ደስታዬን ማመቅ አልቻልኩም!

ደስታዬን ማመቅ አልቻልኩም!

አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ

አርብ፣ ሰኔ ፲፭ ቀን ፳፻፲ ዓመተ ምህረት  ( 6/22/2018 )

ያለንበትን ወቅት ማመን አስቸግሮኛል። ከጥቂት ቀናት በፊት የነበረኝ ግንዛቤ፤ ጠቅልሎ ከኔ ጠፋ። ፍጹም  ያልጠበቅሁት ክንውን፤ ገሃድ ሆኖ፤ አይደረግም ያልኩት ተፈጽሞ፤ የሀገራችን የፖለቲካ ሀቅ ተገለባብጦ ሳገኘው፤ ሰውነቴን ዳሰስኩ። የፈለግሁት ሆነ! ብል ስህተት ነው። ነገር ግን፤ እየተደረገ ባለው ሂደት ያለሁበትን ማመን አቅቶኛል። ደስ ብሎኛል። ሂደቱ መቀጠል አለበት እላለሁ። ደስታዬን ግን ለራሴ አፍኜ መያዝ አልፈልግም። ለዚህም እንኳን ለዚች ቀን እላለሁ። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ድፍረትና ብሩህ ገጽታ አደንቃለሁ። ሀገራችን አሁን ባለችበት የፖለቲካ ሁኔታ መቀመጥ ነበረባት ወይ? አለባት ወይ? በፍጹም!

አሁን ሁላችንም በያለንበት መገንዘብ ያለብን ሀቅ አለ። ሀገራችን አሁን ካለችበት የፖለቲካ አዘቅት ወጥታ ወደፊት መሄድ የምትችለው፤ ያለንበትን ተጨባጭ ሀቅ ተረድተን፤ ምን ሊደረግ እንደሚቻልና እንደምንፈልግ በትክክል ስናውቅ ነው። እኔ የምመጣው ከታጋዩ ወገን ነው። ከዘረኛው መንግሥት ምንም ዓይነት በጎ ተግባር አልጠበቅሁም፤ አልጠብቅም። አሁን የተገኘው ዕድል የተከፈተው፤ በሕዝቡ የአመጽ እንቅስቃሴ ነው። ሕዝቡ ከፍተኛ መስዋዕትን ከፍሎ ነው! ለዚህ የበቃነው። መሉ ምስጋና ለሕዝቡ!

በተጨማሪ፤ እውነተኛ የሕዝብ መንግሥታዊ ስርዓት እንዲከተል፤ ብዙ መደረግ ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ለዚህ ደግሞ፤ የሕዝቡ የትብብር ጥረት የግድ ነው። ይህ ጥረት፤ ማንንም ለመጥቀም ወይንም ለመርዳት አይደለም። ጥረቱ ጠቅላይ ሚንስትር አቢይን ለመርዳት አይደለም። ራሳችንን ለመርዳት ነው። የሀገራችን የፖለቲካ ሂደት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማቅናት፤ እንደ አንድ ሕዝብ ወደፊት ለመሄድ፣ እስካሁን የተበተነውን የጥላቻ ፖለቲካ ለመግራት፣ እያንዳንዱ ዜጋ ግለሰባዊ ነፃነቱ ተመልሶለት ሀገሩን እንዲወድ፣ ትክክለኛ ልማት እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት ሥር እንዲሰድ፣ ተስፋ እንዲነግሥ፣ ሙስና እንዲገታ፣ ዘረኝነት እንዲከስም፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ርስ በርሳችን እንድንዋደድ በር ይከፍታል።

በፖለቲካ አመለካከታችን ለመሰለፍና በዚያ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመመሥረት ገና መንገድ ላይ ነን። ከዚያ በፊት ሊጠፋ የተዘመተበት ዐማራ፤ የደረሰበት በደል መታወቅ አለበት። የተተከለው የዐማራ የጥላቻ ዘመቻ፤ ለረጅም ጊዜ በመካከላችን የሚኖር ክስተት ነው። በሀገራችን ታሪክ ያልተደረገና በደንብ ተጠንቶ፤ መልሶ አንገቱን እንዳያቀና መመታት ያለበት ክንውን ነው። ለዚህ ሀገራችን ትኩረት ሠጥታ፤ ሙሉ ጥናት ተደርጎበት፤ መስተካከል የሚገባው ተስተካክሎ፤ ሙሉ ጥገናው ተከናውኖ፤ ወደፊት መሄድ አለብን። ወደኋላ ስንዞር አንኖርም። ወደፊት ለመሄድ ግን የነበርንበትን መፈተሽ ግዴታ ነው። ለዚህ በቅተናል። ያማረ ወደፊት እንዲኖረን ደግሞ፤ ሙሉ ኃይላችንን ማስተባበር አለብን።