የስድሳዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ( ክፍል ፪ )

ስድሳዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ( ክፍል ፪ )
አንዱዓለም ተፈራ        eske.meche@yahoo.com
ማክሰኞ፤ ግንቦት ፱ ቀን፤ ፳ ፻ ፰ ዓመተ ምህረት ( 05/17/2016 )

ሀገራችን ኢትዮጵያ በጣም ኋላቀር ነበረች ስል፤ በፖለቲካው፣ በምጣኔ ሀብት ስርጭቱ፣ በእደ ጥበብ ዕድገቱ፣ በመንግሥታዊ አወቃቀሩ፣ በትምህርት ደረጃው፣ በጤና ጥበቃ ይዘቱ፣ በሙሉ ነበር። የተፈጥሮ ሀብት ያላነሳት ሆና፤ የአስተዳደር ፍልስፍናው መሠረቱ ሳይዛባ፤ ለዘመናት የቆየውን የአንድ ቤተሰብ ፍጹም ቆራጭ ገዥነት የተከተለ ስለነበር፤ ለውጭ ሃሳብም ሆነ ለሥልጣን መጋራት በሩን ቀርቅሮ የዘጋ ነበር። እናም ከቤተሰቡ ውጪ እንኳንስ የተለዬ፤ ተመሳሳይ ሃሳብ እንኳን አይቀበልም ነበር። የሥርዓቱ መሠረት የሆነው የምጣኔ ሀብት ሥርጭቱ፤ በጢሰኛውና በቦታው የሌሉ የመሬት ባለቤቶች መካከል የነበረው የሻገተ የመሬት ስሪት ነበር። ስለዚህ ሥርዓቱ ባለበት ውስጡ ተቦርቡሮ ነበር። ታሪክ ሥርዓቱን በቆመበት ጥሎት ሄደ።

የትምህርቱ ጉዳይ፤

በዚህ ላይ ነበር እንደ ጋቢ የሚደረብ የውጭ ትምህርት በኅብረተሰቡ ላይ እንዲጫን የተደረገው። ይህ ከልብ የመነጨ ሀገርን ለማሻሻል የተደረገ ጥረት ነበር? ወይንስ ሁኔታው ግድ ስላለ፤ ሥርዓቱ ራሱ የሚቆጣጠረው የትምህርት ሂደት ለመግዛት? የፋሽስቱ ወራሪ ጣሊያን በሀገራችን ያሳየው የሀገራችን ወደ ኋላ መቅረትን ለማስተካክል ነበር? ወይንስ ለመምሰል? ነው ብለን እንቀበልና ሂደቱን እንከተል። ይህን ጥረት ሀገራዊ እንዳይሆን ሁለት እንቅፋቶች ገጠሙት። ትምህርቱን ለማስፋፋት የፈለጉት ወጣት ንጉሥ፤ ለሥልጣናቸው መደላድል በነበረው መደብ ሙሉ አዛዥነታቸውን ለማስረገጥ ሊጠቀሙበት የዘረጉት ነበር። ይህ የትምህርት ሥርዓት በመጀመሪያ ደረጃ፤ ሀገራዊ የሆነው የሥርዓቱ ተጠቃሚ ክፍል ዋና ተቃዋሚው ሆነ። በገዥው ቤተሰብ ዙርያ፤ የሥርዓቱ አቅንቃኞችና ተጠቃሚዎች፤ የነበረውን ሥርዓት ፍጹማዊ፤ ለውጥ የሚባለውን ነገር በሙሉ ደግሞ ጠላት አድርገው ስለወሰዱ፤ አዲሱን የትምህርት እንቅስቃሴ አጥብቀው ተቃወሙት። በወቅቱ የሰማሁት ትዝ ይለኛል። ተማሪዎች አዲስ ሃሳብ ያመጣሉ ብለው የፈሩት ራስ ካሳ፤ አፄ ኃይለ ሥላሴን፤ “ተው ተፈሪ፤ ይሄን የድሃ ልጅ አስተምረህ፤ ኋላ ራሳችን ላይ ታወጣብናለህ!” ብለው መክረዋቸዋል ይባል ነበር። ቀጥለውም ተማሪዎች መንቀሳቀስ ሲጀምሩ፤ “ይች ባቄላ ውላ ካደረች አትቆረጠምም!” በማለት ቆራጥ እርምጃ እንዲወሰድባቸው፤ መክረዋቸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከውጪ የትምህርቱን ሥርዓት መሠረት ለመጣል የመጡት የውጪ ሀገር ሰዎች ነበሩ። እኒህ ሰዎች፤ የሀገራቸውን ጥቅም አስጠባቂ እንጂ ለኛ ጥቅም ቋሚ እምነት ስላልነበራቸው፤ የራሳቸውን ሃይማኖት እንጂ በኢትዮጵያ ያሉትን ሃይማኖቶች ስለማይወዱ፤ የነሱ ሥልጣኔ ግንዛቤና የኛ ለመሠልጠን ያለን ግንዛቤ የተለያየ በመሆኑ፤ ትምህርቱ የተንሳፈፈ ነበር። የትምህርት ይዘቱንም ሆነ ጠቀሜታውን ለመግለጽ፤ “ዘመናዊ – የቀድሞ” “የአስኳላ ተማሪ – የቆሎ ተማሪ” በማለት፤ የኛን ማጣጣልና ከውጪ የመጣውን ማንቆለጳጰስ ተያዘ። ትምህርቱን የተንሳፈፈ ለማለት ምን መረጃ አለኝ?

ለመጠቆም ያህል፤ በጎንደር ክፍለ ሀገር፣ ከአውራጃ ወረዳ፣ ከወረዳም በታች ምክትል ወረዳ እንኳን ባልሆነች አንዲት ትንሽ ከተማ፤ በ፲ ፱ ፻ ፶ ፬ ዓመተ ምህረት፤ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። ሁሉንም ትምህርት በእንግሊዝኛ ነበር የምንማረው። የኅብረ-ትምህርት መጽሐፋችን፤ ማርች ኦቭ ታይምስ የሚባል ነበር። ስለ አውሮፓ የአስራ ዘጠናኛው ክፍለ ዘመን ግዛት በዝርዝር እናጠና ነበር። ያኔ እንኳን ስለ አፍሪቃ፤ ስለኢትዮጵያ የሚያስተምር አንድ መጽሐፍ ሆነ ዝግጅት አልነበረንም። እንደገና፤ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ፤ በክፍላችን ውስጥ፤ ከኋላ ዓይናችን በመሃረብ ተሸፍኖ፤ በጥቁሩ ሰሌዳ ላይ በተዘረጋው የዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ ካርታ፤ የተጠየቅነውን የአንድ ስቴትስ ቦታና ዋና ከተማ በጣታችን እንድንጠቁም እንታዘዝና፤ ከክፍሉ መጨረሻ ተነስተን፤ ወደ ጥቁሩ ሰሌዳ በመጓዝ፤ በቀጥታ እንጠቁም ነበር። ያኔ “የባሌ ክፍለ ሀገር ዋና ከተማ ማነው?” ተብለን ብንጠየቅ መልስ የምንሠጠው በጣት አንቆጠርም ነበር።

ይኼን የምዘረዝረው፤ የሚያስጎመዥ ሳኡንሳዊ ትንታኔ በመሥጠት፤ ግንዛቤ እንዲኖራችሁ ከማድረግ ይልቅ፤ በቀጥታ የነበረውን ባትት፤ የበለጠ ግልጽ ይሆንላችኋል ብዬ ስላመንኩ ነው። እንግዲህ ከዚህ ላይ፤ ሁለተኛ ደረጃ ሲገባ፤ የአሜሪካውያን ፒስ ኮሮፕስ፤ የሕንድ አስተማሪዎች ሲጨመሩበት፤ ትምህርቱ እንኳንስ ኢትዮጵያዊ ሆኖ የሀገራችንን ችግር አጥንተን መፍትሔ እንድናስገኝ ሊያዘጋጀን፤ ኢትዮጵያዊ ጋቢ እንኳ አልደረበም ነበር። በሀገራችን የነበሩት የመኪና መንገድ መስመሮች ውስንነት፣ የሕክምና በባለሙያዎች እጥረትና የመሠረታዊ የሕልክምና ጣቢያዎች አለመስፋፋት፣ በገጠር ከነበሩት የትምህርት ቤቶች ቁጥር ጋር ስናገናዝበው፤ የሀገራችንን የሥልጣኔ ቦታ መገንዘቡ ቀላል ነው።

ታዲያ በዚህ ወቅት የመማር ዕድል አግኝቶ ትምህርት ቤት የገባው ተማሪ ቁጥር ምን ያህል ነበር? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ገና በሃያዎቹ የመጀመሪያዎች ሚሊዮኖች በሚቆጠረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ፤ የትምህርት ዕድሉን አግኝቶ የነበረው ተማሪ፤ በተለዬ አትኩረን ዩኒቨርሲቲ የገባውን ተማሪ ብናጤን፤ ከአምስት ሺ አንድ ቢሆን ነበር – ( ማለትም – 0.02% )። ይህ ቁጥር፤ እንዲያው የተማረ በጣም በሚከበርበት ሀገር በመሆኑ ከፍተኛ ቦታ ተሠጠው እንጂ፤ በጣም ከቁጥር የማይገባ ነበር። ተማሪዎች፤ ከቤተሰብ ይዘውት የሚመጡት አመለካከትና ግምት አላቸው። ቀጥሎ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤታቸው የቀሰሙት አመለካከትና ግምት አላቸው። ከዚያ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሆነው የቃረሙት አመለካከትና ግምት አላቸው። ይሄን ሁሉ አጠራቅመው ነው ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚገቡት።

በዩኒቨርሲቲው የነበረው አስተዳደርና የመምህራኖቹ ግንዛቤና ትምህርት አሠጣጥ ሌላው ጉዳይ ነበር። የትምህርቱ ይዘትና አሠጣጥ፣ የአስተዳደሩ አካሂያድ፣ የዩኒቨርሲቲው ኑሮ፣ ጥቂት የነበሩት ከተለያዩ የአፍሪቃ ሀገሮች የመጡ ተማሪዎች፣ ውጪ ሀገር ተምረው የመጡ ኢትዮጵያዊያን፣ የወቅቱ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው ከመግባታቸው በፊት የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ፤ ለተማሪዎቹ የወደፊት የዩኒቨርሲቲ ሕይወት ወሳኝ ነበር። የተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ኑሮ፤ አብዛኛዎቹ ከመጡበት ኑሮ በጣም የተሻለ የነበረ ቢሆንም፤ ቀደም ብሎ ከነበረው እያሽቆለቆለ የሄደ ነበር። እናም “ተጓደለብን!” የሚለው መነሻ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጥያቄ ነበር። ተማሪዎች ከመማር አልፎ አሁኑኑ ለሀገራችን ኃላፊነት አለብን እና ምን ማድረግ አለብን የሚለውን አንግበው ተነሱ።

አንድ ነገር መገንዘብ አለብን። በማንኛውም ሕዝባዊ እንቅስቃሴ፤ በጣት የሚቆጠሩ ታታሪ ጀማሪዎች ናቸው ከፍተኛውን መስዋዕትነት እየከፈሉ ሂደቱን የሚገፉት። በሀገራችንም ቢሆን ይኼው ነው የተከሰተው። እዚህ ላይ አንድ ትልቅ ጉዳይ በትክክል መታየት አለበት። በወቅቱ ሰፊ የሆነ የትምህርት ዕድል የነበራቸውና የዓለም አቀፉን የፖለቲካ ስሌት ለመገንዘብ ጊዜውና ሁኔታው ያነበራቸው፤ ከተመቻቸና አንጻራዊ የንብረት የበላይነት ከነበራቸው ቤተሰብ የመጡ ተማሪዎች ነበሩ። የሚገርመው ደግሞ፤ ከማንኛችንም የበለጠ ሊያገኙ የሚችሉትን የሚያጡና የሚጎዱ፤ እኒሁ ነበሩ። እኔ ዩኒቨርሲቲውን ስቀላቀል፤ በብዛት ከአመራር በኩል የነበሩት ተማሪዎች ከዚሁ ክፍል የመጡ ነበሩ። ጥላሁን ግዛው፣ ማርታ መብራቱ፣ መስፍን ሀብቱ፣ ዳዊት ስዩም፣ መሐሙድ ማሕፉዝ፣ ወዘተ. . . የነኚህ ተማሪዎች ተሳትፎ፤ ሊያገኙ የሚችሉትን ስላጡ አልነበረም። ሀገራቸው በዓለም ደረጃ የነበረችበትን በመረዳት፤ የበለጠ መሆን አለባት በማለት ነበር።

በዚያን ጊዜ የኔን ጉዳይ በሚመለከት፤ ከቤተሰቦቼና ከቅርብ ዘመዶቼ መካከል፤ እስከ አያቶቼ ወላጆች ድረስ፤ ከታናናሾቼ በስተቀር የትምህርት ዕድል አግኝቶ ትምህርት ቤት የገባ አንድም አልነበረም። እንደኔው ካልተማረ ቤተሰብ ከመጡት መካከል፤ የጢሰኞችንና የመሬት ባላቤቶችን ግንኙነት አጥብቀው የተረዱ ነበሩ። የነኝህ ተማሪዎች አስተዋፅዕ ከፍተኛ ነበር። በመሬት ስሪቱ ምክንያት ቤተሰቦቻቸው የተጉላሉ ነበሩ። በአካባቢያቸው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት ከሩቅ ዘመድ ተጠግተው የተማሩ ነበር። ይህን ሁኔታ ያጤኑ ነበሩ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ታታሪ ገፊዎች።

ዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተጋጋሉ ውይይቶች ጦፈው ነበር። የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ከንጉሱ ጋር በመሆን፤ የተማሪዎችን ነፃ የራስ ማህበር መመሥረትና ከነሱ ውጪ “ልቅ” መሄድ ፍፁም ለማገድ ሌት ከቀን ይጥሩ ነበር። ሁኔታው ግን እጃቸውን ጠምዝዞ፤ ትንሽ በትንሽ እንዲለቁ አስገደዳቸው። ተማሪዎችም ከግል የግቢ ጥይቄዎቻቸው ውጪ፤ ሀገራዊ ጉዳዮችን መዳሰስ ያዙ። ከዚያ በኋላ፤ ታታሪ ተማሪዎቹ፤ ከትምህርታቸው ይልቅ፤ በሀገራቸው ለውጥ እንዲከተል መግፋት ያዙ። ትዝ ይለኛል፤ በጥላሁን ግዛው የዩኒቨርሲት ተማሪዎች ማህበር ፕሬዘዳንትነት ምረቃ በዓል፤ ዘሩ ክሽን፤ “ አይ አም ዘ ኦልደስት ስቱደንት ኢን ዘ ዩኒቨርሲቲ!” ብሎ ሲናገር። መውጣትና መግባት ያዘወትሩ ነበር ታታሪ ተማሪዎቹ። ጥላሁን ግዛው፤ “ኢፍ ዘ ራት ኢዝ ኮርነርድ ባይ ዘ ካት፤ ኢት መስት ሬክት!” ብሎ ሲናገር ትዝ ይለኛል። መስፍን ሀብቱ፤ እጆቹን በሰርባው አነባብሮ፤ በጣም ቀለል ባለና ለኔ በሚገባኝ እንግሊዝኛ፤ የልደት አዳራሹ ውስጥ፤ እኛ ከባድ ኃላፊነት አለብን። ታሪክ እኛን ጠርታናለች!” ሲል በደም ሥሮቼ የሚነዝር ነሻጭ መልዕክት ተላልፎልኛል። እኒህ ናቸው የስድሳዎቹን ተማሪዎች እንቅስቃሴ መልክ ያስያዙት። የጥላሁን ግዛው ግድያ፤ በተማሪዎችና በንጉሰ ነገሥቱ መንግሥት መካከል መመለሻ የለለው መካረርና የማይታረቅ ልዩነትን አሰመረበት። ከዚያ በኋላ ሥርዓቱን በመለወጥ ደረጃ ተማሪው አሰበ።  ( በክፍል ሶስት ይቀጥላል )