የትግሬዎች ተቆርቋሪ ወይንስ የትግሬዎች መንግሥት ደጋፊ?

የትግሬዎች ተቆርቋሪ ወይንስ የትግሬዎች መንግሥት ደጋፊ?
ቅዳሜ፣ ሐምሌ ፱ ቀን፤ ፳ ፻ ፰ ዓመተ ምህረት ( 7/16/2016 )
አንዱዓለም ተፈራ  –  የእስከመቼ አዘጋጅ

በጎንደር የወልቃይትን ማንነት ይዞ የተነሳው ወገናችን ጥያቄ፤ የማንነቱን ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ያነሳው፤ የወራሪውን አምባገነን ወገንተኛ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ መሠረት የሚንድ ጥያቄ ነው። እናም የዚህን ወራሪ ገዢ ሕልውና በጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው። በዚህ ሂደት፤ የትግሬዎች መንግሥት ንብረት ስለሆኑትና በጎንደር ስለተቃጠሉት ተቋሞች፤ በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ የትግራይ ስብስቦች መግለጫ አውጥተዋል። አልፎ ተርፎም “ይህ ጠባብነት ነው!”። “ሀገር ያፈራርሳል!” እያሉ የኢትዮጵያ ጠበቃ ሆነው፤ ያስጠነቅቁናል።

የነዚህ መግለጫዎች ዋና ፍሬ ሃሳብ፤ “ከትግራይ ክልል ውጪ፤ እኛ እንደልባችን በምንኖርበት ቦታና በአካባቢው ሕዝብ ላይ በኛው መንግሥት ድጋፍ ባካበትነው የሕዝቡ ንብረት ላይ፤ ምንም ዓይነት ጥፋት መድረስ የለበትም!” ነው። “ይህ ባይሆን፤ የአካባቢው መንግሥት ተጠያቂ ሆኖ፤ የትግሬዎች መንግሥት፤ በዚህ አካል ባሉ የአካባቢው መንግሥት ሠራተኞች ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት!” ነው። እዚህ ላይ ሁለት ክፍሎችን ለይተን እንመልከት። የመጀመሪያው የወጡትን መግለጫዎች ይዘት ይሆናል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እኒህን መግለጫዎችን አውጭዎቹን ይመለከታል።

የወጡት መግለጫዎች ትልቅ መልዕከት አላቸው። ትግሬዎች፤ ከትግራይ ውጪ፤ በኢትዮጵያ፤ የትም ቦታ በበላይነት የመኖር መብታቸው የተጠበቀ ይሁን እያሉን ነው። በተጨማሪ ደግሞ፤ ከመንግሥታቸው ድጋፍ በማግኘት፤ የአካባቢውን ወሳኝ ንብረቶች ላይ ባለቤትነትን በማግኘት፤ በአካባቢው ወገናችን ላይ የበላይነትን ጨብጠው፤ የአካባቢውን የንዋይ ስምሪት መቆጣጠራቸው በግልጽ እየታወቀ፤ ይከበርላቸው፤ እያሉን ነው። ከትግራይ ጎንደር መጥቶ፤ መሬት አርሶ፤ ጉድጓድ ቆፍሮ የሚኖር የለም። ያለው፤ ከትግራይ መጥቶ፤ ቀድሞ የነበሩትን ክፍተኛ ገቢ ያላቸው ንብረቶችን ከመንግሥቱ ተቀብሎ፤ ደልቶት የሚኖር የትግሬዎች መንግሥት አባልና ደጋፊ ነው። በተጨማሪ ደግሞ የነሱ መንግሥት በሠጠው መግለጫ መሠረት፤ በጥቆማና በመረጃ ተግባር የተሰማሩ ናቸው። በመግለጫዎች እንደጠቆሙልን፤ ትግሬዎቹ፤ አማራው ጉራፈርዳ፤ ጠፉን መሬት አልምቶ፣ ክብት አርብቶ በዝቅተኛ ደረጃ ሲኖር እንደነበረው አይደሉም። በአውሮፓና በአሜሪካ ሀገሮች፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ተንደላቀው የሚኖሩ ትግሬዎች፤ ከትግራይ ውጪ በጎንደር ለሚኖሩ ትግሬዎች ጠበቃ ሆነው፤ እኒህን መንካት ያስቀጣል ይሉናል! አቤት ያንት ያለህ!

እስኪ ተመልከቱ፤ እኒህ በከተማዋ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ የንግድ ተቋማት ናቸው። ከትግራይ መጥተው ትግሬዎች እንዴት እኒህን ከፍተኛ ተቋማት ሊቆጣጠሯቸው ቻሉ? ብሎ መጠየቅ የወግ ነው። ያን ግን ለሌላ ጊዜ።

ሁለተኛው ደግሞ መግለጫ አውጪዎቹ ናቸው። ትናንት በጉራፈርዳና በሌሎች የደቡብ፣ የሶሚያ፣ የኦሮሚያና የቤንሻንጉል ክልሎች፤ አማራዎች ንብረታቸው ብቻ ሳይሆን፤ በትግሬዎች መንግሥት መሪነት፤ በአካባቢው ቡችሎቻቸው አቤት ባይነት ሕይወታቸው ያለምንም ይሉኝታ ሲጠፋ፤ አንገታቸው ሲቀላ፤ እርጉዝ ሴቶች ሲበለቱ፣ የነሱ ጉዳይ ካለመሆኑም በላይ፤ ትክክል ነው በማለት አብረው ጨፍረዋል። ለአማራው ይቁሙ ማለቴ አይደለም። ታሪክ ግን፤ የትግሬዎችን መንግሥት አባላት ብቻ ሳይሆን፤ ደጋፊዎቻቸውንም ይጠይቃል። ፍርድም ይሠጣል። ብቻ ያ ቀን ይድረስ!

ለመሆኑ፤ የትኛዋን ኢትዮጵያ ይሆን ትፈራርሳለች የሚሉን? እድሜ ለነሱ እንጂ፤ ምን የቀራት አለና! ወይ ጅራፍ፤ ራሱ ገርፎ . . .