እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣቷ የምንማረው፤

እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣቷ የምንማረው፤

ረቡዕ፣ ሰኔ ፳ ፱ ቀን፤ ፳ ፻ ፰ ዓመተ ምህረት ( 7/6/2016 )

እንዱዓለም ተፈራ የእስከመቼ አዘጋጅ

የዓለም የንዋይ ስምሪት አውታር ክንፎች አጥናፋቸውን ሲያሰፉ፣ የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ቁልልፍ እየተወሳሰበ ሲሄድ፤ ግለሰቦች ከራሳቸው ከባቢ ውጪ ያለውን ክንውን፤ በንቃት መከታተል ግድ ይሆንባቸዋል። ምክንያቱም በዚህ በተወጠረ የዓለም ትስስር ሕልውና፣ አንዱ አካባቢ የሚነጥረው ጠጠር ሌላውን አካባቢ ያረግባልና! ለዚህ ነው ከኢትዮጵያ በስደት አሜሪካ ተቀምጬ፤ አውሮፓ የሚካሄደውን የእንግሊዝ ከአውሮፓ ኀብረት መውጣት በንቃት የተከታተልኩት። እናም እነሆ ግንዛቤዬ።

በመጀመሪያ ደረጃ፤ የታላቋ ብሪታንያ ሕዝብ ዴሞክራሲያ መብቱን ተጠቅሞ ውስኔ ለመሥጠት መቻሉ የሚደነቅ ነው። በዚህ ረገድ፤ ዴሞክራሲያዊ አሰራር ምን ያህል የተከበረበት ሀገር መሆኑን እንማራለን። አንዳንድ ሞዕራባዊ ልሂቃን፤ ዴሞክራሲ ቅጥ ሲያጣ ብለው አትተዋል። ነገር ግን ዴሞክራሲ በተግባር ሲውል የግድ ሁልጊዜም ትክክለኛ ውጤት ያስከትላል ማለት እንዳልሆነ ተረዳን እንጂ፤ ዴሞክራሲ ቅጥ አጣ አያስብልም። ዴሞክራሲ አንድ ወጥ በሆነ ሀገር፤ በጣም ረዳት መሣሪያ ነው። የሕዝቡን የበላይነት አስምሮ፤ መንግስታዊ ግዛቱን ተጠያቂ ያደርገዋል። አንድ ወጥ ባልሆነ ሀገር ደግሞ፤ የየክፍሉ የጥቅም ሩጫን በተንተራሰ መዘዝ፤ ሀገሪቱን አደጋ ላይ ይጥላል። በእንግሊዝ የሚሆነው ይህ ነው። ዝርዝሩን ዝቅ ብዬ አቀርባለሁ።

ቀጥሎ ለምን “እንገንጠል!” የሚለው አቸነፈ? የሚለውን ማየት ነው። እዚህ ላይ መጤን ያለበት፤ ይህ የ “እንገንጠል!” ጉዳይ ሲነሳ፤ የጉዳዩ መሠረት ምንድን ነው? ጠባብነት ወይንስ የነፃነት ጥማት? ፀረ-ስደተኛ መሆን ወይንስ አፍቃሪ እንግሊዝ መሆን? ለምን ለንደን ዙሪያ፤ ስኮትላድና ሰሜን አየርላንድ አለመገንጠሉን ወደዱ? ይህ የአክራሪዎች ግፊት ነው ወይንስ የነፃነት ፈላጊዎች ጩኸት? ቅስቀሳው እንዴት ነበር? ይሄን በቅርብ መመልከቱ ተገቢ ነው። ሆኖም ግን፤ አሁን እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት ወስናለች። ተወደደም ተጠላም፤ ይህ የሕዝቡ ውሳኔ ነውና መተግበሩ የግድ ነው። እናም ይሄንን ውሳኔ ነው የማብጠለጥለው። የገረመኝ፤ የቆየው ስደተኛ (የሕንድ ሶስተኛ ትውልድ) ፤ የቅርብ ሰደተኞችን (አዲስ ፖሊሾች) “ይውጡ!” የሚል መፈክር ይዞ ሳየው ነው።

አሜሪካ ተቀምጬ በእንግሊዝ ሀገር የነበረውን የውድድር ሂደት በዓይኔ ቀርቤ ሳልመለከት፤ “እንዲህ ቢደረግ ኖሮ!” ወይንም “እንዲያ አለማድረጋቸው!” እያልኩ ማንሳትና መጣሉ አያስኬደኝም። ነገር ግን፤ ባጠቃላይ ያለውን የለውጥ ፈላጊዎች ስነ ልቡና መረዳቱ አይከብድም። እዚሁም ያለሁበት አሜሪካ፤ “ዶናልድ ትራምፕ!” የሚባል ተመሳሳይ ደመና አንዣብቦበታል። “እንገንጠል!” ባዮቹ፤ ያሉበት ሁኔታ ያጎደለባቸውን አንግበው ለውጥ ፈለጉ። በማንኛውም ጊዜና ቦታ፤ ለውጥ ፈላጊዎች ታታሪዎች ናቸው። ተሯሯጮች ናቸው። አይታክቱም። ዓላማ አላቸው። የተነቃቁ ናቸው። የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ይህ የለውጥ ፈላጊዎች ዋና መሣሪያቸው ነው። በተቃራኒው ያሉት ለውጡን የማይፈልጉት፤ አንድም በንቀት ለውጥ አይመጣም ብለው ተንፈራጠው ይቀመጣሉ፤ አለያም ደግሞ በቂ ያልሆነ ጥረት በማድረግ፤ ውስን፤ አደረግን ለማለት ይነሳሉ። እኒህ ለውጡን የማይፈልጉ አካላት፤ በሁለቱም በኩል የሚያደረጉት ደካማ የሆነ ተሳትፏቸው፤ ውጤት አልባ ያደርጋቸዋል።

በኔ እይታ፤ ይህ “የእንግሊዝ ከአውሮፓ የመገንጠል!” ውሳኔ፤ ዓለም አሁን ያለችበትን የፖለቲካ ሀቅ ያገናዘበ አይደለም። እንግሊዝና የእንግሊዝ ኢኮኖሚ፤ ምን ያህል ከአውሮፓና ከዓለም ገበያ ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ያጤነ አይደለም። በዚህ ውስኔ፤ ራሷ እንግሊዝ ምን ያህል ትጎዳ ወይንም ትጠቀም እንደሆነ ረጋ ተብሎ የተጤነበት አይመስልም። ይሄን ለማለት ያስቻለኝ፤ አሁን አሜሪካ የዓለም ብቸኛ ልዕለ-ኃያል ሆና፣ የሩስያ ብሔራዊ ስሜት በፑቲንና በፔትሮሊየም ጉልበት ተገፍቶና ተጋግሎ፣ ቻይና ተጠርንፎ በተያዘ የፖለቲካና ኢኮኖሚ መንግሥታዊ ግዛት ፈርጥሞ አለሁ ባለበት ሰዓት፤ ከአውሮፓ ኅብረት መገንጠሉ፤ ምን ያህል ደካማና ትንሽ ልትሆን እንደምትችል አለመገንዘባቸው ነው።

ሰፋ አድርጎ ለመመርመር፤ እንግሊዝ በመገንጠሏ ምን አተረፈች? በዓለም ላይ ያላትን የፖለቲካ ተደማጭነትና የኢኮኖሚ ጉልበት ምን ያህል ተዳከመ? በውስጧ ኗሪዎቿ መካከል ምን ተከተለ? የፓውንዱ ማሽቆልቆልስ እንዴት ይታያል? የለንደን የዓለም የፖለቲካና የገበያ ስፍራ ምን ያህል ተናጋ? ዋና ዋና የተባሉ የንግድ ድርጅቶች ማዕከላቸውን ወደ አውሮፓ ለማዞር መወሰናቸው ምን ያህል እንግሊዝን ይጎዳል? እንግሊዞችስ በአውሮፓ እንደልባቸው መንሸራሸር ሲቀር ምን ይላሉ? ከዚህ የተረዳሁት፤ በእንግሊዝ ውስጥ ከሁለትና ከሶስት ትውልድ በላይ ተወላጅነታቸውን የማይቆጥሩ አደጋ ላይ መሆናቸውን ነው። ይህ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን፤ መላ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የፈለሱትንና እንግሊዝ የሰፈሩትን ሁሉ ያጠቃልላል። በሃይማኖት፣ በመልክ ቀለም፤ በምግብ ልዩነት ምክንያት፤ ውጥረት ይከተላል። የ “እንገንጠል!” ባዮች መዳራሻ ዓላማ፤ የድሮዋ አንድ የእንግሊዞች ብቻ ሀገር እንድትሆን ነው። ምግባቸው፣ ሃይማኖታቸው፣ ገበያቸው፣ ልብሳቸው፣ ንግግራቸው፣ መንገዱ ሁሉ እንደጥንቱ እንግሊዝ እንግሊዝ እንዲሸት ነው። ከማዕከላዊው መንግሥት በልጦ፤ የአካባቢው ሰው፤ በ “እንግሊዝ አይደለም!” በሚለው ግለሰብ ላይ ያሻውን የሚያደርግበት ክስተት እንዲከተል ነው።

አልፎ ተርፎ ደግሞ፤ የስኮትላንድን እና የሰሜን አየርላንድን መገንጠል የሚያስከትል ነው። በዚህ ብቻም አይቆምም። መቼም በጊዜዋ “የእንግሊዝ ግዛት ፀሐይ አይጠልቅበትም!” እያለችና እንደተባለላትና በከፋፍለህ ግዛ ስሌቷ ዓለምን እንደበጠበጠች፤ አሁን በተራዋ ራሷ አንድ ሆና መቆም ሊያቅታት ነው። አንድነት ወይንስ መገነጣጠል የሚለው በእንግሊዞች ስነ-ልቡና ገብቷል። ወደፊት ወይንስ ወደኋላ የሚለው አስፈሪ ሀቅ ከፊታቸው ተጋግሯል።

ከዚህ እኛ ምን እንማራለን?

በሀገራችን የፖለቲካ መስክ፤ አንድ ነን አይደለንም፤ በጨቋኝ ገዥዎችና በተጨቋኝ ሕዝቡ መካከል ያለው ቅራኔ ነው ወሳኝ፤ የለም ወሳኙ ቅራኔ በገዥው ብሔርና በተገዢ ብሔሮች መካከል ነው ባዮች አሉ። ደግሞ በአንድነት ገዥውን ቡድን እናስወግድ፤ የለም በየፊናችን ቡድኑን አስወግደን ከዚያ በኋላ ከወደድን እንተባበራለን፤ የሚሉም አሉ። እንግዲህ እየዋኘን ያለነው በዚህ የትግል ሂደት ውስጥ ነው። በዚህ እውነታ ውስጥ ስንዋዥቅ፤ የእንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት “መገንጠል!”፤ ምንም እንኳ ፍጹም ተመሳሳይ ያልሆነና የማይገናኝ ቢሆንም፤ ምን ትምህርት እናገኛለን? በርግጥ ውሎ አድሮ ከአውሮፓ አልፎ በራሷ በእንግሊዝ ውስጥ የውስጥ ቀውሷ ሲነሳ፤ ማለትም የስኮትላድ፣ የሰሜን አየርላድ ጉዳይ ሲነሳ ተመሳሳይነቱ አያጠራጥርም።

በእንግሊዝ ሀገር፤ ይህ ምርጫ በችኮላና ረጋ ተብሎ ባልታየበት ሁኔታ የተካሄደ ነው ባዮች አሉ። ተቻኩሎ መደረጉ ነው ለዚህ ያበቃን ብለው የተጸጸቱ አሉ። እኛስ በዚህ ደረጃ፤ ያለንበትን የትግል ሂደት ዞረን ለማየት የሚያስችለን ትምህርት መገብየት እንችል ይሆን?

ምንም እንኳ “ከተገነጠልን እኛ የበለጠ እንጠቀማለን!” የሚለውን አጀንዳ ያነገቱ ምን ጊዜም ቢሆን፤ ምክንያትም ባይኖር ምክንያት ፈጥረው ግፊታቸውን ባያቆሙም፤ ይህ የእንግሊዝ ከተመሠረተው የአውሮፓ ኅብረት በአነስተኛ ምክንያትና በችኮላ መገንጠል፤ በራሷ በእንግሊዝ ላይ ያደረሰውና የሚያደርሰው ጉዳት ማጤን ያስፈልጋል። በኛ ሀገር፤ እኛ ብዙ ስለሆን የበለጠ ጥቅም እናገኛለን። እኛ የለማ መሬት ስላለን ሀብታሞች እንሆናለን። እኛ እስከዛሬ ስለተበደልን፤ የራሳችንን በዳዮች ማብቀል አለብን። የመሳሰሉትን ያነሱ አሉ። ጉዳዩን አቅልዬ መመልከቴ አይደለም። ሀቁ እንዳለ ሆኖ፤ ትምህርቱን ለመገብየት ማነጻጸሬ ነው።

መገንጠያ ምክንያቶችን ላለመገንጠል ከሚሆኑ ምክንያቶችን ጋር በማነጻጸር አመዛዝኖ፤ አንዱ ሊያስገኘው የሚችለውን ጥቅም ሌላው ሊያስገኘው ከሚችለው ጥቅም ጋር አወዳድሮ፤ መመዘኑ ተገቢ ነው። እዚህ ላይ የኤርትራን ሀቅ ማካተቱ ይረዳል። ኤርትራዊያን ተጠቀሙ ወይንስ . . . ? ኢሳያስ ተጠቀመ ወይንስ . . . ?

መገንጠል ወደፊት መሄድ ነው ወይንስ ወደኋላ? ከመገንጠል በኋላ የየአካባቢው ገዥዎች ይፈጠራሉ። እኒህ ገዥዎች ( እንደ ኢሳያስ ያሉ ) የሁሉም ነገር የበላይ ሆነው ይገዛሉ። ይህ ለቀሪው የተገነጠለ ወገን ምን ይረዳል? የትስ ላይ ነው መገንጠሉ የሚቆመው? እንዲያው ለመጠየቅ ያህል!