የስድሳዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ( ክፍል ፩ )

ስድሳዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ( ክፍል ፩ )
አንዱዓለም ተፈራ       eske.meche@yahoo.com
ማክሰኞ፤ ግንቦት ፪ ቀን፤ ፳ ፻ ፰ ዓመተ ምህረት ( 05/10/2016 )

በሃምሳ ዓመት ዙሪያ የሚያስቆጥረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ፤ በተለያዩ ጎራዎች የተለያዩ አመለካከቶች ይንጸባረቁበታል። አሁን በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን፤ የሳይንስና እደ ጥበብ እመርታ ከዓመት ዓመት መለኪያውን እየበጣጠሰ በሚነጉድበትና ከዚያን ዘመን እስካሁን ያገኘነውን ተመክሮ ሰንቀን፤ ፍርድ በነዚያ ወጣቶች ላይ ስንሰነዝር፤ ማጤን ያሉብን ጉዳዮች አሉ። በርግጥ አሁን ላለንበት ምስቅልቅል የፖለቲካ ሀቅ፤ እኛው የአሁኖቹ ባለቤቶች ተጠያቂ እንዳልሆንና መፍትሔ እንዳናስገኝ፤ ማምለጫ አድርገን በዚያ ወቅት በነበሩ ተማሪዎች ላይ የፍርድ ጅራፋችንን መሰንዘሩ፤ አዋቂ አያደርገንም። የቄሳርን ለቄሳር ነውና! በሌላ በኩል ደግሞ ወርቃማው ትውልድ በማለት፤ የተለዩና ምትክ የሌላቸው አድርጎ መሳሉ፤ በወቅቱ ለነበሩት ሆነ ላልነበሩት፤ ትክክለኛ ፍርድ አይደለም። በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ ያሉ ወጣቶች፤ በወጣትነታቸው፤ የተፈጥሮን ሽግግር ተከትሎ፣ ልዩ የኅብረተሰቡ ሚና አላቸው። ይህ ሚናቸው ደግሞ፤ በታሪካዊ ወቅቱ፣ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ አሰላለፉና ኅብረተሰቡ ባለበት ተጨባጭ ሁኔታ ይገዛል። ከዚያ ወጥተው ተዓምር አይሠሩም። መለኪያው የዚያን ታሪካዊ ኃላፊነት መውስድና ማከናወናቸው ወይንም አለመቀበልና መሸሻቸው ነው። በዚህ ግንዛቤ፤ የስድሳዎቹን ተማሪዎችና እንቅስቃሴያቸው፤ ተከታታይ በሆኑ ክፍሎች፤ የነበሩበትን ወቅት ዓለም አቀፍና ሀገራዊ የፖለቲካ ሀቅ፣ በተማሪነታቸው የነበሩበት እውነታ ማለትም፤ ትምህርት ቤቱ፣ መምህሩ፣ ትምህርቱና ማንነታቸው፣ በወቅቱ ያነሷቸው ጥያቄዎች፣ እና የተማሪ እንቅስቃሴ ወስን ደንበሩን በመዳሰስ፤ በጎ ሠርተዋል ወይንስ አጉድለዋል የሚለውን ለመመዘኛ ያመቻችሁ ዘንድ ለአንባቢያን አቀርባለሁ።

በቅድሚያ ግልጽ ማድረግ ያለብኝ ጉዳይ አለ። እኔ የስድሳዎቹ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ወደ ታሪካዊ ጣራው በተቃረበበት ወቅት፤ በ ፲ ፱ ፻ ፷ ፪ ዓመተ ምህረት የመዘጋጃ ትምህርት ቤት (ላብ ስኩል) በመቀላቀል፤ የዚህ እንቅስቃሴ ተሳታፊ ነበርኩ። እናም ለበጎውም ሆነ በጎ ላልሆነው፤ አብሬ ተጠያቂ ነኝ። ስለዚህም፤ የነበርኩበትን መሠረት አድርጌ ነው የማቀርበው። ይህ ጽሑፍ በምርምርና በጥናት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፤ በቀጥታ በቦታው በተሳተፈ ሰው የቀረበ ዘገባ ነው።

መግቢያ

የካቲት ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓመተ ምህረት፤ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ፤ መሠረታዊ ለውጥ የተከተለበት፤ በጣም ልዩ የሆነ ክንውን ነበር። በታሪክ ከሚጠቀሱት፤ የሀገራችንን ማንነትና ምንነት ወደ መድረክ አቅርበው፤ የነበረው እንዳይቀጥል፤ አዲስ ክስተት እንዲከተል ካደረጉት ዋና ዋና እውነቶች አንዱ፤ ከፍ ሲደረግም ቁንጮው ነበር ማለት ይቻላል። የካቲት ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓመተ ምህረት፤ ለረጅም ዘመናት ኢትዮጵያን ሲገዛ የነበረው ዘውዳዊ ሥርዓት ፍጻሜን አስከተለ። የማይጠየቅ፣ የማይከሰስ፣ ያሻውን የሚያደርገው የሰለሞናዊ ቤተሰብ ዝርያ የግዛት ሂደት፤ ላንዴና ለሁሌም ቀጥ ብሎ እንዲቆም ሆነ። ሕዝቡ ያለ አንድ አዲስ ንጉስ ወይንም መሪ፤ በቃኝ ብሎ ተነሳ። ምን እንደሚከተል ማንም በወቅቱ ባይተነብይም፤ የነበረው ግን እንዳይቀጥል ሕዝቡ አምኖበት ተነሳ። ለዚህ እንቅስቃሴ፤ በጣም አጭር በሆነ ታሪካዊ ወቅት ውስጥ፤ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ከላይ እስከታች በእመርታ ተነስተው፤ ለለውጡ አስተዋፅዖ አድርገዋል። ሴቶች በበኩላቸው የእኩልነት ጥያቄ አንግበው፤ ሠራተኞች በደላቸውን ዘርዝረው፣ የከተማው ነዋሪ ችግሩን ገልጾ፣ አረሶአደሮች የኑሮ አሻራቸውን ተሸክመው፣ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ሁለተኛ ዜግነቱ በቃን ብለው፣ መምህራን፣ ታክሲ ነጅዎች፣ ተማሪዎች በአንድነት ተነሱ። የወታደሩ ክፍልም የኅብረተሰቡ አካል በመሆኑ፤ ዘግይቶም ቢሆን የራሱን ጥያቄዎች በማንገብ ተነሳ። የሁሉም ትኩረት የነበረው በዘውዳዊው አገዛዝና በአጫፋሪዎቹ ላይ ነበር።

እንግዲህ ይሄንን ክንውን ሆነ ለዚህ ክንውን መከሰት ያበቁትን ሂደቶች፤ ከዚያ ወዲህ ለተከሰተውና ለጎደለው ተጠያቂ ማድረግ፤ ስህተት ነው። ከዚያ ወዲህ ለተከተለው ተጠያቂዎቹም ሆኑ ተሞጋሾቹ፤ በሂደቱ የነበሩት ክፍሎች ናቸው። አሁን ወደኋላ ዞሮ፤ ይሄ መደረግ ነበረበት ወይንም ያ መደረግ አልነበረበትም ማለቱ፤ የታሪክ ተጠቃሚዎች በመሆናችን ያተረፍነው እውቀት እንጂ፤ በወቅቱ ከነበሩት ተንቀሳቃሾች የበለጥን አዋቂዎች መሆናችንን አያመለክትም። የኅብረተሰብ ዕድገት፤ ከነበረው ትውልድ የተከተለው ትውልድ፤ አንድም የነበረውን በመረዳትና ከዚያ ትምህርት በመውሰድ፤ ሌላው ያንን አዳብሮ አዲስ ግንዛቤን በመገብየት፤ የተሻለ አመለካከት ማዳበሩ በታሪክ የተዘገበ ነው። ይህ አንጻራዊ ግንዛቤ፤ የአሁኖቹን ከነበሩት የበለጠ አዋቂ አያደርጋቸውም። የነበሩት በነበሩበት፤ ያለነው ደግሞ ባለንበት ነውና የምንመዘነው! በርግጥ ለዚያ ወቅት የተደረገውን ግስጋሴ ከተማሪው እንቅስቃሴ ውጪ አድርጎ ለይቶ ማየቱ ከባድ ነው። ለዚህ ነው የወቅቱን ተጨባጭ ሀቅ ዘርዝሮ ማየቱ፤ የስድሳዎቹን ተማሪዎችና እንቅስቃሴያቸውን በትክክል ለመገንዘብ የሚረዳው።

በዚህ ርዕስ፤ የስድሳዎቹ ተማሪዎችና እንቅስቃሴያቸው ስንል፤ ከ፲ ፱ ፻ ፶ ዓመተ ምህረት፤ እስከ ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓምተ ምህረት ባለው ጊዜ፤ በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በሌሎች ከፍተኛ ተቋማትና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የነበሩትን ተማሪዎችና እንቅስቃሴያቸውን ማለታችን ነው። ለዚህ ዋነኛው ምክንያቱ፤ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ብለን የምንዘግበው ወቅትና ይህ የተማሪዎች እንቅስቃሴ፤ ነውጠኛ የሆኑትን ሀገራዊ ጥያቄዎች ያነገበበት ክፍለ ጊዜ በመሆኑ ነው። በዚህ ጽሑፍ ትኩረት የተሠጠው፤ የማውቀውን የመጨረሻውን ሩብ ነው። በርግጥ ለመንደርደሪያ ወደ ኋላ ትንሽ ዞሬ ዳስሻለሁ።

ክፍል አንድ –

ሀ)    የወቅቱ የዓለም አቀፍ የፖለቲካ አሰላለፍ

የዚያ ዘመን የዓለም አቀፍ የፖለቲካ አሰላለፍ፤ በሁለት ግዙፍ ተጻራሪ ኃያላን መንግሥቶች የተሽከረከረ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካና በሶቪየት ኅብረት። የመጀመሪያው የሶሺያሊስትና ኮምኒስት አቀንቃኝ ሀገሮችን አማክሎ በምሥራቁ የዓለም ክፍል ሲሽከረከር፤ ሁለተኛው ደግሞ ካፒታሊስት ሀገሮችን ያማከለ የምዕራባዊያን ስብስብ ነበር። በመካከል ቤት፤ እንደ ገበጣ ጠጠሮች የሚያንከባልሏቸው “በመሠልጠን ላይ ያሉ” ሀገሮች ነበሩ። እኒህ “በመሠልጠን ላይ ያሉ” የሚባሉት ሀገሮች ከሞላ ጎደል ሁሉን የአፍሪቃ ሀገሮች ሲያካትት፣ የላቲን አሜሪካንም በሙሉ ይዟል። ከእስያ በኩል በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙትን የአረብ ሀገሮች፣ የሩቅ ምሥራቅ ሀገሮችን፤ ከሶቪየት ኅብረትና ቻይና ውጪ ያሉትን በሙሉ ያቅፋል። እኒህ የዓለምን አብዛኛውን ሕዝብ የያዙ ሀገሮች፤ በዩናይትድ ስቴትስና በሶቪየት ኅብረት ፍላጎትና ፍትጊያ፤ የነጋቸውን ሳያውቁ የሚግተለተሉበት ሀቅ ነግሦ ነበር። በወቅቱ አብዛኞች የቅኝ ግዛት ሀገሮች፤ የይስሙላ የሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ ነፃነትን የተቀዳጁበት ሰዓት ነበር። ከሰንደቅ ዓለማ ማወለብለብ በላይ ያለሙት ከፍተኛ ቅጣት ተጣለባቸው፤ የኮንጎው ሉቡምባ፤ የጋናው ንክሩማ፣ የደቡብ አሜሪካው ቸ ጉቤራ፣ የቢየትናሙ ሆቺ ሚን፣ ያቺሊው አየንዴ፣ የዚያን ጊዜ የፖለቲካ ስልት ስልቦች ናቸው። በርግጥ ይህ የማመስ ተግባር ዛሬም ቢሆን አልቆመም። አሁንም ይሄው ጆርጅ ቡሽ ኢራቅን ሲወር፣ ቭላድሚር ፑትን ምሥራቅ አውሮፓን ሲያምስ የምናየው ሀቅ ነው። ቻይናም በጃፓንና በቪየትናሞች ላይ የበላይነት ለማንገስ ይሄው ትውተረተራለች።

ለ) የወቅቱ የሀገራችን ተጨባጭ የፖለቲካ ሀቅ

ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ፤ ከላይ ለተጠቀሰው የጢባ ጢቦ ጨዋታ ጠጠር ነበረች። ሀገራችን በመጀመሪያው ዙር የጣሊያንን ወራሪ ጦር ዓለምን ባስገረመ ሁኔታ፤ በአፄ ሚኒሊክና በእቴጌ ጣይቱ መሪነት ደባልቃ አፈር ካስጋጠች በኋላ፤ ከኒህ መሪዎች ተከትሎ ባለው የሥልጣን ሹክቻ፤ ባለችበት መሄድና ወደ ኋላ መጎተት ያዘች። ዓለም ወደፊት ገሰገሰ። ቁጭቱን ስንቅ አድርጎ ፋሽስት ጣሊያን ዳግም መጣ። አምስት ዓመት ሙሉ እንደሾህ የሚናደፉ አርበኞቻችን መቀመጫ አሳጥተውት፤ ተመልሶ ጭራውን ጠቅሎ ወደ ሀገሩ ነጎደ። ይህ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የተጀመረው ከፋሽስቱ ጣሊያን የአምስት ዓመት ጦርነት፤ ሀገራችን ራሷን ተከላክላ አንገቷን ቀና ባደረገችበት ጊዜ ነበር። በርግጥ ፋሽስት ጣሊያን ተጠራርጎ ከወጣ ገና ሃያ ዓመት እንኳ አልሞላውም ነበር። በዚህ ወቅት ሥልጣንን ለማጋራት ፈቃደኛ ያልነበረው ጥንታዊው ዘውዳዊ ሥርዓት፤ ራሱን ለማሻሻልና የዓለምን የሥልጣኔ ግስጋሴ ለመገንዘብ ፊቱን አልሠጥም አለ። ለራሱ ሕልውና አስፈላጊ የሆነውን የቢሮክራሲ አንቀሳቃሽ ኃይል እንኳ፤ በልጓም ይዞ ሊነዳው የሚችለውን ነበር የፈቀደው። ከዚያ ውጪ ምን ሲባል ተሞክሮ! ተባለ።

ከዓለም አቀፍ ተጨባጭ እውነታ አንጻር፤ ሀገራችን በጣም በሥልጣኔ ወደ ኋላ ከመቅረቷ በላይ፤ ድህነት፣ ረሃብ፣ በሽታ፣ ድንቁርና ነግሰውባት ነበር። በተጻራሪው ለተማሪው፤ ኢትዮጵያ የሥልጣኔ መሪ፣ የዳቦ ቅርጫት፣ የነፃነት ምልክት፣ ወዘተ. እየተባለ ይነገር ነበር። በዚህ እውነታ መካከል ነበር፤ ከሕዝቡ ቁጥር አኳያ፤ እጅግ በጣም ትንሽ ቁጥር የነበራቸው ተማሪዎች፤ የሀገራችንን ጉዳይ የራሳቸው ጉዳይ አድርገው፤ ከነሱ የነገ ምቾትና ሹመት፤ የሀገራቸውን ወደ ሥልጣኔ ጎዳና ማቅናት በማሰብ፤ የተማሪዎችን እንቅስቃሴ የገፉት።    ( ክፍል ፪ ይቀጥላል )

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s