የአደባባይ ፖለቲካ

የአደባባይ ፖለቲካ፤
እሁድ ጥር ፳ ፰ ቀን ፳ ፻ ፱ ዓመተ ምህረት (2/5/2017)

የአደባባይ ፖለቲካ የሚባል አለ እንዴ? የአደባባይ ፖለቲካ ደግሞ ምንድን ነው? ከሌላው የሚለየው በምን መንገድ ነው? ችግር አለበት ወይ? ጠቀሜታ አለው ወይ? አሁን ካለንበት ሀቅ ጋር ምን አገጣጠመው? ይህ ነው የዚህ ጽሑፍ ማዕከላዊ ማጠንጠኛ ነጥብ። ይሄን ሳብራራ፤ አብረው ተያይዘው የሚከተሉትን በመመርመር፤ የዳበረ ውይይት ይከተል ዘንድ በሩን እከፍታለሁ።

ፖለቲካ ላንዳንዶቻችን ውሸት ማለት ነው። “ይሄን ፖለቲካህን ተወኝ! ከነፖለቲካህ ገደል ግባ!” ሲል፤ ፖለቲካ መጥፎ፣ ውሽት፣ ጎጂ አድርጎ በመሳል ነው። ፖለቲካ ላንዳንዶቻችን የገዥዎች ሥራ ነው። “እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም! በለሥልጣን የመሆን ፍላጎት የለኝም!” ሲል፤ ፖለቲካ የኔ ጉዳይ አይደለም፤ የተለዩ ሰዎች ሥራ ነው፤ ማለቱ ነው። ፖለቲካ ላንዳንዶቻችን የፖለቲካ ድርጅቶች የተለየ ተግባር ነው። “እኒህ ድርጅቶች ምንም ያደረጉት ነገር የለም! እንዲህ ሊያደርጉ ይገባል! እንዲያ ማድረግ የለባቸውም! ድርጅቶች አይረቡም!” ሲል፤ ይህ የድርጅቶች ጉዳይ ነው። እኔን አያገባኝም። የሀገሬ ፖለቲካ የፖለቲካ ድርጅቶች ልዩ ተግባር እንጂ፤ የኔ አይደለም፤ ብሎ መፈረጁ ነው። ፖለቲካ ለንዳንዶቻችን ሳይንስ ነው። በጥናት የሚገበይ እውቀትና፤ በዚያ ሥራ የሚያዝበት። ሁሉንም ነገር በማንበብ መልስ የሚገኝበት፤ የምርምር ውጤት ብቻ ነው።

ለአንድ ተማሪ፤ ፖለቲካ የሚጠና አንድ የትምህርት ዓይነት ነው። ይህ የትምህርት ዓይነት፤ ባጠቃላይ ስለ መንግሥት ስነ ምርምር፤ ዘርዝር ባለ መልኩ ደግሞ፤ ከአስተዳደርና ከመንግሥታዊ ግዛት ጋር በተያያዘ፤ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሥልጣን ለመያዝ የሚያደርጉትን ውድድር፣ በመካከላቸው የሚደረገው የመደራደርና የመፎካከር ሂደትን ያካተተ የመንግሥታዊ ግዛት ጉዳይ ነው። አምባገነን ገዥዎች ባሉባቸው ሀገራት ደግሞ፤ ፖለቲካ የአምባገነኖች የግል ጉዳይ ሆኖ፤ ሕዝቡ የማያገባው ተመልካች፤ አልፎም ሊርቀውና ባጠገቡ እንዳይዞር የሚፈራው ተሰቦ በሺታ ነው። ከዚያ በተረፈ ፖለቲካ፤ ብዙ ዓይነት ግንዛቤዎችን በሰዎች ውስጥ ያስያዘ ጽንሰ-ሃሳብ ነው። እንግዲህ በመጀመሪያ ሁላችን ልንስማማበት የሚንችልበትን የፖለቲካ ምንነት አስቀምጠን፤ ከዚያ ደግሞ የ “አደባባይ ፖለቲካ” ምን እንደሆነ በመዘርዘር፤ ለምን ወደኛ ትግል ውስብስብ ሂደት ውስጥ ሊቀርብ እንደቻለና ያስከተለውን አንደምታ አስፍራለሁ።

በዚህ ጽሑፍ ላይ፤ ፖለቲካ፤ በግለሰብ ደረጃ፤ ግለሰቦች፤ በሌሎች እንደራሳቸው ባሉ ግለሰቦች ዘንድ፤ የራሳቸው አመለካከት ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያግባቡበት ነው። የሕዝብን ጉዳይ በተለመከተ፤ ባጠቃላዩ ስብስቡ አንድነት ድምዳሜ ላይ በመድረስ፤ አንድ ውስኔ መሥጠትን ያቀፈ ነው። በሂደቱንም መነታረኩንም ይይዛል። በሕዝቡ መካከል፤ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበና ተለዋዋጭ የሆነ እውቀት እና ተግባር ነው። ይህ ወቅታዊ መሆኑ፤ እንደየሁኔታዎች ተለዋዋጭ መሆኑንና ከጊዜ ጋር የሚለዋወጠውን የአመለካከት ጉዳይ ለመጠቆም ነው። በርግጥ፤ በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ፤ የፖለቲካን ትርጉም ስንወስደው፤ ከሞላ ጎደል አንድ ነው። በሂደት ከአሪስቶትል ጀምሮ መልኩን እያሳማረ የመጣ የእውቀት ዘርፍ ነው። አሁንማ “ፖለቲካ የተራራቀና ፍጹም ጠበኞች የሆኑ  ሰዎችን ያስተቃቅፋል!” ይባላል። ጉልበቱ ቀላል አይደለም።

ፖለቲካ የግለሰብ ጉዳይ አይደለም። ባንድ መንገድ ወይንም በሌላ፤ በአንድ አካል ውስጥ ተያይዘው ያሉትን ሁሉ የሚያነካካ የስብስቡ ጉዳይ ነው። የጥቅሉን የበላይነት በመያዝ፤ በተደራጀ መልክ የቁጥጥር ወሳኝነቱን ለማግኘት የሚደረግ ሩጫና ያንን መተግበሩን ያቀፈ ነው። በዚህ መካከል ትክክል የሆነና ያልሆነ አካሄድ አለ። ሕጋዊና ሕገ ወጥ የሆነ ሂደትም አለበት። እንግዲህ ይሄን ሁሉ አጠቃሎ ማየት፤ ፖለቲካ የሚለውን ለመገንዘብና እውቀት ለማግኘት የተደላደለ መሬት ላይ ለመሆን ያመቻል። ታዲያ ፖለቲካ ጥበብ ነው። ፖለቲካ እውቀት ነው። ፖለቲካ ዘዴ ነው። ፖለቲካ መሰሪነት ነው። ፖለቲካ የዋህነት ነው። ፖለቲካ ሞኝነት ነው። ፖለቲካ ሰዎች በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ፤ የሚኖራቸው ግንዛቤና ከአንድነቱ አኳያ፤ በአንድነቱ መካከል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ፤ የበላይነቱን ለመያዝ የሚያደጉት ክንውን ነው። ባጭሩ፤ ፖለቲካ ጣጣው ብዙ ነው።

ታሪኩን፣ ብልቱን፣ ጥምዝምዙን ለፖለቲካ ሊቆች ትተን፤ ለኛ የፖለቲካ ቀጥተኛ ትርጉም፤ የመንግሥታዊ አስተዳደር ሰነ ጥናትና ዜጎች ከመንግሥታዊ ግዛቱ ጋር ያላቸውን ትስስር ገላጭ የትምህርት ዘርፍና፤ የፖለቲከኞች የሙያ መስክ ነው። በዚህ ትንታኔ ላይ፤ በጥናት የተደገፉ የፖለቲካ ተግባራዊ ሂደቶችን የሚዘረዝሩ ክፍሎች አሉ። ዛሬ ደግሞ እኔ፤ አዲስ ዘርፍ አብቅየለታለሁ። “የአደባባይ ፖለቲካ” የሚል። ምንድን ነው የአደባባይ ፖለቲካ ደግሞ? ልትሉኝ ይገባል። ፖለቲካን እንደ አንድ ተቋም ሁሉም በግሉ የየራሱን ጨብጦ፤ ትርጉምና ይዘት፣ ቅርጽና ጥልቀት እንደያቅሙ ሠጥቶ፤ ራሱ ባበጀው ክልል ሲንፏለልበት፤ የ “አደባባይ ፖለቲካ” ሆነ ማለት ነው። እንግዲህ፤ ጉዳዩ ሁሉን የሚነካ ሆኖ፤ መፍትሔውንና የመፍትሔ መሳሪያውን ባንድነት ማበጀቱና መያዙ ቀርቶ፤ እያንዳንዱ የየራሱ አድርጎ የሚኬድበት ሀቅ፤ የአደባባይ ፖለቲካ ነው። እዚህ ላይ ክስተቱ ራሱ፤ ራሱን በራሱ መጋረጡን አልክድም። እንዴት ተብሎ የጋራ የሆነውን እውነታ፤ የተለያየና የየግል ማድረግ ይቻላል? እንደምትሉኝ እርግጠኛ ነኝ። እንኳን ደህና መጣችሁ። ይህ የአደባባይ ዓለም ነው። ያደባባይ ዓለም፤ ሁሉም የየራሱን እጀጠባብ አጥልቆ፤ በየራሱ አደስና እጣን ተሽፍኖ፣ በየራሱ ኩል ተውቦና ያልሆነውን ሆኖ፤ “ልታይ!” “ልታይ!” የሚልበት እውነታ ነው። ይህ ነው አደባባዩ ፖለቲካ! ፖለቲካው አደባባይ! የሆነበት ዓለም። እስኪ ዘርዝረው ብትሉኝ፤

በአንድነት ተሰደን በየግል ለየብቻ ተሰደናል። ባንድነት ተበድለን በየግል ለየብቻ ተበድለናል። ባንድነት ተጎድንተን በየግል ለየብቻ እናለቅሳለን። ይህ ነው ፖለቲካችን። ታዲያ ይሄን ፖለቲካ፤ ባደባባይ፤ በድረገጾች፣ በሬዲዮ፣ በፓልቶክ፣ በፌሰቡክ፣ በትዊተር፣ ስናቀርበው፤ ሕዝቡን በ “እኔ” ተክተን፣ ድርጅትን በ “እኔ” ተክተን፣ አንድነትን በ “እኔነት” ተክተን ነው። እናም፤ ሌሎችን በሙሉ ከያዝነው “እኔ” አንጻር በማስቀመጥ፤ ፖለቲካውን የ “እኔ” ፖለቲካ እናደርገዋለን። የሕዝቡን የኑሮ ተጨባጭ ሀቅ፤ በጭንቅላታችን በምንፈጥረው ዓለም እናደርገዋለን። ያንን ሀቅ “እኔ” በመጠሩ፤ አድራጊም ፈጣሪም “እኔ” ን ስለሚያደገው፤ “እኔ” ብቻ ትክክለኛ በመሆን፤ ሌሎች በሙሉ ስህተተኞች ይሆናሉ። “እኔ” ን የተቃወመ በሙሉ የሕዝቡ ጠላት ነው። ሌላውንማ ምኑን እነግራችኋለሁ!

ይህ ስሌት ነው እንግዲህ፤ የማናውቀውን ግለሰብ፤ ባደባባይ አንድ የማንወደውን ቃል ስለጣለ፤ “አንተ ወያኔ!” “ምናባህ . . .” እያልን እንድንዘረጥጥ ሕጋዊ ፈቃድ የሠጠን። እግዚዖ!!! የፓልቶክ ክፍል አስተዳዳሪ ቀዩን ካርድ የሚዠልጠው ይሄ ሥልጣን ስላለው ነው። አንዱን ተናጋሪ ድራሹ እንዲጠፋ፤ ያቺን ጣት ልኮ ቀጭ የምትለዋን የጅ ጣቶች ማስፈሪያ ቁልፍ የሚያስጮኻትም፤ ይህ ሥልጣን ስላለው ነው። በማያገባው ገብቶ፤ “በሌሎች ጉዳይ ገብቼ ካልፈተፈትኩ!” ያሚያሰኘውም ያደባባይ ፖለቲካችን ነው። ይህ የብዙኀኑ የፖለቲካ አዋቂ መሆን ጉዳይ አይደለም። ብዙኀኑ የፖለቲካ አዋቂ የሆነበት ወገን፤ ትክክለኛ እውቀቱ ስላለ፤ መግባባቱ አለ። አንድነቱን ለማግኘት ብዙ መጣር አይሰፈልግም። ባጭሩ ይገኛል። ሌሎችን ለማድመጥ ፈቃደኝነቱ ሞልቷል። ችግር የለም። ችግሩ ያለው፤ የፖለቲካ እውቀቱ ባነሰበት ወገን ነው። የፖለቲካ እውቀት ባነሰበት ወገን፤ ሁሉ የፖለቲካ አዋቂ ነው። ለምን ቢባል፤ የእውቀቱ መለኪያ ደረጃው በጣም ዝቅ ያለ ነውና።

ልመለስና የ “አደባባይ ፖለቲካ” ዬን ላስምርበት። ፖለቲካ አንድን ስብስብ የሚገዛ ነው። በመካከላቸው ያለውን ግንኙነትና የሚያስተሳስራቸውን ስነ ሥርዓት፣ ባንድነት የሚደርሱበትን ውሳኔና የሚያከናውኑትን ተግባር ይገልጻል። በግል ሳይሆን በጥቅል! ይህ የተገላቢጦሽ የሚሆነው፤ እያንዳንዱ “እኔ” ስብስቡ ነኝ። “እኔ” የምለው የስብስቡ ነው። የስብስቡ አዋቂ “እኔ ነኝ” ያሉ ጊዜ፤ ፖለቲካው ያደባባይ ሆነ። ባጭሩም አንድ የሚያደርግ ሳይሆን የሚበታትን ፖለቲካ ጥፍሩን ዘረጋ ማለት ነው። “ሌሎችም እንደኔው ባለጉዳዮች ናቸው!” የሚለው ርቆ ሄደ። እናም የትም የማይደርስ፤ ነገር ግን ባለበት የሚረግጥ ፖለቲካ ነገሠ ማለት ነው። ብዙም ሳላትት የራሳችንን የፖለቲካ እውነታ ቁጭ አድርጌ አቀረብኩት! አይደል!

የ “አደባባይ ፖለቲካ” የሚባል አልነበረም። እኔው ነኝ የፈጠርኩት። የ “አደባባይ ፖለቲካ” የፖለቲካ አላዋቂዎች ፖለቲካ እናውቃለን ብለው የሚጨፍሩበት መድረክ ነው። ባደባባይ የ “አደባባይ ፖለቲካ” ጨዋታ ማድረጋችን ግን፤ እኔ የፈጠርኩት ሀቅ ሳይሆን፤ የኛ ተጨባጭ የፖለቲካችን ሀቅ መሆኑን ከኔ የበለጠ እርስዎ አንባቢው ያውቁታል። ታዲያ የኛ የ “አደባባይ ፖለቲካ” የተለየ የሆነው፤ ስደተኞች መሆናችን ዘንግተን፤ ባደባባይ ቁም ነገር ፍላጋ ሳይሆን፣ አንድነትን ለማጣት ስንጥር በማየቴ፣ መዘረጣጠጥን የፖለቲካ ሙያችን ስናደርገው ስላየሁ፣ ባለንበት ስንረግጥ ስላየሁ፣ ድርጅቶች ሲበጣጠሱ ማየቱ ስለሰለቸኝ፣ ታታሪ ግለሰቦችና ታጋይ ድርጅቶች በየድርሻቸው ተለይተው ማድረግ ያለባቸውን ለይተው ሲያደርጉ ስላላየሁ፣ በሃሳቦች ላይ ሳይሆን በግለሰቦች ማንነት ላይ ትኩረቱ ስላስጠላኝ፣ ለብዙ ዓመታት በፖለቲካ መድረኮች የዋሉ ሰዎች፤ ባደባባይ መዋሉን እንደትግል ቆጥረው ሲንፏለሉ ስላየሁ፣ ስድብን እንደ የፖለቲካ ዕውቀት ቆጥረው፣ በዚያ ተክነው ማዕረጉን ተኮናንበው አደባባዩን የተቆጣጠሩት ሲበዙ ስላየሁ፣ በማያውቁት ጉዳይ ደረትን ገልብጦ በመሐይም ድፍረት የመምሰል ሩጫው ስላስቆጣኝ፣ ትርጉም የማይሠጥ የቃላት ድርድራና የሌሎችን ንግግሮች መደጋገሙ አዋቂነት የሆነበት ስብሰባ ስላሰለቸኝ፣ የማወቄን እወቁልኝ ሩጫን ማየቱ ስለደከመኝ፣ ትናንትም ዛሬም ያው ሆኖ ስላልጣመኝ፣ ሁኔታውን መመርመሪያ መሳሪያ ፈለግኩና፤ የ “አደባባይ ፖለቲካ” ን አገኘሁ። እናም ለናንተ አካፈልኩ።

የ “አደባባይ ፖለቲካ” ችግር አለበት ወይ? መዓት! የ “አደባባይ ፖለቲካ” ትክክለኛ ፖለቲካ አይደለም። የፖለቲካን ውዳቂ ቦታ የያዘ ዝቃጭ ወለሉ ነው። የ “አደባባይ ፖለቲካ” የቁም ነገረኛ ሰዎች መዋያ አይደለም። የ “አደባባይ ፖለቲካ” አፍራሽ ነው። የ “አደባባይ ፖለቲካ” ግለሰቦችን እንጂ ሕዝቡን አያቅፍም። የ “አደባባይ ፖለቲካ” የሕዝቡ ጉዳይ ሳይሆን የግለሰቦች አውቃለሁና ማወቄን እውቁልኝ አደባባይ ነው። የ “አደባባይ ፖለቲካ” ስሜት ምክንያታዊነትን፣ ግለት ጥልቀትን የተካበት ቦታ ነው። የ “አደባባይ ፖለቲካ”  አንድ ዓይነት ሕዝበ-ውሳኔ ላይ አያደርስም። የ “አደባባይ ፖለቲካ” መጨረሻው መበጣጠስ ነው። የ “አደባባይ ፖለቲካ” ምንም ጥቅም የለውም። የ “አደባባይ ፖለቲካ” ብዙዎቻችን የተዘፈቅንበት ሜዳ ነው።

በዚህ ጽሑፍ ያስቀመጥኩት ያመንኩበትን ቢሆንም፤ እኛ ያለንበት ከዚህ የተለየ ቢሆንና እኔ ብሳሳት እመርጣለሁ። እኔ ተሳስቼ ብገኝና ከሳልኩት በተሻለ ቦታ ላይ ተገኝተን አንገቴን ብደፋ ደስታውን አልችለውም። “እዩኝ!” “እዩኝ!” “እኔ አውቃለሁ! እኔን ብቻ አዳምጡኝ”! እያልን ካልሆነ፤ እኔ ተሳስቻለሁ። “አንተ ወያኔ!” “ከዚህ ጥፋ!” “የወያኔ ድርጅት!” “ምን ታውቃለህ! አፍክን ዝጋ!” “ምናባክ!!!” እየተባባልን ካልሆነ፤ የሌለ ስዕል ቀርጫለሁ። ድርጅቶች እየተስማሙ፣ ምሁራን እያስተማሩ፣ ታጋዮች እየተባበሩ፤ ያለበትን ሁኔታ አግማምቼው ከሆነ፤ ተሳስቻለሁ። ትንሽም ብትሆን እውነት አለህ ካላችሁኝ፤ ወደ መፍትሔው እናምራ።

በየትም ቦታ፤ “እኔ” ብለን ራሳችንን በምንስለው ብራና፤ ሌሎችም ተመሳሳይ ስዕል ይዘው እንደሚቀርቡ እንቀበል። የራሳችንን አመለካከት ለማቅረብና፤ የሌሎችን አመለካከት ለማደመጥ ሁሌም ዝግጁ እንሁን። የተለየ ነጥብ ማለት መርዝ ማለት አይደለም። አይምረረን። አንፍራው። ሌሎቹ የኛን መነፅር አላጠለቁም። የራሳቸው መነፅር አላቸው። በምንነጋገርበትና የሌሎችን በምናዳምጥበት ወቅት ነው ሌሎችም የኛን የሚያዳምጡት። በአንድነት መፍትሄ ለማግኘት ነው የተሰበሰብነው። እዚህ ቦታ እያንዳንዳችን ለሕዝቡ ለምናደርገው አስተዋፅዖ፤ የበኩላችን ድጋፍ ለማበርከት እንጂ፤ ከሌሎቻችን አንድም ጥቅም ለመውሰድ አልመጣንም። ስለዚህ በእኩልነት እንተያይ። ወደ አንድ ለመምጣት ነው የምንነጋገረው። የ “አደባባይ ፖለቲካ” ሳይሆን የሕዝብን ሕልውና የሚወስን ጉዳይ ነው የምንነጋገርበት ያለው! ከ “እኔ” በላይ የሕዝብ ጉዳይ መኖሩን አንርሳ። ከ “እኔ” ድርጅት በላይ የሕዝብን ጉዳይ መያዛችንን አንርሳ። ቅድሚያ ለባለጉዳዮች እንሥጥ። ቅድሚያ ለሕዝቡ እንሥጥ። ቅድሚያ እንድንሰበሰብ ላደረገን ጉዳይ እንሥጥ። በጉዳዩ ዙርያ፤ ራሳችንን እንደ አንድ ተገጣጣሚ አካል እንጂ፤ ሙሉ ብቸኛ አካል አድርገን ዕንይ። ሃሳቡን ከአቅራቢው ለይተን፤ በራሱ ብቻ በቂ ግንዛቤ እንሥጠው። ጠቃሚ ወይንም ጠቃሚ ያልሆነ ሃሳብ ሊሆን ይችላል። በቃ! ሃሳቡን ከዚህ የጥቅም ሚዛኑ አንጻር ብቻ እንየው። ተስፋዬ፤ በዚህ ርዕስ ተወያይተን አንድ ውሳኔ ላይ እንድንደርስ ነው።