ዓመት (እስከ 2012 እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ) እንደሚያስገብርላችሁ ለያንዳንዳችሁ ቃል እገባላችኋለሁ። የኔ ዘዴ ቀላል ነው። ማንኛዉም የቤተሰባችሁ አባል ወይንም የምትቀጥሩት ሹም ሊጠቀምበት ይችላል። በባሪያዎች መካከል ብዙ ልዩነቶችን ዘርዝሬ አውጥቻለሁ፤ ልዩነቶችንም አግዝፌያቸዋለሁ። ፍርሃትን፣ አለመተማመንንና ቅናትን ለመቆጣጠሪያ ተጠቅሜያለሁ።

እነዚህ ዘዴዎች፤ በዌስት ኢንዲስ፤ ራሴን ሳላሞካሽ ባለኝ መካከለኛ የአዝመራ ተክሌ፤ ሠርተዋል፤ እዚህ በናንተም በደቡቡ ክልል፤ ከላይ እስከታች በሙሉ ይሠራሉ። የሚከተለዉን ቀላል የልዩነቶች ዝርዝር ውሰዱና አስቡበት። ከዝርዝሬ ቁንጮ የተቀመጠው “ዕድሜ” ነው፤ ከዚያ ላይ እንዲቀመጥ የተደረገው ግን፤ የእንግሊዝኛ ቋንቋችን የመጀመሪያው ፊደል በሆነው በ”ዐ” ስለጀመረ ብቻ ነው። ሁለተኛው “የቆዳ ቀለም” ወይንም የቀለሙ ድምቀት ደረጃ ሲሆን፣ አዋቂነት አለ፣ የሰዉነት ግዝፈት፣ ፆታ፣ የአዝመራው ስፋትና በዚሁ አዝመራ ባሪያው ያለው ደረጃ፣ የባለቤቱ ጠባይ፣ ባሪያዎቹ የሚኖሩት በሸለቆ ዉስጥ ነው ወይንስ በተራራማ ቦታ፣ በምሥራቅ የሀገሪቱ ክልል፣ በምዕራብ፣ በሰሜን፣ በደቡብ፣ ባሪያውስ ፀጉሩ ለስላሳ ነው፣ ከርዳዳ ነው፣ ወይንም ረጂም ወይስ አጭር የሚሉት አሉ። እንግዲህ የልዩነቶችን ዝርዝር ይዛችኋል፤ ጠቅለል ያለ የተግባር ንድፍ እሰጣችኋለሁ። ከዚያ በፊት ግን፤ አለመተማመን ከመተማመን፣ ቅናት ከማኮማሸት፣ ከማክበር ወይም ከማድነቅ የጠበቀና ጥልቀት ያለው መሆኑን አረጋግጥላችኋለሁ። ጥቁሩ ባሪያ፤ ይህን የኔን የባሪያ መግሪያ ከቀመሰ በኋላ፤ መገዛቱን እርስ በርሱ እየተማማረና ለልጅ ልጁ እያወረሰ፤ ለመቶዎችና ምንአልባትም ለሺዎች ዓመታት ተገዢያችሁ ይሆናል። አዛዉንቱን ጥቁር ወንድ፤ ከወጣቱ ጥቁር ወንድ፤ ወጣቱን ጥቁር ወንድ፤ ከአዛዉንቱ ጥቁር ወንድ፤ ማናከሱን እንዳትዘነጉ። የቆዳ ቀለማቸው በጣም የጠቆሩትን ባሮች ፈካ ያለ የቆዳ ቀለም ካላቸው ባሮች፤ ፈካ ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸውን ባሮች በጣም ጠቆር ያለ ካላቸው ባሮች፤ ቀለማቸውን መለያ በማድረግ፤ ማጋጨቱን መጠቀም አለባችሁ። ሴቶችን በወንዶች ላይ መጠቀም አለባችሁ። ወንዶችንም በሴቶች ላይ። ነጭ አገልጋዮቻችሁና ቅጥረኛ ሹሞቻችሁ ጥቁሮችን እንዳያምኗቸው ማድረግ አለባችሁ። ባሮቻችሁ እኛን እንዲያምኑና በኛ ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ማድረጉ ግዴታ ነው። እኛን ብቻ መውደድ፣ ማክበርና ማመን አለባቸው። ክቡራን መኳንንት፤ እኒህ ክትት ያሉ መቆጣጠሪያ ቁልፎቻችሁ ናቸው። ተጠቀሙባቸው። ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ እንዲጠቀሙባቸው አድርጉ፤ የተገኘ ዕድል አያምልጣችሁ። ለአንድ ዓመት በማረባረብና በጥብቅ ከተግባር ላይ እንዲዉል ከተደረገ፤ ባሪያዎቹ እርስ በርሳቸው ለእስከመቼዉም የማይተማመኑ ይሆናሉ።

አመሰግናለሁ ክቡራን መኳንንት

ባሪያ እንግራ

ተጨባጭ ውጤትን በማገናዘብ፤ የሰዉን ተፈጥሯዊ ባህሪ፤ በተለይም የባሪያን ተፈጥሮ ማጥናት፤ ለባሪያ ጌቶች ጉዳያቸዉና ጥቅማቸው ነው። እኔና ብዙዎቹ መሰሎቼ፤ በዚህ ረገድ አስገራሚ የሆነ ቅልጥፍና አግኝተናል። እኒህ መሰሎቼ፤ መሬት፣ እንጨት ወይም ደንጋይ ሳይሆን፤ ሰዎችን ነው ያስተዳደሩት። በማንኛውም መንገድ ለራሳቸው ደህንነትና ለብልፅግናቸው ሲሉ ደግሞ፤ የሚያስተዳድሩትን ክፍል ጠንቅቀው ማወቅ ነበረባቸው። በየሰዓቱ የሚያደርጉት ፍርደ ገምድልነትና ስህተት በአእምሯቸው ውስጥ ስላለ፤ የዚህ ግፍ ተጠቂዎች እነሱ ቢሆኑና ራሳቸው በዚያ ቦታ ቢቀመጡ ምን እንደሚያደርጉ ስለሚያውቁ፤ ሁሌም የሚፈሩት፤ የበቀል ፍንጩ ብቅ የሚልበትን መምጫ ሁልጊዜ በንቃት ይጠብቁ ነበር። እናም በሰለጠነና በሰላ ዓይን አተኩሮ፤ የበለጠ ባነጣጠረ ትክክለኝነትም የባሪያዉን የልብና የመንፈስ ርጋታ ከፊቱ ገፅታ ማንበብ ተማሩ። ያልተለመደ መረጋጋት፣ ግልፅ መቅበዝበዝ፣ ልግምትና ቸልተኝነት፤ እንዲያውም ማንኛውም የተለዬ አድራጎት፤ መጠራጠርን አስከትሎ፤ ክትትል እንዲደረግበት መንገድ ጠርጓል።

እስኪ እንግዲህ ባሪያ እንግራ። ምን ያስፈልገናል? ከሁሉ መጀመሪያ አንድ ጥቁር ጥቀርሻ ወንድ፣ አንዲት ያረገዘች ጥቀርሻ  ሴትና አንድ ወንድ ሕፃን ጥቀርሻ ልጇን እንፈልጋለን። ሁለተኛ ፈረስን ለመግራት የምንጠቀምበትን መሠረታዊ መመሪያዎች፤ ቀጣይነትን ከሚያስገኙ አግባቦች ጋር በማዋሃድ እንጠቀማለን። ፈረስን በምንገራበት ጊዜ የምናደርገው፤ ተፈጥሮ ካደላቸው የሕይወት ባህሬያቸው አውጥተን፤ አሳንሰን፤ ወደ ሌላ ባህሪ አስገድደን እንቀይራቸዋለን። ተፈጥሮ ቀጣይ ትውልዳቸውን የመንከባከብና የማሳደግ ችሎታ ከሕልውናቸው ጋር ስታድላቸው፤ እኛ ያን የተፈጥሮ ተከታታይ ነፃነት ከነሱ ገፈን፤ የጥገኝነት ስሜት ዕርከን በመፍጠር፤ ለመዝናኛችንና ለንግዳችን አምቺ የሆነ አመርቂ ምርት ከነሱ ልናገኝ እንችላለን።

ጥቀርሻ ፊትን መግሪያ ወሳኝ ሕጎች

የወደፊቱ መጪ ትውልዳችን የእኒህን ጥንድ አውሬዎች ባንድነት፤ ፈረስና ባሪያን፤ የመግራት ሥርዓት አይረዱትም የሚል ፍራቻ አለን። ያጭር ጊዜ የምጣኔ ሀብት ስምሪት ዕቀዳ፤ ጊዜ ጠብቆ የሚደጋገም የገበያ ትርምስ እንደሚያስከትል እንረዳለን። የገበያው ትርምስ እንዳይከሠት ለማድረግ፤ ሰፊና ጥልቅ የረጂም ዘመን አጠቃላይ ዕቅድ እንዲኖረን ያስገድደናል፤ ሁለቱንም ሰፊና ጥልቅ ያልናቸዉን የነጠረ ግንዛቤ እንዲያካትቱ መሠመር አለበት። ለረጂም ዘመን አጠቃላይ የምጣኔ ሀብት ስምሪት ዕቅድ፤ ከዚህ የሚከተሉትን ሕጎች እናስቀምጣለን። ሁለቱም፤ ፈረስና ባሪያዎች ተፈጥሮ ባደለቻቸው የሕልውና ደረጃና ዘላን እያሉ ለምጣኔ ሀብታችን ስምሪት ዋጋ የላቸውም። መልክ ላለው ምርት፤ ሁለቱም መገራትና በአንድነት ተጠምደው መታሠር አለባቸው። የወደፊቱ የሰላ እንዲሆን፤ ለሴቷና ለመጨረሻ ወጣት ዝርያዎች፤ የተለዬና የነጠረ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ሁለቱም ልዩ ልዩና ለሥራ ክፍፍል አመቺ የሆነ ቡቃያ እንዲያስገኙልን መዳቀል አለባቸው። ሁለቱም ልዩ ለሆነ አዲስ ቋንቋ፤ ቀናና ተገዢ እንዲሆኑ፤ ልናስጠናቸው ይገባል። ለሁለቱም፤ ጠፍርቆ መያዣ የመንፈስና የአካል መመሪያ፤ መፈጠር አለበት። እውነቱ በግልፅ እንደሚታይ ሁሉ፤ ፈረስንና ባሪያን የመግራትንና ባንድነት አስሮ የመጥመድን ምጣኔ ሀብት ሥምሪት ዉይይት በተከተለ መስመር፤ ስድስቱን ወሳኝ ሕጎች አጥብቀን እንይዛቸዋለን። ይህም ከዚህ ቀጥለው በሚቀርቡት ስድስቱ ሕጎች የተጠቃለለ ነው። ማሳሰቢያ፤ አንዱ መመሪያ ብቻ ለመልካም ምጣኔ ሀብት ሥምሪት በቂ አይደለም። ለሀገሪቱ መልካም ስነ ሥርዓት ሲባል ሁሉም መመሪያዎች በተግባር መዋል አለባቸው። እናም ሁለቱም፤ ዘላን ፈረስና ዘላን ወይም በተፈጥሮ ነፃነቱ ያለ ጥቀርሻ ፊት፤ ተይዘው እንኳ አደገኛ ናቸው፤ የተለመደ ነፃነታቸውን ለማግኘት ዝንባሌ ስላላቸው፤ ይህን ሲያደርጉ፤ ተኝታችሁ ሳለ ሊገድሏችሁ ይችላሉ። ልታርፉ አትችሉም። እናንተ ነቅታችሁ ሳለ፤ እነሱ ይተኛሉ፤ እናንተ ተኝታችሁ ሳለ ደግሞ፤ እነሱ ንቁ ናቸው። በመኖሪያ ቤታችሁ አጠገብ አደገኞች ናቸው፤ ከቤታችሁ ራቅ ሲሉ ደግሞ፤ እነሱን መቆጣጠር ብዙ ጉልበት ይጠይቃል።  ከሁሉ በላይ ደግሞ፤ በተፈጥሮ ደረጃቸው እያሉ ልታሠሯቸው አትችሉም። ከዚህ የምንረዳው፤ ፈረሱና ጥቀርሻ ፊቱ መገራት አለባቸው፤ ይኼም ማለት ካንድ የመንፈስ ደረጃ ወደ ሌላ መግራት ነው። ሰዉነታቸው አእምሯቸውን እንዲቆጣጠረው አድርጉት፤ በሌላ አነጋገር፤ አንገት ደፍተው ተገዢ እንዲሆኑ የተከላካይነት ቀንዳቸውን ስበሩት። እንግዲህ ለፈረስና ለጥቀርሻ ፊቱ አገራሩ፤ ትንሽ ብቻ በጥንካሬው ክብደት መጠን ይለያያሉ እንጅ፤ አንድ ነው። ድሮም እንዳልነው ግን፤ የረጂም ዘመን የምጣኔ ሀብት ሥምሪትን ለማቀድ ጥበብ ይጠይቃል። ዓይኖቻችሁና ሃሳቦቻችሁ በፈረሱና በጥቀርሻ ፊቱ ሴትና ተከታይ ትውልድ ላይ ማተኮር አለባቸው። ጥቂት የተከታይ ትውልድ አስተዳደግ ትንተና እሰጥ አገባ ማድረጉ፤ ለአስሊ የምጣኔ ሀብት ሥምሪት ጥሩ በር ከፋች ይሆነናል። የመጀመሪያው መግራት ለተደረገበት ትውልድ ሃሳብ አይግባችሁ፤ ይልቁንስ በሚቀጥሉት ትውልዶች ላይ አተኩሩ።

ስለዚህ፤ ሴቷን እናት ከገራችኋት፤ እሷ ልጇን ገና በወጣትነት የዕድሜ ዕድገት ትገራለችና፤ ቡቃያዋ ለሥራ ሲበቃ፤ ራሷ አንጠልጥላ ታመጣላችኋለች፤ ምክንያቱም፤ የተለመደው የሴትነት ተንከባካቢ ዝንብዝሌዋ፤ መጀመሪያ እርሷ በምትገራበት ሂደት ከአእምሮዋ ተፍቋልና። ለምሳሌ ያልተገራ አለሌ ፈረስ፣ አንዲት እንስት ፈረስና ለጋ ግልገል ፈረስ ጉዳይ ውሰዱና የመግራት ሂደቱን፤ ከሁለት በተፈጥሮ ሕውናቸው ያሉ የተማረኩ ጥቀርሻ ፊት ወንዶች፣ ከእንቡጥ ልጇ ጋር ያለች ዕርጉዝ ጥቀርሻ ፊት ሴት ጋር አወዳድሩት። አለሌ ፈረሱን ውሰዱ፤ በጠባብ አጣብቂኝ ቦታ ግሩት። ሴቷን ፈረስ እስከመጨረሻው ግጥም አድርጋችሁ ሸር እስክትልና እናንተ ወይንም ሌላ ሰው ሲጋልባት ሰጥ ለጥ ብላ እንድትሽከረከር ግሯት። ሴቷን ፈረስና አለሌውን ፈረስ የምትፈልጉትን የፈረስ ዝርያ እስክታገኙ ድረስ አሳርሯቸው። ከዚያ በኋላ አለሌውን ልትለቁት ትችላላችሁ፤ ዳግመኛ እስክትፈልጉት ድረስ። ሴቷን ፈረስ ከእጃችሁ እንድትበላ አስልጥኗት፤ ኣሷም በተራዋ ግልገሉን ፈረስ ደግሞ ከጃችሁ እንዲበላ ታሠለጥነዋለች።  ያልሠለጠነዉን ጥቀርሻ ፊት በመግራት ረገድ፤ ይኼንኑ ሂደት ተጠቀሙ፤ የአእምሮዉን ጠቅላላ ቅየራ ለማጠናቀቅ፤ የመግሪያ ክብደቱን ደረጃ ቀያይሩት፤ የጥንካሬውን መጠንም ከፍ አድርጉት። ወጠምሻ፣ መናጢና ተቅበዝባዡን ጥቀርሻ ፊት ምረጡ። በቀሪዎቹ ሌሎች ወንድ ጥቀርሻ ፊቶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ጥቀርሻ ፊቶች ፊት ልብሱን ግፈፉት፤ ካርታሜ በሰዉነቱ ላይ ለቅልቃችሁና ላባ በሰውነቱ ሰካክታችሁ፤ ፊትና ጀርባ ከቆሙ ሁለት ፈረሶች ላይ፤ አንድ እግሩን ካንዱ ፈረስ፤ ሌላ እግሩን ከሁለተኛው ፈረስ አስራችሁ፤ በሌሎች ጥቀርሻ ፊቶች ፊት እሳት ለኩሱበትና፤ ፈረሶቹ ሰዉነቱን እየጎተቱና እንዲበጣጥሱት መጪ በሏቸው። የሚቀጥለው እርምጃ የበሬ አለንጋ ይዞ ቀሪዎቹን ወንድ ጥቀርሻ ፊቶች ነፍስ ዉጪ ነፍስ ግቢ እስኪሁን ድረስ በሴቶቹና በሕፃናቱ ፊት መግረፍ ነው። እንዳትገድሏቸው፤ ፈጣሪዉን እንዲፈራ አድርጉት፤ ለወደፊቱ ማዳቀያ ይጠቅማልና።

የአፍሪቃዊዋን ሴት የመግራት ሂደት

ሴቷን ውሰዱና፤ ለፍላጎታችሁ በፈቃደኝነት ታጎበድድ እንደሆነ ለማየት፤ የተለያዬ (በማስገደድ የመድፈር) ሙከራዎች አድርጉባት። በሁሉም መንገድ ፈትኗት፤ ለመልካም ምጣኔ ሀብት ሥምሪት ዋነኛዋ አካል እሷ ናትና። ሙሉ ለሙሉ ለፈቃዳችሁ ላለማጎበድድ የመከላከል ፍንጭ ካሳየች፤ የበሬውን ጅራፍ አውጥታችሁ ትንሽም ብትቀር የመጨረሻዋ የተቃዉሞ ቅሬት ከአእምሮዋ ተሟጦ እንዲወጣ፤ ልትለቀቁባት እንዳታወላዉሉ። እንዳትገድሏት ተጠንቀቁ፤ ያን በማድረግ፤ መልካም የምጣኔ ሀብት ሥምሪትን ገደል ትከታላችሁ። ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥራችሁ ሥር በምትሆንበት ጊዜ፤ ግልገሎቿን ገና በሕፃንነታቸው፣ አድገው ለአቅም ሲደርሱ፤ ጥሩ አገልጋይ እንዲሆኑ ታሠለጥናቸዋለች። ዋናው ነገር ይህን መገንዘብ ነው። ስለዚህ፤ ሴቷን ጥቀርሻ ፊት በመግራት ሂደት ምን ዉጤት እንዳስገኘን በሚመለከት ጉዳይ ርዕስ ላይ፤ ጠለቅ ብለን እንገባለን። በተፈጥሮ ያልሠለጠነ ባህሪዋ የነበራትን ባልሠለጠነው ጥቀርሻ ፊት ወንድ ላይ ጠንካራ መተማመን ገልብጠን ቀይረንባታል፤ ወጣት ወንድ ነፃ ልጇን የተወሰነ የመንከባከብ ስሜት ይኖራታል፤ እናም ወጣት ልጇ እንደሷው ጥገኛ እንዲሆን አድርጋ ታሳድገዋለች። ተፈጥሮ ለዚህ ዓይነት ሚዛን መጠበቂያ አበጅታ ነበር። ይኼን የተፈጥሮ ሚዛን፤ እሷ ባለችበት፤ አንድ የሠለጠነ ጥቀርሻ ፊት በማቃጠልና ሰዉነቱን በመበጣጠስ፤ ሌሎችን በበሬ ጅራፍ ልባቸው እስኪጠፋና ከሞት አፋፍ እስኪደርሱ በመግረፍ፤ ቀየርነው። መከታ ነው የምትለው የወንድ ምስሏ ተደምስሶ፤ ያለተንከባካቢ ብቻዋን ተጋልጣ በመቅረቷ፤ ሲቃ ሰቆቃው ከስነ ልቡና ጥገኝነት የመንፈስ ደረጃ አውጥቶ፤ በደነዘዘ ራሷን ተንከባካቢ ነሆለል የመንፈስ ደረጃ እንድትዘፈቅ ገፋት። በዚህ የደነዘዘ ራሷን ተከባካቢ ነሆለል የመንፈስ ደረጃ፤ ወንድና ሴት ልጆቿን በተገላበጠ ሚና ታሳድጋቸዋለች።

ለወጣት ወንዶቿ ሕይወት በመፍራት፤ በስነ ልቦና ረገድ፤ አእምሮው ደካማና ጥገኛ፤ ሰዉነቱ ግን ጠንካራ እንዲሆን አድርጋ ታሣድገዋለች። በስነ ልቡናዋ ራሷን የቻለች ስለሆነች፤ ሴት ልጇንም በስነ ልቦናዋ ራሷን የቻለች እንድትሆን አድርጋ ታሳድጋታለች።  አሁን በጃችሁ ምን አለ? በግንባር ቀደም ጥቀርሻ ሴቶች ሲቀርቡላችሁ፤ ወንዱ ጥቀርሻ ፊት በፍርሃት ተሸማቆ ከኋላ አለላችሁ። ይህ ጉድፍ የማይወጣለት የሰላም እንቅልፍና የምጣኔ ሀብት ሥምሪት ነው። ከመግራቱ ሂደት በፊት፤ ቀን ከሌት በንቃት ራሳችንን ለመጠበቅ ጥንቁቅ መሆን አለብን።

አሁን ተረጋግተን መተኛት እንችላለን። ከደነዘዘ ፍርሃቷ የተነሳ የጥቀርሻ ፊቱ ባሪያ ሴት ለኛ ዘብ ትቆማለች። እሱ ከሷ የመጀመሪያው የባሪያ መግራት ሂደቷ አልፎ፤ የትም ትርው አይልም። እሱ አሁን በለጋ ዕድሜው ከፈረስ ጋር ሊታሠር የተዘጋጀ ጥሩ መገልገያ መሣሪያ ነው። አንድ ጥቀርሻ ፊት ልጅ አሥራ ስድስት ዓመት ሲሞላው፤ ፍፁም ተገርቶ፣ ለረጅም የተረጋጋና ቅልጡፍ አገልጋይነት ኑሮና ለቀጣይ አገልጋዮች አምራችነት ዝግጁ ነው። ያልሠለጠነው አዉሬ ጥቀርሻ ፊት በሚገራበት ጊዜ፤ በማከታተል ሴቷን ጥቀርሻ አውሬ ወደ የደነዘዘ የስነ ልቦና፤ ራሷን የመቻል ነሆለል የመንፈስ ደረጃ ውስጥ በመክተት፣ መከታ የሆነዉን የወንድ ትከሻ ምስል በመግደል፣ እና የወንዱን ጥቀርሻ ፊት ባሪያ አጎብዳጅና ተገዢ ጥገኛ አእምሮ በመፍጠር፤ አንድ ክስተት ብቅ ብሎ የወዱንና የሴቷን ቦታ ካልቀየረ በስተቀር፤ በራሱ አሹሪት ዘለዓለሙን እምቧለሌ የሚሽከረከር ክብ ፈጥረናል። ምን እያልን እንደሆን በማስረጃ እናሳያለን። ሁለት የሸቀጥ ባሪያ ቡድኖችን ውሰዱና ጠጋ ብላችሁ አጥኗቸው።

የጥቀርሻ ፊቶች ጋብቻ

ሁለት ጥቀርሻ ፊት ወንዶች ሁለት ጥቀርሻ ፊት ሴቶችን እንዲያስረግዙ አደረግን። ቀጥለን ሁለቱን ጥቀርሻ ፊት ወንዶች ከጥቀርሻ ፊት ሴቶቹ ነጥለን ወሰድንና በሥራና በማንከራተት ጠመድናቸው። አንዷ ጥቀርሻ ፊት ሴት አንድ ጥቀርሻ ፊት ሴት፤ ሌላዋ ደግሞ አንድ ጥቀርሻ ፊት ወንድ ሰጡን እንበል። ሁለቱም ጥቀርሻ ፊት ሴቶች፤ በአባትነት የሚያሳድግ የጥቀርሻ ፊት ወንድ በሌለበት ቦታ፤ በደነዘዘ የሰው የለሽ ስነ ልቦና፤ ልጆቻቸውን ከተለምዶ ባህሪያቸው በተገላቢጦሽ ያሣድጓቸዋል። የሴት ልጅ የያዘችው፤ ልጇን እንደሷው፤ መጠጊያ የሌሽና እንደፈለጓት ተሰባሪ እንድትሆን ታስተምራታለች (እኛ በሷ በኩል፣ ከሷ ጋርና በሷ እንደፈለግን እናሽከረክራታለን)። የጥቀርሻ ፊት ወንድ ልጅ የሠጠችን፤ የደነዘዘች በመሆኗና በሕሊናዋ ለሕይወቱ ፍራቻ ስላላት፤ በመንፈሱ ደካማና ጥገኛ፤ በሰዉነቱ ግን ጠንካራ እንዲሆን አድርጋ ታሣድገዋለች፤ በሌላ አነጋገር ሰዉነቱ አእምሮዉን የሚገዛበት ማለት ነው። እንግዲህ ከጥቂት ዓምታት በኋላ እኒህ ልጆች በለጋ ዕድሜያቸው ለዝርያ ሲደርሱ፤ እናዳቅላቸዋለንና ይኼንኑ ደግመን ደጋግመን እያሽከረከርን እንገፋበታለን። ይህ ጥሩ፣ አስተማማኝና የረጅም ዘመን አጠቃላይ ዕቅድ ነው።ማስጠንቀቂያ፤ ሊከሰቱ የሚችሉ ተወራራሽ መጥፎ ጎኖች፤

ቀደም ሲል ፈረስና ጥቀርሻ ፊቱ በልቅና በተፈጥሮ ባህሪያቸው ሳሉ፤ ለምጣኔ ሀብት ሥምሪታችን ጠቀሜታ እንደሌላቸው ተነጋግረናል፤ እነሱን ለትክክለኛ ምርት አገልግሎት አብሮ ስለመግራትና አብሮ ስለማሠር መርሆች ተነጋግረናል። በተጨማሪም፤ ለሴቷ አውሬና ለልጇ ልዩ ትኩረት ስለመስጠት አውርተናል። ቀጥለን ደግሞ በቅርብ፤ የሴቷንና የወንዱን አውሬዎች የተፈጥሮ ቦታ በማቀያየር፤ የተፈጥሮ ቦታቸውን መልሶ የሚያስረክባቸው አንድ ክስተት ብቅ ካላለ በስተቀር፤ በራሱ ዘለዓለሙን እምቧለሌ የሚሽከረከር ክብ መፍጠራችንን አስፍረናል። ሊቆቻችን፤ አእምሮ እንግዳ ለውጥ ሲደረግበት፤ በጊዜ ሂደት፤ አንድ የቆዬ በአእምሮ የተመዘገበ የታሪክ ክንውንን ከታሸገበት የሚቀሰቅስ ካጋጠመው፤ ራሱን የማረምና ደጋግሞ የማስተካከል ጠንካራ አቋም አለው በማለት፤ ይህ ክስተት ብቅ ሊል የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ አስጠንቅቀዉናል። ይህን ክስተት ለመቋቋም የነጠረው መንገድ፤ ብለዉናል ሊቆቻችን፤ የጠብደሉ የአእምሮ የታሪክ መዝገብ የያዛቸውን ክስተቶች፤ ሟጥጦ ደምስሶ፤ በቦታቸው የሚተኩ፤ ዝብርቅርቅ ያሉ በናኝ የቅዠት ብዙ ቅጂ ክስተቶችን መፍጠር፤ እናም እያንዳንዱ ቅዠት በራሱ አምድ ልክ በባዶ ሕዋ እንደሚንሳፈፉ ኳሶች በአእምሮው ይሽከረከራል።

ዝብርቅርቅ ያሉ፤ በናኝ የቅዠት ብዙ ቅጂ ክስተቶችን ለመፍጠር፤ ፈረሱንም ሆነ ጥቀርሻ ፊቱን ከላይ በጠቀስነው መሠረት ማዳቀል ግድ ይላል። የዚህ ዋነኛ ዓላማው የተለያዬ የሥራ ክፍፍሎችን በማበጀት፤ የተለያዩ የሥራ ደረጃዎችን በመፍጠርና በየሥራዎች የመገናኛ ደረጃ ላይ፤ የተለያየ የብዥታ ዋጋ ክብደት ለመፍጠር ነው። ውጤቱም የያንዳንዱ የብዥታ ክልል የመጀመሪያ መነሻ መዘበራረቅና ተቆራርጦ መለያየት ነው። ለምጣኔ ሀብታችን ሥምሪት ዕቅድ የፈረሶችንና የጥቀርሻውን ማዳቀል ዓላማ፣ ምክንያትና ጫና ስናስቀምጥ፤ ጉዳዩ ወደፊት ስንገፋ የበለጠ ይመሰቃቀላል የሚል ስሜት ስላለን፤ ለወደፊቱ ከኛ ተከትለው ለሚመጡ ዝርያዎቻችን የሚከተለውን የትርጉም ዝርዝር እንደረድራለን።

እምቧለሌ መሽከርከር ማለት፤ አንድ ነገር በተሠጠው መስመር መዞሩ ማለት ነው። አምድ ማለት፤ አንድ አካል በሱ ላይ ወይንም በዙሪያው የሚሽከረከርበት ማለት ነው። ክስተት ማለት፤ ከተለመደው ፅንስ ውጪና አድናቆትንና ግራሞትን የሚፈጥር ነገር ማለት ነው። ብዙ ቅጂ ማለት፤ ቁጥሩ የበዛ ማለት ነው። ክብ ማለት፤ ድፍን ቅል ማለት ነው። ፈረስን ማዳቀል ማለት፤ ፈረስን ወስዶ ከአህያ ጋር በግብረ ሥጋ ማገናኘትና ነፎ ኋላቀር ረጂም ራስ ያለው ደደብ የማያስወልድና እርስ በርሱም የማይወልድ በቅሎ ታገኛላችሁ።

ጥቀርሻ ፊቶችን ማዳቀል ማለት፤ ብዙ የጥሩ ነጭ ደም ጠብታዎችን ወስዶ፤ ጠብታዎቹን በምትፈልጉት የቀለም ድምቀት ደረጃ መለያይትና፤ ከዚያም እርስ በርሳቸው እንዲዳቀሉና የፈለጋችሁትን የቀለም ድምቀት የሚያስገኝ ዝርያ እስክታገኙ ድረስ፤ በተቻለው መጠን ብዙ የጥቀርሻ ፊት ሴቶች ውስጥ ማስገባት ነው (ይህ ማለት የጥቁር ሴቶችን በመድፈር፤ ማስረገዝና የሚወለዱትን እርስ በርሳቸው ማዳቀል ማለቱ ነው)። ይህ እንዲህ ማለት ነው፤ ጥቀርሻ ፊቶቹንና ፈረስን ባንድ የማርቢያ ገቦ ክተቷቸው። ጥቂት አህዮችንና ጥቂት ጥሩ የነጭ ደም ዘንቁ፤ እና ምን ታገኛላችሁ? ብዙ የተዘበራረቀ ኋላ ቀር አህያ፣ የተለየ ጥቀርሻ ፊት፣ እየተራወጠ፤ ከኋላ ቀር አህያ ረጂም ራስ ያለው በቅሎ ጋር ታስሮ፤ አንደኛው ወላድ ሌላው መካን ታገኛላችሁ። ( አንደኛው ዘለዓለም ቋሚ ሌላኛው ሟች፤ ጥቀርሻውን ቋሚ አድርገን፤ በቅሎዋን ግን በሌላ መገልገያ መሣሪያ እንተካታለን) ሁለቱም በቅሎና ጥቀርሻ ፊት አንዱ ከሌላው ጋር ተጠምዶ፤ አንዳቸውም ሌላኛው ከየት እንደመጣ ሳያዉቁና አንዳቸዉም ለራሳቸው ሳይሆኑ ወይንም አንዳቸው ከሌላው ሳይነጠሉ የኛ መገልገያ ይሆናሉ።

ቋንቋቸውን በቁጥጥራችሁ ሥር አውሉ

ማዳቀሉ ከተጠናቀቀ በኋላ፤ ከመጀመሪያ መነሻቸው የበለጠ ለማቆራረጥ፤ የአዲሱን ጥቀርሻ ፊትና የአዲሷን በቅሎ የአፍ መፍቻ ቋንቋ፤ ፍፁም ድራሹን ማጥፋትና አዲሱን የሥራ ሕይወታቸውን ያቀፈ አዲስ ቋንቋ በሥራ ላይ ማዋል አለብን። ቋንቋ የተለየ ተቋም መሆኑን ታውቃላችሁ። ወደ አንድ ሕዝብ ልብ ዉስጥ ይመራል። አንድ የዉጭ ተወላጅ ስለ አንድ ሀገር ቋንቋ ብዙ ባወቀ ቁጥር፤ በዚያ የኅብረተሰብ ሁሉም ደረጃዎች ውስጥ እንደልቡ ብዙ መንሸራሸር ይችላል። ስለዚህ፤ የውጭ ሀገሩ ተወላጅ የሀገሪቱ ጠላት ከሆነ፤ የቋንቋውን ገላ ዕውቀቱ በፈቀደለት መጠን፤ ያን ያህል ሀገሪቱ ለውጭ ሀገር ወራሪ ባህል የተጋለጠች ናት። ለምሳሌ፤ አንድን ባሪያ ዉሰዱ፤ ስለቋንቋችሁ ሁሉን ነገር ካስተማራችሁት፤ ሁሉን ሚስጥራችሁን ያውቃል፤ እናም ከዚያ በኋላ ባሪያ አይሆንም፤ ልትሸዉዱት አትችሉምና። ለምሳሌ አንድን ባሪያ “ሰብላችንን” በማሰባሰብ እንዲሠማራ ብትነግሩት፤ ቋንቋውን አጠናቆ ያውቃልና፤ “ሰብላችን” የሚለው እሱን የማያጠቃልልና እውነተኛ “ሰብላችን” ኣንዳልሆነ ያዉቃል፤ እናም የባሪያው ሥርዓት ይነኩታል፤ ምክንያቱም ምን ማለት እንደሆን ከሚያውቀው ጋር “ሰብላችን”ን ያዛምደዋልና። እና አዲሱን ቋንቋ ስታዘጋጁ መጠንቀቅ አለባችሁ፤ ምክንያቱም ባሪያዎች ቋንቋውን ካወቁ ወዲያው ቤታችሁ ውስጥ ይገባሉ፤ እናንተን “አንድ ለአንድ” ያናግሯችኋል፤ ያ ደግሞ ለምጣኔ ሀብታችን ሥምሪት ሥርዓታችን ፍፃሜ ነው። በተጨማሪ፤ የቃላትና የአባባሎች ፍቺ፤ የሂደቱ ቅንጣት ክፍል ብቻ ነው። ዕሴቶች በቋንቋው አካል በሚደረግ ልውውጥ እንዲፈጠሩና እንዲጓዙ ይደረጋሉ። አንድ የተሟላ ኅብረተሰብ፤ እርስ በርሳቸው የተጠላለፉ የዕሴት ሥርዓት አሉት። ሁሉም በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ዕሴቶች፤ በስነ ሥርዓት በኅብረተሰቡ በተቀናበረ መልክ እንዲሠሩ፤ የቋንቋ ድልድዮች አሉዋቸው። ለነዚህ የቋንቋ ድልድዮች ግን፤ ያን ያህሉ የዕሴት ሥርዓቶች ጠንክረው ይጋጩና የውስጥ ቀውስ ይፈጥረሉ ወይንም የርስ በርስ ግጭት ያስከትላሉ፤ ለግጭታቸው መክረር፤ በመካከላቸው ያለው የጉዳያቸው ጥንካሬ ወይንም በመካከላቸው ያለው የማንኛውም ዓይነት አንፃራዊ የጉልበት መበላለጥ ይወስነዋል።

ለምሳሌ፤ አንድን ባሪያ በአሳማ ማጎሪያ አስቀምጣችሁ፤ በዚያ እንዲኖር አሠልጥኑትና ያንን ኑሮ የጠቅላላ ሕይወቱ ትርጉም የመሆን ክብር እንዲሠጠው አድርጉት፤ ትልቁ ከሱ የሚመጣባችሁ ችግር፤ የታጎረበትን ፅዳት መጠበቂያ መሣሪያዎች ይስጡኝ እያለ መጨቅጨቁ ነው፤ ወይም በዚያው ማጎሪያ ሆኖ አንድ ጊዜ አምልጧችሁ በቋንቋው ውስጥ ቤትን ከማጎሪያው የበለጠ የሚያከብርበት ነገር አክሉና፤ ጉዳችሁ ይፈላል። ወዲያው ቤታችሁ ውስጥ ይገባል።

About አንዱዓለም ተፈራ

በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ፤ ለዐማራው ያለኝን ተቆርቋሪነት ወደ ላይ አጡዞት፤ የምችለውን በሙሉ ለዚህ ለተዘመተበት ዐማራ ሕልውና ለማድረግ የቆምኩ ታጋይ።
This entry was posted in ስነ ጽሑፍ - Literature. Bookmark the permalink.

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s